የኮንስትራክሽኑ ዘርፍ ከኢትዮጵያ በጀት 60 በመቶው የሚመደብለት ነው። ዘርፉ በአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት እድገት ውስጥ ከግብርናው ዘርፍ ቀጥሎ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠው ሲሆን፣በስራ እድል ፈጠራም ተጠቃሹ ነው። ዘርፉ ከፍተኛ ሀብት የሚንቀሳቀስበት በርካታ ባለድርሻዎች ያሉትም ነው።
ዘርፉ ከፍተኛ ሀብት የሚንቀሳቀስበትና ለሙስና ተጋላጭ በሚል በአለም አቀፍ ደረጃም ይታወቃል። ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣም የግንባታ መጓተት በስፋት ይስተዋላል። መንግስትን ጨምሮ የዘርፉ ባለድርሻ አካላትም ዘርፉ ሙስና የተንሰራፋበት መሆኑን ይገልጻሉ። በጎንደር ደምቢያ ወረዳ ጯሂት በምትባል ከተማ የተወለዱትና በዘርፉ የሚሰሩት ኢንጂነር ለምለሙ ብዙአለምም ይህን ይጋራሉ ።
ኢንጂነሩ አንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በተወለዱበት ከተማ ጯሂት፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በቆላድባ ጨርሰዋል።ከዛም በኋላ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕንጻ ኮሌጅ ገብተው በቢዩልዲንግ ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፤ በኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂም አድቫንስድ ዲፕሎማቸውን አግኝተዋል።
ኢንጂር ለምለሙ ትምህርታቸውን እንደ ጨረሱ ወደ መንግስት ቤት አላመሩም፤በግል የኮንስትራክሽን ድርጅት ውስጥ በመቀጠር ነው የስራውን አለም የተቀላቀሉት።በተለያዩ የግል የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች ውስጥ በፕሮጀክት መሀንዲስነት እና ማናጀርነት ሰርተዋል።የራሳቸውን የኮንስትራክሽን ድርጅት በማቋቋም መስራት ከጀመሩም ቆይተዋል።
ከኢንጂነር ለምለሙ ጋር በሀገራችን ስላለው የኮንስትራክሽን ዘርፍ ተስፋና መሰረታዊ ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው ዙሪያ አዲስ ዘመን ያደረገውን ቆይታ ለዛሬ ይዞ ቀርቧል። ይከታተሉት።
አዲስ ዘመን፡– ወደ ሥራ አለም መቼ ገቡ ?
ኢንጂነር ለምለሙ፡– ተቀጣሪ ኢንጂነር ሆኜ በመንግስት ቤት ሰርቼ አላውቅም። መጀመሪያ ካቦ ኮንስትራክሽን በሚባል የግል ድርጅት ውስጥ አዲስ አበባ ውስጥ በተቀጣሪነት ለሁለት አመት ተኩል ሰርቻለሁ።ድርጅቱ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች/ፓሎች/ና ሽቦዎችን እያመረተ ለገበያ የሚያቀርብ ነው። አሁን ከተማችን ላይ የምናያቸውን የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች በብዛት ያመርታል።
ካቦ ኮንስትራክሽንን ለቅቄ ከወጣሁ በኋላ አፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን ውስጥ ለአምስት አመት ሰርቻለሁ። ሁሉም ፕሮጀክቶቹ አዲስ አበባ ውስጥ ነበሩ። የኦሮሚያ ባሕል ማዕከል፤ የኦፒዲኦ ጽ/ቤት፤ የአልሳም ባለቤቶች ረጲ ሳሙና ፋብሪካ፤ አዲሱ ምኒሊክ ሪፈራል ሆስፒታል ላይ በፕሮጀክት ማኔጀርነት ሰርቻለሁ። ሳሪስ ኦሮሚያ ግብርና ምርምር ፤ ሳር ቤት ያለው የኦሮሚያ ጽ/ቤቶች ጠቅላላ ግቢ ውስጥ 17ቱ ቢሮዎች የገቡበት ስራዎች ሲሰሩ በፕሮጀክት መሀንዲስነት ሌሎቹን በፕሮጀክት ማኔጀርነት ነው ያገለገልኩት። ከእነዚህ ስራዎች በኋላ ወደ ራሴ የግል ስራ ነው የገባሁት።
አዲስ ዘመን፡–በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማ ራው ድርጅትዎ ማን ይባላል ?
