ዶክተር አልማዝ ባራኪ
የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ መምህር
ልጆችን ማሳደግ ማለት በአካል፣ በስነልቦናና በማህበራዊ ህይወት ማነጽ ማለት ነው። በዚህ ላይ የወላጆች ሚና ገና ህጻናት ሲጸነሱ ጀምሮ ራሳቸውን ያለእገዛ መምራት እስኪችሉ ድረስ የሚያስፍለገውንና ተገቢውን አካልዊ፣ ስነልቦናዊና ማህበራዊ እንክብካቤ ማድረግ ማለት ነው።
አካላዊ እንክብካቤ ማለት ምግብ፣ መጠጥ፣ ልብስ፡ መጠለያ የመሳሰሉትን ያካተተ ነው። አንድ እናት ከጸነሰችበት ጊዜ ጀምሮ በቂና ተመጣጣኝ ምግብ መመገብ፣ በቂ እንቅልፍ መተኛት፣ በአጠቃላይ አካላዊ ምቾቷን በመጠበቅ የጽንሱን ምቾት መጠበቅ ይጠበቅባታል። ይህ የተሟላ ሲሆንና በተከታታይ የጤና ምርመራ በመታገዝ ጤናማ ህጻን እንዲወለድ ያደርጋል። ህጻኑ ወይም ህጻኗ ከተወለደች በኋላ ደግሞ የልጆች አካላዊ ምቾት እንዳይጓደል ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል።
የልጆችን ስነልቦናዊ ወይም አእምሮአዊ እድገታቸውን ለማዳበር ደግሞ ገና ድክድክ ሲሉ ጀምሮ በጎ ስብእና፣ ባህሪንና ሌሎች ነገሮችን በማሳየት ምሳሌ መሆን፣ እየተጫወቱ፣ እየጠየቁ፣ እየነካኩ፣ እየሞከሩ፣ እየሰበሩ እንደልባቸው እያወሩና ያለመታከት እየተሰሙ እንዲያድጉ፤ አካላቸው እንዳይጎዳ እየጠበቅን ሁኔታዎችን የማመቻቸት ኃላፊነት የወላጆችና የአሳዳጊዎች ነው።
ልጆች ሲያደጉ በየአንዳንዷ እንቅስቃሴ ውስጥ በጎውንና መጥፎን የሚቀሰሙባት አጋጣሚ አለች። የትምህርት ግቡ ደግሞ በእውቀት፣ በክህሎትና በስነ ምግባር የታነጹ ዜጎችን ማፍራት ነው። ይህን ግብ ለማሳካት ታዲያ የሁሉም ባለድርሻ አካልን ርብርብ ይጠይቃል። እነኚህ ባለድርሻ አካላት ወላጅ፣ አሳዳጊ፣ ማህበረሰብ፣ መምህር፣ ጓደኞችና አካባቢ (መንደር፣ ከተማ፣ አገር) ናቸው።
ወላጆች ለልጆቻቸው መስጠት ያለባቸው ነገሮች አሉ፥
1. ቤተሰብ መሃል ያለ ፍቅር ( በአባትና እናት መካከል፣ በልጆችና ወላጆች መካከል፣ በልጆች መካከል፣ በልጆችና ሌሎች የቤተሰብ አባላት መካከል)
2. ወላጆች ራሳቸውን በመንከባከብ በጤናና፣ በአቅም ማነስ ምክንያት ልጆቻቸውን ስጋት ላይ እንዳይጥሉ መጠንቀቅ
3. ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር የማይረሳና የወላጆቻቸውን ፍቅር የሚያጣጥሙበትን ጊዜ ማመቻቸት
4. መሰረታዊ የህይወት ክህሎቶችን እንዲያዳበሩ ማገዝ
5. በራስ እንዲተማመኑ ማድረግ ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 12/2012
በሞገስ ጸጋዬ