ሰርተው መብላት የሚችሉ እጆች በተለያየ ምክንያት ለእርዳታ ሲዘረጉ ምናልባት ሰጪው ደስታም እርካታም ቢኖረውም፤ ለተቀባዩ ግን አንገት መድፋትን በሰዎች ፊት መለብለብን ማስከተሉ አይቀሬ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በልቶ ማደር ግድ ነውና ሁሉን ችሎ እጅ ለመዘርጋት፤ የተሰጠንም ለመቀበል ያስገድዳል፡፡ በተለይ በዚህ ዘመን ከጎዳና ሆኖ ስራ ሰርቶ ማደር በሚቻልበት ሁኔታ ውስጥ ሴት ልጅ ያውም ሁለትና ሶስት ልጆችን ይዛ በጎዳና ወይም በሸራ ተጠልላ ይሄን አለማድረግ እንዴት ይቻላል?
ይሄን እንድል ያስገደደኝ ከሰሞኑ በማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር ላይ ያገኘኋቸው እናቶች ስሜት ነው፡፡ እነ ወይዘሮ ዴሎ ዱጋ እና እነ ወይዘሮ ትዕግስት ምስጋናውን ጨምሮ 50 ሰዎችን ከጎዳና ደርሶ የተመለከተው ይህ መርሃ ግብር በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት የተዘጋጀ የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር ነበር፡፡ ድርጅቱ ከ105 እስከ 110 ሺህ ብር በመመደብ ለ50 የጎዳና ሰዎች በፊንፊኔ ባህል አዳራሽ እየተገኙ ለአንድ ወር ምሳ እንዲመገቡ የሚያስችላቸውን መርሃ ግብር ያለፈው ማክሰኞ አስጀምሯል፡፡
በመርሃ ግብሩ ተሳታፊ ከሆኑ እናቶች አንዷ ወይዘሮ ዴሎ ዱጋ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ የሚኖሩት ሸራ ቤት ውስጥ ቢሆንም፤ የሰው እጅ ከማየት በሚል ቀደም ሲል ሰው ቤት ልብስ አጠባ ይሰሩ ነበር፡፡ አሁን ግን ቤቶቹም ስለፈረሱ፤ በሽታውም ስለመጣ ስራውን ሰርተው መኖር አልቻሉም፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ለእለትም ቢሆን በዚህ መልኩ ምሳ እንዲበሉ መደረጉ እፎይታን የሰጣቸው ቢሆንም፤ ከክረምቱም ሆነ ከኮሮና ወረርሺን ጋር ተያይዞ ችግራቸው ከፍ ያለ ነው፡፡ በተለይ ሶስት ልጆችን ይዞ ያለ መጠለያ በክረምት የሚያጎርሱት ሳይኖር በጎዳና ላይ ማደር ችግሩን የሚያገዝፈው ነው፡፡
ህይወትን ለማሸነፍ ቡናና ሌሎች ስራዎችን የሞከሩ መሆኑን የሚናገሩት ወይዘሮ ዴሎ፤ ሰርተው ማደርና ከራሳቸውም አልፎ ለሌላ መትረፍ በሚችሉበት እድሜ የሰው እጅ መመልከት እጅጉን ህሊናም የሚያሳምም፤ ሰው ፊት ቆሞ ድጋፍ መቀበሉም አንገት የሚያስደፋ ስለመሆኑ ይገልጻሉ፡፡ ለእንዲህ አይነት ኑሮና ለሸራ ቤት የተዳረጉት በ2004 ላይ በመንገድ ምክንያት ቤታቸው ስለፈረሰባቸው እና ቤት እንዲሰጣቸው የሚመለከታቸውን አካላት ቢጠይቁም ምላሽ በማጣታቸው ምክንያት እስከዛሬም ቤት ማደር እንደናፈቃቸው ይገልጻሉ፡፡ ይባስ ብሎም ሰሞኑን ቤት እየፈረሰ እንደመሆኑ የሚኖሩባት ሸራ ቤትም ትፈርሳለች በሚል ተነሱ በመባላቸው ያለችንን ቡቱቶ አስረን ቁጭ ብለናል ይላሉ፡፡ በመሆኑም ከህዝብም ሆነ ከመንግስት በመጠለያም በድጋፍም ከጎናቸው በመሆናቸው ሰርተው የመለውጥ ብርቱ ጉጉት እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡
እንደ ወይዘሮ ዴሎ ሁሉ፣ ወይዘሮ ትዕግስት ምስጋናው በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት ሚካኤል ቤተክርስቲያን ውስጥ የምትኖር እናት ናት፡፡ የሶስት ልጆች እናት መሆኗንና እንደሷው ሁሉ በጎዳና የሚኖሩ በርካታ እህትና ወንድሞች መኖራቸውን የምትገልጸው ወይዘሮ ትዕግስት፤ ልጆች ይዞ ያውም በክረምት የሚበላና የሚለበስ በሌለበት ያለመጠለያ እጅጉን ከባድ ስለመሆኑ ታስረዳለች፡፡
ቀደም ሲል የሰው ልብስ አጥበንና አሻሮ ቆልተን ነበር የምንተዳደረው የምትለው ወይዘሮ ትዕግስት፤ አሁን በኮሮና ወረርሺኝ ምክንያት ያ ሁሉ በመቅረቱንና ስራም ባለመኖሩ ምክንያት ቢያንስ ክረምቱም ማሳለፊያ የምትሆን ቤት ለመከራየት ቀርቶ ጎርሶ ማደር የሚቻልበት አቅም መጥፋቱን ትገልጻለች፡፡ በፊት ማንኛውም ሰው ጠርቶ ልብስ እጠቢልኝ ይል የነበረው አሁን ለፈጣሪ ሰላምታ ሁሉ ሸሸን፤ በዚህ በከፋ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ የደረሱላቸውን በማመስገንም፤ ለአንድ ወር ቀርቶ ለአንድ ቀን በልቶ ማደርም ትልቅ ነገር መሆኑን ታስረዳለች፡፡
እኛ ሰርተን መለወጥ የምንችል ሰዎች ነን፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ ከህብረተሰቡም ሆነ ከመንግስት ድጋፍ ቢደረግልን መልካም ነው፡፡ በተለይ አሁን ላይ ለጎናችን ማረፊያ የምትሆን ቤት ብናገኝ፤ ለእለት ጉሮሯችን ብንችል ሰርተን ባናገኝ ለምነን ለማደር አንቸገርም፡፡ ሆኖም መንግስትም ሆነ ህዝብ ችግራችንን ተመልክቶ ራሳችንን ችለን ሰርተን የምንኖርበት እድል ሊፈጥሩንል ይገባል፡፡ ምንም እንኳን ሁለትና ሶስት ልጆች ያሉን ብንሆንም አብዛኛው ወጣት በመሆኑ የስራ ቦታ ቢሰጠንም እንሰራለን፡፡ ግን እንዴት አድርጎ መስራት ይቻላል ስትል ትጠይቃለች፡፡
ምክንያቷ ደግሞ እኔ አንድ ቦታ ካልሲ ይዤ ብቀመጥ ደንቦች መጥተው ከወሰዱብኝ ከማግኘት ይልቅ ኪሳራ እንደሚሆንባት ትገልጻለች፡፡ በመሆኑም በዚህ በኩል ያለውን አሰራር ማሻሻል በራሱ በርካቶች ሰርተው እንዲበሉ ብቻ ሳይሆን ጎዳና እንዳይወጡ የሚያደርጋቸው ስለመሆኑም ታስረዳለች፡፡ ለእርሷም ከጎዳና አለመነሳት ምክንያት የሆናት ቀደም ሲል ሻይ ቡና ትሰራ በመነበረት ወቅት የሻይ ቡና እቃዋን ስለሰባበሩባት እንደሆነ ትገልጻለች፡፡ ይህ ደግሞ በደንቦች አሰራር ባለው የጥቅም ወይም እጅ መንሻ መልመድ ምክንያት እንደሆነም ትናገራለች፡፡
ሌላዋ የምሳ ማዕድ ማጋራት ተካፋይ የሆነችው የሁለት ልጆች እናትና የአምስት ወር ነፍሰጡሯ ወይዘሮ መሰረት ጌታቸው እንደምትለው፤ ያገኙትን እየተመገቡና በአንዳንድ ለጋስ ሰዎች ድጋፍ ልጆቻቸውን እያሳደጉ ካሉ ቴዎድሮስ አደባባይ አከባቢ በመጠለያ ውስጥ ከሚኖሩ እናቶች አንዷ ናት፡፡ ይሁን እንጂ ያ መጠለያቸው በቅርቡ በመፍረሱ ለህጻናት የሚያለብሱት ልብስና ጎናቸውን የሚያሳርፉባት ብጣሽ ፋራሽም ተቃጥላባቸዋለች፡፡ እናም ሁለት ልጆች ይዛ ሸራ እንኳን ወጥረው ለመኖር ያልቻሉበት እድል ተፈጥሯል፡፡
