ዓባይ ላለፉት አራት ሺህ ዓመታት መነሻውን አድርጎ ለታችኛዎቹ ተፋሰስ ሀገራት ለግብጽና ሱዳን ሲሳይ ሲሆን ለምንጭቱ ሐገረ ኢትዮጵያ ደግሞ ከአካፋይነት ያልዘለለ ሚና ሲጫወት ቆይቷል። አሁን ግን ላለፉት ሃምሳ ዓመታት ኢትዮጵያውያን ስናልመው ቆይተን ባለፉት አሥር ዓመታት ደግሞ ወደ መሬት ህልማችንን በማውረድ በገዛ ህዝባችን አቅም ግድቡን በመገንባት ዓባይን ልናስገብረው ወደ ውሃ ሙሌት ደረጃ ደርሰናል።
ዓባይ ለእኛ የሙሴ በቅርጫት የመንሳፈፊያ ባህር የቤተመንግስት መግቢያ በር ብቻ አይደለም፤ ዓባይ የባህልና ትውፊት መፈንጠቂያ፣ የብሉይ ኪዳን እምነት መሸጋገሪያ ዓምባችንም ነው። ለግብጽ ደግሞ የፈርኦን ልጆች መንቦጫረቂያ፣ የግንቦቹ ጡብ መጠፍጠፊያ፣ በበረሃ ላይ ፒራሚድ መገንቢያ፣ የሚሊዮን ህዝቦቿ ዳቦና ፈጢራ መጋገሪያ፣ የታላላቅ የጥጥ ፋብሪካዎቿ ጥሬ ሰብል ማምረቻና የዘመናት የድል መሸጋገሪያ ህልም መፍቻዋ ነው።
ግብጽ በአባይ ላይ ታላላቅ ዘመናዊ የእርሻ ማሳዎች ለአውሮፓ ገበያ ልዩ ልዩ አትክልቶች ማቅረቢያ ማፍሪያ፤ የወይን ፋብሪካዎቿ ጥሬ ምርት ማቅረቢያ፣ የስንዴ ማሳዎቿ መሰብሰቢያ፣ ከሁሉም በላይ 98 ከመቶ የሆነ ህዝቧ የኃይል ምንጭ ጉልበቷ ነው። እንደወንድም ህዝብ እንኳን ሆነላት፤ ነው የምንለው።
ይህንን በቁጭት በማውራት የምንተክዝበት፣ በዳሸን ተራሮች ላይ ቆመን አሻግረን በማየት የምንቁለጨለጭበት ጊዜ ማብቃት አለበት ብለን ግን አሁን ተነስተናል። መሰረቱ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ተጥሎና በከፊል ሥራው ተጀምሮ፤ አሁን ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፣ አባይ ከዜማ ሀብትነት ወደ ዘመናዊ ኃይልነት ሊቀየር ጫፍ የደረሰበት ልዩ ምዕራፋዊ ዕለት ላይ ደርሰናልና፤ ያስጀመረንና ወደ ፍጻሜውም እንድንገሰገስ አቅምና አቋም ያስወሰደን አምላክ ስሙ ይባረክ።
እንደ ተማሪ ባሳለፍኩበት የልጅነት ዘመኔ ወላጆቼና አያቶቼ “አባይ አባይ”፣ እያሉ በቁጭት ከማዜም የተረፈ ነገር ሳይውልን ቆይተናል። “ዓባይ እኔ የማውቅህ ከደረት አንተ የምታውቀኝ በጉልበት” እየተባለ፤ ጉልበቱን ሳንጠቀምና አቅሙን ሳንበደረው ለሌላው አቅም ሆኖ እኛ በእንቅልፍ ያሳለፍናቸውን ዘመናት ወደኋላ ጥለን የምንነሳበት ጊዜ ላይ ነን። በነገራችን ላይ ግብጽ በናይል ተፋሰስ ሀገሮች ስብሰባ ላይም ሆነ የዕቅድ ትግበራ ላይ ሳንጀምር በፊት እንደም ንጀምረው ሁሉ ታውቅ እንደነበር ስንቶቻችን እንደምናውቅ አላውቅም። ግን ታውቅ ነበር፤ ኢትዮጵያ በራሷ ችላ አትገነባውም ብላ ስለምታምንም አበዳሪ አካላት ከቶውንም ለእኛ እጃቸውን እንዳይዘረጉ ለማድረግ ተሳክቶላታል።
