በያዝነው ዓመት ከሕትመት እስከ ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች የመቃብር ቦታ(በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ) ጣሪያ ነካ ሲሉ በቅብብሎሽ ዘግበውት ነበር። ታዲያ ይሄን የሰማው ከተሜ ለአኗኗሩ ሳይሆን ለመቃብሩ ይጨነቅ ጀምሮ ነበር። አንዳንዱም የሰማውን ማመን እስኪያቅተው የሚያውቃቸውን በሙሉ በመጠየቅ አጃኢብ ማሰኘቱን በሕብረት ተርኳል። ሌላው ደግሞ ‹‹ምን ዓይነት ዘመን ላይ አደረስከኝ?›› ሲል በሕይወት ለመኖር ሲከፍል የነበረውን ትንቅንቅ ረስቶ ዕድሜው ዘልዛላ ሆኖ ይሄን ጉድ እንዳሳየውና አይኑ እያየ ነገሮች የተቀየሩ ያህል የተሰማው አይጠፋም። በጎነት ዘጠኝ ክንድ ተምሶ የተቀበረ ያህል የሚወቅስም አታጡም። በዚህ የተነሳም ዘመኑን እና ትውልዱን ቀማኛ አድርጎ የደመደመው ሰው ቁጥሩ ቀላል አይደለም። አስክሬንን(ጀናዛን) ያለ አስር ሳንቲም አጥቦ፣ በመኪና ጭኖ፣ ማረፊያ አዘጋጅቶ የሚቀብር አካል መኖሩን የሰማ ‹‹ኧረ ተው እኔ ያየሁት በቁም ቀባሪ ነው›› ይል ይሆን?
በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያዊ ባህሉ፣ እምነቱ፣ ወጉ፣ ልማዱ፣ አንድነቱ፣ አብሮነቱ፣ ቸርነቱ፣ መዋደዱ፣ መከባበሩ…ወዘተረፈ በአጠቃላይ መልካም እሴቶቹ የጉም ያህል ብን ብለው የጠፉ ያህል የተሰማቸውም ሰዎች ነበሩ።
በተመሳሳይም ፖለቲካው ዘርቶ፣ አጠጥቶ፣ አብቅሎ፣ ኮትኩቶ፣ ለፍሬ ያበቃቸውን አልፎ አልፎ በአገሪቱ የሚስተዋሉ መጥፎ ድርጊቶች በእምነቶች መካከል፣ በብሄረሰቦች መካከል፣ በማህበረሰቡ መካከል የሆኑ፣ የተደረጉና የተፈጠሩ አድርገው የሚነዙ አካላት አይጠፉም። ይሄ የኢትዮጵያዊነትን የትስስር፣ የመዋደድ፣ የአንድነት፣ የፍቅር ማሰሪያ ውል ጥልቀት በፖለቲካቸው ጮርቃ ሚዛን ከመለካት የሚመነጭ የለጋ እሳቤ ውጤት ነው።
ማህበረሰቡ ለኢትዮጵያውነት ብያኔ አይሻም። ማህበረሰቡ ኢትዮጵያዊነትን በተግባር በየዕለቱ የሚኖረው እውነት ነው። ማህበረሰቡ የኢትዮጵያዊነት ወግና ባህሉን፣ የልብ አብሮነቱን በተግባር የሚመነዝርበት፣ደስታና ኀዘኑን የሚካፈልበት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ያለው ነው። ይሄን ሐቅ በተግባር ቋንቋ ከሚነግሩንና ከሚያስረዱን በርካታ ተግባራት መካከል በማህበራት ተሰባስበው ለወገኖቻቸው ጉልበት እና እስትንፋስ የዘሩ ብዙ ናቸው። ከእነዚህ መካከል ዕድሜው ለጋ ድርጊቱ ለግላጋ፣ ከተመሰረተ ቅርብ መልካም እጆቹ የደረሱት ሩቅ፣ ከዕድሜ ጠገብነት የዓላማ ቁርጠኝነት ያጠነከረውን፣ ከመነሻ እስከ መዳረሻ፣ አቅዶ የሚሠራ የልማትና የመረዳጃ ማህበር አስተዋውቃችኋለሁ። በጎነትን ከበጎዎች፣ በበጎዎች፣ ለምስኪኖች ብንለውስ? ‹‹አፋቅ››ን።
