አሻም አዲስ ዘመኖች
የዝነኛው የአፋን ኦሮሞ ሙዚቀኛ ድምፃዊ ሃጫሉ ግድያ በአይረሴ ሀዘን ያጠመቀንን ያክል “ግን ለምን” ለሚለው የሁላችን ጥያቄም በመሰለኝ እና በደሳለኝ ለሚደረደሩ መላምቶችም እንዳጋለጠን እንቆቅልሽነቱ አሁንም ድረስ ከእያንዳንዳችን አእምሮ ያቃጭላል። በእኔ እይታ ይህ ጉዳይ ከአጭር ጊዜ አኳያ እንቆቅልሽነቱ አብቅቶ እልባት የሚያገኝ አይመስለኝም። ሃዘናችንን እያደር ጥልቅ የሚያደርገውም ይኸው ነው። ግድያው ፖለቲካዊ እንደሆነ ከመናገር ባሻገር የየትኛው ፖለቲካዊ ወገን ሴራ ስለመሆኑ አሳማኝ ነገር ሊያሳየን የቻለ አካል እስከአሁን አልተገኘም።
እዚህ ላይ ስለ አርቲስት ሃጫሉ ታላቅነት እና ግለታሪክ ወይም አውቶባዮግራፊ መዘርዘር የዛሬው ፅሁፌ ዓላማ አይደለም። እንደው ለመንደርደሪያ ያህል አንዳንድ ነጥቦችን በእርሱ አንደበት በዋቢነት ለመጠቃቀስ ከመሞከር ባለፈ። አርቲስቱ በሙዚቃ ሥራዎቹ “ማለን ጂራ” ከተሰኘው ሁለተኛው አልበሙ ወዲህ ከህዝብ መድረክ ላለፉት ሁለት የለውጥ ዓመታት ርቆ ነበር። አልፎ አልፎ በሙዚቃ ኮንሰርት መድረኮቹ ከሚያቀርባቸው ዝግጅቶች ውጭ በአብዛኛው ወደ ግል ህይወቱ አትኩሮ እንደሰነበተ ለመጨረሻ ጊዜ በኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ የቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጠው ቃለምልልስ አረጋግጠናል።
ያቺ መዘዘኛ የቴሌቪዥን ቃለመጠይቅ! ደግሞም የመጨረሻዋ የስንብት ንግግር! ከዚህ በፊት ልክ በለውጡ መባቻ የኢሬቻ ክብረ በዓል ዋዜማ ያዜማት “ጂራ” የተሰኘውን ተምሳሌታዊ ዜማ ለህዝብ ካቀረበ ወዲህ ሃጫሉን በጣፋጭ ሥራዎቹ ናፍቀነው ነበር። ይህቺ በአማርኛ ቋንቋ ፍቺዋ “አለን” የተሰኘችው የለውጥ ጉዞን አብሳሪ ነጠላ ዜማ ለብዙዎቻችን ተስፋን የሰነቀች እንዲሁም ኢትዮጵያዊ አንድነትንና ሀገራዊ ብልጽግናን ያመላከተች ከመሆኗም በላይ ጥልቅ መልዕክትን ያዘለች ዜማ ነበረች። ናትም። በመግነጢሳዊ ዜማዎቹ ተከሽነው የሚሳኤልን ያክል ልብ አርድ ስንኞች የተቋጠሩላት “ጂራ” የህዝባችንንም ሁለንተናዊ እሳቤዎች ለመከርከም አይነተኛ መሳሪያው ነበረች። አይ የኛ ነገር” በማለትም ያለፍንባቸውን የጭቆናና የአፈና ዘመናት ዘንግተን ድንገት በተቸረን የነፃነት አየር መቅዘፍ ተስኖን ትላንታችንን እስከመናፈቅ እና ወደዚያ ለሚመልሱን ዝንባሌዎች በቀላሉ እንደምንሳብ በሚገርም መልኩ የሂስ በትሩን አሳርፎብናል። ግና ይህ አባታዊ ምክሩ ለአንዳንዶቻችን እንደ ገንቢ ሂስ ሳይሆን እንደ ክህደት በመቁጠር ሃጫሉን ለመውቀስ ብርታት የሆነንም አልጠፋንም።
የሌላውን ወገን ትቼ የመንግሥትን ድርሻ ነጥዬ ስመለከተው በርካታ ቀዳዳዎች ይታዩኛል። ድርጊቱን ብዙዎች እንደሚሉት መንግሥት ፈፅሞታል ለማለት ባልደፍርም ነገርግን ከአደጋው በኋላ የመንግስትን ቁርጠኝነት በሚጠይቁ አካሄዶች ላይ ያሳየው እንዝላልነት ከወቀሳዬ የሚያድነው ሆኖ አላገኘሁትም።