በሌላ በኩል በልጆቿ ብርታት ህልሟን እውን ለማድረግ ስትነሳ ደግሞ በድርድርና ቴክኒካል ጉዳዮች ሰበባ ሰበብ ግንባታው የሚጎተትበትን ካልሆነም የሚሰናከልበትን ገመድ ጉተታ ለመፈጸም ልዩ ልዩ ዘዴዎችን እየተጠቀመች ነው። አሁን ዓባይን አስግረን ለጉልበት፣ ዓባይን አስግረን ለብርሃን ልንጠቀምበት እናም ድህነት የፈጠረውን አካላዊ ጨለማ ለማስወገድ የቆረጠ ኢትዮጵያዊ ትውልድ መነሳቱ ገብቷታል።
ስለዚህም ልዩ ልዩ ማሰናከያ በረጅምም በድንክም እጆች ለመፍጠር መትጋቷ ባይቀርም አሁን ጊዜው ደርሷልና አናንቀላፋም። ቀኑ መጥቷልና አንዘናጋም።
ግብጾች “ዓባይ ለግብጽ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው” ከሚለው ትርክታቸው ባሻገር፤ የኢትዮጵያ ነው ብለው ለማንም ነግረው አያውቁም፤ ለግብጽ ህዝብ ለራሱ ይህንን አውርተውት አያውቁም። ሀገራችንም የዓባይ መነሻ እኔ ነኝ ብላ ለእነርሱም ነግራ አታውቅም። ግብጾች በተለያዩ ጊዜያት ለሀገራችን የቤት ሥራ በመስጠት ፊታችንን ወደልማት እንዳናዞር ያደረጉትን ያህል ሆነንላቸው መቆየታችን ማብቃቱን ልቧ ነግሯታል። አሁንም ግን በራሳችን ልጆችና በራሳችን አኩራፊዎች መሰል በጥባጭ ድርጊት ብታከናውን አይገርመኝም። የእኛ ተፋሰስ ሀገራት በማያባራ መልክዓ-ምድራዊ ፖለቲካ በየጊዜው የሚደፈርስ በመሆኑ ጥቃት አሾልኮ ለማስገባት አስቸጋሪ አይደለም። የመለያያ መንገዱም ሰፊ ነው፤ ሲሻቸው በሃይማኖት፣ (ብዙ ጊዜ ሞክረው አልተሳካላቸውም)
ሲሻቸው በቋንቋ ካልሆነም ወሰንተኛነትን ከሌላ ዜግነት ጋር በማስተሳሰር ሊያጠቁን መሞከራቸው አይቀርም።
ግንባታው እውን እንዳይሆን የምታደርገው ጥረት በሁሉም አቅጣጫ የሞት ሽረት ትግል ሆኖባት ከአውሮፓ እስከ ዓረብ ሀገራትና የተባበሩት መንግሥታት መድረኮች ድረስ እየተሯሯጠችበት ነው፤ ያልገባት ነገር ግን ውሃው በላይኛው ተፋሰስ ሀገራት “ስልጣን” ፈቃድና ተግባቦት ስር መሆኑን ለመቀበል አለመሻቷ ነው። ወትሮም ዳኝነትን ከሌላ አካል መሻት መልካም ቢሆንም ያዳሉልኛል ብላ ወደምታስባቸው ሀገራት ፊቷን ማዞሯ ከትዝብት በስተቀር የሚያተርፍላት ነገር የለም።