ኢንጂነር ለምለሙ፡– ኤልኤስ ኢንጂነሪንግ ኤንድ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ይባላል። ለምለሙና ሰይድ የኢንጂነሪንግና የኮንስትራክሽን ድርጅት ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡– መቼ ተመሰረተ? የት የትስ ሰራ?
ኢንጂነር ለምለሙ፡– በ2003 ዓ.ም ነው የተቋቋመው።መጀመሪያ እኛ ስፔሻላይዝድ በሆነ ስራ ነው ስራ የጀመርነው፤በዋና ኮንትራክተርነት ሳይሆን በስፔሻል (ልዩ) ኮንትራክተርነት ነው ስራ የጀመርነው።
አዲስ ዘመን፡– ስፔሻል(ልዩ) ኮንትራክተርነት ምንድነው?
ኢንጂነር ለምለሙ፡– በኮንስትራክሽን ኢንዱስት ሪው ውስጥ የተወሰኑ ስራዎችን ለመስራት በወተር ፕሩፊንግ እና በፊኒሺንግ ስራዎች ነበር መጀመሪያ እንቅስቃሴ የጀመርነው። እያደገ ሲሄድ ደግሞ በሙሉ የኮንስትራክሽን ስራ እየሰራን አሁን እቃዎችንም እያስመጣን እንሸጣለን፡
አዲስ ዘመን፡– ምን እቃዎችን ታስመጣላችሁ ?
ኢንጂነር ለምለሙ፡– የአልሙኒየም እቃዎችንና ከዚሁ ጋር የተያያዙ መለዋወጫዎችን (አክሰሰሪስ) ከወተር ፕሩፊንግ ከውሃ ዝቅጠት ጋር የተያያዙ ከዝቅጠት መከላከል ስራ ጋር የተገናኙ እቃዎችንም እናስመጣለን።
አዲስ ዘመን፡– ድርጅታችሁ ከተቋቋመ በኋላ የት የት ሰራችሁ? ዋነኛ የምትሉት የኮንስትራክሽን ስራና ስኬታችሁን ብትገልጹልኝ?
ኢንጂነር ለምለሙ፡– በጣም ብዙ ሰርተናል። የመጀመሪያው ትልቅ የስኬት ስራችን ነው ብለን የምንወስደው ለአዲስ አበባ ውሃ አቅርቦት የሚውለውን
የለገዳዲ የውሃ ስራ ማስፋፊያ ከቻይናዎች ሰብ ኮንትራት/ንኡስ ኮንትራት/ ወስደን የሰራነው ነው። ከዚያ በኋላ የተለያዩ የአልሙኒየም ፕሮጀክቶችና የወተር ፕሩፊንግ ስራዎች፤ ትምህርት ቤቶች፤ ዌር ሀውሶች ( ትላልቅ ግምጃ ቤቶች) ሰርተናል።
በዚህ ላይ በአዲስ አበባም ከአዲስ አበባ ውጭም ብዙ ሰርተናል። በጣም አስቸጋሪ በሆኑ የገጠር ቦታዎች ጭምር ነው እየገባን የሰራነው። ግንደ በረት ከአምቦ ጊንጪ ተገንጥሎ ያለ ቦታ ነው። እዚያው አካባቢ ሰዎች ለሰዎች /ሜንሽን ፎር ሜንሽን/ የተባለ የጀርመን ግብረ ሰናይ ድርጅት እስከ 8ተኛ ክፍል ድረስ ያስገነባውን ትምህርት ቤት እኛ ነን የገነባነው። ትምህርት ቤቱ አንድ ቢሮ አራት መማርያ ክፍሎች ሁለት መጸዳጃ ቤቶች ያሉት ሲሆን፣ ጠቅላላ 7 ህንጻዎችን ሰርተናል።
ተርጫ ደቡብ ክልል ውስጥ የዳውሮ ዞን ዋና ከተማ ነው። በአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ለገበሬዎች የሚሰራ ምርት ለማሳደግ የሚረዳ የዌር ሀውስ ፕሮጀክት ነበር እሱንም የሰራነው እኛ ነን።
በኦሮሚያ ክልልም ሁለት ትምህርት ቤቶች ገንብተናል። የመጀመሪያው ከዩኒሴፍ ወስደን የትምህርት ቤት ስራዎች 3 ቀበሌዎች ላይ ጊንጪ ዙሪያ ጃምጃም ከወለንኮሚ ወጣ እንዳልክ የምትገኝ የገጠር ቀበሌ ነች። ላጋባቱ፤ ጋሪ አሬራ ጊንጪ ከጭልሞ ጫካ ስር ነች። ጎሩ ሶኮሩ የሚባሉ ቀበሌዎች ላይ ትምህርት ቤቶች ሰርተናል። በኮንስትራክሽን በፖስት ኢፊሸንት ጂ ፕላስ 7 አፓርትመንቶች አለም ባንክ ሰርተናል። ጎንደር 01 ወለቃ ቀበሌ የንብ ማነብ ትምህርት ቤት በአሜሪካ ጂውሽ ኤጄጄዲሲ ከሚባል ምግባረ ሰናይ ድርጅት ከእነሱ ጋር ለመስራት ሞክረን ነበር፤ፕሮጀክቱ በመሬት ይገባኛል ጥያቄ የተነሳ ተስተጓጉሏል፤ እስከ አሁንም ችግሩ አልተፈታም። በአልሙኒየም ላይም ብዙ ፕሮጀክቶች ሰርተናል።
አዲስ ዘመን፡– አልሙኒየም በግንባታው ዘርፍ ላይ በስፋት እየተስተዋለ ነውና በዚህ ላይ ምን ሰራችሁ?
