ከረዥም ዓመታት በፊት የተለየሁትን አብሮ አደግ ጓደኛዬን የአራት ኪሎው የቆጥ መሻገሪያ ፊት ለፊት አገናኘኝ፡፡ ለአፍታ ቆመን ተሳሳምን፡፡ ሌላ ተላላፊ ከነመኖሩ ዘንግተነዋል፡፡ ደንግጠን ተላቀቅን፡፡ እንደ ልጅነታችን ትከሻ ለትከሻ ተቃቅፈን በአቅራቢያው ከሚገኝ አንድ ካፍቴሪያ ገብተን ቁጭ አልን፡፡ ደመቅ ያለ ወሬ በናፍቆት ማውራት ጀመርን፡፡ በወሬው መካከል በመጀመሪያ ዲግሪ መመረቁን የጠፋው በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅቶ የማያላውስ ሥራ በመሥራት ላይ መሆኑን ነገረኝ፡፡
ከአጠገባችን የተቀመጡ በዕድሜ ጠና ያሉ ሰው ጃኬቱን ሳብ አደረጉና ‹‹ ይቅርታ የጉንጭህን ሳትጨርስ አቋረጥኩህ›› አሉት፡፡ ‹‹ኧረ ያዘዝነው መች መጣና አላቸው›› ፈጠን ብሎ፡፡ ‹‹ወግህን እንጂ›› አሉት ሳቅ ብለው፡፡ ‹‹ወሬን ወሬ ያነሳዋልና›› ብለው ቀጠሉ፡፡ በእኛ አገር የተማረም ይሁን ያልተማረ በከተማም ይሁን በገጠር የሚገኙ ወጣቶችን የሚያመሳስላቸውንና አንድ የሚያደር ጋቸውን ባህሪ ታውቀዋለህ፤እስኪ ንገረኝ? ሲሉ ጠየቁት፡፡ ‹‹አፍላነታቸው ነዋ!›› ብሎ ከአፋቸው ሳይጨርሱ መለሰ፡፡ ራሳቸውን ግራና ቀኝ ነቅነቅ አድርገው መሳሳቱን ገልጸው፤ ‹‹ በጥቃቅን ሲደራጁ ያላቸው ሙሃባ›› ነው አሉት፡፡ ‹‹መዋደዳቸው ለዚያች ቅጽበት ብቻ ባይሆን ኖሮ….›› እንዳሉ ብድግ ብለው ሄዱ፡፡
በርካታ ወጣቶች ብድር ከመንግሥት እስኪቀበሉ ድረስ እንጂ ከዚያ በኋላ ከእነ ማህበሩም ስም አያስታውሱትም ይባላል፡፡
በሌላ በኩል በአገሪቱ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው ውጤት ያስመዘገቡ ሞዴል ወጣቶችም አሉ፡፡ እነዚህ ወጣቶች ለአቻዎቸው በጽናት መሥራትን ይመክራሉ፡፡
በደቡብ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ሐዋሳ ከተማ የሚገኘው ወጣት ያሬድ እስጢፋኖስ የያሬድ ብረታብረት ሥራ እና ማሽነሪ ሥራዎች የፈጠራ ሥራ ዋና ሥራ አስኪያጅ ነው፡፡ የአውቶ መካኒክ ትምህርትን መቅሰሜ ወደዚህ ሥራ እንድገባ አድርጎኛል ብሏል፡፡ የተለያዩ የሞተር ዕቃዎችን በማሻሻል የጀመረው ሥራ አሁን ላይ ትክክለኛ ዲጂታላይዝ የማሽን ዕቃዎችን ያመርታል፡፡ ከዛሬ አስር ዓመት በፊት እውቀቱን ብቻ ይዞ ከአምስት ቤተሰቦቹ ጋር በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው የጀመሩት ሥራ አሁን ላይ ከሃምሳ በላይ ለሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ ሦስት ሴቶችና ሁለት ወንዶች ሆነን ነው ሥራውን የገባንበት የሚለው ወጣት ያሬድ መንግሥት ድጋፍና የብድር አገልግሎት እንዳመቻቸላቸው ተናግሯል፡፡