ይሁንናም ግድቡን ገንብተን አኩሪ ደረጃ ላይ ደርሰናል። እናም፤ “ግድቡ የእኔ ነው” ስል ግድቡ የሚያስገኘው ጥቅምና ትሩፋት የብርሃን ሃይሌ ነው፤ ማለቴ ነው። ግድቡ የእኔ ነው፤ ስል ቅጠል ከዱር ለቅማ ጭራሮ ሰብስባ ለእለት ፍጆታዋ የምታውለው አክስቴ ወገብ ከሸክም ማረፊያ ነው፤ ማለቴ ነው። ግድቡ የእኔ ነው ስል፣ በሀገሬ ባላገር ጎጆዎች በኩራዝ የሚጨናበሱ ወገኖቼ ዓይን ደህንነት ሊጠበቅ ነው፤ ማለቴ ነው። ግድቡ የእኔ ነው፤ ስል የካይሮን ጎዳና መብራቶች በአውሮፕላን ቁልቁል እያየሁ በዜማ ቁጭት እያንጎራጎርኩ……
“ዓባይ ክፉው አባት ሺህ በሺህ ተጉዘህ፣
አፈርና ውሃውን ከምድሬ ጠራርገህ፤
የሰው ሐገር በረሐ ለምለም ታደርጋለህ፣
‘አባ-ካና’ ሳትል ታሾፍብኛለህ!?
ወይ ነዶ ክፋትህ፣
ወይ ነዶ ጭካኔህ፤
ረሐብ ላይ አሹፈህ፣
የጠገበውን ሰው ደግሞ ታጠግባለህ?! …?!” እያልኩ ከመቁለጭለጭ በመውጣትና ሰቀቀናም እንጉርጉሮ ከማሰማት ታቅበን የምንነሳበት ሰዓት ነው፤ ብዬ አምናለሁ።
አሁንም የመጨረሻ ካርድ አድርጋ ወደ አፍሪካ ህብረት መጥታለች። ወትሮም ሀገራችን ሽምግልና በሀገር ሰው ሽምግልናው አፍሪካዊ እንዲሆን ስትጥር ስለነበር አቋሟን በአፍሪካዊ ወግ አቅርባለች። ሁሉም ንግግራችን እና የንግግራችን መቋጫ ታዲያ አባይ ለልማታችን ማዋላችን አይቀርም የሚል ነው። አሁንም ይህንኑ ሐሳብ ለሲሪል ራማፎሳ (የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር) እንዲሁም ለሙሳ ፋኪ ለህብረቱ ኮሚሽነር፤ በጨዋ ደንብ አሳውቃለች። እንገነባዋለን፤ ውሃችንን እንሞላለን የትኛውም መነሻ እሳቤያችንም ሆነ ዓላማችን ግን ግብጽንም ሆነ ሱዳንን ለመጉዳት የሚደረግ ዘመቻ ግን አለመሆኑን እርሷም (ግብጽም) ታውቃለች፤ እኛም እናውቃለን። በየትኛውም ውይይትና ንግግር፣ ዓላማችን ግብጽን ማናደድና ማሳፈር ሳይሆን፣ ረሀብና ስደትን ማሳፈር ነው።
እኛም፤ ለብዙ ሺህ ዓመታት ያለመንቃታችን ምስጢር ተገልጦልን ጨለማችንን ጥሰን ለመውጣት ስንነሳ፣ “ከዘፈንና ፉከራ አያልፉም” ብላ ያሰበችበት ግምት ፉርሽ መሆኑን ስታውቅ በቀቢፀ-ተስፋ መንፈራገጧን እንገምታለን። የእኛ በአባይ ላይ መንቃት ለግብጽ እንግዳ ስሜት መፍጠሩ የሚጠበቅ ነው። አዎ፣ ግብጽ ሆይ ከዘመናት ድባቴያችን አሁን ነቅተናል፤ የአእላፍ ዓመታት ክዳናችንን ግጣም ፈንቅለን ወጥተናል፤ በላያችን የተጫነውን የድንቁርና ቡልኮ አሽቀንጥረን ተነስተናል። ስንነሳ ግን እንደጨለመብን