ኢንጂነር ለምለሙ፡– አሁን እጃችን ላይ ያለውን ለመጥቀስ እንኳን የአዲስ አበባ ሕጻናትና ወጣቶች ቢሮ ፍላሚንጎ አካባቢ በሚያስገነባው አዲስ ባለ 12 ወለል ሕንጻ ላይ እየሰራን ነው። አሁን አራት ኪሎ ያለው የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ኮሚሽን ዋና መስሪያ ቤት ያኔ በሚኒስትር ደረጃ ነበረ። እሱንም እየሰራን ነው። ከሚሴ የኦሮሚያ ዞን አስተዳደር ዋና ሕንጻን አልሙኒየም ስራ ሰርተናል። ወሎ ቦረና ወረዳ መካነ ሰላም ልዩ ወረዳ ነች የአልሙኒየም ስራውን ሰርተናል። ባሕርዳር የአማራ ሕንጻ ስራዎች ዋና ጽ/ቤትን የእሱን የአልሙኒየም ስራ እየሰራን ነው።
የመለስ ዜናዊ አካዳሚ አሁን ወደ ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ኮሌጅ ተቀይሯል የሱን አልሙኒየም ስራ ጠቅላላ እኛ ነን የሰራነው። አፋር አዋሽ ኬላ የፍተሻ ስራውን የሳይት ስራ የገቢዎችና ጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያ አለ እንዳለ ሳይቱን የሰራነው እኛ ነን። በኢትዮጵያ ምርት ገበያ /ኢሴክስ/ የሀዋሳ ቅርንጫፍን የአልሙኒየም ስራ ሰርተናል። አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የአልሙኒየም ፕሮጀክቶች ከኮንትራክተሮች ላይ ሰብ ኮንትራት ወስደን ሰርተናል።
አዲስ ዘመን፡– በኢትዮጵያ ውስጥ የአልሙኒየም ስራ ውጤታማ ነው ?
ኢንጂነር ለምለሙ፡– የአልሙኒየም ስራ ኢትዮጵያ ውስጥ ገና ያልተነካ ስራ ነው። የአልሙኒየምን ስራ ከዚህ በፊት ብዙ የውጭ ድርጅቶች ነበሩ ሲሰሩት የነበረው። በሂደት ኢትዮጵያውያን ቴክኒኩን በመቅሰም ስራው እየተለመደ መጥቷል። በጣሊያን ጊዜ የነበሩ ፕሮፋይሎች ናቸው አሁንም ቻይና እየተመረቱ ሀገራችን ውስጥ በስፋት የምናያቸው አሉ። ድሮ ከኢጣሊያን ሲስተም የተወሰዱ ናቸው። ገና ያልተነካ ዘርፍ ነው።
አዲስ ዘመን፡– እናንተ ምን ዘርፍ ላይ ነው የምትሰሩት ?
