ያለነው ጸጥ ባለ ባህር ላይ አይደለም፤ ገና የሚሰክኑ፣ ገና የሚታረሙና ገና የሚረጋጉ ነገሮች አሉን። ይህ የለውጥ ህግ ነው። በለውጥ ውስጥ አንድ ዓይነት ገጽ የሚባል የለም። ለውጥ፣ ልዩ ልዩ ገጾች አሉት። ይህ ለኢትዮጵያችን፣ ወረድ ሲል ለክልሎቻችን ሲያልፍም ዞንና ወረዳዎቻችን አለፍ አለፍ እያሉ፣ እነዚህን ጎርባጭ ክስተቶች እያስተናገዱ ያለንበት ወቅት ላይ ነው፤ ያለነው። ለዚህም ነው፤ ፀጥ ባለ ባህር ላይ አይደለንም ያልኩት።
ስለዚህም በጣት ወይም በእጅ የሚቆጠሩ ሃይላት በትርና ነገር አንጠልጥለው ችግር ሲፈጥሩ ድርጊቱን “የስኒ ማዕበል” ነው፤ ብለን መናቅ የለብንም። የአጥፊ ትንሽ የለውም። አስኮናኝ ብለን የምንተዋቸው ነገሮቻችን ነገ ግዙፍና ቋጥኝ የሚያህሉ ጋሬጣዎች በመፍጠር መከራችንን ሊያራዝሙት ይችላሉ። የመከራ ሌሊቶች ደግሞ ቶሎ አይነጉም፤ ጣርም ፀርም አለባቸው። ያለንበት ጊዜ ትኩረት የሚሻ ነው፤ ስለዚህ ትኩረት፣ ብልሃትና ጥበብ እንጂ እልህ ከቶውንም አያስፈልግም። እልህና ቁጣ በነገሰበት በዚያ ፍትህ ስፍራ ታጣለችና።
ችግሩን በሚገባ ማጤንና ለመፍትሄው መስራት ይገባናል። ሰላማዊ ስፍራ ቆመን፣ “ነፍስ ይማር” እያልንም አንዘልቅም። ከቶውንም ከዚህ ብዙ አልፈን፣ የጠፋው፣ የታመመውና የተጎዳው በቁጥር ጥቂት ነው፤ እንደተፈራው አይደለም ትንሽ ነው፤ እያልን፣ በቁጥርም በስሌትም መጫወት አቁመን በጥንቃቄ ልንቆም ነው፤ የሚገባን። የሚባክን ነጠላ ነፍስ። የሚባክን ነጠላ አካል የለንም፤ ፈጣሪ ለሙከራ የሰራው ነፍስም አካልም የለንምና።
ኦሃድ ቤንዓም የተባሉ ኢትጵያዊ ምሁር በቅርቡ ከአንድ መገናኛ ብዙሃን ጋር ቃለ-መጠይቅ ሲያደርጉ “ማንም በትናንት ጉብዝናው የቆየ የለም፤ የሚቆይም የለም፤ አስተሳሰቦች ይለወጣሉ፤ ጉልበቶች ይደክማሉ፤ ሰበቦች ያጥራሉ፤ ካለፈው ድክመታችን ተምረን ጥሩውን ማጎልበት ካልቻልን ተቸክለን በአሮጌ የታሪክ ሰበዞች ላይ ቆመን የትም አንደርስም፤ ያለፈውን ደጋግመን መውቀስ የአሁኑን ጠንካራ አያደርገውም፤ በዚህም አስተሳሰብ የምናሳድገው ሐገርም የምንደርስበትም ግብም ፍሬያማ አይደለም። ” ሲሉ ተደምጠዋል። (ለዚህ እንዲስማማ ተደርጎ የቀረበ ነው)