በመጀመሪያው ዙር ሃያ ሺህ ብር ብድር ነው ያገኘነው፡፡ ያንን በተገቢው ተጠቅመን መመለስ መቻላችን በቀጣይ ሃምሳ ሺህ ብር ብድር እንድናገኝ ረድቶናል፡፡ በሦስተኛ ዙር አንድ መቶ ሃያ ሺህ ብር ማግኘት ቻልን፡፡ አሁን ላይ ከሰላሣ በላይ ትልልቅ ማሽኖች፣ ደረጃውን የጠበቀ ወርክ ሾፕና በሚሊዮን የሚቆጠር ጥሬ ገንዘብ ባለቤት ሆነናል፡፡ ካፒታል የተባለ ማሽን አቅራቢ በቀጥታ በትዕዛዝ የተለያዩ ማሽኖች ከእኛ ምርት ተቀብሎ ለተጠቃሚዎች በሊዝ ያስተላልፍል፡፡ ማሽኖቹ ዲጂታል በመሆናቸው በትዕዛዝ የሚሠሩ ናቸው፡፡
ያለፉበት በርካታ ውጣ ውረድ የነበረበት መሆኑን ጠቁሞ ዓላማ ይዘህ ስትሠራ ጉልበት ይሆንሃል፡፡ ተስፋ የሚሆን ጠንካራ ሥነልቦና በውስጥህ መገንባትን ይጠይቃል፡፡ የሚሠራበት ገንዘብ ይጠፋል፤ምርቱ እያለህ ገበያ ሊጠፋ ይችላል፡፡ ስለዚህ የአካባቢውን ማሕበረሰብ ፍላጎት መሰረት አድርገን ለመሥራት እንጥራለን፡፡ ገበያን የማስተዋወቅም ሥራ የግድ ነው እንሠራለን፡፡ በተለያዩ ተቋማት በአካል ተገኝተን ከውጭ በውድ የሚያስገቡትን ማሽን በተመጣጣኝ ዋጋና ጥራት እኛ ማቅረብ እንደምንችል እናስተዋውቃለን፡፡ ለመከላከያም የጦር መሳሪያ ክፍሎች ጭምር አምርተናል ሲል በትግል የደረሱበት ሥኬት መሆኑን ተናግሯል፡፡
ሥራዎቻቸውን የአምስት ዓመት እቅድ እየነደፍን በየጊዜው ወቅቱ የሚጠይቀውን ማሻሻያዎች እናደርጋለን፡፡ በየወሩ የሥራዎቻችንን አፈጻጸም እንገመግማለን፤ ጥንካሬና ድክመቶቻችንን እንለይና እናርማለን ሲል ተናግሯል፡፡
በአገሪቱ የትኛውም አካባቢ የሚገኝ ወጣት በዚህ ወቅት እንዴት ራሱን መለወጥ እንዳለበት፣እንዴት የሥራ ሰው መሆን እንደሚችል፣ እንዴት ቤተሰቦቹን መርዳት እንደሚገባው ነው ማሰብ ያለበት፡፡ ምክንያቱም አላስፈላጊ ድርጊቶች ዋጋ ያስከፍላሉ፡፡ ራሱን መጠበቅ አለበት ሲል ወጣቱን መክሯል፡፡ በድርጅቱ ውስጥ ሥራ የሌላቸው ወጣቶችንና ከቴክኒክና ሙያ ተመርቀው የሚወጡ ወጣቶችን እንደሚያሳትፉ ገልጿል፡፡
የጥገና (በሜንቴናንስ) ሥራ የጀመረው ድርጅት ወደማንፋክቸሪንግ ተለወጠ፡፡ ከዚያም ለአካባቢው አገልግሎት ብቁ የሆኑ ዲጂታል ማሽኖችን በበቂ ሁኔታ የማምረት አቅም ገንብቷል፡፡በቀጣይም ለጎረቤት አገራት ለመላክ አቅደን ዝግጅት አድርገናል፡፡ ተሽከርካሪ ወደማምረቱ ለመግባት ግኝቱ ተጠናቋል፡፡ የእውቅና ፈቃድ ብቻ ነው በመጠበቅ ላይ የምንገናኘው ብሏል፡፡
ምን ምን ዓይነት ማሽኖችን በዋናነት እንደሚሠሩ ላነሳንለት ጥያቄ፤ማንኛውም የማሽነሪ ሥራ ይሠራል፡፡ የዳቦ ማሽኖች፣ ሚክሰር ማሽኖች፣ የሊጥ ማቡኪያ፣የእስቲም ማሽኖች፣የብሎኬት ማምረቻዎች፣ የበርበሬ መደለዣ፤ ዘመናዊ ወፍጮዎች፣ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በማሽነሪ ዓይነቶች ውስጥ ለአገልግሎት የሚውል ሁሉ እንሠራለን፡፡ ማሽኖቹ በቀላል የኤሌክትሪክ ፍጆታ አገልግሎት መስጠት መቻላቸው በገበያ ላይ ተመራጭነታቸው እንዲጨምር አድርጓል፡፡ በተለይ ትኩረታችንን የሚመራው በህብረተሰቡ ፍላጎት መሰረት ነው ሲል መልሷል፡፡
ወጣት አዳነ ማሞ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው በበሬ ማድለብ ሥራ ውጤታማ ከሆኑ ወጣቶች ተጠቃሽ ነው፡፡ ወጣቱ እንደገለጸው፤ ሥራ አጥ ሆነን በተቀመጥንበት ወቅት በዚህ መንገድ ሥራ መፍጠር እንደሚቻል ማሰብ ጀመርን፡፡ አምስት ሁነን ተደራጅተን በ2010 ዓ.ም ሥራውን ጀመርነው፡፡ አሁን ላይ ጥሩና ውጤታማ የሚያደርግ ሥራ በመሥራት ላይ ነን፡፡ ከአስራ ሦስት በላይ በሬዎች ደልበው በእጃችን ይገኛሉ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ሥራ አለን ብለን አዕምሯችንን አረጋግተን በሥራ ላይ መዋል ችለናል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ባሳየነው የተሻለ ሥራ ከሞዴል ወጣቶች ጎራ መሰለፍ ችለናል፡፡ አንድ መቶ ሺህ ብር ብድር ወስደን ነው ወደ ሥራ የገባነው፡፡ አሁን ያለንን አጠቃላይ የካፒታል መጠን በውል ለይቼ መናገር አልችልም ብሏል፡፡
አቶ በሱፍቃድ አስረስ የአሶሳ ከተማ ቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዞች ልማት ጽህፈት ቤት ዋና የሥራ ሂደት አስተባባሪ ነው፡፡ ወጣቶች የሚፈጠሩላቸውን ምቹ ሁኔታዎች ተጠቅመው ጥሪት አፍርተዋል ወይ? ምንስ ተግዳሮቶች አሉባቸው ? በሚል ላነሳንላቸው ጥያቄ ሲመልሱ በመቼውም ጊዜ መታየት ይኖርበታል፡፡ በቂ ጊዜ ተወስዶ የአዋጭነት ጥናቶችና የተጠናከረ ክትትልና ድጋፍ አለማድረግ፤ ተደራጅተው ወደ ሥራ የሚሰማሩት አካላት በቂ ሥልጠና እንዲወስዱ አለማድረግ ጥቂቶቹ ምክንያቶች ናቸው፡፡ በይድረስ ይድረስ የሚሠሩ በርካታ ተግባራት አሉ ብለዋል፡፡
ወደ ሥራ የሚሰማሩ ወጣቶች የተለያዩ ችግሮች ይስተዋሉባቸዋል፡፡ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ለመክበር ማሰብ፣ ገንዘቡን ካወጡ በኋላ ተከፋፍሎ መጥፋት፣ ከተደራጁበት የቡድን ሥራ ድርሻቸውን እያነሱ መውጣት፣ ጠንካራ ሥነልቦና አለማዳበር፣ተስፋ እየቆረጡ መምጣት፣ ፈተናዎችን መቋቋም አለመቻል፣ የገንዘብ አያያዝ ችግር፣ ከአባላት ጋር መጋጨትና ማማረር ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ውጤታማ ያልሆኑ በርካታ ኢንተርፕራይዞችም አሉ፡፡ሠርተው የተቋቋሙም አሉ፡፡ ነገር ግን በሚፈለገው ደረጃ አይደሉም፡፡ ቁጥራቸውም ጥቂት ነው፡፡
በአጠቃላይ በአሶሳ ከተማና በ74 የገጠር ቀበሌዎች ብቻ ከ95 በላይ ኢንተርፕራይዞች ተደራጅተዋል፡፡ በዙር በዙር ተደልድለው የተመደበላቸውን ከአስር ሚሊዮን ብር በላይ ወስደው ወደ ሥራ ገብተዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 16/2011
ሙሐመድ ሁሴን