ኢንጂነር ለምለሙ፡– እኛ የምንሰራው ሰፕላይ ኤንድ ፊክስ ላይ ነው። (መገጣጠም)። ሕንጻው ላይ አልሙኒየሙን በርና መስኮት፤ የደረጃ መውጫ ላይ፤ የፓርቲሽን ግድግዳዎች አሉ፤የአልሙኒየም በሮችን እነዚህን በሙሉ እንሰራለን። ትልቁ የመጀመሪያው ነገር ከአልሙኒየም የሚሰሩት ስራዎች ያላቸው ውበት ነው። ዝገት የሚባል ነገር አያውቁም። የመቆያ ግዜያቸው በጣም ረዥም ነው። ጣሊያን የሠራቸውን የድሮ ሕንጻዎች ብታያቸው አልሙኒየሙም ፕሮፋይሉም ያምራል። ከድሮው አንጻር ሲታይ አሁን የአልሙኒየም ጥራቱ ቀንሷል። ወርዷል። ድሮ ከአልሙኒየም የተሰሩትን ሕንጻዎች ላይ ሲታይ አሁንም ቢሆን ሲጸዱ ፍሬሽ ናቸው። ውበታቸው ይወጣል። ይደምቃል። አዲስ ሕንጻ ነው የሚመስሉት። እንደውም አዳዲሶቹ እነሱን ያህል አይሆኑም።
ብረትን ስታየው በአልሙኒየም ተተኪ ነው። ብረት አንደኛ ከክብደት አንጻር ከባድ ነው። ከግዜ በኋላ ዝገትና ቆሻሻ የመያዝ ነገር ስላለው ተመራጭ አይደለም። አልሙኒየም በዋጋው ደረጃ ትንሽ ወደድ ቢልም ቀላል ነው።
አዲስ ዘመን፡– በሀገራችን ስለአልሙኒየም ስራ ስልጠና የሚሰጥ ድርጅት ኮሌጅ ወይም ዩንቨርሲቲ አለ?
ኢንጂነር ለምለሙ፡– የአልሙኒየም ስራን ማስተማር የጀመሩ የግል ኮሌጆች አሉ። እኔ የማውቀው ኢኤም ዲ የሚባል እንግሊዝ ኤምባሲ አካባቢ የነበረ ወጣቶችን እያሠለጠነ ቴክኒሻኖችን እያፈራ ነበር።
የአራት ወር ስልጠና እየሰጣቸው ሌላውን ደግሞ ስራ ውስጥ ገብተው በልምድ እያዳበሩ ይሄዳሉ። በክልል የሚገኙ የተለያዩ ቴክኒክና ሙያዎች ይሞክራሉ። ግን ስራውን ለማሳየት ተማሪዎቻቸው እውቀቱን እንዲያገኙ የሚያደርጉበት መድረክ የላቸውም። ለስሙ ተምረው ይወጣሉ። ስራ ላይ ሲገቡ ምንም የሚያውቁት ነገር የለም።
አዲስ ዘመን፡– የተሳካ የኮንስትራክሽን ስራ ሰራን የምትሉት ፕሮጀክት የትኛው ነው ?
ኢንጂነር ለምለሙ፡– እኛ ብዙ የተሳካና ውጤታማ የሆነ ስራ ሰርተናል። የተሳካ ስራችን ነው የምንለው ከሚሴ፤ መካነሰላም ያሉን ፕሮጀክቶች፤ዳውሮ የገበሬዎች ሕብረት ስራ ማህበር የተሰራው ትልቅ መጋዘን፤ በጣም ሩቅ እጅግ አስቸጋሪ በሆኑ ቦታዎች የሰራናቸው ትምህርት ቤቶች ግንደ በረት ወረዳ ውስጥ፤ ኤርጃጀን የምትባል ቀበሌ ነው። ፋሲሊቲ የሚባል የለህም። ውሃ ራሱ ከወንዝ በአህያ እየተመላለሰ ነው የሰራነው። በማሕበራዊ ልማትና እድገት በጣም ወደኋላ ከቀሩ አካባቢዎች አንዱ ነው። በጣም ተቸግረን ነበር። በጥራቱ ደረጃ በጣም ተመስግነን የጨረስንበት ፕሮጀክት ነው። ሁለት ጂ 7ትም የቤቶች ልማት ፕሮጀክት ከ18 ኮንትራክተሮች በአፈጻጸም አንደኛ ተብለን ጨርሰን እያስረከብን ያለበት ሁኔታ ነው ያለው።
አዲስ ዘመን፡– የሀገራችን የኮንስትራክሽን ዘርፍ መሰረታዊ ችግሮች እንዳሉበትም ይገለ ጻል። በእርሶ አይታ ዋና ዋናዎቹ ችግሮቹ ምንድን ናቸው?
