ከዛሬ 80 ዓመታት በፊት በቀድሞው አጠራር በኤርትራ ጠቅላይ ግዛት መንደፈራ ወይም አዲጉሪ እየተባለች በምትጠራው አካባቢ ነው ተወልደው ያደጉት። በዛው አካባቢ ይገኝ በነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስ ትምህርት ቤት የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታተሉ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ አስመራ ከተማ ልዑል መኮንን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ነው የተማሩት። ይሁንና ገና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳሉ ለውትድርና ተመልምለው ስለነበረ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ በቀጥታ ሆለታ በሚገኘው የቀዳማዊ ኃይለስላሴ የጦር ት/ቤት ለስልጠና ይገባሉ። ከ18 ወራት ስልጠና በኋላ ኦጋዴን ተመድበው ለስድስት ዓመታት አገለገሉ። ኦጋዴን በነበራቸው ቆይታም ባሳዩት ከፍተኛ አፈፃፀም የትምህርት እድል አግኝተው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጂዮግራፊ ትምህርት ለመሰልጠን ትምህርት ይጀምራሉ። ይሁንና የመጀመሪያውን አንድ ዓመት ከተማሩ በኋላ ንጉሰ ነገስቱን የሚቃወሙ ሃይሎች እየተበራከቱ፤ ሁከትና ብጥብጥም እያየለ ሲመጣ ከውትድርና የመጡ ተማሪዎች ወደ ጦር ሠፈራቸው እንዲመለሱ ትዕዛዝ ይተላለፋል። በዚህም ምክንያት ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ተገደዱ።
የተማሪው ተቃውሞ ያይልና የአፄ ኃይለስላሴ መንግስት መንበረ ስልጣኑን ለደርግ መንግስት በሃይል ያስረክባል። መላው የጦር ሰራዊትም በአዲስ ወታደራዊ ሃይል ስር ይገባል። የዛሬው የዘመን እንግዳችንም በተለያዩ የጦር አውዶች ላይ ተሳተፉ። ከተራ ወታደርነት እስከ ብርጋዴል ጀነራል ድረስ ሺዎችን አስከትለው በተመደቡበት ሁሉ ለአገራቸው አንድነት ብዙ ዋጋ ከፈሉ። በተለይም በኢትዮ- ሶማሊያ ጦርነት በቶጎ ውጫሌ ውጊያ እንዲሁም በሰሜን ኤርትራ በኩል ይደረግ በነበረው ጦርነት ላይ ዘምተው ሃላፊነታቸውን ተወጥተዋል። ነቀምት በሚገኘው የጦር ማሰልጠኛ አዛዥ ሆነው በማገልገል ላይ ሳሉ ግን በሰሜን በኩል ይደረግ የነበረው ጦርነት እየተባባሰ በመምጣቱና የደርግ አመራርም እየተደካመ በመምጣቱ ሸሽተው ከነቀምት ጅማ፤ ከጅማም ጋምቤላ በእግራቸው አቆራርጠው በመግባት ይሸሸጋሉ። ስልጣኑን የተረከበው የኢህአዴግ መንግስት ለቀድሞ ጦር ሰራዊት አባላት ጥሪ በሚያደርግበት ጊዜ ግን ያለምንም ማንገራገር አዲስ አበባ ድረስ በመምጣት እጃቸውን አሳልፈው ይሰጣሉ። መሳሪያቸውን ቢያስረክቡም የደርግ ሰራዊት አባል በመሆናቸው ብቻ ከሌሎች የደርግ ባለስልጣናት ጋር ተደምረው ለአራት ዓመታት ወህኒ ቤት ከረሙ።
እንግዳችን በእርስር የቆዩባውን ዓመታት አያማርሩም፤ ይልቁንም ራሳቸውን ለማየትና ለማዳመጥ ጥሩ አጋጣሚ የፈጠረላቸው መሆኑን ነው የሚገልፁት። ከእሳቸው መታሰር ጋር ተያይዞ አራቱም ልጆቻቸው ለስደት ተዳረጉ። በተወለዱበት ቀዬ በ18 ዓመታቸው ለቀው የወጡት እንግዳችን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ከልባቸው ይወዳሉ፤ ዛሬም ድረስ ኢትዮጵያና ኤርትራ እንደ ሁለት አገር ማየትን አይሹም። በቅርቡ ደግሞ የሁለቱ አገራት ህዝቦች ዳግም በሰላም የሚኖሩበት እድል መፈጠሩ ታላቅ ብስራት ፈጥሮላቸዋል። ይህም የህዝብ ፍቅርና ሰላም ተጠናክሮ ዳግም ወደ አንድ ይመጣል የሚልም ተስፋም መሻትም አላቸው። አዲስ ዘመን ጋዜጣ ከብርጋዴል ጀነራል አሰፋ አፈርዖም ጋር በተለየዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርጓል። እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኮነሬል መንግስቱ ሃይለማርያም በመፃሃፋቸው ላይ ደርግ ከስልጣን የወረደው ህዝባዊ ድጋፍ ስላልነበረው ሳይሆን የውጭ ሃይሎች ተፅዕኖ ስለነበረበት እንደሆነ አንስተዋል፤ በእርሶ እምነት በወቅቱ የደርግ መንግስት ህዝባዊ ድጋፍ ነበረው ማለት ይቻላል?