ሌላው የመላምት በርን የከፈተው ክስተት የግድያው ዜና እንደተሰማ ቀድሞውኑ አድብቶ የህዝብ እሳትን ለመሞቅ ሲጠባበቅ የነበረው ፀረ- ሰላም ኃይል በተለይ በኦሮሚያ ክልል ላደረሰው ቀውስ የፀጥታ አካላት አደጋውን ለማስቆም ያሳዩት ቸልተኝነት ነው። የሰዎችን የስም ዝርዝር ሳይቀር አሰናድቶ ማንን እንደሚያጠቃ የለየን የጥፋት መንጋ ማስቆም ይቻል ነበር ባይ ነኝ። ቢያንስ ቢያንስ አደጋውን መቀነስ ይቻል ነበር የሚል እምነት አለኝ። ከተለያዩ ምንጮች እንደምንሰማው የመንግስት አካላት ሳይቀሩ ብጥብጡ ሰርግ የሆናቸው አንዳንድ አካላት ዜጎች በብሔርና በኃይማኖት እንዲተላለቁ ባላየ ባልሰማ አልፈውታል። የድረሱልን ጥሪ ሲቀርብላቸውም ትእዛዝ አልተሰጠንም በሚል ተልካሻ ምክንያት ዜጎች እንደ ከብት ሲታረዱ፣ ንብረታቸው በእሳት ሲጋይ ዳር ቆመው ተመልክተዋል። ይኸንን ስትመለከት ቀድሞውኑ የሃጫሉ ግድያ መንስኤ እንጂ አደጋ አይደለም ያስብልሃል። የህዝቡን በሌላ ርዕስ እራሱን አስችዬ እመለስበታለሁ።
የዳውን ዳውን ፖለቲካ ደግሞ የለውጥ ጉዞውን ይባስ እንዲመሰቃቀል አድርጎታል። የአስቀያሚነቱ ጥግ የኖቤል ሽልማቱን እስከማስወረስ የሚዘልቅ ተጋድሎ በተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች በተደረጉ ትእይንተ ህዝቦች ሲስተጋባ ሰምተናል። ጎበዝ የዘንድሮው የኖቤል የሰላም ሽልማት የመላው አፍሪካውያን ድል ነው ተባብለን አልነበር እንዴ? የቱን ያህል በዶክተር አብይ ቅያሜ ቢያድርብን እንዴት ነው የሀገርን ገመና በአደባባይ ያውም በሰው ሀገር እርቃኑን ለማስቀረት የበረታነው? ይኸ በጣም ያስተዛዝባል። ለሀገር ለወገን መታገል ክፋት አልነበረውም። እንዲያውም ይበል የሚያሰኝ እንጂ። ግን አቢይ ይውረድ ሽልማቱንም ተቀበሉት እያሉ የፈረንጆችን ደጅ መጥናት የጤና ነው ብዬ መውሰድ ይከብደኛል።
ለዘመናት የሀገራችን የዴሞክራሲ፣ የእኩልነትና የፍትህ ጥያቄዎቻችን እየተንከባለሉ ከአንዱ ጥግ ወደሌላኛው ጥግ ከመላጋት በቀር እፎይ የሚያስብሉ ሆነው ለመታየት አሁንም ገና ጥሬ ናቸው ብሎ መውሰድ ይቻላል። እርግጥ ነው ለበርካታ ምዕተ ዓመታት እንደ ቋሚ ባህል ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው የባርነት ቀንበር እንደው በለስ ቀንቶን በሆነ ጀምበር የነፃነት ተስፋ ቢነፍስብን እንደ እርግማን ሆኖ ሮጠን በመረባረብ መልሰን ለማጨለም ማንም አይቀድመንም። የማይካደው ነገር የችግሩ ፈጣሪዎችም እኛው፣ ለመፍትሄው የምንዋደቀውም እኛው ነን። በሁለቱም አካሄድ ወጪው የአንድ ቤት ነው። የኛው የኢትዮጵያዊያን። ሌላ ማን ሊደማልን? ማንስ ሞቶ ነፃ ሊያወጣን?
