አዲስአበባ፡- የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃና የሀብት ልማት ስራ በመንግሥት ትኩረት ስላልተሰጠው የእንስሳቱን ህልውና የሚፈታተኑ ተግዳሮቶች እያጋጠሙ መሆኑን የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚና የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ቲንክ ታንክ ቡድን ጥናት አመለከተ፡፡
የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ሀብት ልማትና ጥበቃ ላይ የሚስተዋሉትን ተግዳሮቶችና ወደፊት መከናወን ስላለባቸው ስራዎች ትናንት በጊዮን ሆቴል ከተለያዩ የመንግስትና የግል ተቋማት ተወካዮች ጋር በጥናታዊ ፅሁፎች ላይ ባካሄደው ውይይት በእቅድ ያልተመራ የመሰረተ ልማት ግንባታ፣ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ፣በዱር እንስሳት መኖሪያ ውስጥ የሰዎች መስፈር፣የህግ መላላት፣ለዘርፉ ተገቢውን በጀት መድቦ ስራዎችን በሰለጠነ የሰው ኃይል አለመምራት፣የመጤ አረም በፓርኮች ውስጥ መስፋፋት እና ሌሎችም ተግዳሮቶች የዱር እንስሳቱን ህልውና እየተፈ ታተኑ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ዋይልድ ላይፍ ኮንሰርቬሽን ቲንክ ታንክ ዋና ፀሐፊ ዶክተር መክብብ እሸቱ በውይይቱ ላይ ባደረጉት ገለጻ፣በሀገሪቷ ግልጽ የሆነ የመሬት አጠቃቀም ባለመኖሩ የፓርኮችን ህልውና የሚነካ ስራ ይሰራል፡፡ፓርኮችን ከተለያዩ ጥቃቶች ለመከላከል የሚያስችል ጠንካራ ህግ አለመኖር፣ የዘርፉን አስፈላጊነትና ጥቅም በአግባቡ አለመረዳትና ግንዛቤ ለማስጨበጥም የሚደረገው ጥረት አናሳ መሆን፣መንግሥት የሚሰጠው ትኩረት የሚጠበቀውን ያህል አለመሆን በዘርፉ ላይ ተደራራቢ የሆኑ ችግሮች እንዲጋረጡበት ሆኗል፡፡
የችግሩ መስፋት ደግሞ በፓርኮች ልማትና በዱር እንስሳት ጥበቃ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ በማሳደሩ ዝሆንና አውራሪስ ቁጥራቸው እንዲመናመን ማድረጉን የጠቆሙት ዶክተር መክብብ፤ የአዋሽ ፓርክ በሚገኝበት የባቡር መንገድ ዝርጋታና የከሰም ስኳር ፋብሪካ ግንባታ፣በኦሞ ፓርክም በተመሳሳይ የሚከናወነው የስኳር ፋብሪካ ግንባታ፣በማጎ ፓርክ ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ መስፈር፣በጋምቤላ ከኢንቨስትመንት ጋር ተያይዞ የተከናወነው ተግባር ለፓርኮቹ አደጋ እንደሆኑ ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡
በአውደ ጥናቱ የተሳተፉት የሰንቀሌ ቆርኪዎች መጠለያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደስታ በዳሶ በሰጡት አስተያየት በመጠለያው ልቅ የሆነ ግጦሽ መኖሩና በሚፈጠር ንክኪ ከቤት እንስሳት ወደ ዱር እንስሳት የሚተላለፉ በሽታዎች ማጋጠማቸው፣ በአካባቢው ማህበረሰቡን ያሳተፈ ስራ ቢከናወንም ከዘርፉ ተጠቃሚ ባለመሆናቸው፣ መጠለያው ከመኖሪያቤቶች አለመለየቱ፣ በዞንና በወረዳ ደረጃ ተጠያቂነት አለመኖሩ ካጋጠሙት ችግሮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ማስረሻ ፈጠነ በበኩላቸው አካዳሚው በዱር እንስሳት ሀብት ልማትና ጥበቃ ላይ ያሉትን ችግሮችና መፍትሄዎች የምርምር ስራዎችን በማከናወን ለመንግሥትና ለፖሊሲ አውጭዎች በማቅረብ ችግሩ እልባት እንዲያገኝ የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት በእንቅስቃሴ ላይ መሆኑን ገልፀው፤ የአሁኑን አይነት የጋራ መድረክ በማዘጋጀት ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ የአቅም ግንባታ አጫጭር ስልጠናዎችን በመስጠት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የአካባቢ፣ደንና የአየርንብረት ለውጥ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፈቃዱ በየነ ዘርፉ ተግዳሮቶች እንዳሉበት ይታወቃል፡፡ ተግዳሮቶቹን ወደ ዕድል ለመቀየር መንግስት ብቻውን የሚያ ከናውነው ባለመሆኑ እንደ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚና ቲንክ ታንክ ቡድን ካሉ አጋር ድርጅቶች ጋር በመስራት መፍትሄ ለመስጠት ኮሚሽኑ ለአዲስ አደረጃጀት በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ አለመኖር ተጽዕኖ ማሳደሩን የጠቀሱት ኮሚሽነሩ በመንግሥት እየታየ መሆኑንና ፖሊሲው ሲጸድቅ ለችግሮች እልባት እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 17/2011
በለምለም መንግሥቱ