ብርጋዴል ጀነራል አሰፋ፡- ህዝቡ በጦርነት ለረጅም ዓመት ተሰላችቶ ነበር። ወላጆች ልጆቻቸው ለብሔራዊ ውትድርና እየተማገዱ ልጆቹን የሚያጣበት ጊዜ ስለነበር ከዚህ ጦርነት የሚላቀቅበትን ቀን ነበር የሚጠብቀው። ሊቀመንበሩ እንዳሉት ግን የውስጥና የውጭ ጠላቶች አሰፍስፈው ስለነበር የደርግ መንግስት አንድ አድርጎ ለማስቀጠል ያደርግ የነበረው ጥረት ህዝቡ ሙሉ ለሙሉ ባይገነዘበውም እንኳን የአገሪቱ አንድነት እንድትቀጥል ይፈልግ ነበር። በመሆኑም ህዝባዊ ድጋፍ አጥቶ ነው ለማለት እቸገራለሁ። ብዙዎቻችን እንደምናውቀው በሶማሊያም በኩል ጦርነት ነበር። ያንን መልሰን ስናበቃም፤ በሰሜን በኩል የነበረው ጦርነት ግን እንደቀጠለ ነበር። ውጊያው ማቆሚያ አልነበረውም። አሁን ላይ በመንግስት ላይ እየደረሰ እንዳለው ጫና ጋር ተመሳሳይ የሆነ ችግር ነበር በአገሪቱ በወቅቱ የነበረው። ከፍተኛ ውጥረት ነበር። ነፃ አውጪ ግንባሮች የበዙበት እንዲሁም አንጃ የተበራከበት ወቅት ነበር። ሊቀመንበሩ እንዳሉትም ከውጭ ደግሞ ኢምፔሊያሊስት ሃይሎች የሚባሉት እነ አሜሪካ ሶሻሊስቱ ደርግ እንዲወድቅ ይፈልጉ ስለነበር አማፂ ቡድኖች ይደግፉ ነበር። ስለዚህ በእኔ እምነት እነዚህ ሁሉ ነገሮች ተዳምረው ነው ለደርግ መንግስት መውደቅ ምክንያት የሆኑት።
አዲስ ዘመን፡- ምስራቅ አፍሪካ ውስጥ የተለያዩ የአረብ አገራት የጦር ሰፈሮች መኖራቸው ይታወቃል። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከህዳሴ ግድብ ላይ ከግብፅ ጋር ካላት ፍጥጫ ጋር በተያየዘ ምን አይነት አሉታዊ ሚና ይኖረዋል ብለው ያምናሉ?
ብርጋዴል ጀነራል አሰፋ፡- ይህ ሁኔታ በኢትዮጵያ ላይ አሉታዊ ሚና እንደሚኖረው ግልፅ ነው። ምክንያቱም አብዛኞቹ አረብ አገራት የግብፅ ደጋፊ እንደመሆናቸው የጦር ሰፈር በእኛ አቅራቢያ መኖራቸው ስጋት መፍጠሩም አይቀርም። በነገራችን ላይ ከምንም በላይ የኢትዮጵያ መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ ከኤርትራ መንግስት ጋር መነጋገር ለህዝቡም እውነታውን ማሳወቅ ይገባዋል የሚል እምነት አለኝ። ምክንያቱም በህልውናዋ ላይ የሚቃጣ አደጋ በመሆኑ ነው። የኤርትራ መንግስት ምንም እንኳ ከኢትዮጵያ ጋር ሰላማዊ ግኑኝነት ቢኖረውም ከአረብ አገራት ጋር ያለው ግልፅ ያልሆነ ግኑኝነት እንደመንግስት ሊፈተሽ ይገባል። የሁለቱ አገራት የቀረበ ወዳጅነት በተግባር ሊገለፅ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ባለፉት 27 ዓመታት የመከላከያ ሰራዊትም አደረጃጀት ፖለቲካ ተኮር ሆኖ መቆቱ ምን አይነት ጉዳት አስከትሏል ብለው ያምናሉ?
