የሚያዩዋቸውን ችግሮች ወደስራ ፈጠራ በመቀየር ይታወቃሉ። በሰሯቸው የፈጠራ ስራዎችም ለበርካታ ችግሮች መፍትሄ አበጅተዋል። ይህንኑ የስራ ፈጠራ ተሰጧቸውን በመጠቀምም የራሳቸውን የወተት ማቀነባበሪያ እስከ መክፈት ደርሰዋል። በዚሁ ማቀነባበሪያቸውም ለበርካታ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል ፈጥረዋል። አሁንም ልዩ ልዩ የፈጠራ ስራዎችን እየሰሩ ሲሆን፣ በዚሁ የፈጠራ ስራ ችሎታቸው በመተማመን ቀደም ሲል የከፈቱትን ፋብሪካ ወደ ሌላ ዘርፍ እየቀየሩት ይገኛሉ -የአለሚ ትኩስ ወተት ፋብሪካ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ አስማማው ታፈሰ።
አቶ አስማማው ታፈሰ የተወለዱት በአርሲ ነገሌ ገጠራማ አካባቢ በሰቆ በተሰኘች ወረዳ ነው። በ1983 ዓ.ም ልክ ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ሲመጣ በልጅነታቸው ወደ ሃዋሳ ከተማ ገብተው አደጉ። በትውልድ ሀገራቸው ያቋረጡትን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ከአራተኛ ክፍል በመቀጠል እስከ ስድስተኛ ክፍል ድረስ በዛው ሀዋሳ ተከታትለዋል።
በወቅቱም የወፍጮ ቤት ጋሪ በመግፋት፣የመኪና ወንበሮችን በመጠገን፣ በመኪና ረዳትነትና በአሽከርካሪነት የተለያዩ ስራዎችን ሰርተዋል። ሥራቸው ከትምህርት ጊዜያቸው ጋር በመጋጨቱ በማታው መርሃግብር የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ከአስራ አንደኛ ክፍል ወደ አስራ ሁለተኛ ክፍል ከተሸጋገሩ በኋላ አቋርጠዋል። በረዳትነትና በአሽከርካሪነት ስራ ላይ እያሉ ቀደም ሲል ተቀጥረው ይሰሩበት የነበረው የመኪና ወንበር ጥገና ስራ በአእምሯቸው ውስጥ ተቀርፆ የነበረ በመሆኑ የራሳቸውን የወንበር ጥገና ከፍተው መስራት ጀመሩ። ይህንኑ ስራ እየሰሩም በ1993 ዓ.ም ትዳር መሰረቱ።
በትውልድ አካባቢያቸው አርሲ ነገሌ ከፍተኛ ወተት እንደሚመረትና ከዚህ በተቃራኒ በወቅቱ በሃዋሳ አካባቢ ከፍተኛ የወተት እጥረት እንዳለ የተገነዘቡት አቶ አስማማው፤ ከአርሲ ነገሌ ወተቱን ከገበሬዎች በመሰብሰብ ሃዋሳ ላይ ለመሸጥ አሰቡ። ታናሽ ወንድማቸው አርሲ ነገሌ ላይ ወተቱን እንዲያሰባስቡ ካደረጉ በኋላ ሃዋሳ በመውሰድ ወተቱን መሸጥ ጀመሩ። ይህንኑ የወተት ንግድ ቀስበቀስ በማስፋፋት ሂደትም ሰብስበው ለገበያ የሚያቀርቡት ወተት እየባከነ ሲያስቸግራቸው የፈጠራ ስራ ተሰጥኦዋቸውን በመጠቀም ከትንሽ እስከትልቅ የወተት መናጫዎችን አሻሽለው በመስራት ጥቅም ላይ አዋሉ።