የማይጠቅሙንን ጉዳዮች እያነሳን በሆኑት ባለፉትና አሁን በማይጠቅሙን ነገሮች ላይ ከተወዛገብን በማበጠሪያ እንደሚጣሉ መላጦች ነው፤ የምንሆነው። መላጣ እኮ፣ “መላ አጥ”ም፣ የሚሆነው በዚህ በዚህ ጊዜ ነው። በተቻለን መጠን፣ በሁኔታዎች ላይ ለምን፣ በምን ምክንያትና እንዴት ከማን ጋር እንደምንነጋገርበት ማወቅም አስተዋይነት ነው። አንዳንዴ የምንወዛገብበት ምክንያት ረብ -የለሽና በውጤቱ ማንም ተጠቃሚ የማይሆንበት ጊዜና ብዙ ነው። ስለዚህም ነው፤ ያወዛገበን ነገር ምንድነው፤ ብሎ መጠየቅ ተገቢ የሚሆነው። ይጠቅመናልን ? እውነት ነው? ያንጻል ? ጉዳዩ በሚገኝበት ሳይሆን በሚሆንበት፣ በመገኘቱም የምንጠቀምበት ምን ያህል ነው፤ ብሎ መገመትና መመዘን እጅግ ጠቃሚ ነው።
ልብ ብላችሁ ከሆነ ብዙ ጊዜ፣ በቤት ውስጥ የሚነሱ ችግሮች፣ ጭቅጭቆች እና ንትርኮች መነሻ ነገሮች ትናንሽ ሆነው ነው፤ የሚገኙት። ዋናው ነገር ግን እውነተኛውንና ቡጡን ወይ እምብርቱን ነገር ትተን በማይረቡ ግንጥል ነገሮች ላይ ወይም ድርጊቶች ላይ እናተኩራለን። ብዙ የተጣሉ ባልና ሚስቶች በልዩ ልዩ ምክንያት አለመግባባት ፈጥረው፣ ለመደራደርም ይሁን ለመሸማገል ወደ አሸማጋዮች ይመጣሉ። በዚህ ጊዜ የሚያነሷቸው ነገሮች ብዙ ጊዜ አስገራሚ ናቸው። ቀደም ሲል የነበረውን የባሏን ስም ደጋግማ በማንሳት አጠገቧ መሆኔን ትክዳለች። ስለእርሱ ማውራት ከጀመረች ማቆሚያ የላትም። ይላል ባል። እርሷ ስትጠየቅ ደግሞ የድሮ የሴት ጓደኛውን ፎቶ አልበም ውስጥ አስቀምጦ አገኘሁት። ይህ ምን ማለት ነው፣ መቼም አይክድም፤ ግን የሆነ ነገር በልቡ ካልቀረ የእርሷ ፎቶ አልበሙ ውስጥ ምን ያደርጋል፤ ትላለች።
ከዚህ ሌላስ ስትባል ስናገር አይሰማኝም፤ ለቤታችን እና ለልጆቻችን የሚሆነውን ነገር ሳነሳበት በተሰላቸ መልክ ነው፤ የሚሰማኝ። እንዲያውም አንዳንዴ “ተይኝ”
ይለኛል። እንዴት ነው ተይኝ የሚለው? አብረው እያሉ ተይኝ ማለት ወደቀደመ ፍቅሩ ለመመለስ መንገድ መጥረግ አይደለም ወይ፣ ትላለች።
እርሱ ደግሞ በበኩሉ አልጋችንን በልዩ ልዩ ክፍል እናድርገውና ስንፈልግ “ተነፋፍቀን” እንገናኝ ስላት ሰለቸኸኝ፤ ማለት ነው፤ ወይ ብላ የድሮ አልበም ታገላብጣለች። ደግሞ የቀድሞ ባሏን ስም ደጋግማ ታነሳለች፤ ይላል።
በሁለቱም ባለትዳሮች መካከል ባለፈና በቀረ ሰው ስምና መልክ መነሳት ሳቢያ የተፈጠረው ነገር የችግራቸው መነሻ ይመሰል እንጂ ዋናው ነገር ከነገሮች መካከል ጥሩው ነገር ለማየት ያለመቻልና ይህንንም በቀና ልብ አይቶ ለመነጋገር ያለመዘጋጀት ችግር ነው።