ብርጋዴል ጀነራል አሰፋ፡- እንደሚታወቀው ኃይለስላሴም ሆነ በደርግ ጊዜ ሰራዊት የሚመለመለው በችሎታና በእውቀት እንዲሁም ለአገር ባለው ፍቅር እንጂ ብሄርን ወይም አካባቢን መሰረት አድርጎ አልነበረም። ምንም እንኳ ከየአካባቢው የተመለመለ ወታደር ቢኖርም ቅሉ የሚዋጋውም ሆነ የሚሰራው ለአንድ አገር እንጂ ለተወለደበት ወይም ለመጣበት ብሄረሰብ አልነበረም። በዚህም ምክንያት ሰራዊቱ ለአገሩ ከፍተኛ ፍቅር ያለውና በመካከሉም ምንም አይነት መከፋፋል አልነበረውም። ሁሉም ከየትም መጣ ከየት ይገባባል፤ ይነጋገራል፤ይወያያል። ደርግ ስልጣን በሃይል ይያዝ እንጂ በኢትዮጵያ አንድነት የሚያምንና ለዚያም ሲታገል የኖረ መንግስት ነው። የአመራር ጥበብ ቢጎለውም እንኳ ዜጎችን በብሄር ከፋፍሎ የሚያይ አልነበረም። ለ17 ዓመት ሲዋጋም በአንዱ ብሄር ላይ የተለየ ጥቃት ለማድረስ ወይም አንዱን ለመጥቀም አልነበረም። ይህም ሲባል ከሰራዊቱም ሆነ ከህዝበቡ የሚሱ ጥያቄዎች አልነበሩም ማለት አይደለም።
ኢህአዴግ ስልጣኑ ከተረከበበት ጊዜ ወዲህ ግን ለዘመናት ለአገራቸው ደማቸውን ያፈሰሱ የጦርሰራዊቶችን በተነ፤ የራሱን አደረጃጀት ፈጥሮ ለአንድ የፖለቲካ መዋቅር የሚወግን መዋቅር ዘረጋ። ምንም እንኳ ሥርዓቱ ፌደራሊዝም ነው ተብሎ ቢናገርም በመካለከያም ሆነ በሌሎች መንግስታዊ መዋቅር ውስጥ ሁሉንም ማዕከል ያደረገ አደረጃጀት አልነበረም። የአንድ ብሄር የበላይነት በተለይም የህውሃት ተፅእኖ የነገሰበት ሥርዓት ነው የዘረጉት። የአገሪቱን ሀብት ያለማንም ከልካይነት ሲዘርፉ ኖሩ። በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅበት ሁኔታ ሙስና በሰራዊቱ ውስጥ ዘልቆ ገባ። ከትንሽ እስከ ትልቅ ባለስልጣናት ያለውን ጥቅማጥቅም ሁሉ በእጃቸው ይዘው ህዝብ ሲያሰቃዩና ሲበድሉ ነው የኖሩት።
በእኔ እምነት ኢህአዴግ የገነባ መስሎ የሚያፈርስ ፓርቲ ጨቋኝ መንግስት ነው። ብዙዎቻችን በሚሰራው ፎቅና መንገድ ተታለን ኖረናል። ነገር ግን ከስር ከስሩ ሀብታችንን ሲቦጦብጥና እርቃናችንን ሲያስቀረን ነው የኖረው። በተለይ አዲስ አበባ ላይ የድሆችን ቤት እያፈረሰና እያባረረ የራሱን ጥቅመኞች ፎቅ ሲገነባ ነው የኖረው። ይህ በነዋሪው ላይ የተፈፀመው ግፍ በታሪክም ሊሰራ የሚችል አይደለም። ከነፃ አውጭነት ወደ አንድ ዘራፊ መንግስትነት ነው የተለወጠው። በእኛ ጊዜ አለቃውም ሆነ ምንዝሩ ከየትኛውም ብሄር የመጣ ሊሆን ይችል ነበር። ባለፉት 27 ዓመታት ግን አብዛኛውን የሃላፊነት ቦታ የያዙት የህወሃት አባላት ናቸው። በነገራችን ላይ ፌዴራሊዝም ተብሎ ቢነገረንም የትኛውም ክልል ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበት ሥርዓት አልተፈጠረም፤ አላየንም። የአንድ ብሄር የበላይነት መንገሱ ደግሞ ከየትኛው ጊዜ በላቀ ፍፁም አህዳዊ ሥርዓት እንዲፈጠር አድርጎታል። ሌሎችን አሀዳዊ እያለ ቢያወግዝም አሰራሩም ሆነ አካሄዱ በአንድ ብሄር ቁጥጥር ስር የነበረ፤ በአንድ ማዕከል ሰዎች የሚመራና የሚገዛ ስልጣን ተንሰራፍቶበት ነው የኖረው። ሌላው ይቅርና ህወሓቶች አገር እየመሩ ኢትዮጵያ የሚለውን ስም እንኳ በቅጡ መጥቀስ አይፈልጉም ነበር።