ኢንጂነር ለምለሙ፡– ዋነኛው ችግር የግዢ ስርዓቱ በጣም አስቸጋሪ መሆኑ ነው። ገና ጨረታ ሳይወጣ አንዳንዴ ማን ኮንትራክተርነቱን ወስዶ እንደሚሰራው ሁሉ ተዘጋጅቶ የሚቀመጥበት ጊዜ አለ። በጣም የአሰራር ግልጽነት የጎደለው አሳታፊ ያልሆነ ሁኔታ ይታያል። ለምሳሌ አንድ ፕሮጀክት ሲወጣ ውድድር አለ ለማስባል ብቻ በሚመስል መልኩ ለሆነ ሰው ቅድመ ሁኔታዎች ተመቻችተው ያ ሰው ማሟላት የሚችላቸው መስፈርቶች ብቻ ተዘጋጅተው ይወጣሉ።
አይተን አይተን እንዲሁ መወዳደር መወዳደር ብቻ ሲሆን ተስፋ ቆርጠን የተውናቸው ብዙ ፕሮጀክቶች አሉ። ጨረታ አገኛለሁ ማለት አስቸጋሪ ነው። ማን እንደሚሰራው ቀድሞ ይዘጋጃል። ድሮ ሁሉን ነገር በሞኖፖል የያዙ በጣም ትላልቅ ኮንትራክተሮች አካባቢዎችን ሳይቀር ይከፋፈሉ ነበር። ደቡብ የእኔ ነው፤ ወደ አፋር የእኔ ነው የሚሉ ነበሩ። ይሄ ነገር አሁን ቆሟል፤ አዳዲስ ኮንትራክተሮችም እየመጡ ናቸው። ግዢና ጨረታው ከፍተኛ ችግር አለው።
አዲስ ዘመን፡– መፍትሄው ምንድነው ይላሉ ?
ኢንጂነር ለምለሙ፡– በጀት አለው። በበጀቱ መሰረት ምን አይነት ኮንትራክተሮች ሊሳተፉ እንደሚገባቸው ስታንዳርድ( ደረጃ) ተዘጋጅቶ በዚያ መሰረት ብቻ ውድድሩ ቢደረግ መልካምና ግልጽ የአሰራር ስርዓት ይሰፍናል የሚል እምነት አለኝ። ዋነኛ መፍትሄው ትክክለኛ ሁሉን አሳታፊ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው የአሰራር ስርዓት መዘርጋትና መስፈርቶች ማዘጋጀት ነው። ለምሳሌ አንድ ፕሮጀክት በመሀንዲስ ግምት የ50 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት ነው ተብሎ ቢያዝ ለዛ 50 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት የሚያስፈልጉ መስፈርቶችን ቀድሞ ማዘጋጀት ይቻላል። ከዛ በኋላ የሚሆነው በተዘጋጀው መስፈርት መሰረት ማሟላት የሚችለው ይወዳደራል ማለት ነው። እንደዛ ቢሆን የተሳታፊውም ቁጥር ይጨምራል ። ውድድሩም ፍትሀዊ ይሆናል። እዚህ ላይ ለፕሮጀክቱ የማያስፈልገውን ኢኪፕመንት፤ የሰው ኃይል፤ ቢሮ አደረጃጀት ይጠይቁሃል።
አዲስ ዘመን፡– የእርስዎ የኮንትራክተር ደረጃ ስንት ነው ?
ኢንጂነር ለምለሙ፡– ኮንትራክተር አራት ነው። ደረጃዬ እስከ 110 ሚሊዮን ብር ድረስ በአንድ ፕሮጀክት መስራት ይችላል። እስከ አሁን በአጠቃላይ ውስንነት የለውም።ይሄ ስራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር ያወጣው መስፈርት ነው።
አዲስ ዘመን፡– ማሕበር አላችሁ ? ችግሩን ከመንግስት ጋር በመነጋገር ለመፍታት ጥረት አድርጋችኋል?
ኢንጂነር ለምለሙ፡– ደረጃ አንድ ኮንትራክተሮች ናቸው በብዛት በማህበር የተሰባሰቡት። በእኛ ደረጃ በማህበር አልተሰባሰብንም። እንግዲህ ወደዛው ነው የምንሄደው። ለመብትና ጥቅማችን የሚቆም የሚከራከር ማህበር የግድ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡– ምን ያህል ሠራተኞች አላችሁ ?