‹‹አፋቅ የልማትና የመረዳጃ ማህበር›› ይሰኛል። ለብዙዎቻችን ‹‹አፋቅ›› የሚለው ቃል ፊደል ተሳስተን ያነበብነው አለያም በትየባ ስህተት የተዘለለ ወይም ተቆርጦ የቀረ ነገር ያለው ሊመስለን ይችላል። ግን ትክክል ነው። ‹‹አፋቅ›› ማለት የአርብኛ ቃል ሲሆን፤ ትርጉሙም አጥናፍ፣ አድማስ፣ ከጥግ እስከ ጥግ አንድምታን ያዘለ ነው። አዎ! እይታው እሩቅ ነው፤ መዳረሻውም ከጥግ እስከ ጥግ ኢትዮጵያዊነት ነው ብያችሁ የለ።
አፋቅ የልማትና የመረዳጃ ማህበር የተመሰረተው በ2008 ዓ.ም በወረሃ ነሐሴ ነው። ለዚህ ደግሞ የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ አንዱ መነሻ ነው። ድህነት የኢትዮጵያ ዓይነተኛ መለያ መሆኑን ተከትሎ ማህበረሰቡም በአብዛኛው ከጎስቋላ ሕይወት ጋር ተላምዷል። ሥራ አጥነት ተንሰራፍቷል። የሚሠሩ እጆች እዚህም እዚያም ልመናን ባህል ያደርጉት ይዘዋል። በሽታ ለአፍታ የማይለያቸውና የቅርብ ጓደኛ አድርጎ የሚጎበኛቸው ዜጎች በርክተዋል። በእነዚህ ዳፋዎች ሕፃናት ወላጆቻቸውን በሞት በማጣት(የቲሞች) ሆነዋል። ወላጆች ልጆቻቸውን የሚያስተምሩባቸው አቅሞች እያጡ፣ እጅ እያጠራቸው ሕፃናት በመማሪያ ዕድሜያቸው ቤታቸው ይውላሉ። አረጋውያንም ተንከባካቢ በማጣት በየደሳሳ ጎጆዎች ያለጠያቂ ቀንና ሌሊቱ አንድ የሆነባቸው በየሰፈሩ ሞልተዋል። ትኩረት ተነፍገው ኖረዋል። ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ኑሮ ሕይወቱን የሚገፋው ወገንም የሚያግዘው፣የሚያቋቁመው፣የሚደግፈውና የሚያበቃው የፋይናንስ ተቋም አለ ለማለት ይቸግራል።
እነዚህና ሌሎች በርካታ ገፊ ችግሮች ለአፋቅ የልማትና የመረዳጃ ማህበር መመስረት በመንስኤነት ተቆጥረዋል። እነዚህ ችግሮች በዘላቂነት ሊቀረፉ የሚችሉት በውጭ ዕርዳታ ሳይሆን የማህበረሰቡን ሀብት፣ አቅምና ገንዘብ በተገቢው በመጠቀም ከዕለት ጉርስ በዘለለ ችግሮቹን ከመሰረታቸው በመፍታት በሚሠራ ሥራ እንደሆነ
ያምናል። በመሆኑም ለትምህርት የተለየ አጽንኦት በመስጠት በግለሰቦች በተናጠል የሚሰጠውን የገንዘብ ልገሳ በዘለቄታዊነት ችግር ፈቺ በሆነ መልክ ለልማት የማዋል ዓላማን የሰነቀ አገር በቀል የመረዳጃና የልማት ተቋም ነው። ኮልፌ ክፍለ ከተማ አየር ጤና አካባቢ ይገኛል።