ሴቷ ልጅ ደጋግማ የምታነሳው የትኩረት አይነፈገኝ ጥያቄ ሲሆን፣ ትኩረት አለመነሳቷን ለማረጋገጥ የምታነሳቸውን ሐሳቦች “ሁሉ”፣ እንዲቀበላት መፈለጓ ነው። ይህንንም የሀሳብ አመንጪነት ስፍራ ሙሉ በሙሉ ለራሷ ስለሰጠች ለእርሱ የሚሆን ስፍራ ነስታዋለች፤ ወይም ከልክላዋለች። በአንድ ቤት ሆነን እንነፋፈቅ ማለትን ልብ ብለን ካሰብነው ክፋት የለውም። ሌላ ሴት ወደማሰብ መሄድን አያሳይም፤ ማሰብም አይደለም። አሮጌ አልበም ፍለጋም ማስኬድ አልነበረበትም። ይሁንናም የድሮዋን ሴት ፎቶ፣ ሚስት አገኘች እንበል፤ ፎቶው ጀርባ ላይም፣ “የኔ ፍቅር አንቺን ማጣት ለእኔ ሞት ነው፤” የሚል ጽሑፍና ከዘፈን ግጥምም አንድ ሁለት ዘለላ ስንኝ ተጽፎበት አለ፤ እንበል። የዛሬ 15 ዓመት፣ ከቀድሞዋ ፍቅረኛው ጋር አንድ ላይ ሳሉ የጻፈውን ፅሑፍ የዛሬ መወንጀያ ወይም መካሰሻ አድርጎ ማቅረብ ተገቢነት የለውም። ያኔ ይህንን ሐሳብ የገለጠበት ዓውድና የግንኙነት ምዕራፍና ገጽታ ዛሬ የለም። የዛሬ 15 ዓመት በአፍላ ፍቅር ላይ ከነበረበት ፍቅርማ ተፋርሶ፣ ዛሬ ይህችኛዋን ሴት አግብቶ እየኖረ ነው፤ ያችም ሴት ሌላ ባል አግብታ የራሷን ኑሮ እየመራች ነው፤ ምን ይሁን ተብሎ ታዲያ ለድሮዋ ፍቅረኛው ያንን ቃል ይዞ ተገኘ፤ ይህንንስ ቃል ከፎቶው ጀርባ አገኘሁኝ? ብሎ መቆላጨትን ምን አመጣው። ምንም። ይህ አሁን ላለመግባባት ምክንያትም መነሻም አይሆንም። ይልቅ በድሮ ነገር አሁን ለመነታረክ አንዳቸው ለአንዳቸው የነፈጉት ትኩረት ነው፤ ዋነኛው ምክንያት።
እርሱም ቢሆን ከእርሱ በፊት ባል እንደነበራት ሳታስበው በሞት እንዳጣችው። እና ባለፈም በገደምም ሁኔታዎችን አስረግጣ ለማሳየት ስትል የምታነሳው አሁን ያለው ባሏ እንደ ከዚህ በፊቱ ሰው እንዲሆንላት ከመመኘት እንደሆነ በማሰብ እንጂ ያንንማ ቆማ አፈር አልብሳዋለች። አሁን ራስንም ከሞተ ሰው ጋር ማመሳሰል ለራስም ለትዳሩም አይጠቅምም። ባይሆን በግልጽ ቋንቋ “እባክሽ በረባ ባልረባው ምክንያት ደጋግመሽ የበፊት ባልሽን ስታነሽው ቅር ይለኛልና በተቻለሽ መጠን በቂ
ምክንያት ካላገኘሽ አታንሺው። ” ማለት ተገቢ ነው። ነገሩን ለራስ እያወሩ ራሴን አሳነሰች። ብሎ ራስን መጣልና መጉዳት እርሷን ወደ መጉዳት ይወስዳል። ይህ ደግሞ ትዳሩን ታማሚ ያደርገዋል። ሄዶሄዶም ትዳሩ በቀላሉ በንግግር ሊፈቱ በሚችሉት ችግሮች ሳቢያ ወደሞት ይሄዳል። ለሁሉም የሚረባው ግን በነገሮች ላይ በለዘብታ መነጋገር ነው።