ኢንጂነር ለምለሙ፡– በቢሮ ደረጃ ቋሚ 12 ሠራተኛ አለን። በየፕሮጀክቶቹ ግን የቀን ሠራተኞች እንደ ፕሮጀክቱ አይነት ብዙ ሙያተኞች ነው ቀጥረን የምናሰራው። እስከ 270 ሠራተኛ ደርሶ የሚያውቅበት ጊዜ አለ።
አዲስ ዘመን፡– በኮንስትራክሽኑ መስክ የተለያዩ ቦታዎች ስትሰሩ የሚገጥማችሁ መሰረታዊ ችግር ምንድነው ?
ኢንጂነር ለምለሙ፡– መሰረታዊው ችግር ለስራው አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶች እጥረት ነው። ከፍተኛው ችግራችን እሱ ነው። በተለይ በሲሚንቶ ግብዓት ላይ በየጊዜው ገበያው ላይ የመዋዠቅ ነገር አለ። በአንድ ወቅት እንደ ልብ ይገኛል። በሌላ ጊዜ ደግሞ ሰው ሰራሽ ችግር ይፈጠርና የምርት ልዩነት ሳይኖር ዋጋው ይሰቀላል። እንዲህ ሲሆን ፕሮጀክቱን ተዋውለን ለመስራት ከያዝነው ዋጋ አንጻር የሚደርስብን ኪሳራ በጣም ከባድ ነው።
ብረትን ብትወስድ በጣም ባልተጠበቀ ሁኔታ ነው ዋጋው የሚጨመረው። አሁን እየተረጋጋ ነው። በተለይ ከለውጡ በኋላ ብዙ የኢኮኖሚ ሳቦታጅ (አሻጥር) ከተደረገባቸው አንዱ በተለይ ብረት ነው። የብረት ዋጋ
በጣም በሚዘገንን ሁኔታ ነበር የጨመረው። በአንዴ 150 በመቶ ነው ጭማሪ ያሳየው። 19 ብር የነበረ የብረት ዋጋ 52 ብር ሁሉ ተሸጧል። ያኔ የጨመረው ወደ 200 በመቶ ሊደርስ ምንም አልቀረው። ከዛ በኋላ የተወሰዱ የማስተካከያ እርምጃዎች ነበሩ። አሁን 39 እና 40 ብር አካባቢ ቆሞ ትንሽ ተረጋግቶ ነው ያለው። አንዴ ግን ሲጨምር ለመጀመሪያ ጊዜ ከ19 ብር ተነስቶ ወደ 52 ብር ነበር የገባው። በብረት ንግድ በስፋት የተሰማሩ ድርጅቶችን ተክተው የሚሰሩ በመምጣታቸው ገበያው ትንሽ ተረጋግቷል።
አዲስ ዘመን፡– ብረቱ ከውጭ ብቻ ነው የሚመጣው ወይንስ የእኛም አምራቾች አሉ ?
ኢንጂነር ለምለሙ፡– ከውጭ ይገባል። እኛም ሀገር የሚያመርቱ አሉ። አቢሲኒያ ባርስ የሚባል አኮሎ ብረት የሚባልና ሌሎችም የተለያዩ የሀገር ውስጥ ብረት አምራቾች አሉ። ቆራሌ ከተማ ውስጥ ይሰበስብና ያንን ያቀልጣሉ። የሀገር ውስጦቹ የጥራት ጥያቄ ይነሳባቸዋል። የሀገራችን ምርቶች የሆኑ ጥሩ የጥራት ደረጃ ያላቸውም ብረቶች አሉ። በላብራቶሪ ተፈትሸው ከውጭ ተመርቶ ወደ ሀገር ውስጥ ከሚገባው ጋር እኩል( አቻ ) የሆኑ የሀገር ውስጥ የብረት ምርቶችም አሉ። በዛው ልክ በጣም የወረዱ የሀገር ውስጥ ምርቶችም አሉ።
አዲስ ዘመን፡– በሀገር ውስጥ ያለውን የኮንስትራክሽን ሴክተር እንዴት ያዩታል ?