ለገበያ የሚያቀርቡት ወተት ለምን ፓስቸራይዝድ አይሆንም የሚል ሃሳብ በመሃል ስለመጣላቸው በሀገሪቷ የሚገኙ የወተት ፓስቸራይዝድ ማሽኖችን ጎበኙ። እነዚህኑ የፓስቸራይዝድ ማሽኖች ቴክኖሎጂ በጥልቅ ከተመለከቱ በኋላ የፈጠራ ችሎታቸውን በመጠቀም በአንድ ጊዜ 100 ሊትር ወተት ፓስቸራይዝድ የሚያደርግ ማሽን ሰሩ። ለወተት ማቀዝቀዣ ደግሞ ቺለር ተጠቀሙ። ማሸጊያዎችን ደግሞ ከቻይና በማስመጣት ወተት ወደማቀነባበር ስራው ገቡ። አይብ፣ ቅቤ፣እርጎም አዘጋጅተው ለገበያ ማቅረብ ጀመሩ። በወቅቱም አርባ ሰባት ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር ቻሉ።
የወተት ማቀነባበር ስራውን ለሶስት አመታት ያህል እንደሰሩም በ2006 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ 9 ሚሊዮን 128 ብር እንደተፈቀደላቸው አዲስ የወተት ማቀነባበሪያ ማሽን በመግዛት ፋብሪካውን ሀዋሳ ላይ ተከሉ። ይህን ትልቅ ፋብሪካ በ2007 ዓ.ም በ27 ሚሊዮን ብር ወጪ ወደስራ ካስገቡ በኋላም 115 ለሚሆኑ ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ አድል ፈጥረዋል።ፋብሪካው በቀን እስከ 20 ሺ ሊትር ወተት የማቀነባበር አቅም ያለው ሲሆን፣ፓስቸራይዘድ ወተት፣የተለያዩ ጣዕም ያላቸውን እርጎዎችንና ቅቤዎችን ያመርታል።
ፋብሪካው ተቋቁሞ ወደስራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ በሃዋሳና አካባቢው የወተት ነጋዴዎች እየጨመሩ መጥተዋል። በዚህም ምክንያት ወተት ወደ ፋብሪካ የሚያቀርበው ነጋዴ ቁጥር እየቀነሰ በመምጣቱና ጥሬ ወተት ሻጭ በመጨመሩ የወተት እጥረት ተከስቶ አዋጭነቱ ላይ ችግር ያጋጥም ጀመር።
ይህንኑ ችግር ለመቅረፍም ፋብሪካው ገበሬዎችን የሚያሰለጥንና ጥራት ያለው የወተት ምርት እንዲያመርቱ የሚያስችል ራሱን የቻለ ኢንሰቲትዩት አቋቁሟል።በወተት ማሽን ኦፕሬተርነት ስልጠናዎችን መስጠትና ወደ ወተት ማቀነባበር ዘርፍ ለመግባት ፍላጎት ላላቸውም የማማከር ስራዎች ተሰርተዋል። ለወተት የሚሆኑ ላሞችን ለማርባት የተደረገው ጥረትም እስከ ፌደራል ድረስ መሬት እንዲሰጥ ጥያቄ ቢቀርብም በቂ ምላሽ ባለማግኘቱ ሊሳካ አልቻለም። በዚህም ፋብሪካው ጫናውን መቋቋም ባለመቻሉ በአሁኑ ወቅት ለኪሳራ ተዳርጓል። ከተቋቋመ አምስት አመት ያስቆጠረው ፋብሪካው ባሳለፍነው በጀት አመት ብቻም 7 ሚሊዮን ብር ኪሳራ አጋጥሞታል።