እርስ በእርስ ጊዜ ወስዶ ማውራትና ሊነሱም ሊደረጉም በማይገቧቸው ነገሮች ላይ ተነጋግሮ እልባት መስጠት ተገቢ ነው። በተነገሩና በተወሩ ነገሮች ላይ የራስን ትርጉም ሰጥቶ፣ ከራስ አውርቶና ተጎድቶ መቅረት ከቶውንም አይረባም። ይህ የአጋርነትን እና የመደጋገፍን “ሀ-ሁ” የሚያፈርስ ተግባር ነው። ውሎ አድሮም ቤት ያፈርሳል። አንዳንዴ ሳይን ብዙ ጊዜም ለንግግር ሁሉ አንድምታዊ ትርጉም። መስጠት ማለትም እንዲህ ያለችው፣ በዚህ ምክንያት ነው፤ እንዲህ ስትልም እንዲህና እንዲህ ልትል አስባ ነው፤ ብሎ መተርጎም አፍራሽ ነው።
ነገሮችን በአዎንታዊ ስሜት ለማየት ካልቻልን፣ ትናንሽ ጉዳቶች በተበዳይነት ስሜትና ትርጓሜ በማየት ትዳር ይፈርሳል አንዳንዴም ቤተሰብ ይበተናል። ዋናው ጉዳዬ ይህ አይደለምና ከዚህ በላይ በዝርዝር አልሄድበትም። ሆኖም ብዙ ጊዜ፣ በባለትዳሮች መካከል እንደምክንያት የሚነሱት ነገሮች፣ በማበጠሪያ እንደሚጣሉ መላጦች አስቂኝ ትእይንት የሚፈጥር ነው።
በወላጆችና በልጆች፣ በአያቶችና በልጅ ልጆች፣ በተጣማሪዎች፣ በሥራ ባልደረቦች፣ በጓደኞችና በወዳጆች መካከል ያለውን የመስተጋብር ድልድይ የሚያፈርሰው አጉል ትርጉም ነው። “ምን ቢንቀኝ ነው፤ እንዴት ብታየኝ ነው፤ እንዴት ቢደፍረኝ ነው፤ እንዴት ብታስብ ነው” በመባባል መልካሙን ነገር ማጣመም በሌለ ፀጉር ለማበጠሪያ እንደመጣላት ነው። እንዲያውም ማበጠሪያው ይገባኛል፤ ወደፊት ገዝቼ የማደርገውን ጸጉር አበጥርበታለሁ፤ ካላልን በስተቀር። ገና ለገና ለሚገዛ ጸጉር በማበጠሪያ መጣላትም እኮ አስቂኝ ነገር ነው፤ ጎበዝ።
ይህንን ጉዳይ ወደሐገር አስፍተን ካየነውም የሚደራደሩንን ለማሸነፍ ወስኖ መነጋገር የትም አያደርሰንም። ምክንያቱም የሚረታም የሚርረታም ሐሳብ እንዳለን ማወቅና መገመት የተገባ ነው። የኔ ሐሳብ፣ በሁሉም መለኪያ ወደረኛ የለውም፤ የሚወድቅለትና የሚጣልለት ስንጥር ነገር የለውምና ተቀበሉኝ፤ ለማለትማ አዋጅ እንጂ ውይይት አያስፈልግም። ዳኝነቱን ለሌላ ትቶ ወደንግግሩ መግባት ነው፤ የሚያዋጣው። ሐገሬን የጎዳት እናንተ አያገባችሁም። ሁሉም ነገር የሚመለከተው እኔንና እኔን ብቻ ነው፤ ማለት ነው። ስለዚህ ስንነጋገር ጭብጥ ጭብጡን እየለየን በሚያስማማን እየተስማማን፣ በሚለያየን እየተለያየንም እየተቀባበልንም ስንሄድ ነው፤ የሚያምረው። ለዚህ ነው የሚያሸንፍ ሐሳብ የሌላቸው ሰዎች፣ ወደ ጦርነትና ወደግጭት ማለፍ የሚቀናቸው።