ሌላው ይጨልምበት፤ እንደተራብን ሌላው ይራብ ብለን አይደለም። ጥያቄውና ለመልሱ ያለን ትጋት የተተለመው ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ላይ ነው። ግብጽ ሆይ፣ ሩጫሽ፣ “እኔ እየበላሁ እናንተ ተራቡ፤ እኔ በብርሃን እየተጫወትኩ፣ እናንተ በጨለማ ተደናበሩ” ከሆነ ግን አይቻልም ነው መልሳችን። የእኛ አቋም፣ እናንተ እንደበራላችሁ እኛም ይብራልን ነው፤ እናንተ እየበላችሁ እኛም እንብላ ነው።
ግብጻውያን እኮ፣ ወደ ሳውዲ ሲጓዙ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ሆነው፣ ወደ ኢምሬቶች ሲሄዱ ኢንጂነሮች ሆነው፣ ግብፆች ወደ ባህሬን ሲጓዙ መካኒኮች ሆነው፣ ግብጻውያን ወደ አውሮፓ ሲሄዱ ለላቀ ትምህርት ራሳቸውን አዘጋጅተውና ኢንቨስት ለማድረግ፤ ወደ ኦማን በባህር ሲቀዝፉ ምርጥ ቱሪስቶች ሆነው ነው። የሀገሬ ጎረምሶችና ልጃገረዶች ግን በየዓመቱ ሥራ ፍለጋ የአረቡን ባህር አቋርጠውና በባብዔል መንደብ ወደ የመን፣ ሲሰደዱ የባህር እራት ከመሆን የተረፉት ሲደርሱ፣ እህቶቻችን የአረብ ቤት ሰራተኛ፣ ወንድሞቻችን ዘበኛ ሆነው ነው የሚገኙት። ያውም ከባርነት ባልተናነሰ ህይወት ኑሯቸውን እየገፉ ሊኖሩ። ይህ ስደት እንዲያበቃ ነው፤ አባይን በፍትሀዊ መንገድ እንጠቀም የምንለው።
ለግብጻውያን የኩራት ምንጭ የሆነውን አባይ ኩራት እንጋራ ማለት ፍትሐዊም ተገቢም ጥያቄ ነው፤ ብለን እናምናለን። ለእነርሱ ሲሆን የተገባው ኩራትና እራት፣ ለእኛ ግን ረሀብና ጽልመት ሊሆን አይገባም፤ “የግብጽን ኩራት መጋራት አይደለም ሃጢያት፤” የምንለው ለዚህ ነው። እኛ ካይሮ እየራባት፣ አዲስ አበባ ትጥገብ አላልንም፤ የግብጽ ብልጽግና ምክንያት የሆነው አባይ ለኛም ይሁን ነው፤ እንጂ።
በግብጽ ምድር አቋርጠው አንድም ወደ እስራኤል አለዚያም፣ በቆጵሮስና ማልታ አድርገው በሜዲትራኒያን ባህር በኩል የሚሰደዱት ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ፤ አውሮፓ ለመድረስ በሚያቋርጡት መንገድ ላይ ከደላሎች ባዶ ሽንገላና “የእልፍ ዶላር ዝቆሽ” ወሬ ተርፈው፣ አውሮፓ ሲደርሱ አካል አጉድለው እንደሚደርሱ ከመስማት የበለጠ የሚዘገንን ነገር የለም። በዚህ መንገድ ወደ አውሮፓ ስለሚሰደድ አንድም ግብጻዊ ግን ሰምተን አናውቅም፤ ግብጽ ባላት የተፈጥሮ ሀብት ታላቅነት ሳይሆን አባይ በሚያስገኝላት ትሩፋት