የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 29(2) ማንኛውም ሰው ያለምንም ጣልቃ ገብነት ሀሳቡን የመግለጽ ነጻነት አለው። ይህ ነጻነት በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሑፍ ወይም በህትመት በሥነ ጥበብ መልክ ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ ማንኛውንም አይነት መረጃና ሀሳብ የመሰብሰብ የመቀበልና የማሰራጨት ነጻነቶችን ያጠቃልላል ይላል። ይህ አንቀጽ የወረቀት ላይ ንቅሳትነት ዘመኑ አብቅቶ ሳይሸራረፍ ተግባራዊ መደረግ የጀመረው ከለውጡ ወዲህ ባሉት ሁለት ዓመታት ነው። ታዲያ ኃላፊነት በተመላበት መንገድ ሙያዊ ስነ ምግባርን ተላብሰው ነጻነቱን ማጣጣም የቻሉት ሚዲያዎች ጥቂቶች ናቸው። የተቀሩት ነጻነቱን ከሕግ በላይ የመሆኛ ፍቃድ አድርገው ቆጥረውት ደጋግመው ቀያይ መስመሮችን ተላልፈዋል።
ጽንፈኛ ፖለቲከኞች የሚዲያዎችን መሪ በጨበጡበት አገር የፕሬስ ነጻነት እውን ሲሆን “ማጅክ ቡሌት ሞዴል” ተብሎ የሚጠራው የሚዲያ ተጽዕኖ ንድፈ ሀሳብ በተግባር ይተረጎማል። መርፌ፣ ጥይት ወይም ስሪንጅ ይህን ንድፈ ሀሳብ ለመግለጽ ማንጸሪያ ሆነው ይጠቀሳሉ። ንድፈ ሀሳቡ ከሚዲያ የሚተላለፍ መልዕክት ልክ እንደተተኮሰ ጥይት ወይም በስሪንጅ እንደተሰጠ መድኃኒት በፍጥነት ውጤት ያመጣል ባይ ነው። ከለውጡ ወዲህ በሀገራችን በተከሰቱ ግጭቶች ለተቀጠፉ ህይወቶች፤ ለደረሱ የአካል ጉዳቶችና ለወደሙ ንብረቶች ያገኙትን ነጻነት ባልተገባ መንገድ የተጠቀሙ የተለያዩ ሚዲያዎችና ማህበራዊ ድረ ገጾች ከፍተኛ አስተዋጾኦ ማድረጋቸው የአደባባይ ምስጢር ነው።
የበዙ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች፣ ጋዜጦችና መጽሔቶች ያገኙትን ነጻነት ኃላፊነት በተመላበት መንገድ ለመጠቀም ሲቸገሩ ተስተውለዋል። በግልጽ ውግንና ይዘው ፖለቲካዊ አቋሞችን አራምደዋል። በትንታኔ ስም የአንድን ወገን ፖለቲካዊ ፍላጎት ለማስፈጸም ቀኝ አዝማች፣ ግራ አዝማችና ፊታውራሪ ሆነው ተሰልፈዋል። ለዘመናት በመንግሥት ቁጥጥር ስር የነበረውን ኳስ ለውጡ ወደ እጃቸው ቢያንከባልለውም፣ እነርሱ ግን ህግጋቱን ጠብቀው በነጻነት በመንቀሳቀስ ፈንታ ህዝብን ግጭትና ሁከት ውስጥ ለመክተት የማያቋርጥ ቅስቀሳ ማድረግን የሙጥኝ ብለዋል። ለዘመናት አብሮ የኖረን ህዝብ ለመከፋፈልና በጠላትነት እንዲተያይ ለሚያደርጉ የፈጠራ ትርክቶች ሰፊ ሽፋን ሰጥተዋል። የዘር ፍጅት ሊያስከትሉ የሚችሉ የአመጽ ጥሪዎችን በቀጥታ ስርጭት አስተላልፈዋል። እኩይ ዓላማቸውን ለማሳካት ሲሉ ውሸት አምራችና አከፋፋይ ሆነው ወደቀ ሲባል ተሰበረ፤ ታመመ ሲባል ሞተ እያሉ ዘግበዋል። ተዘግቶ የቆየ ቤት ሲከፈት ከሚኖረው ሽታ በላይ ከርፍተው ተጠፍንገው የታሰሩበትን ሰንሰለት የናፈቁ መስለዋል። በነጻነት ሀዲድ ላይ ሆነው ወደ ባርነት ሽምጥ ጋልበዋል።