ለዚህ ነው የሀገሬ አንድ ገጣሚ። ቀጥሎ ያለውን ግጥም የገጠመው።
“… በደግ ልብ ካልሰማሽ አድናቆቴን።
በጥርጣሬ ካየሽው ነገሬን፣
ከሰጠሁሽ ግምት ይልቅ፣
ራስሽን አንቺው በማድቀቅ፤
ወድቀሽብኛል ከማዕረግሽ፣
ስለዚህ ሁሉም ይቅርብሽ። ” (ያልታተመ ) እንዳለው እየሆንን ነው።
ስለዚህ እህ… ብሎ ለራስ የተሰጠን ክብር በበጎነት አይቶ መቀበል፣ ከፍ ባለ ደረጃ ራስን ማስቀመጥን ያስከትላል። ከዚያ ይልቅ የተባለውን አድናቆት ማጣጣልና በራስ አስተሳሰብ ብቻ መመራት ደግሞ ወዳልተፈለገ ምናልባትም ወደክፉ መደምደሚያ ያመጣል።
ለግጭት የሚተርፍ ጉልበት መከራን ለመሸከም የሚሆን ትከሻ የጨረስን ይመስለኛል። ስለዚህ ቁጭ ብለን ተነጋግረን ነገራችንን መልክ እናስይዝ። የምናቋርጠውን ትልቅ የልማት ባህር ለመግራት በተነደፉ እና በአማራች ስትራቴጂዎች ላይ መነጋገር እንጂ፤ የሚውጠንን የመከራ ኩሬ እዚህም እዚያም ለመቆፈር በህገወጥ መንገድ መኮድኮድ አያዋጣንም። በጨለማዎቻችን ላይ ብርሃን ማብራትና እንቅፋቶቻችንን መጥረግ እንጂ፤ ብርሃናችንን የሚያዳፍኑ ሴራዎችን መወጠን የትም አያደርሰንም።
የሰላምን ዋጋ ጠንቅቆ ለማወቅ በጦርነት ማለፍንና በጦር ስለት መፋጨትን ማንም ለኢትጵያውያን አያስተምረንም። ምክንያቱም ታሪካችን በዚህ በኩል አልፎ ያሳለፈንና የተረፈልንን ነገር ስናየው ኖረናል። ስለዚህ የሚያዋጣን በሰላምና በሰላም ብቻ መነጋገር ነው የሚያዋጣን። ተገድደን የምንገባበት ግጭት እንኳን ቢኖር መዘዙ የሚያስከትለውን አበሳ በሚቀንስ መንገድ ማካሄድና መቋጫ ማበጀት ተገቢ ነው።
በቀላሉ የምንፈታቸውን ችግሮች አካብደን ማየት ከጀመርንና ችግሩን የምንፈታው በአስቸጋሪ መንገድ ብቻ ነው፤ ብለን ከወጠንንና ይህንም ለመተግበር የጨለማና የደም መንገድ ከመረጥን እኛ ራሳችንን ለመፍትሔ አካልነት ሳይሆን ለችግሩ አካልነት ያዘጋጀን መሆናችንን ማወቅ አለብን።