ተጠቅማ ዜጎቿን በመጥቀሟ እንጂ። እኛም እንደገና በዚህ ክብረህሊናን ዝቅ በሚያደርግ የስቃይ መንገድ ላለመጓዝ አንዱ መፍትሄ አቅጣጫ አባይን በፍትሐዊ መንገድ መጠቀም መሆኑን ጠንቅቀን ተገንዝበናል። አባይ ለሁሉ ጥያቄያችን መልስ ባይሆንም፣ ለሥራ አጥነታችን በመጠኑ፣ ለኃይል ፍጆታችን በኃይል፣ ለምግብ ምርታችን በሚገባ፣ ለቴክኖሎጂ ከፍታችን ማሳለጫ፤ ለዓሳ ምርታችን እድገት በእጅጉ ይጠቅመናል። በእርሱ እያዘገምን ሌሎቹን ጥያቄዎቻችንን ወደመመለስ እንሸጋገራለን።
ዓባይ ከደሃ እናቶቻችን መቀነት እየተፈታ፤ ከባተሌው ከተሜ ምስጢር ኪስ ተፈልፍለው በሚወጡ ብሮች ነው፤ እየተገነባ ያለው። ከድህነቱ በላይ በህዝቡ የዛሬው የቀረው ቀርቶብኝ ቂጣ ብቻ ልብላ፣ ተብሎ እየተዋጣ ባለ ሳንቲም የሚገነባ ግድብ፣ በግብጽ የግብዝነት ተንኮል የተሞላበት፣ ፍቃድ ስር በፍጹም ሊወድቅ አይገባም። የምንደራደረው ግድባችንን በውሃ ላለመሙላት ሳይሆን ግብጽን ሊጎዳ በማይችል ፍትሐዊ አካሄድ የምንሰራ መሆኑን ሳንታክት ለማስረዳት ነው። የምናወራው በተራበ አንጀት ስለሚገነባ ታላቅ የትንሳኤ ግንባታ ሐውልት እንደመሆኑ ከእርሷ ቡራኬ በመጠበቅ አንሰራውም። እንገነባዋለን ስንል እንገነባዋለን ነው፤ እንሞላዋለን ስንል እንሞላዋለን እንጂ ለመሙላት የግብጽን አረንጓዴ መብራት እንጠብቃለን፤ ማለታችን አይደለም።
ይህንን የሀገር ጸጋ ብርሃን ለመጎናጸፍ፤ የግብጽን የናይል እርሻ ፕሮጀክት ጥጥ አንጠብቅም። ግብጽም ጥጡን አምርቼ ጨርቁን ስልክላችሁ እርሱን አቃጥላችሁ ምሽታችሁን ታደምቁበታላችሁ፤ እስክትለን አንሞኝላትም። የግብጽ ምንም አይነት “እሺ-ነገ” አዘናግቶን አባይ የእኛም ሰማያዊ ስጦታ መሆኑን ከማረጋገጥ ለአፍታም ቸል ማለት አይገባንም።
የግብጽ አዲሶቹ ፈርኦኖችም፣ ድሆች እንጂ አቅመቢሶች እንደሆንን እንዲያስቡ አያስፈልግም። ጥንት በማሃዲስቶችና በአውሮፓ የጦር አበጋዞች አማካይነት ደጋግመው አንዴ በመተማ ሌላ ጊዜ በጉንደትና (ኢስማኤል ከዲቭ 1868 ዓ.ም) በጉራዕ በምስራቅ በር በምጽዋና በሐረር በኩል ደጋግመው በጦር ፈትሸውን ያቃታቸውን ድል ዛሬም አያገኙትም። ምክንያቱም እኛ ኢትዮጵያውያን የድልና ሽንፈት ታሪኮቻችንን ጠንቅቀን የምንማር፣ የሌላን የማንነካ የራሳችንንም የማናስነካ ብርቱዎች መሆናችንን እናውቃለንና።