ብዙዎቻችን እንደምናውቀው ከፌዴራል መንግስቱ በልማት ሰበብ የመንግስትና የህዝብ ገንዘብ እየተበደሩ የግል ኪሳቸውን ሲያደልቡ የነበሩት በርካታ የህውሃት አመራሮች ነበሩ። ጥቅም ባለበት ክልል ሁሉ እየሄዱ በኢንቨስትመንት ስም መሬት እያጠሩ ግን ደግሞ አንዳችም ልማት ሳይሰሩና ለአካባቢው ህዝብ የሚውል ጥቅም ሳይሰጡ ለዓመታት ሀብት ያከማቹበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው። ሃይለስላሴ በየገጠሩ መሬት እያሰረሱ ያስገብሩ የነበሩት ለሰራዊታቸው የሚከፍሉት ገንዘብ በእጃቸው ስላልነበረ ነው። ያም ሆኖ ግን ለአንድ አገር ነበር ሲሰሩ የነበሩት። በዚያን ጊዜ ግን የነበረ ወታደር እንኳን ሀብት ሊያጋብስና ቤት ሊሰራ ቀርቶ ልጆችን እንኳ በቅጡ ማሳደግ አይችልም ነበር። በደርግም ቢሆን ከፍተኛ የተባሉት መኮንኖች እንደው ለመዝናናት ሲሉ ድግስ ያበዙ ይሆናል እንጂ በዚህ ደረጃ አይን ባወጣ ሙሰኝነት አይዘፈቁም ነበር። ይሄኛው መንግስት ግን ለጥቂት አመራሮችና ቡድኖች ሲባል ብዙዎችን ለስቃይ ሲዳርግበት የኖበት ጊዜ ነበር። በአንድ መልኩ የመከላከያ አባል የሆኑ በሌላ መልኩ ደግሞ አስመጪና ላኪ ሆኖ የሚገኝበት አጋጣሚ ሰፊ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ባለፉት ሁለት ዓመታት እንደሚያውቁት ሰራዊቱን በአዲስ መልክ የማደረጀት ስራ ሲሰራ ቆይቷል፤ ይህም ምንም እንኳ ሁሉንም ማዕከል ያደረገ አደረጃት ቢፈጥርም የቀድሞውን ያህል ጠንካራ ላይሆን ይችላል የሚል ስጋት ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች አሉ፤ እርሶ ይህንን ስጋት ይጋራሉ?
ብርጋዴል ጀነራል አሰፋ፡- እንዳልሽው ከዶክተር አብይ መምጣት ጋር ተያይዞ ሰራዊቱን በአዲስ መልክ የማደራጀትና የማዘመን ስራ እየተሰራ መሆኑን ሰምቻለሁ። ይህም አስቀድሜ ሳነሳልሽ የነበረውን ችግር ከመቅረፍ አኳያ ትልቅ ሚና ይኖረዋል የሚል እምነት አለኝ። ምንም እንኳን ሙሉ ለሙሉ ተለውጦ ከፍተኛ መሻሻል አምጥቷል ለማለት ጊዜው ገና ቢሆንም ዳግም መደራጀቱ ሙሰኛውንና ብሄርተኛውን ወደ ጎን ለማግለል ያስችላል። ለአንድ ወገን ሳይሆን ለአገር ፍቅር በችሎታውና በእውቀቱ የሚመራ ሃይል ለመፍጠር ያግዛል የሚል እምነት አለኝ። ግን ደግሞ ወደ ትግራይ ሸሽቶ የሄደው ሃይል ለዓመታት በመከላከያ አቅሙ የተደራጀ እንደመሆኑ፤ መሳሪያም ሲያግበሰብስ የኖረ እንደመሆኑ አሁንም ያለው አቅም ቀላል ነው ማለት አይቻልም።
ከዚህ ቀደም እንደምታስታውሺው «ከትግራይ ጦሩ አይወጣም» በሚል ምንአይነት ውዝግብ እንደተነሳ ታውቂያለሽ። ሆኖም ግን ዶክተር አብይ የጀመረው መከላከያውን የማደስ ስራ ቀድሞ የነበረውን በአንድ የፖለቲካ ቡድን ዙሪያ የነበረውን መዋቅር ሙሉ ለሙሉ በማፈራረስ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚሳተፉበት ሀገራዊ የመከላከያ ሰራዊት እንዲኖር ያስችላል የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- በትግራይ መንግስትና በፌዴራል መንግስት መካከል በተፈጠረው ውዝግብ እየተካረረ ሄዷል፤ ይህ ሁኔታ ወደ ጦርነት ሊያመራ የሚችልበት አጋጣሚ አለ ብለው ያምናሉ?