የድሃ ድሃ ተብለው የተያዙ ቢሆንም፤ ቤታቸው ሲፈርስና ልብስና ፍራሾቻቸው ሲቃጠል ወረዳው አናውቃቸውም እንዳላቸው የምትናገረው ወይዘሮ መሰረት፤ ይህ ሁኔታ ሸራ ለብሰው እንዲኖሩ ብቻ ሳይሆን ኑሮን በእጅጉ እንዳከበደባቸው ትናገራለች፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ በዚህ ድርጅት የተደረገላቸው የምሳ መብላት መርሃ ግብር ቢያንስ ልጆቻቸውን አጉርሶ ለማደር እንደሚያስችላቸው በመግለጽም፤ ይሄን አይነት ድጋፍ ብቻውን የእለት ጭንቀትን ከማቃለል የዘለለ ችግሮቻቸውን በዘላቂነት የሚፈታ ባለመሆኑ በህዝብም ሆነ በመንግስት በኩል ራሳቸውን ችለው ከተረጂነት የሚወጡበትን እድል ሊፈጠርላቸው እንደሚገባ ትናገራለች፡፡ እርሷም ቢሆን ከዚህ አይነት የእለት እርዳታ ይልቅ የተወሰነ ድጋፍ ብታገኝ ሰርታ መለወጥ እንደምትችልና ይሄን የማድረግ ዓላማም እንዳላት ትናገራለች፡፡
ወይዘሮ ዝይን ገድሉ፣ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት የኮሚዩኒኬሽንና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ቺፍ ኦፊሰር ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ ያለንን ነገር ለሌላቸው ለሌሎች ዜጎችና የህብረተሰብ ክፍሎች ማጋራት እንደ ሰውም ሰዋዊ ተግባር፤ እንደ ተቋምም የማዕድ ማጋራት አገራዊ አቅጣጫ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለዜጎች አለንላችሁ፤ ከጎናችሁ ነን የሚለውን ስሜት የሚፈጥር ሲሆን፤ እንደ ኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅትም ይሄን ሲያደርግ ማህበራዊ ሃላፊነቱም የሚወጣበት አንዱ መንገድ አድርጎ በመውሰድ ያከናወነው ነው፡፡
የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት አንጋፋ ተቋም እንደመሆኑ ከሚሰጠው አገልግሎት ባሻገር በርካታ ማህበራዊ ሃላፊነቶችን ሲወጣ እንደቆየ የሚናገሩት ወይዘሮ ዝይን፤ ይሄን የማዕድ ማጋራት ሲያከናውንም አንድም ለህዝብ ያለውን ወገንተኝነት ለማሳየት፤ ሁለተኛም አገራዊ የማዕድ ማጋራት ጥሪውን ለመፈጸም መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሰረት ለአንድ ወር የሚቆይ የምገባ መርሃ ግብር የጀመረ መሆኑን በመጠቆም፤ አንዳችን የሌላችን ጠባቂ እንደመሆናችንም በመርሃ ግብሩ 50 የጎዳታ ተዳዳሪ ሰዎችን ምሳ እንዲበሉ ማድረግን ታሳቢ ያደረገ ሆኖ የሚተገበር መሆኑን አስረድተዋል፡፡
እንደ ወይዘሮ ዝይን ገለጻ፤ ድርጅቱ ከዚህ ቀደም አረጋውያንን ይደግፋል፤ ወላጅ የሌላቸው ህጻናትን ይደግፋል፤ ለዚህም የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችን በማቅረብና የትምህርት ክፍያን ጭምር በመክፈል ማህበራዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ ያለ ነው፡፡ በማዕድ ማጋራት ዘመቻው የምሳ ማብላት መርሃ ግብሩ ተሳታፊ የሆኑ ሰዎች የተመረጡት ከልደታ ክፍለ ከተማ ሲሆን፤ በአመዛኙም በኮቪድ 19 ወረርሺኝ ምክንያት ተንቀሳቅሰው መስራትና የእለት ችግራቸውን እንኳን ማለፍ ያልቻሉ በከፋ ችግር ውስጥ ያሉ ሴቶችና ህጻናትን ያቀፈም ነው፡፡ ወደፊትም ይሄንን ማህበራዊ ሃላፊነቱን የሚወጣ ሲሆን፤ በቀጣይም ያለውን ሁኔታ በማየት በሚፈለገው ቦታ ላይ ድጋፉ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ሐና ዓርኣያ ሥላሴ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ድርጅቱ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ለ126 ዓመታት በተለያየ መልኩ ሲያገለግል የቆየ ድርጅት ነው፡፡ ከሚሰጣቸው መደበኛ ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች ባለፈም ማህበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ይገኛል፡፡ በእለቱ ከጀመረው የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር ባሻገርም የተለያዩ ግለሰቦችና ተቋማትን በችግሮቻቸው ከጎናቸው በመቆም እያገዘ ያለ ድርጅት ነው፡፡
በእለቱ የተጀመረው የ50 ሰዎች የምሳ ማዕድ ማጋራት ወጪ የተሸፈነው ከድርጅቱ ትርፍ ላይ ሲሆን፤ በቀጣይም በእለቱ የተገኙ ቤተሰቦችን ጨምሮ ሌሎችንም ሰዎች ቋሚ በሆነ መንገድ መርዳት በሚቻልበት ሂደት ላይ ከሌሎችም ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋር እየተመካከሩ ይገኛል፡፡ በዚህም ከማዕድ ባለፈ ለቤታቸው የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማሟላት በድርጅቱም በሰራተኞችም በኩል አስፈላጊውን መዋጮ በማዋጣት እየተሰራ ነው፡፡ ይህ ሲሆን ድጋፉ በገንዘብም በአይነትም የሚደረግ ሲሆን፤ ድጋፉም ዓመቱን በሙሉ እንዲቀጥል ጥረት ይደረጋል፡፡
ይህ መረዳዳት በህዝቡ ባህል ውስጣ ያለ ቢሆንም እንደ ድርጅት ግን ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን በመወጣት ረገድ ብዙ መስራት እንዳለባቸው የሚናገሩት ወይዘሮ ሐና፤ በእንደዘህ አይነት ችግር ወቅት ድርጅቶች ለወገን ደራሽነታቸውን በማረጋገጥ ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ይገልጻሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ገንዘብ በመስጠት ብቻ ሳይሆን የሃሳብ ድጋፍን ጨምሮ በተለያየ መልኩ በማከናወን ለወገን አለኝታነትን ማረጋገጥ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ ድጋፉ ቀጣይነት እንዲኖረውም ተቋማት ከሰራተኞቻቸው ጋር በመነጋገርና በማሳተፍ ችግሮችን ሊለዩና ሊረዱ የሚገባቸውን ሰዎች በትክክል ተረድቶ ተገቢውን ድጋፍ በተገቢው ቦታ ማድረስ እንዳለባቸውም መክረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 17/2012
ወንድወሰን ሽመልስ