እኛ አባይን በማስገበር፣ በበረሐ የሚደረገውን የወንድምና እህቶቻችንን ስደት ለማስቀረት የምንተጋ፤ እኛ በዓለም ፊት በተመጽዋችነት የሚታወቀውን መዝገባችንን ለመለወጥ የምንጥር፣ ህዝቦች በመሆናችን ከማንም የሚነሳውን የተግዳሮት ግፊት ለመቋቋም ወደኋላ አንልም። ስለዚህ እንደገና በድህነት ከምንማቅቅ፣ እንደገና በስደት ከሰው በታች ሆነን ከመንገላታት ይልቅ ይህንን ታላቅ ፕሮጀክት እውን በማድረግ በሀገራት ከፍታ መቆምን መርጠናል። ይህ ደግሞ ህጋዊም፣ ሰብዓዊም ሞራላዊም ምርጫ ነው። ለዚህም የሌላን መልካም ፍቃድ አንጠይቅም፤ ይልቅ መብታችንን እንዲያውቁልን በመጠየቅ የሚከፈለውን መስዋእትነት ሁሉ ለመክፈል ዝግጁዎች መሆናችንን ማሳወቅ ነው፤ የምንፈልገው።
ግብጽና ሱዳን ከታላቁ የአስዋን ግድብ ሌላ ተጨማሪ ዘጠኝ ግድቦችን በአባይ ውሃ (ናይል ይሉታል እነርሱ) ገድበው መጠቀማቸው መልካም ነው። ለዚህ የእኛም ፍቃድና ዕውቅና አላስፈለጋቸውም፤ እንደዚሁ ሁሉ ለእኛም ፍቃዳቸውን ሳይሆን እውቅናቸውን መንፈግ የትም አያደርሳቸውም። ግድቡን በእርግጥ የምንሰራው ማንንም ለማሳዘን ሳይሆን ከራሳችን የኃይል እጥረት ኀዘን ለመውጣት ነው፤ እርሱንም እንሰራዋለን!!
ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ፣ ለግድቡ የምናዋጣው እያንዳንዷ ብር አንድ ጡብ የምታቀብል ጉልበት እንጂ የምትባክን ምናምንቴ ብናኝ አይደለችም። በሌላ የህይወት መስኮች ሀገራችን ከእኛ የምትጠብቀውን ሙያዊና መንፈሳዊ ሥራዎች ሳናስተጓጉል በመፈጸም፣ ግድቡን በአንድ ልብ ሆነን እየሰራን፤ እንጠብቀዋለን። ሙሌቱንም እንጀምራለን፤ እንቀጥላለን፤ የኃይል ፍላጎታችንንም እናሟላለን።
በዚህ ሥራ ላይ ያላንዳች ማቅማማት፣ በሳምንት ሰባት ቀን በቀን 24 ሰዓት ሳትታክቱ የበረሀውን የአየር ንብረት ግለት በመቋቋም ራሳችሁን ለአደጋ አጋልጣችሁ ግንባታውን እያጧጧፋችሁ ያላችሁ የሐገሬ መሐንዲሶች፣ አሽከርካሪዎች፣ የዝርጋታ ባለሙያዎች፣ ግንበኞች፣ የጥበቃ አምደኞች፣ የላብና ደማችሁ ውጤት የሆነው ሥራ ወደላቀ ምዕራፍ ለመሸጋገር ጫፍ ላይ ደርሷልና ክንዶቻችሁ እንዲጠነክሩና መንፈሳችሁ ይበልጥ እንዲጸና፣ ፀጋው በፍቅር ይብዛላችሁ፤ እላለሁ፤ አመሰግናለሁ።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ፍቅር ታፍራና ተከብራ ትኑር!!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 11, 2012
ከአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