አንዳንድ ጊዜ በጎ ተጽእኖ ማሳደር የሚያስችሉ መሳሪያዎች በአጠቃቀም ችግር ጥፋትን ጋባዥ ይሆናሉ። ዝና አያያዙን ላወቀበት አውንታዊ ተጽዕኖ መፍጠሪያ መንገድ ነው። ማጣፊያው ለጠፋው ደግሞ ራሱንና ተከታዮቹን የሚያደማ ዘነዘና ይሆንበታል። ሚዲያዎችም እንዲሁ ናቸው። ከተሰጣቸው የነጻነት ቀጠና ውጭ ገደብ አልፈው ግጭት የሚቀሰቅሱ ዘገባዎችን ማቅረብ ከተያያዙ፣ ሽብር አንጋሽና እልቂት ደጋሽ ይሆናሉ። የብዙኃን መገናኛ ጠበብቶች እንደሚናገሩት እንኳንስ ግጭትን እንደሚጋብዝ እየታወቀ የሚነዛ የፈጠራ ወሬ፣ ተጨባጭ መረጃ የተገኘበት ጉዳይ እውነት በመሆኑ ብቻ አይዘገብም። በሀገርና በወገን ላይ ሊያደርስ የሚችለው ጉዳት ከግምት መግባት አለበት።
ትናንት ተበዳይ የነበረው ሚዲያ ዛሬ አገርንና ህዝብን በዳይ ሆኖ መገኘቱ አግራሞትን ያጭራል። ኢትዮጵያ ውስጥ ለሶስት የመንግሥት ሥርዓቶች የዘለቀ የፕሬስ ነጻነት አፈና ነበር። ፕሬሱ እንዴት ካለ ረጅም ጨለማ በኋላ ንጋት እንደሆነለት ለማሳየት ራቅ ከሚለው የቀዳማዊ ኃይለስላሴ እና ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ዘመን አንድ አንድ፣ ቅርብ ከሆነው ከኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ) ዘመን ደግሞ በርከት ያሉ አስረጂዎችን ለመጥቀስ እወዳለሁ።
ቀዳማዊ ኃይለስላሴ በኢትዮጵያ የጋዜጣ ህትመት እንዲጀመርና የሬዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እንዲከፈቱ ከፍተኛ ሚና መጫወታቸው አይካድም። ነገር ግን የሃሳብ ብዙኃነትን በማስተናገድ እረገድ ጉልህ ችግር ነበረባቸው። በንጉሡ የመጨረሻ የስልጣን ዘመናት የማስታወቂያ ሚኒስትሩ ዶክተር ተስፋዬ ገብረ እግዚአ በወቅቱ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ለነበሩት አቶ ተገኝ የተሻወርቅ ጥር 30 ቀን 1964 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ አንድ መመሪያ ሰጥተው ነበር። ይህ መመሪያ 26 ነጥቦችን በማንሳት ምንም አይነት ጽሑፍ እንዳይጻፍባቸውና አስተያየት እንዳይሰጥባቸው ይከለክላል። በክልከላው ከተካተቱት ነጥቦች መካከል የንጉሠ ነገሥቱን አገዛዝና ዘውግ እንዲሁም የኢትዮጵያን ሕገ መንግሥት የሚነካ፤ የንጉሣውያንን ቤተሰቦችና የሚኒስትሮችን ክብር የሚነካ፤ የሥራ ፈት ብዛትን፣ የአሰሪና ሰራተኛ ግጭትን፣ የተማሪዎችን ሁከት፣ የግብር ጭማሪን፣ የኑሮ ውድነትን፣ የደመወዝ ጭማሪን፣ የመንግሥት ሠራተኞች የሚያነሱትን ቅሬታ እና አድማን የሚመለከት ጽሑፍ የሚሉት ይገኙበታል። የደብዳቤው መልዕክት የሚቋጨው “እነዚህ እነዚህን የመሳሰሉ ነጥቦች ላይ አስተያየት መስጠት በጥብቅ የተከለከለ ነው” በሚል ዓረፍተ ነገር ነው።
የመውረስ አባዜ የተጠናወተው የደርግ መንግሥት በበኩሉ ግለሰቦች ያቋቋሙትን ጋዜጣ መውረስ ደረጃ ደርሷል። የቀድሞ አዲስ ነገር ጋዜጣ ነሐሴ 16 ቀን 2001 ዓ.ም ባስነበበው ሁለተኛ ዓመት ቁጥር 96 እትሙ ዋና አዘጋጁ ታምራት ነገራ “የበሪሳ ውጣ ውረድ” በሚል ርዕስ የጻፈውን፣ ጋዜጣዋ ያለፈችበትን አስቸጋሪ መንገድ የሚዳስስ ጽሑፍ አስነብቦ ነበር። በዚህ ጽሑፍ እንደተገለጸው በ1966 ዓ.ም ንጉሳዊው ሥርዓት ተወግዶ ሶሻሊዝም በይፋ ሲታወጅ የብሔሮችን ፖለቲካዊና ማህበራዊ መብት ማስጠበቅ የአገሪቷ ይፋዊ መመሪያ ሆነ። ከዚሁ የሶሻሊዝም መታወጅ ጋር ተያይዞ መንግሥት የብሔር ብሔረሰቦችን ቋንቋና ባህል ለመጠበቅና ማክበር ያስችላሉ ያላቸውን የተለያዩ አዋጆች አጸደቀ።
በዚህ ፖለቲካዊና ባህላዊ ለውጥ የተነቃቁ ግለሰቦችም በኢትዮጵያ ፕሬስ ታሪክ በኦሮምኛ ቋንቋ የምትታተመውን በሪሳ (በአማርኛ ንጋት ማለት ነው) የተሰኘችውን ጋዜጣ አቋቋሙ። የጋዜጣዋን የመጀመሪያ እትምም መስከረም ሁለት ቀን 1968 ዓ.ም ለገበያ አቀረቡ። ጋዜጣዋ በሁለት ሳምንት አንድ ጊዜ ሐሙስ ዕለት ትታተም ነበር። በዘመኑ እንደነበሩት የህትመት ውጤቶች ለቅድመ ምርመራ ትቀርብም ነበር። በቋሚነት ሐሙስ ቀኗን ጠብቃ ግን መታተም አልቻለችም ነበር። ይህ የሆነበት ምክንያትም አብዛኞቹ ጋዜጠኞች ቋሚ ሥራ ኖሯቸው ጋዜጣዋን በትርፍ ጊዜ ይሰሩ ስለነበረ ነው። በጋዜጣዋ ስለ ጭቆና፣ ስለ ኦሮሚያ ቀኝ መገዛትና ስለ ኦሮሞ ባህልና ቋንቋ የሚያትቱ ሀሳቦች ይጻፉ ነበር።
የኋላ ኋላ በሪሳ በሪሳ አንደ አጀማመሯ የአስተዳደርና የኤዲቶሪያል ነጻነት ኖሯት መቀጠል አልቻለችም። ጋዜጣዋ በመንግሥት ላይ ጤናማ ያልሆነ ትችት አቅራቢና አፍራሽ ተደርጋ ተፈረጀች። ታህሳስ 22 ቀን 1969 ዓ.ም የሚኒስትሮች ምክር ቤት በወመ1/127/16050 በጻፈው ደብዳቤ ጋዜጣዋ ከየካቲት 1968 ዓ.ም ጀምሮ በማስታወቂያ ሚኒስቴር ኃላፊነት የምትታተም ሳምንታዊ ጋዜጣ እንድትሆን ተወሰነ። ጥር 5 ቀን 1969 ዓ.ም ይህን ውሳኔ አስመልክቶ አዲስ ዘመን ጋዜጣ በፊት ገጹ ዜና ሰራ። በሪሳ ጋዜጣ በመንግሥት እንድትወረስ የተላለፈው ውሳኔ ገቢር ሆነ። ጋዜጣዋ ከመወረሷ በፊት በአንድ እትም 20 ሺ ገደማ አንባቢ ነበራት። ከተወረሰች በኋላ ግን ይህ ቁጥር ወደ 2500 ዝቅ ብሏል።