ብርጋዴል ጀነራል አሰፋ፡- እንደተባለው አሁን ያለው ሁኔታ ብዙ ደስ የሚያሰኝ አይደለም። ሁለቱ ሃይሎች እንደመሪ ቁጭ ብሎ ከመነጋገር ይልቅ እርስበርስ መወነጃጀል ነው የየያዙት። በተለይም የህውሃት አመራሮች ትግራይ ክልል ራሷን ችላ እንደወጣች አንድ አገር ሁሉንም ነገር በራሳቸው ለመምራት የሚያደርጉት ጥረት ፀብ አጫሪ አካሄድ እንደሆነ እረዳለሁ። ከዚህም አልፈው ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የጦርነት ነጋሪት እየጎሰሙ ህዝቡን ወደ አላስፈላጊና ወደተሰለቸ ጦርነት ለመገፋፋት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው። በእኔ እምነት ጦርነት ለማንም አይበጅም፤ ብዙዎችን ህይወት ያሳጣል፤ ይማግዳል፤ ኢኮኖሚም ያቃውሳል።
በለውጡ አመራር በኩልም ተናቦ ያለመሄድና የበላይነትን ለማሳየት የሚደረጉ ጥረቶች አሉ። ምንም እንኳ ዶክተር አብይ የኢትዮጵያዊነትና የአገር ስሜት ያላቸው መሆናቸው፤ ይህንኑ ደግሞ በተግባርም ያረጋገጡ ቢሆኑም ሁሉም አመራር የእሳቸው አይነት የአገር ፍቅር ስሜት አለው ብዬ አላምንም። ለዚህም ነው «የሌላ ክልል ተወላጅ ከክልላችን ይውጣልን» እየተባለ በርካቶች የተፈናቀሉትና ጉዳት እየደረሰባቸው ያለው። ይህ ሁኔታ በዚህ ከቀጠለ አገሪቱ እንደ አገር ላትቀጥል የምትችልበትን መጥፎ አጋሚ ይሰፋል ብዬ አምናለሁ።
በዚህ ጉዳይ ላይ የለውጥ ሃይሉ ቁርጠኝነቱን በሚገባ ማሳየት አለበት። ዶክተር አብይ ተቃዋሚዎችን ሁሉ በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ ያለገደብ ለቀዋቸዋል፤ ይህ ሁኔታ ደግሞ በተለይ ዴሞክራሲን በቅጡ ያልተረዳው ፖለቲከኛ ለክፉ አላማ ሲጠቀምበት አስተውለናል። በቅርቡ የተፈጠረው ችግር የሚያሳየን ይህንን ነው። ከተፈጠረው ችግር ጋር ተያይዞ ረብሻ ያስነሱ ፖለቲከኞችን በቁጥጥር ስር በማዋል በህግ እንዲጠየቁ ማድረጉን እደግፋለሁ። እኔም ሆንኩ ብዙዎቹ ዜጎች በአዲስ አመራር ላይ ቅሬታ የነበረን ቶሎ እርምጃ ያለመውሰዱ ላይ ነው። በአሁኑ ወቅት ግን ሆደ ሰፊነቱን አብቅቶ በህዝብና በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሱ ሃይሎች በህግ እንዲጠየቁ ማድረጉ የህግ የበላይነት መኖሩን በተግባር ያረጋገጠበት ነው ባይ ነኝ።
በነገራችን ላይ ለዚህ ሁሉ ግጭትና ሁከት መንስኤ ብዬ የማስበው «ስልጣኔን ተቀማሁ» ብሎ የሚያምነው አኩራፊው ሃይል በሚፈፅመው ደባና ሴራ ነው። በእኔ እምነት መንግስት አኩራፊዎችንና ሴረኞችን ዝም ብሎ እየለመነና እየተለማመጠ አገር መምራት አይችልም። የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ አለበት። ማንም ይሁን ማን ህግ ከተላለፈ ተጠያቂ መሆን አለበት። የኢትዮጵያ አንድነት ስጋት የሆኑ ሃይሎችን ማስወገድም ይገባዋል። ይህንን ማድረግ ካልቻለ ግን በገዛ እጃችን ለውጭ ጠላቶቻችን ምቹ ሁኔታ ነው የምንፈጥረው። በተለይም ለአገራችን እድገት ትልቅ ተስፋ የጣልንበት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፍፃሜ እንዳያገኝ ትልቅ እንቅፋት ነው የሚፈጥሩብን። በመሆኑም የህግ የበላይነትን የማስከበሩ ተግባር ቀጣይነት ሊኖረው ይገባል ባይ ነኝ።
