አዲስ አበባ፡- በሱማሌ ክልል በሰብዓዊ መብት ጥሰትና ንብረት በማውደም የተጠረጠሩ ግለሰቦች በህግ ተጠያቂ እየሆኑ እንደሆነ የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህገ አስታወቀ፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ትናንት ለመገናኛ ብዙሃን በሰጠው መግለጫ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ ዝናቡ ቱኑ እንደተናገሩት፤ በሱማሌ ክልል ከሃምሌ 28 እስከ 30 ቀን 2010 ዓ.ም የተፈፀመውን ኢሰብዓዊነት የተሞላበት ድርጊት አስመልክቶ ተሳትፈዋል ተብለው ከተጠረጠሩ 46 ግለሰቦች የክልሉን የቀድሞ ርዕሰ መስተዳድር ጨምሮ በስድስቱ ላይ ክስ የተመሰረተ ሲሆን፤ 40ዎቹ በሌሉበት ክስ የተመሰረተባቸው በሌሉበት ነው፡፡
በሱማሌ ክልል በተፈጸመው ጥቃት የ58 ሰዎች ህይወት ማለፉን ያስታወሱት አቶ ዝናቡ፤ በ266 ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል፡፡ በርካታ ዜጎች መፈናቀላቸውንም አመልክተዋል፡፡ 412 ሚሊዮን 468 ሺ ብር የሚመገት ንብረት የወደመ ሲሆን፤ የግለሰብ ንብረቶች፣ የመንግስት ተቋማትና ቤተ እምነቶች መውደማቸውን ተናግረዋል፡፡
እንደ ኃላፊው ገለጻ፤ በዚህ ተግባር ውስጥ የተሳተፉ ተጠርጣሪዎችን ለህግ አስተላልፎ የመስጠቱ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ከተጠርጣሪዎች ውስጥ ያልተያዙ ቢኖሩም በህግ ከለላ ስር መሆናቸው አይቀሬ ነው፡፡ ያለመከሰስ መብት ያላቸው አካላትም ጉዳይ በህግ አግባብ እየታየ ይገኛል፡፡
ወንጀሉ በተጠና መንገድ በመፈጸሙ የማጣራት ሥራውን ውስብስብ አድርጎታል ያሉት አቶ ዝናቡ፤ በክልሉ በወንጀልን በሙስና የተጠረጠሩ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ከተጠያቂነት ለማምለጥ ጥረት እያደረጉ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ በተደራጀ ሁኔታ የተፈፀመ ወንጀል በመሆኑ ምርመራው ጊዜ ወስዷል፤ የፍርድ ቤት ምልልስም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው ብለዋል፡፡
በተያያዘ ዜና የቀድሞ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሰፋ ከፈተጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ጋር ተያይዞ በመጠርጠራቸው ወደ ህግ ለማቅረብ ከትግራይ ክልል ጋር አስፈላጊ ተግባራት እየተከናወነ መሆኑ በመግለጫው ተመልክቷል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 18/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር