እንዴት ከረማችሁ አዲስ ዘመኖች? ክረምቱ እንዴት ይዟችኋል? የአዲስ ዘመን ዝግጅትስ? ሁለቱንም ማለቴ ነው። የቱንና የቱን አትሉኝም? የጋዜጣውን የተለመደ ዝግጅት እና አዲሱን ዓመት ለመቀበል ያለውን ሽርጉድ ማለቴ ነው።
እናንተዬ እየተገባደደ ያለው የዘንድሮው ዓመት መቸም በሰላም ይሂድ እንጂ እጅግ ፈታኝ ዓመት ነበር ማለት ይቻላል። በግሌ 2012ን “ዓመተ ኮሮና” ብንለው ራሱ አይከፋም ባይ ነኝ። ምን ትላላችሁ? ዓለም የእኛን የዘመን አቆጣጠር ባትከተልም ምጣቱ የሁላችን ነውና ይህን ሃሳቤን መላው ዓለም ሳይስማማበት እንደማይቀር መገመት አያዳግትም። ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ደግሞ ከዚህም ሌላ በርካታ ፈተናዎችን ያሳለፍንበት ዓመት ነውና በልዩ ስሜት የምናስታውሰው ነው። ዘንድሮአችን። አሁንም ከዚያ ውጥንቅጥ ጨርሰን አልተገላገልንም። እውነቴን ነው የምላችሁ ያንዣበበብን አደጋ ጥላው አሁንም ድረስ ተላያችን ላይ አልተገፈፈም። ያሳዝናል ሃጫሉን የመሠለ ድንቅ ኢትዮጵያዊ የነጠቀን ዓመት ነበር።
የነሐሴን ከባድ ዝናብ ተገን አድርጎ ሌላ ውርጅብኝ እንዳይመጣብን ሁላችንም ወደ ላይ ማንጋጠጥን እንዳንረሳ አደራ አደራ እናቶቼ። ብቻ ያስፈራል! ፈጣሪ ሆይ ከክረምቱም ጨለማ ወደ “ቦቃ ቢራ”፣ ካለፍንበት የመከራ ዓመት ወደ ስርየት በሰላም በደስታ በጤና አሸጋግረን። አሜን!
የዛሬው መልዕክቴ ሙሉ በሙሉ 2012ን በወፍበረር መታዘብ ላይ ያተኮረ ነው። የኔ ነገር! ዓመትን የሚያክል ጊዜ ያውም የዘንድሮውን ዓይነት ዓመት የክስተት መዓት በአንድ ገጽ ፅሁፍ ለመታዘብ መሞከር በራሱ በጣም የሚያስተዛዝብ ነው። ሆሆ!
በባለፉት ሁለት ፅሁፎቼ የዘንድሮውን ጨምሮ የአምናና ከአቻምና ሰኔዎችን ክስተቶች መታዘባችንን ደግሜ በትዝብት መነፅር ላስቃኛችሁ። የአንበጣ መንጋ ወሮን ሳር ቅጠሉን ወደ አመድነት ቀየረ። በዚህም የምግብ ዋስትናችን ለአደጋ ተጋለጠ። ሚሊዮኖች በረሃብ አለንጋ የመገረፍ አደጋ አንዣበበባቸው። ብዙም ሳይቆይ የዓለማችን የዘመኑ መቅሰፍት እርካቡን ተረክቦ ይጋልበን ጀመር። አጅሬ ኮሮና ማለቴ ነው። መንፈቅ ሳይሞላን ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ህይወትን ቀጠፈ። በአስር ሚሊዮን የሚቆጠሩትን የአልጋ ቁራኛ አደረገ። ይኸ ሁሉ የተፈጥሮ ቁጣ እየወረደብን እኛ የሰው ልጅ የተባልን ፍጡራን ደግሞ እሳቱን ከማጥፋት ይልቅ እርስበርሳችንን ስንማግድ ተስተውሏል። ወረርሽኙን ባመጣው እጃችን ዘሩ እንዲበረክትም ሌት ተቀን ስንደክም እንታያለን።
ይህ አምላካዊ ቁጣ ነው በሚለው ሀፍረት የሚባል ነገር ባልፈጠረልን አንደበታችን እሳት የሚተፉ የጥላቻ ቃላትን ከየአቅጣጫው ስናስወነጭፍ ውለን እናድራለን። ዓለም ስትቃጠል አድራ ስትቃጠል ትውላለች። ከሁሉ በላይ የፖለቲካው ሰደድ እሳት ደግሞ በተለይ ለእንደኛ ሀገር ላሉ ሁሉ አማረሽ የፖለቲካ ዳንኪረኞች ጥሩ ማፋፋሚያ ሆኗል። አንዱ አንዱን ጥሎ እራሱን ለማንገስ እናቱንም ለመግደል ቅንጣት ታክል እንደማያቅማማ በአይናችን እየተመለከትን ነው። ለፖለቲካ ሸፍጥ የሀገር ቤቱ ሜዳ አልበቃ ብሎ እስከ ጎረቤት ሀገር ድረስ በመዝለቅ እና “ገሌ” በመግባት እቆምለታለሁ እታገልለታለሁ ለሚላት እናት ሀገር ሳይቀር ወዲያ ማዶ ቆሞ በባንዳነት እራሱን በመሸጥ ለተጋጣሚ ቡድን ተሰልፎ ሲጫወት እና በትውልድ ሀገሩ ላይ ጎል ሲገባ በደስታ ለመስከር “በሬ ከአራጁ” እንዲሉ ከጠላት ጎን ሲቆም ታያለህ። ይህን ስል ግብፅ ወደ አእምሯችሁ እንደምትመጣ አልጠራጠርም።
መቸም እንደኛ ሰላም ወዳድ ማህበረሰብ ያለ አይመስለኝም። በዚያው ልክ ደግሞ በበርካታ የጎረቤት ጣውንቶች የተከበበ ህዝብም ስለመኖሩ እጠራጠራለሁ። ከሁሉም ጋር በሰላም በፍቅርና በመቻቻል መኖር የምንፈልግ፤ ለዚህም የፈጀውን ቢፈጅም ማንኛውንም ዋጋ ከፍለን ከጎረቤቶቻችን ጋር በእኩልነት መኖርን የምንሻ በዚህ ደግሞ ከማንም በላይ የተካንን ህዝቦች እንደሆንን ግብዝነት ካልሆነ በቀር ድፍን ዓለም የሚመሰክርልን አፍሮ ኢትዮጵያዊያን ነን። ሶማሊያ ትጠየቅ፣ ኬኒያ ትመስክር፣ ሱዳንም ትፍረደን። የግብፅ እንኳ የተለየ ነው። የርሷ የቆየ ቂም ነው። አዎ ታሪክ
የማያዳላ ብይን ሰጥቷልና። አሳምረው ያውቁናል እናውቃቸዋለንም። ይኸ ዛቻ አይደለም ሐቁ እንጂ። ቢመረንም መቀበል ግድ ይላል። አረብኛ የሚናገሩ የሀገሬ ልጆች ይህን መልዕክቴን ቱረጁማን ሆነው ለፈርዖኖቹ እንደሚያደርሱልኝ እተማመናለሁ። ኢትዮጵያን አይንሽን ለአፈር የተባለችውም በዚሁ የሐበሻ ዓመት ስለነበር ነው ይህን ማለቴ።
እዚሁ እስቲ ትንሽ ግብፅን ልማላችሁ። ወይም አብረን እንማት። በርካታ የዘርፉ ተመራማሪዎች እንደሚስማሙበት እና ስለግብፅ ሰፋ ያለ ግንዛቤ ያላቸው ምሁራን እንደሚናገሩት ግብፃውያን የአረብ ተንኮለኞች ናቸው ይላሉ። ለድርድርም ለድብድብም የማያመቹ። በዚህ ሲሏቸው በዚያ የሚያፈተልኩ እምነት የማይጣልባቸው የመንግስትነትም የህዝባዊነትም አፈጣጠር ግድፈት ያላቸው መሆናቸውን በመጥቀስ የሃሜት መንደርደሪያ ሃሳቤን ያጠናክሩታል፤ ምሁራኑ!
የካይሮ ሰዎች ድርቅና መነሻውም መዳረሻውም የሚታወቅ ጉዳይ ነው። እዚያ ውስጥ ገብቶ መዳከር እርባና የሌለው ስለሆነ አልፈዋለሁ። የተነሳሁበትም ዓላማ ርዕሴ ስላይደለ ማለት ነው። እኔን ይበልጥ የገረመኝና የብዙዎቻችን የትዝብት መነፅርን የሚስበው የሀበሻ ግብፃውያን ነገር ነው፤ ባንዳዎቹ። ጎበዝ ሰው እንዴት ወደ ጓዳው ዞሮ ይሸናል? አጂብ አሉ አረቦቹ እራሳቸው። እንተርት እንጂ በእነርሱም ቋንቋ። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሱዳን እንደ ገበቴ ላይ ውሃ መዋለልም ትዝብትን የሚያጭር እንደሚሆንባችሁ እሙን ነው። ልክ እንደ ግብጥ ሁሉ እዚሁ ሀገር ቤት ያሉና በአረብኛ ዳዴ የሚንተባተቡ ሀበሻ ሱዳናውያን አልጠፉም።
ከቤት ስወጣ የእኛን ገመና በትዝብት በትር መኮርኮርና አሉታዊ ጎናቸው ሰፋ ያለውን ከርከም ከርከም አድርጎ ለከርሞ የተሻለ አበቃቀል እንዲበቅል እና ለተሻለ ነገ እንዲለመልም ለማስቻል የታየኝን ሃሳብ ለመሰንዘር ነው። ያው የትዝብት ፈረስ እኔንም በሚያስተዛዝብ መልኩ ከግራ ከቀኝ እያላጋ የማነሳውንና የምጥለውን እስኪያሳጣኝ እየባከንኩ መሆኔን እናንተም ታዝባችሁኝ እንደሆነ ልክደው አልችልም። እንግዲህ ትዝብትም አይደል? መተዛዘብ ነው። መተዛዘን እስክንችል ወይም ይህንኑ ባህሪ ማዳበር እስክንችል ማለት ነው።
መግቢያው ላይ ጠቀስ አድርጌ ለማለፍ እንደሞከርኩት የሰኔ ሃያ ሁለቱን የአርቲስት ሃጫሉ ግድያ ተከትሎ ኮሮናን አስንቅ የፖለቲካ ወረርሽኝ ውስጥ መዘፈቃችን ፀሐይ የሞቀው ሀገር ያወቀው ጉዳይ ነው። ክስተቱ ቅስም ሰባሪ እና የአንድ እንቁ ኢትዮጵያዊ ህይወት በጭራቆች በመጥፋቱ አዝነን ሳናበቃ በሌላ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ሞት መታጀቡ እርግማን እንዳለብን የሚያስረግጥልን መሆኑን ያሳያል። ህይወት ብቻ አይደለም የተቀጠፈው። ዜጎች እድሜ ዘመናቸውን ጥረው ግረው ያፈሩት ሀብታቸው ጭምር ነው በአንድ ሌሊት ወደ አመድነት የተቀየረው። ይህም ሳያንስ ብጥብጡ ሌላ መልክ እንዲይዝ እና የእልቂቱ ገበያ ይበልጥ እንዲደራ የቋመጡ የፖለቲካ ሴራ ተዳዳሪዎች የሚቻላቸውን ሁሉ አደረጉ። ወጣቱን ማገዱት። በተፋፋመው እሳት ደግሞ እንደልማዳቸው ዳር ቆመው ይሞቁ ጀመር። አይገባቸውም እንጂ ይህ የራሳቸው ሞት ነበር። እዚህ ላይ የዛሬ አብሮነት ብቻ አይደለም የደፈረሰው። ትልቁ እና ለኔ በጣም አሳሳቢው የነገ የጋራ ተስፋችን ነው በአፍጢሙ የተደፋው። ጠላት ዛሬ ከሩቅ አይደለም የሚመጣው። ከጎንህ ያለው ጎረቤትህ ድንገት አራስ ነብር ሆኖ ብድግ ይልብሃል። የምታውቀው አብሮ አደግህ ከመቅፅበት ተለውጦ አውሬ ሆኖብህ “በለው፣ ግደለው” እያለ ጦሩን ሲሰብቅብህ ከናካቴውም ሰው መሆንን ትጠላለህ። መፈጠርህን ትረግማለህ። ትናንት በሞራል ልዕልና ብዙ የተባለላትን እናት ሀገር ኢትዮጵያን እንደማታውቃት ከራስህ ጋር ትስማማለህ። ይህ ሁሉ ሲሆን ኮሮናም ዳር ቆሞ ያጨበጭባል። አይ የኢትዮጵያ ልጆች!
