በሱማሌ ክልል በተፈጠረው ግጭት እጃቸውን በማስገባት ወንጀል ሰርተው ከሀገር የወጡ የቀድሞ የሱማሌ ክልል ባለስልጣናትን ወደሀገር በመመለስ በህግ ተጠያቂ ለማድረግ ከተሸሸጉባቸው ሀገራት ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አስታወቀ።
የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱኑ ዛሬ ከሰዓት በኋላ በፅ/ቤታቸው በሰጡት መግለጫ በሱማሌ ክልል ተፈጥሮ በነበረው ግጭት የሰው ህይወት እንዲጠፋ፣ ህገመንግስታዊ ስርዐትን ለመናድ በመንቀሳቀስ ንብረት እንዲወድምና በተያያዥ ወንጀሎች 46 ያህል ተጠርጣሪዎች ተለይተዋል።
ከእነዚህ ውስጥም ስድስት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ሌሎቹ 40 ግን በሀገር ውስጥና በውጪ ሀገር ተሸሽገዋል ብለዋል።
አቶ ዝናቡ ተጠርጣሪዎቹ የተሸሸጉባቸውን ሀገራት ከመግለፅ ተቆጥበዋል፡፡
እንደ አቶ ዝናቡ ገለፃ ከሀገር የወጡ ባለስልጣናትን ወደሀገር በመመለስ በህግ ተጠያቂ ለማድረግ ከተሸሸጉባቸው ሀገራት ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን በሀገር ውስጥ የተደበቁትንም አፈላልጎ በህግ ተጠያቂ ለማድረግ እየተሰራ ነው።
የተወሰኑ ተጠርጣሪዎች ያለመከሰስ መብት ያላቸው በመሆኑ መብታቸውን በማንሳት በቁጥጥር ስር ለማዋል ስራዎች እየተሰሩ ነው ተብሏል።
ተጠርጣሪዎቹ አሁን የተጠረጠሩት ከሀምሌ 28-30/2010 ዓ.ም በሱማሌ ክልል በተፈጠረው ግጭት ጋር በተያያዘ ብቻ ሲሆን በክልሉ የተፈፀሙ ሌሎች የሰብዐዊ መብት ጥሰቶችም እየተጣሩ ነው ተብሏል፡፡
ለአብነትም በጅምላ ከተቀበሩ 200 ግለሰቦች ውስጥ የ37ቱ አስከሬን የወጣ ሲሆን የሌሎቹን ጉዳይም በቅርበት እየተሰራ ነው ብሏል ዐቃቤ ህግ በመግለጫው፡፡
ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ትልቅ ዝግጅት ተደርጓል ያሉት አቶ ዝናቡ ህዝቡ የተሸሸጉ ግለሰቦችን አሳልፎ በመስጠት ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ አስተላልፈዋል።
በድልነሳ ምንውየለት