ይህንንም ተከትሎ አቶ አስማማው የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካውን ከማስቀጠል ይልቅ የፈጠራ ችሎታቸውን በመጠቀም ወደ ባህላዊ የአልኮል መጠጦች ማቀነባበሪያነት በተለይም አረቄን በዘመናዊ መልክ አቀነባብሮና አሽጎ ለሃገር ውስጥና ለውጪ ገበያ ለማቅረብ እየሰሩ ይገኛሉ። ከዚሁ ጎንለጎንም ፋብሪካው ሳኒታይዘርም ወደማምረት እንዲሸጋገር እንቅስቃሴ ጀምረዋል። የፈጠራ ችሎታቸውንና እውቀታቸውን በመተማመንም ቀደም ሲል ለወተት ማቀነባበሪያነት ይውሉ የነበሩ ማሽኖችን ለአልኮልና ሳኒታይዘር ማቀነባበሪያነት እንዲውሉ በማድረግና አዳዲሶችንም በመጨመር በፋብሪካው ውስጥ ሲሰሩ የነበሩ ሰራተኞችንም በመያዝና ሌሎችንም በመጨመር ፋብሪካውን ለማስቀጠል እየሰሩ ይገኛሉ።
ለዚሁ ስራ የሚረዱ አዳዲስ ማሽኖችንም በማምረት ላይ ናቸው። ከዚሁ ጎን ለጎንም የወተት ማቀነባበሪያ ማሽኖችን የመቀየር ስራም እየሰሩ ይገኛሉ። ቀደም ሲል ለፋብሪካው ወተት ሲያቀርቡ የነበሩ ገበሬዎችም ሌላ ገበያ እንዲያፈላልጉ የአንድ ወር ጊዜ ተሰጥቷቸዋል። ከፋብሪካው ወተት ሲረከቡ የነበሩ ሆቴሎችና ካፍቴሪያዎችም ገበያቸው እንዳይስተጓጎል አማራጭ እንዲወስዱ በተመሳሳይ የአንድ ወር ጊዜ ተሰጥቷቸዋል። ለምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የብቃት ማረጋገጫ ማመልከቻም ገብቶ ለአልኮል ስራዎች የሚያስፈልጉ መስፈርቶች እየተሟሉ ይገኛሉ።
ከሚያዩዋቸው ችግሮች በስተጀርባ አንድ መፍትሄ እንዳለ የሚያምኑት አቶ አስማማው፣ የስራ ፈጠራ ችሎታቸውን በመጠቀም ለነዚህ ችግሮች መፍትሄ ያበጃሉ። በዩ ኤስ አይ ዲ አማካኝነት በክልሎች ለሚገኙ ዩኒየኖች፣ ማህበራትና ወተት አቀነባባሪዎች አንድ መቶ የወተት ማቀነባበሪያ ማሽኖች ተሰጥተው ነበር። ይሁንና እነዚህ ማሽኖች መለዋወጫ እቃዎች የሚጎላቸው የነበረ በመሆኑ አቶ አስማማው መለዋወጫ እቃዎችን ዲዛይን በማድረግና በመገጣጠም 76 ያህሉን አጠናቀዋል። ለቀሪዎቹ ማሽኖችም መለዋወጫዎቹን በራሳቸው ዲዛይን በማድረግ እየገጠሙ ይገኛሉ።
አቶ አስማማው በአርሲ ነገሌ አካባቢ አረቄ በብዛት የሚመረት መሆኑን በመገንዘብና አረቄውን ለማምረት እናቶች የሚያወጡትን ጉልበት በመረዳት በቀን እስከ ሶስት በርሜል አረቄ ሊያወጣ የሚችልና በኤሌክትሪክ፣እንጨትና ባዮጋዝ የሚሰራ የአረቄ ማውጫ ማሽን አሻሽለው ሰርተዋል። ይህንኑ የአረቄ ማውጫ ማሽንም ለገበያ አቅርበዋል።
ሃዋሳ ከተማ ሃምሳኛ አመቷን ስታከብር 50 ሜትር የሚረዝም ኬክ በማዘጋጀት ሂደት ሃሳብ አመንጭተዋል፤ አብረውም ጋግረዋል። የሀዋሳ እድገትን የሚያሳዩ የተለያዩ ተሽከርካሪ መድረኮችንም ሰርተዋል።ከስራ ፈጠራቸው በላይ ደግሞ በቆጂን፣ ባህርዳር፣ ደብረብረሃንና ኮምቦልቻ የሚገኙና በቅርቡ ወደስራ የሚገቡ ወተት ፋብሪካዎች ማሽኖችን ተክለዋል። በርካታ የወተት ማሸኖችንም ጠግነዋል። በዚህ የፈጠራ ስራ ችሎታቸውም ከክልሉ ተደጋጋሚ ሽልማቶችን አግኝተዋል።