ሲጀመር ወንድም ወንድሙን ከማስገበር እስከ መግደል የሚያስኬደንን አቅም ያገኘነው የትኛው ፈረንጅ አማክሮን? ወደየትም ጣታችንን መቀሰር አይቻልም። የታሪካችን የኩራት ማማ የሆነው የአድዋ ድል ምስጢሩ ውስጣዊ አንድነታችን እንደሆነ ከላይ ለጠቀስኩት ሃሳብ ጥሩ አስረጂ ሊሆን ይችላል። ያኔ በህብር መቆም ተስኖን ቢሆን ኖሮ ዛሬ ላይ ደረታችንን ነፍተን በየዓመቱ የምንዘክረው የደሀ ድል ባልኖረ ነበር።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ተጠቃሽ የሆኑ የጥቁሮች የድል ባለቤት የመሆኗን ያክል አንገት የሚያስደፋ ክስተቶች የተስተዋሉባት ምድር መሆኗም የሚካድ አይደለም። ሁሌም እንደሚባለው ታሪክ ነጠላ አይደለም። ግራም ቀኝም አለው። መጥፎም ጥሩም ጎኖች እንዳሉት መቀበል ተፈጥሯዊ ነው። እነዚህን መንታ ገፅታዎች መካድም ሆነ ለመነጣጠል መሞከር የከፋ ድንቁርና ነው። እቺን ሀገር ከጠላት ጠብቀዋት ሉዓላዊት ኢትዮጵያን ሊያወርሱን ሲሉ ከብሔር፣ ከኃይማኖት እና ከባህል አጥር ወጥተው አንተ ከየት ነህ፣ ከማንኛው ወገን ነህ፣ ሳይባባሉ በአንድ የጋራ ገመድ በመተሳሰር በአንድ የጦር ግንባርም አብሮ በመሰለፍ እና የማታ ማታም በጋራ ተሰውተው በአንድ ጉድጓድ አብሮ በመቀበር ዛሬያችንን ፈጥረዋል። ይህ ዘላለም የማይሞት ሐቅ ነው። ይህንን በተራችን ጠብቀን ለልጅ ልጆቻችን በተሻለ መሠረት ላይ ገንብተን ማስተላለፍ ደግሞ ከእኛ ከአሁነኞቹ የሚጠበቅ የትውልድ ኃላፊነት ነው።
ወገን ሆይ አብይን ያመጣኸውም አንተው የምትሰደውም አንተው ነህ አውቃለሁ። ግን ደግሞ ሁሉም ነገር መስመር አለው፣ ደንብ አለው። እዚህ ጋር “የአንቺው ታመጪው አንቺው ታሮጪው” ዓይነት ብሂል ወንዝ አያሻግርም። እውነት ነው ህዝብ ገዢ ነው፤ ወቃሽም ነቃሽም ነው። አንጋሽ እና አውራጅም እንደሆነ ሊታመን ይገባል። ይህን እየካድኩ እንዳልሆነ ይያዝልኝ። ህዝብ ያለው ነገር ሁሉ ይሆናል ማለት ግን ዝም ብሎ በዘፈቀደ ማንም ተነስቶ የሚነዳው መንጋ ነው ማለት ግን አይደለም። ህዝብ ሁሉንም ነገር በራሱ ማስኬድ ይችላል ከተባለ ሲጀመር መንግስት የሚባል የህዝብ ጉዳይ አስፈፃሚ አካል ባላስፈለገን ነበር።