እነዚህን የአገሪቱን ነባራዊ እውነታዎች መነሻ በማድረግ ተቋማዊ አሠራር ዘርግቶ፣ የረጅም፣ የመካከለኛ እና የአጭር ጊዜ የመዳረሻ እቅዶች በመንደፍና ዘመኑን በሚመጥን የአስተሳሰብ፣ የአመራር እና የአሠራር ማዕቀፍ የሚመራ ተቋም ነው። በተወሰኑ ቅን ወንድሞች አማካኝነት በማህበረሰቡ ዘንድ በየዕለቱ የሚገጥሙ ተጨባጭ ችግሮችን በጥናት ለይቶ እነዚያን ለመቅረፍ የማህበረሰቡን አቅም በማስተባበር ይሠራል፤ ይመራል። የተለያዩ ስልቶች ቀይሶ የተነሳው አፋቅ የልማትና የመረዳጃ ማህበር በዓለም አቀፍ እሳቤ ቅኝት ባህላዊና ማህበረሰባዊ ትውፊቶችን ሳይለቅ ለሕብረተሰቡ ችግሮች መፍትሔን የሚያበጅ ነው።
አቶ ኤሊያስ ከድር የልማትና የመረዳጃ ተቋሙ ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፣ አፋቅ የልማትና የመረዳጃ ማህበር ዜጎቿ በድሎትና በደስታ የሚኖሩባት ኢትዮጵያን መመልከት፣ በቁሳዊም ሆነ በሞራላዊ ሕይወት የደረጃ፣ ከራሱ አልፎ ሌሎችን መርዳት የሚችል ማህበረሰብ እንዲፈጠር ራዕይ አንግቦ መረባረብ ጀምሯል።
በዚህ ሂደትም በቤተሰብም ሆነ በሕብረተሰብ አኗኗር ላይ ቀውስ ሊፈጥሩ የሚችሉ የትምህርት፣ የጤና፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ችግሮች ለማቃለልና ለማቋቋም ተልዕኮ ያነገበ ነው። በተግባሩም ህብረተሰብን፣ ዘርን፣ ሐይማኖትን ሳይነጣጥል ለሁሉም በሰብዓዊነት ለመሥራት የሚጥር ነው።
በየአካባቢው የተቸገሩ የማህበረሰብ ከፍሎች እየተበራከቱ መምጣታቸውን ተከትሎ በተናጠል ከሚደረጉ ጥረቶች በዘለለ ተቋማዊ አድርጎ ለማቋቋም በማሰብ መመስረቱን ይገልጻሉ።
አፋቅ የልማትና የመረዳጃ ተቋም ሲመሰረት ጀምሮ መነሻና መድረሻዎቹን አቅዶ እየሠራ ስለመሆኑ የተናገሩት አቶ ኤሊያስ፣ የአራት ዓመት ስትራቴጂ ነድፎ በመሥራት ላይ ይገኛል። ዋና ተልዕኮውም ትምህርትን መደገፍ ነው። ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችንም ይሰጣል።
በተመሳሳይም ለችግር የተጋለጡ ዜጎች ችግሮችን በዘለቄታዊ በሚፈቱ አማራጮች ላይ በማተኮር ራሳቸውን የሚችሉበትን መንገድ ይፈጥራል። እንደ ጤናና ትምህርት ያሉ ማህበራዊ አገልግሎቶች ተቋዳሽ ያልሆኑ ዜጎችን በዘለቄታዊ መንገድ ችግሮችን በሚቀርፉ ስልቶች የበጎ አድራጎት ሥራዎችን ያከናውናል። ወላጆቻቸውን በሞት ያጡ(የቲሞችን) ሕፃናትን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ በመርዳት ይንከባከባል። በማስተማርም በስነምግባር የታነጹ ዜጎች የሚሆኑበትን መንገድ በማመቻቸት ቁርጠኛ ዓላማ ነድፎ እየሠራ እንደሆነ ገልጸዋል።
በተጨማሪም በበዓላት ቀን በቋሚነት ድጋፍ የሚደረግላቸው ከ400 በላይ ሰዎች አሉ። ባለባቸው የችግር መጠንና የቤተሰብ ልክ ድጋፉ ይደረጋሉ። ለዒድ አል አዱሃ(አረፋ) 155 በሬዎች እና 42 በጎች ታርደው ለሚስኪኖችና ችግር ላለባቸው በማከፋፈል ከቤተሰቦቻቸው ጋር በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