የሚያዋጣው ሁሉን አሳታፊና አስማሚ በሆኑ የጋራ አጀንዳዎች ላይ እየተስማማን በማያስማሙን ቅርንጫፍ ነገሮች ላይ በሐሳብ ሙግት እየታገልን ለመሄድ መዘጋጀት ብልህነትም ሐገር ወዳድነትም ነው። ከዚያ ይልቅ፣ “ሁሉንም ወይም ምንም” ካልን ግን አማራጫችሁ ውድቀት መሆኑን ማወቅ አለባችሁ። ይሄ ደግሞ ጸጉር ባይኖረኝም ሚዶ ለመላጣዬ ይገባኛል ነው። ለራሰበራ (መላጣ) ሐሩር እንዳይጠብሰው ማበጠሪያ ሳይሆን ኮፍያ ነው፤ የሚገባው ካስፈለገውም። ለዚህ ደግሞ ከማንም ፍቃድም ጸብም አያስፈልገውም።
አንዳንድ ሰዎች፣ በቀላሉ ሊያገኙት የሚችሉትን ነገር ሁሉ ነው ለጸብ የሚጋበዙበት። ከዚያም ስንት ዋጋ ከፍዬ እንዳገኘሁት ብታውቁ ትገረማላችሁ፤ ይሏችኋል። ባርኔጣውን ከሱቅ ወይም ከሰው በስጦታ አገኘኸው እንዳንለው የቄስ ክብሩ ጥምጥሙ፣ የወንድ ልጅ ግርማው ቆቡ እያልክ በማጋነን ያለቃቅሳል። የባርኔጣውን ዋጋ ውድነትም እየዞርክ ለማንም መናገር አያስፈልግህም። ለባርኔጣው ስለከፈልከው ዋጋ ስለባርኔጣ ታሪካዊ አመጣጥና አያትህ ባርኔጣ ማለት ክብር መሆኑን ስለመናገራቸው እያነሳህ በየደረስክበት መናገርና ጉዳትህን ሌሎች እንዲካፈሉህ ማውራት ምንም አይጠቅምህም። ጎበዝ የሚያሳስቡን ነገሮች ያሉት ባርኔጣው ላይ ሳይሆን ባርኔጣው በተሸከመው ጭንቅላት ውስጥ ነው፤ የአስተሳሰብ ሚዛንህ አይዛባ፣ አእምሮህን አትጣ እንጂ ባርኔጣህማ እልም ይበል። ትናንት ያንዱ ነበር፤ ዛሬ አንተ አደረግከው ነገ ደግሞ ሌላ ሰው ያጌጥበታል።
በመላጣ የማበጠሪያ ጸብ ጀምሪያለሁና፤ እንደእኔ መላጦች (ራሰበራ ይላሉ አንዳንዶች ) ሆነው በሚቸገሩ ሰዎች አስተሳሰብ አንድ ነገር ብዬ ልደምድም። አንዳንዱ ሰው ስለተመለጠው ጸጉሩ በእጅጉ ሲያዝን ታገኙታላችሁ፤ ጸጉር እኮ አለኝ፤ ለማለትም የኋላ ጸጉራቸውን አሳድገው ወደፊት በማበጠር “ጸጉር በግዴ” ሲሆኑ ታዩዋቸዋላችሁ፤ ይሁንናም ንፋስ ሲመጣ እና ጸጉራቸውን ሲገልበው መላጣቸው ይታያል፤ በዚያም ይሳቀቃሉ። ካልሆነም መቼም የማያድገውን አርቲፊሻል ጸጉር ተሸፍነው ሲቸገሩ ታዩዋቸዋላችሁ። አሁንም፣ የምንሰጣቸው መልስ ተመሳሳይ ነው፤ አሹ፤ ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ እንኳን ባለጸጉር መሆናችሁ አበቃ፤ ይልቅስ የማሰቢያ አእምሯችሁ ላለማስተዋል አይብቃባችሁ እንጂ የራሰ- በራነት እዳው ገብስ ነው። አዲዮስ!!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 11, 2012
በ አገልጋይ ዮናታን አክሊሉ