የሀገር ቤቱ እንካሰላንቲያ አልበቃ ብሎ ኑሮን ለማሸነፍ በስደት ላይ ያሉ ወገኖቻችንም በያሉበት ሀገር ጎዳና ላይ ወጥተው ሲቃወሙ ተደምጠዋል። ምናልባትም በርከት ያለ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን ባለፈው ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አቀባበል ካደረጉ ወዲህ ይህ የመጀመሪያው ይመስለኛል። ልዩነቱ የያኔው የክብር እና የፍቅር ሲሆን የአሁኑ ደግሞ የፈለጋችሁትን በሉት የውርደት ብየዋለሁ በግሌ። የኢትዮጵያ የአእምሯዊ
ንብረት እንደሆነ የሚነገርለት የዳውን ዳውን ትግል በበርካታ የአውሮፓና የሰሜን አሜሪካ ከተሞች በስፋት ሲካሄድ ሰንብቷል። መሰለፋቸው እና ሀገር ቤት ላለው ቃጠሎ ድምፃችን ሆነው ድምፃቸውን ማሰማታቸው አይደለም ችግር የነበረው። ይህ እነርሱ በሚኖሩበት የሰለጠነው የምዕራቡ ዓለም ቋሚ ባህል ነው። ችግሩ የአንዲት ኢትዮጵያ ልጆች ሀገር ቤት ላለው ቀውስ ማዶ ለማዶ ቆመው ያውም በሰው ሀገር እርስበርስ ሲላተሙና የተቃውሞ አፈሙዛቸውን ሲደቃቀኑ ነው። እጅግ የሚያሳፍር ክስተት። የሞተውም የገደለውም የአንድ እናት የአንድ አባት ልጆች፣ ችግሩም እዚሁ ሀገር ቤት ሆኖ ሳለ ይህን የዘመዶቻቸውን ሰቆቃ ባንድነት ተሰልፈው ለተቀረው ዓለም እንደማሰማት ሁለት ኢትዮጵያ ያለች ይመስል የውርደት ሰልፍ ሲያካሄዱ ተመልክተናል። ቢያንስ በስደት ሀገር ያለ ኢትዮጵያዊ ሀገር ቤት ካለው ይበልጥ አንድነቱ ጠንካራ ነው ብዬ ነበር የማስበው። ግን አይደለም። ይህ ነውር ነው። እኛ መች ሞልቶላቸው ያሰቡት ተሳክቶ በሰላም ወደ እናት ሀገራቸው ተመልሰው አብረን እንኖራለን የሚለውን ስናስብ እነርሱ እዚያው በባዕድ ሀገር ጎራ ለይተው ሲቧቀሱ እያየን ዝም ብሎ ማለፍ የለብንም።
ህፃናት ዛሬ ተምረው እውቀትን ካልገበዩ ሀገርን ለማንም ሳናስረክብ ሜዳ ላይ ትተን እየሄድን ነው ማለት ነው። ልጆቻችን አመቱን ሙሉ አልተማሩም ማለት ይቻላል። በዚያ ላይ መንግስት በቅርቡ ቢማሩም ባይማሩም፣ ቢገባቸውም ባይገባቸውም ክፍል እንዲቆጥሩ ሁላችሁም አልፋችኋል አይነት አዋጅ ማስነገርም ይበልጥ ድድብናን ማንገስ ሆኖ ይታየኛል። ዞሮ ዞሮ ትውልድን ዛሬ ላይ ቀብረን ሀገርን ያለ ተረካቢ ባለቤት እንዳናስቀር ማስተዋል ይኖርብናል። ከሶስቱ የክረምት ዝናባማ ወራት ነሐሴ እጅግ ያስፈራል። መስከረም ከመጥባቱና እንቁጣጣሽ ከመግባቱ በፊት እንዲሁም ክረምትን ከመሰናበታችን በፊት ያለ የአሮጌው መጨረሻ እና የአዲሱ ዋዜማ ነው። ነሐሴ ላይ ሆነህ አዲሱን አመት በቅርበት አሻግረህ ታየዋለህ። ለመሸጋገር ግን የነሐሴን ጎርፍ መጠንቀቅ ይኖርብሃል።
ይህን ፅሁፍ እያዘጋጀው ሳለ አንድ ደስ የሚል ዜና ሰማሁ። ምናልባትም ከፍ ሲል የጠቀስኩትን የአዲስ አመት ተስፋ የሚያበስር ነገር ነው። የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት በተሳካ መልኩ መከናወኑን በመጥቀስ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ያስተላለፉልን የብስራት ዜና። ፈጣሪ በዚሁ አያያዝ አዲሱን አመት የብልጽግና ያድርግልን ምኞቴ ነው።ቸር ያቆየን እንገናኛለን።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 17/2012
ሐሚልተን አብዱልአዚዝ