የደርግ መንግሥት ከተገረሰሰ በኋላ በ1984 ዓ.ም የፕሬስ አዋጅ መጽደቁን ተከትሎ 287 የህትመት ውጤቶች ገበያውን መቀላቀላቸውን እና ከሶስት ዓመታት በኋላ ደግሞ ከ400 የሚበልጡ ጋዜጦችና 170 ያህል መጽሔቶች ለስርጭት መብቃታቸውን ጥናቶች ያመለክታሉ። በተለምዶ የመንግሥት የሚባሉት የህዝብ ሚዲያዎች በወቅቱ የገዢው ፓርቲ ልሳን ተደርገው በመቆጠራቸው የግል ፕሬሱ በሕዝብ ዘንድ ተአማኒነትና ተቀባይነት ማግኘት ችሎ ነበር። ይህን ሁኔታ የተረዳው የወቅቱ ገዢ ፓርቲ ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ የፕሬስ ነጻነት አዋጅን ባጸደቀ ማግስት አፈናና ማዋከብን ምርጫው አደረገ። በኋላም ምርጫ 97ን ተከትሎ በተከሰተው ቀውስ አምስት ጋዜጦችን በቀጥታ አግዷል። 26 ጋዜጦችን ደግሞ እንዳይታተሙ ለማተሚያ ቤቶች ዝርዝራቸውን የያዘ ደብዳቤ በትኖ በህትመት ብርሃን እጦት ከገበያው እንዲወጡ አድርጓል። በአንድ አጋጣሚም መንግሥት “አሳሳቢ ነው” ባለው ጉዳይ ላይ ዘገባ ያሳተመን ጋዜጣ 40,000 ኮፒ ህትመት እንዲቃጠል ተደርጓል። ወትሮውንም ቢሆን “በረጅም ገመድ የታሰረች ዶሮ የተፈታች ይመስላታል” በሚል ቢሂላቸው ከሚታወቁት “ታላቁ መሪ” እውነተኛ የፕሬስ ነጻነትን መጠበቅ የዋህነት ነበር።
ነጻ ሜዳ አገኘን ብለው በነጻነት የተንቀሳቀሱ በርካታ ጋዜጠኞችም ለስደት፣ ለእስርና እንግልት ተዳርገዋል። “ሂዩማን ራይትስ ዎች” የተሰኘው ዓለም አቀፍ ድርጅት እ.ኤ.አ. በጃንዋሪ 2015 “ጋዜጠኝነት ወንጀል አይደለም” በሚል ርዕስ በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት ላይ ተፈጽሟል ያለውን የመብት ጥሰት አስመልክቶ ባወጣው ሪፖርት ማጠቃለያ ላይ “ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ እ.ኤ.አ. በ2010 በተካሄደው ምርጫ 99 ነጥብ ስድስት በመቶ የፓርላማ መቀመጫን ካሸነፈበት ጊዜ አንስቶ ሃሳብን የመግለጽ ነጻነትንና መረጃ የማግኘት መብትን በመገደብ በግል መገናኛ-ብዙሃን ላይ እያሳደረ ያለውን አሉታዊ ተጽዕኖ አባብሶታል። እ.ኤ.አ. ከ2010 ጀምሮ 60 ጋዜጠኞች አገር ለቀው ተሰደዋል፤ ሌሎች 19 ጋዜጠኞች ደግሞ በእስር ላይ እየተሰቃዩ ይገኛሉ። መንግሥት በደርዘኖች የሚቆጠሩ ህትመቶችን ዘግቷል፤ እንዲሁም አብዛኛዎቹን የቴሌቪዥንና የሬድዮ ስርጭቶች በቁጥጥሩ ስር በማድረግ ኢትዮጵያውያን የሀገር ውስጥ የፖለቲካ ጉዳዮችን በተመለከተ ነጻ መረጃና ትንታኔ የሚያገኙበትን እድል አጣቧል።” ሲል መንግሥትን በመክሰስ መሪር ወቀሳን ሰንዝሮ ነበር።
የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ የሆነው የ“ኮሚቴ ቱ ፕሮቴክት ጆርናሊስትስ” (Committee to protect Journalists) መረጃና “የሂዩማን ራይትስ ዎች” ጥናት እንደሚያመለክተው ኢትዮጵያ ከኢራን በመቀጠል በዓለም ላይ በርካታ ቁጥር ያላቸው ጋዜጠኞችን ለስደት የምትዳርግ ሀገር መሆን ደረጃ ደርሳ ነበር። ጋዜጠኞች ወቅታዊ ክስተቶችን አስመልክተው በሚሰሩት ዘገባና ትንታኔ ምክንያት አፋኝ ህጎችን ሽፋን በሚያደርጉ የደህንነት ሰራተኞች ዛቻና ማስፈራሪያ ይደርስባቸው ነበር። አልፎ አልፎም አካላዊ ጥቃት ይፈጸምባቸውና ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ወንጀል ፈጽማችኋል በሚል የሽብር ክስ ይመሰረትባቸው ነበር። የፍርድ ቤት ክርክራቸውም ፍትሃዊ የፍርድ ሂደትን የሚጥሱ አሰራሮች የሚታዩበትና የሚሰጡ ውሳኔዎችም ገለልተኛ ባልሆኑ ዳኞች የሚተላለፉ ነበሩ። የጋዜጠኞች የመረጃ ምንጮች በተደጋጋሚ ለጥቃት እየተጋለጡ ለመገናኛ ብዙሃን መረጃ ለመስጠት ፍርሃት የሚያድርባቸው ሰዎች ቁጥር አሻቅቦ ነበር። በውጭ አገራት በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሚመሩ በርካታ ጦማሮችና ድረ ገጾችም ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይታዩ ሲደረግ ቆይቷል።
እንግዲህ ከዚህ ሁሉ እልህ አስጨራሽ ትግልና ውጣ ውረድ በኋላ ነው በ2010 ዓ.ም የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የተከፈተው። የታሰሩ ጋዜጠኞች ተፈቱ፤ በፍርድ ቤት ጉዳያቸው እየታየ የነበሩም ክሱ እንዲቋረጥላቸው ተደረገ፤ በርካታ ድረ ገጾች የተጣለባቸው እግድ ተነሳላቸው፤ በአሸባሪነት ተፈርጀው የነበሩ ሚዲያዎች አገር ውስጥ ገብተው ጽህፈት ቤቶች ለመክፈትና ስቱዲዮ ለመገንባት በቁ፤ አፋኙ የጸረ ሽብር አዋጅ ተሻሻለ እንዲሁም የዘርፉን ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ አዲስ የፕሬስ አዋጅ የማዘጋጀት ሥራ ተጀመረ።