የልማትና የመረዳጃ ማህበሩ በትኩረት ከሚሠራቸው ተግባራት ትምህርትን ማጠናከርና መደገፍ ዋናው ነው። በዚህ ረገድም ባለፉት ጊዜያት አባታቸውን በሞት ላጡና በችግር ላይ የሚገኙትን በመለየት 37 ተማሪዎችን በስምንት የግል ትምህርት ቤቶች ያስተምራል። የደንብ ልብስና አስፈላጊ የትምህርት ቁሳቁሶች በማሟላት እንዲማሩ በማድረግ ላይ ይገኛል። በዚህም ከ700 ሺህ ብር በላይ ወጪ መደረጉን ይገልጻሉ። አንድ ቤተሰብ ለአንድ ተማሪ የሚል ፕሮጀክት በመቅረጽ በትምህርት ረገድ የሚሠሩ ተግባራትን ለማሳደግ እየተሠራ ሲሆን፤ በ2013 የትምህርት ዘመንም የተማሪዎቹን ቁጥር 50 ለማድረስ ታስቦ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል። በችግር ምክንያት ትምህርታቸውን መከታተል ያልቻሉትን በመለየት አስፈላጊው ግብዓት ተሟልቶ እንዲማሩ ይደረጋልም ብለዋል።
በተሠራ የዳሰሳ ጥናት ላይ ተመርኩዞ ማህበሩ መፍትሔ መንደፉን የገለጹት ዋና ሥራ አስኪያጁ የተቸገሩ እህትና ወንድሞች ችግራቸው በሕይወት ሳሉ ብቻ የሚያልቅ አይደለም። ሲሞቱም የመቀበሪያ ወጪ ችግሮች በማህበረሰቡ በስፋት ከሚያሳስቡ ጉዳዮች ሆነዋል ይላሉ።
በኢትዮጵያ በተለይም በከተሞች አካባቢ ማህበረሰባዊ ችግሮች ተደርገው ከሚቆጠሩት መካከል የመቃብር ቦታና ወጪ ችግሮች ዋና ፈተና ነው። በዚያ ቦታ ላይ ራስን አስቀምጦ መመልከቱ ለችግሩ መፍትሔ እንደሚያስፈልገው በቂ ማስረጃ ነው። ልብንም ይሰብራል፤በመሆኑም መፍትሔ የሚያስፈልገው በመሆኑ ፕሮጀክት ተቀረጸ። በነፃ ተግባሩን እያከናወኑ እንደሆነ ያስረዳሉ።
እነዚህን የማህበረሰብ ችግሮች ማቃለልና መደገፍ ይቻል ዘንድ አፋቅ የልማትና የመረዳጃ ማህበር የነፃ አስክሬን(ጀናዛ) እጥበት ያከናውናል። በራሱ መኪና በማጓጓዝም የቀብር ስነስርዓቱን ያስፈጽማል። ለዚህም አገልግሎት የሚሰጡ የአስክሬን(የጀናዛ) አጣቢዎች የሴትም የወንድም፣ የማጠቢያ ክፍልና ቁሳቁስ፣ መኪና ግዥ፣የሾፌር ቅጥር እና ወጪ የሚሸፍን በማፈላለግ አገልግሎቱን እውን ማድረግ እንደተቻለ ያብራራሉ።
ይህ አገልግሎት ለችግረኛ የማህበረሰብ ክፍሎች ወጪን በማስቀረት በኩል እፎይታን የሰጠ ተግባር ነው። በተያዘው በጀት ዓመት ለ123 ግለሰቦች አገልግሎቱን መስጠት ተችሏል። በወጪ ደረጃም 166 ሺህ ብር ወጪ መደረጉን አቶ አሊያስ ተናግረዋል። ድርጅቱ ከተጀመረ አንስቶ እስከ አሁን ባለው ሂደት ከ500 በላይ ሰዎች አገልግሎቱን በነፃ እንዳገኙ አብራርተዋል። አሁን ባለው ሁኔታ አገልግሎቱ እየተሰጠ ያለው ለሙስሊሙ ማህበረሰብ ቢሆንም በቀጣይ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችና የአገልግሎቱ ሰጭ ሠራተኞችና የማከናወኛ ቦታ እንዲሁም አጠቃላይ ሁኔታዎችን በማመቻቸት የተለያየ እምነት ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በእኩል ደረጃ አገልግሎቱ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