ህወሓት በህገመንግስቱ ላይ አንቀፅ 39ኝ እንዲሰነቀር ያደረገው ለራሱ እንዲመች ብሎ ነው። በነገራችን ላይ ሲጀመርም አገሪቱ የፌዴራል ሥርዓት የምትተገብር አንዲት አገር ሁሉም ራሱን ችሎ የማስተዳደር ስልጣን በህግ እስከተሰጠው ድረስ መገንጠል የሚለው ሃሳብ አስፈላጊነቱ አይታየኝም። እነሱ ለራሳቸው የሚጠቅማቸውን አንቀፅ ሲያሰፍሩ ለምን ብሎ የጠየቃቸው አካል የለም። ላለፉት 27 ዓመታት የፈለጉትን ካደረጉ በኋላ ይህችን አጋጣሚ ለመጠቀም እያኮቦኮቡ ይገኛሉ።
ህውሓት ያከማቸውን ሰራዊትና መሳሪያ በመያዝ ሌሎች ሃይሎችን በማስተባበር ወደ ስልጣኑ ይመለሳል የሚል እምነት የለኝም። ህውሃት እንኳን መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ልብ ሊያገኝ ይቅርና የትግራይ ህዝብም ይቀበለዋል ብዬ አላስብም። ይህ የተሸነፈ ሃይል ህዝቡን ሲበዘበዝ ስለኖረ ዳግመኛ ይህንን አካሂዳለሁ ቢል የሚቀበለው አያገኝም። ደጋፊም አይኖራቸውም። እርግጥ ነው ባከማቹት የጦር መሳሪያ ሊመኩ ቢችሉም የትግራይ ህዝብ ፈፅሞ አይቀበላቸውም። ሌላው ይቅርና ሁሉም በሚባል ደረጃ የራሳቸው ባለሀብቶች ያከማቹት ሀብት ያለው በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች በመሆኑ ጦርነት ቢነሳ ባለሀብቱም ሆነ የህውሃት ካድሬዎች ሀብታቸውን የሚያጡበት እድል በመኖሩ በዚህም በኩል ተቀባይነት አያገኙም።
አዲስ ዘመን፡- በዚህ ረገድ ስልጣን ላይ ባለው መንግስት በኩል ሊሰራ ይገባል የሚሉት ስራ ምንድን ነው?
ብርጋዴል ጀነራል አሰፋ፡- የዶክተር አብይ አመራር ሃይሉንም አመራሩንም ማጠናከር አለበት፤ እንደአመራር ቁርጠኝነቱን በተግባር ማሳየት ይጠበቅበታል። በሌላ በኩል የመንግስትን ደመወዝ እየበላ አገር በሚያፈራርሰውና ትግራይ መሽጎ ባለው ሃይል ላይ እርምጃ መውሰድም ይገባዋል።
አዲስ ዘመን፡- ይህ ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
ብርጋዴል ጀነራል አሰፋ፡- ይህንን ስልሽ የግድ ጦርነት ያውጅ እያልኩሽ አይደለም። ነገር ግን ይህ የመንግስትን ደመወዝ እየበላ ግን ደግሞ አገር በማፍረስ ላይ ያለውን ሃይል በቸልተኝነት ሊታለፍ አይገባም። ሌላው ቢቀር ደመወዙን መንፈግ ይችላል። ይህም ሲባል ህዝቡን በማይጎዳ መልኩና አመራሩ የሚያገኘውን ጥቅማጥቅም በማሳጣት አቅሙን ማዳከም የሚቻልበት እድል አለ። ይህ ሁሉ ተደርጎ ከስህተታቸው የማይመለሱና አገር የማፈራረስ አጀንዳቸውን የሚያስቀጥሉ ከሆነ አልፈው ተርፈውም አዝማሚያው ወደለየለት ጦርነት የሚያመዝን ከሆነ ግን በስልጣን ላይ ያለው ሃይል ራሱን ማዘጋጀት አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ አኳያ የሕወሓት አመራሮች በምን መልኩ ራሳቸውን ሊያስተካክሉ ይገባል ይላሉ?