ቀደም ሲል ተሰማርተውበት የነበረው የወተት ማቀነባበር ዘርፍ ‹‹ከባድና አደጋም ያለው ነው›› ሲሉ የሚገልፁት አቶ አስማማው፤ኢንዱስትሪው ገና ያልተሰራበት በመሆኑ ይበልጥ ማስተዋወቅ እንደሚገባና ከገበሬው ጀምሮ እስከተጠቃሚው ድረስ ትልቅ ስራ እንደሚጠይቅ ያስረዳሉ። ቀደም ሲል ገበሬው ግጦሽ ሳርን በመጠቀም ወተትን ያመርት እንደነበርም ጠቁመው፣በአሁኑ ወቅት የመሬት ጥበት እየጨመረ በመምጣቱና የግጦሽ መሬትም በመጥፋቱ ሰዎች በከተማ ግብርና በትንሽ ቦታ ላይ ከብቶችን በማሰር ወተት እያመረቱ እንደሚገኙ ይጠቁማሉ።
ይህንንም ተከትሎ የከብቶች መኖ እየተወደደ በመምጣቱ፣ የተሻሻሉ የወተት ከብት ዝርያዎችም በመጥፋታቸው፣ የእንስሳት በሽታዎችም በመብዛታቸውና መድኃኒትም በመጥፋቱ ኢንዱስትሪው ትልቅ ፈተና ውስጥ እንደገባም ይጠቅሳሉ። ዘርፉ በባህሪው ተለዋዋጭ በመሆኑና የገበያው ሁኔታም አንዴ ከፍ ሌላ ጊዜ ደግሞ ዝቅ የሚል ከመሆኑ አኳያና ማህበረሰቡም ወተት የመጠጣት ባህሉ እጅግ አናሳ በመሆኑ ሰፊ ስራ እንደሚጠይቅም ይናገራሉ።
ወተት ለሰው ልጅ እጅግ አስፈላጊ ከመሆኑ አኳያ በወተት ልማት ዘርፍ የሚታየውን ችግር ለመፍታት በቅድሚያ የዘርፉ ፖሊሲ በባለሙያዎች ተጠንቶና ተፈትሾ ችግሮቹ ከተለዩ በኋላ ማሻሻል እንደሚገባ አቶ አስማማው ያመለክታሉ። ወተት ከውጪ ሃገር በዱቄት መልክ ወደሃገር ውስጥ እየገባ በመሆኑና በዚህም መንግስት የውጭ ምንዛሬ እያጣ በመምጣቱ በሀገር ውስጥ በወተት ዘርፍ የሚደረገው ኢንቨስትመንት እስኪያንሰራራ ድረስ መንግስት ዘርፉን መደጎም እንዳለበትም ያመለክታሉ። በተለይ በፖሊሲው ውስጥ ያሉ ችግሮች ከተፈተሹ በኋላ ሰፋፊ የእንስሳት መኖ ኢንዱስትሪዎች የሚቋቋሙበትን መንገድ መፍጠር እንደሚገባውና የከብቶች መኖ በግብርና ተረፈ ምርት ብቻ የትም ስለማያደርስ ራሱን የቻለ መኖ የሚዘራበትና የሚዘጋጅበት አሰራር መዘርጋት እንደሚስፈልግ ያብራራሉ።
ለወተት ልማት ዘርፍ ብድር የሚከፈለው የወለድ መጠን ከሌሎች ዘርፎች ጋር እኩል መሆኑ ተገቢ አለመሆኑን የሚጠቅሱት አቶ አስማማው፤ ወተት ለጤና መሰረታዊ ከመሆኑ አኳያ ቢያንስ ለብድር የሚከፈለው የወለድ መጠን ሊስተካከል እንደሚገባ ይጠቁማሉ። የብድር እፎይታ ጊዜውንም ረዘም ማድረግ እንደሚገባና በዚሁ ዘርፍ ላይ አተኩሮ ለሚሰራ ሰውና ልዩ ልዩ ዘመናዊ ማሽኖችን ወደሃገር ውስጥ ለሚያስገባ ዘርፉን ስለሚያዘምነው መንግስት ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገባ መፍቀድ እንዳለበትም ያመለክታሉ።
ማንኛውም የወተት ፋብሪካ የራሱ ከብት እርባታ እንደሚያስፈልገውና በዚህም የወተት ጥራቱን ማስጠበቅ እንደሚቻልም ይጠቁማሉ። የወተት ገበያው የህግ ማእቀፍ የሌለው በመሆኑ መንግስት ይህን ሊያስተካክል እንደሚገባ ፤ ባለሙያዎችም ወደታች ወርደው የወተት ልማቱን መፈተሽና መከታተል እንደሚኖርባቸውም ይናገራሉ።