የተወሰዱትን እርምጃዎች ተከትሎም ሀሳብን የመግለጽ ነጻነት ሰፈነ። አዳዲስ ጋዜጦች፣ መጽሔቶች፣ የሬዲዮ ጣቢያዎችና የሳተላይት ቴሌቪዥን ስርጭቶች ተጀመሩ። “ሪፖርተርስ ዊዛውት ቦርደርስ” በ2011 ዓ.ም ባወጣው ዓመታዊ የፕሬስ ነጻነትን በሚገልጽ የአገራት ደረጃ ኢትዮጵያ በ2010 ዓ.ም ከነበረችበት 150ኛ ደረጃ 40 ደረጃዎችን በማሻሻል 110ኛ ደረጃን መያዟን ገልጸ። ድርጅቱ ኢትዮጵያ ደረጃዋን ለማሻሻል የበቃችው የታሰሩ ጋዜጠኞችንና ጦማሪያንን በመልቀቋ፤ የታገዱ ድረ-ገጾችን በመክፈቷና አፋኝ አዋጆችን ለማሻሻል በመንቀሳቀሷ ነው ሲል አገሪቱ የሚዲያ ነጻነት እንዲኖር በቁርጠኝነት እያደረገች ላለችው እንቅስቃሴ ምስክርነቱን ሰጠ።
ምን ዋጋ አለው! የነጻነት ትርጉም ባልተገለጸላቸው አሊያም ሆነኝ ብለው አይናቸውን በጨፈኑ ሚዲያዎች ዘፈቀዳዊ እንቅስቃሴ ብዙም ሳይቆይ ነገሮች ሌላ መልክ መያዝ ጀመሩ። ለመስኩ ተዋንያን፣ ስንት መስዋትነት ተከፍሎበት የተገኘ ዕድል እንዲህ መጫወቻ ሲሆን ከማየት በላይ የሚያሳምም ነገር የለም። መንግሥት የአመጽ ጥሪ ያስተላለፉ ሚዲያዎችን ጽሕፈት ቤቶች መበርበሩ፤ ማሰራጫ ስቱዲዮዎቻቸው እንዲዘጉና ከሳተላይት ላይ እንዲወርዱ ማድረጉ ይበል የሚያሰኝ እርምጃ ነው። ወደ ፊትም ቢሆን ሚዲያዎችን ሞኒተር በማድረግ ህግ የሚተላለፉት እንዲታረሙ ማስጠንቀቂያ የመስጠትና የአሻፈረኝ ባዮችን የንግድ ፍቃድ የመሰረዝ እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።
በብዙ አገራት የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን እና የተሻለ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ደረጃ ያላቸው ግለሰቦች የሃሳብ መሪዎች ተደርገው ይወሰዳሉ። እነዚህ የሃሳብ መሪዎች ሚዲያው የሚረጫቸውን ጸብ አጫሪ መረጃዎች አቅጣጫ እንዲቀይሩና ማህበረሰቡ ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ የማድረግ አቅም አላቸው። አገራችንም የተለያዩ ፈታኝ ወቅቶችን ስትጋፈጥ ከፊት ሆነው ዜጎቿን ያነቁና ያበረቱ የሀሳብ መሪዎች ነበሯት፤ ዛሬም አሏት። ነገር ግን በየደረጃው ባሉ የማህበረሰብ እርከኖች ላይ የሚገኙት የእነዚህ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሀሳብ መሪዎች ተቀባይነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል። ይህም ፈር የለቀቁ ሚዲያዎችን ይበልጥ ጉልበታምና አስፈሪ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል። ከሚወሰዱ እርምጃዎች ጎን ለጎን ይህን የኃይል አሰላለፍ ወደ ነበረበት ለመመለስ ትልቅ ሥራ መሰራት አለበት።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 11, 2012
በ የትናየት ፈሩ