ብርጋዴል ጀነራል አሰፋ፡- እንደገለጽኩልሽ ህወሓቶች አሁን እያሳዩ ያሉት አዝማሚያና አካሄዳቸው ወደ ለየለት ጦርነት ሊያመራ እንደሚችል ግልፅ ነው። የትግራይ ህዝብን ታጠቅ፤ ተነስ እያሉ እየቀሰቀሱት ነው የሚገኙት። ይህ እንዲሆን የአብይ መንግስት መፍቀድ የለበትም፤ ነገሮች ሁሉ ህወሓቶች እንደሚፈልጉት ወደ ጦርነት እንዳያመሩ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባዋል። አሁን ላይ የምናየው እኮ በህዝብ በህዝብ ወይም በብሄሮች መካከል የሚደረግ ጦርነት ሳይሆን የፓርቲዎች ጦርነት ነው።
ሕወሃቶች ዛሬም ከጦርነት አባዜ አልተላቀቁም፤ ትናንትና ሲመሩት የነበረው ህዝብ በብልሹ አመራራቸው ምክንያት እንደጠላቸውና እንዳልፈለጋቸው አምነው ራሳቸውን ከማረቅ ይልቅ አሁን ባልበገር ባይነት ለእድገትም ለሰላምም እንቅፋት ሆነዋል። ህዝባቸው በብዙ ችግር ውስጥ ነው ያለው፤ ዛሬም ከድህነት አልወጣም። ከሌሎች ክልሎች ባልተናነሰ የመሰረተ ልማት እጥረት አለበት። ከምርጫ በላይ ለዚህ ህዝብ የሚያስፈልገው ሰላምና ልማት ነው። በአገኙት አጋጣሚ የጦርነት ነጋሪት መጎሰም አይጠበቅባቸውም። እኛ ካልመራን አገር አትኖርም ከሚለው አስተሳሰባቸው መላቀቅ ይገባቸዋል። ህዝቡ ለውጥ ስለሻተ ነው፤ ዶክተር አብይን በዚያ ደረጃ የተቀበለው። ይህንን አምነው መቀበል ይገባቸዋል።
ደግሞም የትግራይ ህዝብ በኢትዮጵያዊነቱና በሰላም አስፈላጊነት የሚያምን ነው። የትግራይ ህዝብ የኢትዮጵያ መሰረት ነው። ትግራይ የሌለችበት አገር ኢትዮጵያ ልትሆን አትችልም። ለትግራይ ህዝብ ማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት ታሪክህን ጠብቅ
የሚል ነው። ለኢትዮጵያ መቀጠል ከፍተኛ ድርሻ አለህ ማለት እፈልጋለሁ። የሕወሃት መሳሪያ ከመሆን ራሱን መጠበቅ አለበት። በሀገራቸው ሁለንተናዊ ልማት ግንባር ቀደም ተሳታፊ ሆነው የህዳሴ ግድብን በጋራ ማጠናቀቅ ይገባቸዋል። የህውሃትን አጉል ጩኸት ከመስማትና ሀገሪቱ የውጭ ጠላቶች መሳቂያ፤ መሳለቂያ ከመሆን መታደግ ይጠበቅበታል። አሁን ያለው መንግስት በመደገፍ ከጎን መሰለፍ ይገባዋል። ይህ ማለት ግን ልዩነት ወይም ቅሬታ አይኖረውም ማለት አይደለም። ነገር ግን ቅሬታውን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታለት ነው መጠየቅ ያለበት።
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ አሁን ላለው ወጣት ትውልድ በተለይ ከአገር ፍቅር አኳያ ሊመክሩትና ሊያስተላልፉለት የሚፈልጉት መልዕክት ካለ እድሉን ልስጥዎት?