የሀገር የመጨረሻው መሠረት ቤተሰብ ነው። ቤተሰብ አባወራና እማወራን ጨምሮ በአንድ ጥላ ስር የተሰባሰቡ የአንድ ቤት አባላት የሚተዳደሩበት የታችኛው አስተዳደራዊ እርከን ነው። አመራርም ከዚያ ይጀምራል። ሁሉም የቤተሰቡ አባላት ግን በአንድ ጊዜ ተነስተው እኔ ነኝ አባወራ እኔ ነኝ ንጉሥ ማለት አይችሉም። እንደዚያ ከሆነማ ያ ቤተሰብ ቤተሰብ ሆኖ ሊቀጥል አይችልም፤ ሁከት ካልሆነ በቀር። ለአመራር በቅድሚያ መደማመጥ መቻል ትልቁ የማዕዘን ድንጋይ ነው። ያ ቤተሰብ እንዲበለፅግ፣ ሰላማዊና የስኬት ኑሮ እንዲጎናጸፍ ከተፈለገ የቤተሰባዊ ተቋም አደረጃጀት እና አሰራር ቁመና ሊኖረው ይገባል። በሰው ልጆች የአስተሳሰብ የእድገት ደረጃ አባወራው የቤተሰቡን የአመራር ኃላፊነት እንዲወጣ የተሰየመ ሰው ነው። አባት ማለት ነው። አባት የቤተሰቡ የህግ መሰረት ነው። አባት ከሌለ ቤት ይፈርሳል ይላል ይህን የተገነዘበው የሀገሬ ሰውም። አባት ይፈራልም ይወደዳልም። የሚፈራው ስለሚከበር ነው። የሚወደደው ደግሞ ወላጅ አባት ስለሆነ ነው። ሁለቱም መነጣጠል የሌለባቸው የአመራርነት እሴቶች ናቸው።
ወደ ሀገር ስንመጣ በህዝቦች ውክልና የሁላችን ጎጆ የሆነችን ሀገር በህዝቦች ውክልና እንዲያስተዳድርልን የተሰየመው አካል ነው መንግስት። እንደ ታችኛው የቤተሰብ መንግስት አባወራ ወይም አባት ማለት ነው። አባትነትም መንግስትነትም የህገ-ቤተሰብ እና የህገ-ሀገር ምንጭ ነው። ይፈራል፣ ይከበራል፣ ይወደዳል። ሳይከበር ከተፈራ ፍቅር የሌለበት ቤተሰብ ይሆናል ማለት ነው። ቤተሰቡ ቀድሞውኑ ዋልጌ ሆኗል ማለት ነው። አባወራው ወይም መንግስተ-ወራው ኃላፊነቱን ባለመወጣቱ ለቤተሰቡ ዋልጌነት ተጠያቂ ቢሆንም በቤቱ መፍረስ ደግሞ የቤተሰቡ አባላትም ከተጠያቂነት ሊድኑ አይችሉም። ቤቱ የጋራ ነውና።
አሁን ችግር እየሆነ የመጣው ከታሪክ ጥብቆ መውጣት አለመቻላችን ነው። የታሪክ ቁስልን እንዲያመረቅዝ ነጋ ጠባ እያከኩና እያሳከኩ በዚያው ለመተዳደር እድሜ ልካችንን እያለቀስንና እያስለቀስን መኖር በራሱ የታሪክ ድህነት ነው። ታሪክ ይወረሳልም ይሰራልም። የአባቶቻችንን ታሪክ መውረስ አንድ ነገር ነው። ወርሰን ብቻ ቁጭ ካልን ግን ውሸት ነው ልጆቻችንን አንወድም ማለት ነው። ከኛ በኋላ ለሚመጣው ትውልድ የምናስብ ከሆነ ከኛ በፊት የነበረው የአባቶቻችን ትውልድ ታሪክን እንዳወረሰን ሁሉ እኛም ደማቅ ታሪክን ሰርተን ለልጅ ልጆቻችን ለማውረስ መስራት ይጠበቅብናል። ዛሬ!ቸር ያቆየን
አዲስ ዘመን ሐምሌ10/2012
በሐሚልተን አብዱልአዚዝ