አገሪቱን በገጠማት የኮሮና ወረርሽኝ ስርጭት የመከላከል ሂደትም ማህበሩ ድርሻውን ለመወጣት ሞክሯል። በመሆኑም አገራዊ የሆነውን የጋራ ችግር በጋራ መሻገር ያስፈልጋል ያሉት ሥራ አስኪያጁ፣ የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁሶች እና የአስቤዛ ድጋፍ ለ374 አባዎራና እማዎራዎችን ማገዝ ችሏል። በቁሳቁስና በሞራል ቤት ለቤት የመደገፍ ሥራዎች ተሠርተዋል። በቀጣይ በክረምቱ ቤት ለማደስ መታቀዱን ገልጸዋል። በዚህ በጎ ተግባሩም ከኮልፌ ክፍለ ከተማ የምስጋና የምስክር ወረቀት እንደተሰጣቸው መመልከት ችለናል።
የአፋቅ የልማትና የመረዳጃ ማህበር ዋነኛ የገንዘብ ምንጮቹ አባላቶቹና ደጋፊዎቹ እንደሆኑ ተገልጿል። ከአንድ ሽህ አምስት መቶ በላይ አባላትን ያቀፈው አፋቅ የልማትና የመረዳጃ ማህበር በየወሩ ከአባላቱ ከአስር ብር ጀምሮ እስከ አራት ሺህ ብር ድረስ ሰዎች አቅማቸው የቻሉትን ያህል እንዲደግፉ ቋሚ ወርሃዊ መዋጮ ይከፍላሉ። ከአቅም በላይ የሆነ ወጪ መክፈል አይገደድም፤ አይፈቀድም። የሚሰበሰበው በሕጋዊ ደረሰኝ ሲሆን፤ ሁለት ሞተሮች ከነአሽከርካሪዎቻቸው አባላት በያሉበት በመሄድ በህጋዊ አሠራር ይሰበስባሉ። የአባልነት መስፈርቱ ፍላጎት ብቻ ነው። እስከአሁን ባለው ሂደት ከአባላት በየወሩ ዝቅተኛው አስር ብር፣ ከፍተኛው ደግሞ አንድ ሺህ ብር ድረስ እየተሰበሰበ ይገኛል።
ከዚህ በተጨማሪ ከፕሮጀክት ሽያጭ ገንዘብ የሚሰበሰብ ሲሆን፤ የተገኘው ገንዘብ ለተፈቀደው ዓላማ እንደሚውል ተናግረዋል። በዚህ መሰረትም ተቀርጸው በሥራ ላይ የሚገኙ አምስት ፕሮጀክቶች ይገኛሉ። የአስከሬን(ጀናዛ) እጥበት፣ የማቋቋሚያ ድጋፍ፣ የኢፍጣር እና የኡዱሁያ (አንድ ሰው ለአንድ ቤተሰብ)፣ የሕክምና ድጋፍ(አንድ ድርጅት ለአንድ ወገን) እና የትምህርት ድጋፍ(አንድ ቤተሰብ ለአንድ ተማሪ)የሚሉ ፕሮጀክቶች በትግበራ ሥራ ላይ ይገኛሉ።
ሌላው የገቢ ምንጭ ዘካ ነው። ዘካ በገንዘብ የሚደረግ ኢባዳ ነው (በገንዘብ የሚሰጥ ነው) በመሆኑም ዘካ ለድሆችና በዝቅተኛ ኑሮ ላይ ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ፍላጎትን በማሟላት በኩል ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። በረካን(ረድኤትን) በገንዘብ ላይ ይጨምራል፤ ነፍስን ከሐጥያት ያጸዳል። በዚህ መሰረት አፋቅ ዘካን ከሚያወጡ የሕብረተሰብ ክፍሎች በመሰብሰብ ዘካ ለሚገባቸው አካላት ያደርሳል።