ብርጋዴል ጀነራል አሰፋ፡- በዚህና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ማንሳት የምፈልገው ሃሳብ አለ። የመጀመሪያው ዶክተር አብይ በአሁኑ ወቅት ከቃል ባለፈ በተግባርም ኢትዮጵያዊነቱን ማረጋገጥ ይገባዋል የሚል ነው። በተለይም የህግ የበላይነትን በተጨባጭ ማረጋገጥ አለበት። ሰራዊቱን በሚገባ ማደራጀትና መቆጣጠር ይጠበቅበታል። አምነዋለሁ የሚለው ሠራዊት ለኢትዮጵያ አንድነት ከቆመ ለመገንጠልም ሆነ የህዳሴ ግድብን ግንባታ የሚያደናቅፉ ሃይሎችን በተጨባጭ መከላከል እንደሚችል ማረጋገጥ አለበት። በየከተሞቹ ያሉት ፖሊሶችና ሚሊሻዎች ለህዝብ የቆሙ መሆናቸውን በተግባር ሊያሳዩ ይገባል። በተለይም አዲስ አበባ የዓለም መንግስታትም ሆነ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እንደመሆንዋ ለትርምስ እንዳትዳረግ በሚገባ መጠበቅ ይገባታል።
የፌዴራል ፖሊስም ሆነ የአዲስ አበባ ፖሊስ ችግሮች ከተፈጠሩ በኋላ ሳይሆን አስቀድመው ህዝቡን ከጥቃት መታደግ ይገባቸዋል። በጣም የማዝነው ብዙውን ጊዜ ወንጀል ከተፈፀመ በኋላ በየሚዲያው እየቀረቡ ስለተፈፀመው ወንጀል ተንታኝ ሆነው ሲቀርቡ ነው። የአዲስ አበባ ፖሊስ ለአዲስ አበባ ህዝብ አለኝታነቱን በተጨባጭ ማሳየት ይገባዋል። የእኔነት ስሜትም ሊሰማው ይገባል። በተጨማሪም ህውሓቶች መቀሌ ከመከተማቸው በፊት በአዲስ አበባ ላይ ያስታጠቁት ህቡዕ ድርጅት ካለ መፈተሽ ይገባዋል። በቀጥታ ያሉትን ስውር ቦታዎች ከዚህ በፊት የተሰሩ አጥሮችን አነፍንፈው ማግኘት አለባቸው። ከዚህ በኋላ አዲስ አበባ የተቀበረ ፈንጅ እስኪፈነዳ ድረስ መጠበቅ የለበትም።
በሌላ በኩል ወጣቱ እንደሚታወቀው ለአንድ አገር የጀርባ አጥንት ነው፤ እኛ አብቅተናል፤ ያለን አቅም ከልምዳችንና በእድሜ ካገኘነው እውቀት ለትውልዱ ማስተላለፍ ነው። አሁን ያለው ወጣት ባለፉት 27 ዓመታት ከአገር ስሜትና ከአብሮነት ይልቅ በግለኝነትና በጎሰኝነት አስተሳሰብ የታጠረ እንዲሆን ተደርጓል። የሚገርመው ብሄር ብሄረሰቦች በአንድ ላይ የሚኖሩበትና እንደትንሽ አገር የሚቆጠሩት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንኳ የብሄር ግጭቶች ማዕከል እንዲሆኑ ነው የተደረገው። ባለፉት ዓመታት ያየናቸው ግጭቶች መነሻቸው የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ነበሩ። ወጣቱ በትምህርት እንዲጎለብት ከማድረግ ይልቅ በማንነት አባዜ እንዲናውዝ ተደርጎ ተበርዟል። በመሆኑም የአገር ፍቅር ስሜት ያላቸው አመራሮች ሊሂቃን ይህንን ወጣት ከገባበት አባዜ መታደግ ይገባቸዋል። ወደ ከፋ ችግር ከመሻገሩ በፊት ማስተማርና መለወጥ ይገባል። ለዚህ ደግሞ ሥርዓተ ትምህርቱንም ሳይቀር መቀየር ይገባል ባይ ነኝ። በአንዳንድ ክለሎች የተዘራው ክፉ አስተሳሰቦች ምክንያት የሌላውን ቋንቋ እንዲጠላና እንዳያውቅ በመደረጉ በፈለገው ክልል እንኳ ስራ እንዳያገኝ አድርጎታል። በዚህም በጣም አዝናለሁ። በመሆኑም መንግስት ብቻውን የሚሰራው ባለመሆኑ ከአገር ሽማግሌዎች ከምሁራና ከወጣቱ ጋር በቅንጅት መስራት ይገባዋል የሚል ሃሳብ ነው ያለኝ።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
ብርጋዴል ጀነራል አሰፋ፡- እኔም አዲስ ዘመን ጋዜጣ እኔን እንግዳ በማድረጉ አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 11, 2012
በማህሌት አብዱል