ልጆች! እንዴት ሰነበታችሁ? ወደ ቀጣዩ ክፍል በመሸጋገራችሁ ደስተኞች እንደሆናችሁ አስባለሁ። ወደ ቀጣዩ የትምህርት ክፍል በማለፋችሁ ደስተኞች ብትሆኑም የተዛወራችሁበት ክፍል ትምህርቱ እንዳይከብዳችሁ ከምን ጊዜውም በላይ በክረምቱ ወራት ማንበብ ይጠበቅባችኋል። የቀጣዩ ዓመት የትምህርት ዘርፍ ምዝገባ እስኪጀመር ጠንክራችሁ አንብቡ።
ዛሬ እንግዳዬ አድርጌ ያቀረብኳት ተማሪ ፅዮን ጸጋዬ ትባላለች። የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን የምትማረው በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን አዶላ ወዩ ወረዳ በሚገኘው አዶላ ወዩ አንደኛ ደረጃ እና ሁለተኛ ሳይክል ትምህርት ቤት ነው።
ተማሪ ጽዮን በኮሮና ምክንያት ትምህርት በመዘጋቱ ተከፍታ እንደነበር ትናገራለች። በተለይ ደግሞ የመጀመሪያውን ዓመት ውጤት ሰምታ ለማሻሻል ጠንክራ እያነበበች ባለችበት ጊዜ መሆኑ በጣም ረብሿት እንደነበር ትናገራለች። “አንድ ዓመት ሊቃጠልብኝ ነው ብዬ በጣም አስብ ነበር። ትምህርት እንደተዘጋ ማንበብ የጀመርኩ ቢሆንም በቀላሉ ከመምህራኖቼ ጋር ስለማልገናኝ የማንበብ ፍላጎቴ ቀንሷል። በተለይ ደግሞ በቂ መፅሀፍት ስለሌለኝ መምህሮቻችን የሚሰጡንን አሳይመንት በቤት ውስጥ ለመስራት ስለምንቸገር ትምህርታችንን ለመከታተል ከፍተኛ ችግር ፈጥሮብናል። እንደዚህ ለፍቼ ወደ ስምንተኛ ክፍል ላልዛወር እችላለሁ እያልኩ በምሰጋበት ጊዜ ወደ ቀጣይ ክፍል መዛወሬን ስሰማ በጣም ደስ ብሎኛል። ያልተማርኩትን የሰባተኛ ክፍል ትምህርት በማንበብና ቀድሜ የስምንተኛ ክፍል መጽሀፍትን በመግዛት ቅድመ ዝግጅት አደርጋለሁ።” ብላኛለች።
ልጆቸ እናንተም ልክ እንደ ተማሪ ጽዮን ሁሉ አስቀድማችሁ መዘጋጀት አለባችሁ። በተለይ ደግሞ ወደ ስምንተኛ ክፍል የተዘዋወራችሁ ተማሪዎች በቀጣይ የሚጠብቃችሁ የስምንተኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና በመሆኑ አስቀድማችሁ መጽሀፍት በማንበብና ያልገባችሁን በመጠየቅ ዝግጅት ማድረግ አለባችሁ።
አሁን ሁሉም ተማሪዎች ወደ ቀጣዩ ክፍል ይዛወሩ በመባሉ ምክንያት ለስምንተኛ ክፍል ፈተና ለመዘጋጀት ጉልበት ሆኖኛል የምትለው ተማሪ ፅዮን ሁሉም ተማሪዎች ያልተማሩት ብዙ የትምህርት ክፍል ስላለ ሳይዘናጉ አሁን ያላቸውን ጊዜ በትክክል ሊጠቀሙበት ይገባል ስትል መከራለች። ሁሉም ተማሪ በትክክል የተዛወረበትን ክፍል እንዲመጥኑና በቀጣይ እንዳይቸገሩ ማንበብና መጠየቅ አለባቸው። አሁን ወደ ቀጣዩ ክፍል ተዛውረናል ብለው ሊዘናጉ አይገባም። በተገቢው መንገድ ሁሉንም የመጽሀፋችንን ክፍል ሳንማር በማለፋችን የተነሳ ከምን ጊዜውም በላይ ማንበብ አለብን ስትል ምክሯን ለግሳለች። ማለፋችን ትርጉም እንዲኖረውና በእውቀት የተደገፈ እንዲሆን ሳንዘናጋ እናንብብ ስትል መልዕክቷን አስተላልፋለች።
ልጆች! የፅዮን ሀሳብ እንደተመቻችሁና እናንተም ልክ እንደ ፅዮን ደስተኞች እንደሆናችሁ አልጠራጠርም። ፅዮን እንዳለችው አልፈናል ብላችሁ መዘናጋት የለባችሁም። በደንብ አንብባችሁ በቀጣይ ጥሩ ውጤት ማምጣት አለባችሁ። መልካም ቀን!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 12/2012
በሞገስ ጸጋዬ