ከፍራ የተሰኘው ሌላው የገቢ ምንጭ ነው። ከፍራ በእስልምና አስተምህሮ መሰረት አንድ ሰው ግዴታ የሆነበትን እንደ ረመዷን ያሉ መርሆች ላይ በሕመምና በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች ካልፈጸመ በምትኩ ግዳጁን መካስ እንዳለበት ይታወቃል። በዚህም መሰረት ማህበሩ በሕመምና በተለያዩ ምክንያቶች ግዴታቸውን መወጣት ለማይችሉ በምትኩ ከፍራ(ማካካሻ) የቲምና (እናት አባት የሌላቸው)፣ ምስኪን መመገብ፣ ለሚፈልጉ አካላት በቀጥታ በመቀበል ለተገቢው አካል ያደርሳል።
የባንክ ቅጣትም በገቢ ምንጭነት ተቀምጧል። በኢስላማዊ የባንክ አሠራር ሂደት (ወለድ አልባ) በተለያዩ ምክንያቶች ባንኮች የሚሰበስቧቸው ቅጣቶች አሉ። እነዚህ ገንዘቦች ለበጎ አድራጎት ተቋማት የሚሰጡ ናቸው። ስለዚህ ማህበሩ እንደ አንድ በጎ አድራጎት አካል እነዚህን ባንኮች በመጠየቅ ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል።
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት የገቢ ምንጮች በብቃት ለመሥራት ከ2012 በጀት ዓመት ጀምሮ የአራት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ውስጥ የተካተቱ ናቸው። ወደሥራም ተገብቷል። ከእነዚህ አማራጮች በተጨማሪም ገቢውን ለማሳደግና የሚያደርገውን እገዛና ድጋፍ ለማጠናከር ይረዳው ዘንድ የራሱ የሆነ ሁለገብ ሕንፃ የመገንባት እቅድ ሲኖረው በመንግሥት በኩል አስፈላጊ (መስሪያ ቦታ ያሉ) ድጋፎች ይገኛሉ በሚል ተስፋ አድርጓል።
በአጠቃላይ አፋቅ የልማትና የመረዳጃ ማህበር በአምስት የድጋፍ ፕሮጀክቶች የትምህርት ዕድል ለሚያስፈልጋቸው ሕፃናት አስፈላጊውን እገዛ ይሰጣል። ሌሎች በድህነት ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችም አስፈላጊውን ድጋፍና የማቋቋሚያ ገንዘብ በመስጠት የማህበረሰቡን ችግሮች ለማካለል ጥረት የሚያደርግ አገር በቀል በጎ አድራጎት ድርጅት ነው። ሕጋዊ የእውቅና ፈቃድ ይዞ ላለፉት አራት ዓመታትም በጎ ተግባሩን በበጎነት ለማድረስ ብልጭ የሚሉ ተስፋዎችን ማሳየት ጀምሯል። አቅሙና ፍላጎቱ ያላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች አብረን ለወገናችን እንድረስ ሲልም ጥሪውን አስተላልፏል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ10/2012
ሙሐመድ ሁሴን