ኢንጂነር ለምለሙ፡– እውነቱን ለመናገር በከፍተኛ ደረጃ በሙስና የተጠቃ ሴክተር ነው። ኮንስትራክሽን ሴክተሩ በጣም ለብልሹ አሰራር የተጋለጠ ነው። ያለእጅ መንሻ መላወስ የማይቻልበት፤ በየደረጃው ጠባቂ የበዛበት፤ ውስብስብ በሆነ የቢሮክራሲ አሰራር የተተበተበ፤ በነጻነት በግልጽ መወዳደር የማትችልበት፤ ሁሉም ነገር አስቀድሞ (በሴት አፕ) አልቆ የሚሰጥበት በከፋ ሁኔታ የተበላሸ ሴክተር ቢኖር የኮንስትራክሽን ዘርፉ ነው።
ይሄ በማደግ ላይ ያለውን የኮንስትራክሽን ኢንደስትሪ ክፉኛ ይጎዳዋል።፡ ጎድቶታልም። ከቀድሞው ትንሽ የመሻል ፍንጭ ይታይበታል እንጂ ኮንስትራክሽን ሴክተሩን ጥቂት ሰዎች ከፍተኛ ባለሀብት ስለሆኑ ብቻ ሙሉ በሙሉ ይቆጣጠሩት የነበረበትን ሁኔታ ሁሉ አይተናል። ሁሉንም ስራ እኔ ብቻ ጠቅልዬ ልውሰድ የሚሉ ሰዎች የታዩበትም ጊዜ ነበር። በትውውቅ በቅርበት በዝምድና በቤተሰብ ግንኙነትና ቁርኝት ወዘተ። ይሄ ሀገርና ህዝብን በሙያው የተሰማሩ ታዳጊዎችንም ይጎዳል።
በሙስና የተለወሰና የሚተነፍስ አስቸጋሪ ሴክተር ቢኖር የኮንስትራክሽን ዘርፉ ነው። መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ሊያስተካክለው የሚገባው ዘርፍ ነው።እንደ ኮንስትራክሽን ሴክተሩ በከፋ ሁኔታ የተበላሸ ሴክተር ፈልጎ ማግኘት የሚቻል አይመስለኝም። ሁሉም ጋ ችግር አለ። የዚህ ግን እጅግ የከፋው ነው።
አዲስ ዘመን፡– እንደዜጋ መፍትሄው ምንድነው ይላሉ?
ኢንጂነር ለምለሙ፡– እዚህ ላይ በጣም ጠንካራ መሆን ያለባቸው ተቋማት ናቸው። ኮንስትራክሽን ሴክተሩን በህግ እንዲቆጣጠሩ ስልጣን የተሰጣቸው አካላት አሉ። የኮንስትራክሽን መወዳደሪያ መስፈርቱ ለአንድ ኮንስትራክሽን ጨረታ በተለይ የመንግስት ግዢ ሲፈጸም የመንግስት ፕሮጀክቶች ናቸውና የሚበዙት ግልጽ ሊሆን ይገባል። በዚህ ሀገር ውስጥ ግለሰቡ የተለያዩ አማራጮችን ወስዶ ሊገነባ ይችላል። በሕግ የሚገደድበት ሁኔታ የለም።
የመንግስት ፕሮጀክቶች በእኩልነት ለሁሉም ክፍት እንዲሆኑ ተቋማት ጠንካራ ስራ መስራት ይጠበቅባቸዋል። የውድድር መስፈርቱን ከማስቀመጥ ጀምሮ ለሙስና በራቸውን ክፍት አድርገው በሚሰሩ የመንግስት አካላት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር የማድረግና እርምጃ የመውሰድ፤ አሰራራቸውን የመቆጣጠር ኃላፊነት ወስዶ ሊሰራ ይገባል ብዬ አስባለሁ። ይህን ማድረግ ካልተቻለ ያው ተመልሶ በጭቃ መለወስ ነው የሚሆነው።
አዲስ ዘመን፡– በድርጅታችሁ በኩል ወደፊት ምን አስባችኋል ?
ኢንጂነር ለምለሙ፡– እኛ አሁን ኮንስትራክሽን ውስጥ ብንሰራም ወደፊት የተለያዩ እቅዶችና አላማዎች አሉን። በተለያዩ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ለመሰማራት እያስጠናናቸው ያሉ ስራዎች አሉ። በጅምር ያሉ ስለሆኑ ጊዜው ሲፈቅድ እናየዋለን።
አዲስ ዘመን፡– ስለሰጡን ቃለምልልስ እናመሰ ግናለን።
ኢንጂነር ለምለሙ፡– እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 14/2012
ወንድወሰን መኮንን