‹‹በወተት ማቀነባበር፣ በፈጠራ ስራና አሁን ደግሞ ከወተት ልማት ዘርፍ ወደ አልኮል መጠጦችና ሳኒታይዘር ማምረት ዘርፍ ዕውቀታቸውንና ገንዘባቸውን በማፍሰስ ተሳክቶልኛል›› የሚሉት አቶ አስማማው ፣የስኬታቸው ዋነኛ ሚስጥር ሁሌም አዳዲስ ስራዎችን መፍጠር በመቻላቸውና ለችግሮችም ብልሃት ማበጀታቸው እንደሆነ ይናገራሉ።የፈጠራ ስራዎቻቸው ሁሉ እንደሚሳኩ ራእይ ሰንቀው እንደሚንቀሳቀሱም ገልፀው፤ ያቋቋሙት የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካም ገንዘብ ኖሯቸው ሳይሆን እንደሚሳካ እርግጠኛ ሆነው በመስራታቸው መሆኑንም ይናገራሉ።
አሁን በሚያቋቁሙት አዲስ የመጠጥ አልኮልና ሳኒታይዘር ማምረቻ ፋብሪካ ከ100 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥሩም እርግጠኛ ሆነው የሚናገሩት አቶ አስማማው፤ ይህም ለእርሳቸው ትልቅ ስኬት መሆኑን ይናገራሉ። ከዚህ በፊት ዋነኛ አላማቸው ገንዘብ ማግኘት የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ግን ገንዘቡን በተለያዩ መንገዶች ስራዎችን ሰርተው እንደሚያገኙት ስለሚያወቁ ዋናው ግባቸው ለሌሎችም የስራ አድል መፍጠር መሆኑንም ያስረዳሉ። ሰራ ፈጣሪነታቸውንም እንደ አንድ ስኬት እንደሚቆጥሩትና የፈጠራ ስራቸውን በኢንቨስትመንት በመቀየር ስኬታማ ለመሆን እንደበቁም ይናገራሉ።
የፈጠራ ስራ በዋናነት ገንዘብ እንደሚፈልግ የሚናገሩት አቶ አስማማው፣ የፈጠራ ስራዎችን የሚሰሩ ሰዎች ሰራቸው ወዲያው ይሳካል ብለው ማሰብ እንደሌለባቸው ይገልፃሉ። በስራ ሂደት ወድቆ መነሳት ያለ ነውና ከስህተታቸው ተምረው ተስፋ ሳይቆርጡና ገንዘብን ሳያስቀድሙ ስራቸውን ደጋግመው በመስራት ለስኬት እንዲበቁም ይመክራሉ። ሆኖም የፈጠራ ስራ ወደህብረተሰቡ ገብቶ እንዲያድግና በርካታ የፈጠራ ስራ ባለሙያዎችም እንዲበረታቱ በመንግስት በኩል በርካታ ስራዎች ሊሰሩ እንደሚገባ ያሳስባሉ።
በተለይ መንግስት በቴክኒክና ሞያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ላይ በማተኮር የፈጠራ ስራ ባለሙያዎችን ተሰጥኦ በመለየት ማበረታታትና መደገፍ እንደሚገባው ይጠቁማሉ። በፈጠራ ስራ ሂደት ስራ ፈጣሪዎች ሊበላሹባቸው የሚችሉ እቃዎች በመኖራቸው ይህንን ሊሸፍንላቸው የሚችል አካል ሊኖር እንደሚገባና የፈጠራ ስራቸውም ወደ ኢንዱስትሪዎች ገብቶና በብዛት ተመርቶ ወደህብረተሰቡ ተሰራጭቶ ጥቅም መስጠት እንዳለበትም ያሳስባሉ።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 14/2012
አስናቀ ፀጋዬ