የኢትዮጵያ እግር ኳስ እድገት ለመቀጨጩ በርካታ ምክንያቶች ሊዘረዘሩ ይችላሉ። ከእነዚህ መካከል አንዱና ትልቁ ምክንያት ሆኖ በተደጋጋሚ የሚነሳው ታዳጊዎችን ለማሰልጠን የሚያበቃ አካዳሚ አለመኖሩ ነው። በእርግጥ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በአገር አቀፍ ደረጃ በተገነቡ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከላትና አካዳሚዎች የተለያዩ ስልጠናዎች ደረጃቸውን ጠብቀው በተገነቡ የማሰልጠኛ ማዕከላት መሰጠት ጀምረዋል። ይሁን እንጂ በተገነቡት ዘመናዊ የማሰልጠኛ ማዕከላት እግር ኳሱን ከቁልቁለት ጉዞ ታድጎ አንድ ርምጃ ወደ ፊት የሚያራምድ ፍሬ ማፍራት እንዳልተቻለ ለማንም የተሸሸገ እንዳልሆነ መገንዘብ ይቻላል። የተገነቡትን ዘመናዊ የማሰልጠኛ ማዕከላት ፍሬ እንዲያፈሩ በአግባቡ እንዳልተሰራባቸው አንዱ ማሳያ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን(ካፍ) የተገነባውና ከአስር ዓመት በላይ አገልግሎት ሳይሰጥ የቆየው የካፍ እግር ኳስ አካዳሚ ነው።
በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ አያት አካባቢ የሚገኘው አካዳሚው ግንባታው የተጀመረው በ1997 ዓ.ም ሲሆን፤ በሶስት ዓመት ለማጠናቀቅ ነበር የታቀደው። ሆኖም ግንባታው በመዘግየቱና ከተጠናቀቀም በኋላ አገልግሎት መስጠት አለመጀመሩ በርካታ መዋዕለ ንዋይ የፈሰሰበትን መሰረተ ልማት አገልግሎት ሳይሰጥ እንዲባክንና ጉዳት እንዲደርስበት ሆኗል። የስፖርት ቤተሰቡ በዚህ የተነሳ ተደጋጋሚ ቅሬታ ሲያቀርብ ቆይቷል። ይህንንም ተከትሎ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተካሄደ እንቅስቃሴ አካዳሚው ስራ አስኪያጅ ተመድቦለትና ለብልሽት ለተዳረጉ ስራዎች እድሳት ተደርጎባቸው ተስፋ ማሳየት ጀምረዋል። ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻም የስፖርት አመራሮች እንዲሁም የስፖርት ማህበራት ኃላፊዎች በቦታው ተገኝተው ጉብኝትና የችግኝ መትከል መርሃ ግብር አካሂደዋል። በወቅቱም አካዳሚው ስላለበትና ቀጣይ እጣ ፈንታው ምን እንደሚሆን ማብራሪያ ተሰጥቷል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጂራ፤ የልህቀት አካዳሚው 15 ዓመት እንደሆነው በማስታወስ፣ ካፍ በአህጉሪቷ የእግር ኳስ ልህቀት አካዳሚውን ለመገንባት ሲነሳ የመረጣቸው አገራት ካሜሩን፣ ሴኔጋል እና ኢትዮጵያ መሆናቸውን ይናገራሉ። በወቅቱ የካፍ ፕሬዚዳንት የነበሩት ኢሳ ሃያቱ ካሜሮናዊ በመሆናቸው በአገራቸው የሚገነባውን ተመሳሳይ አካዳሚ ግንባታ ወደራሳቸው በማድላት በዲዛይኑ መሰረት በጥሩ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ማድረጋቸውን አቶ ኢሳያስ ያስረዳሉ። በዚህ ወቅትም ሁሉም መሰረተ ልማት የተሟላለትና ስፖርተኞችን እያፈራ እንደሚገኝ ይናገራሉ። በሴኔጋል የተገነባው ተመሳሳይ አካዳሚም ቢሆን ከዋና ከተማዋ ዳካር 80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የአገሪቱ መንግስት ገንዘብ በመመደብና በማደስ ብሄራዊ ቡድናቸውን ያሳርፉበታል።
የኢትዮጵያው አካዳሚ እስካሁንም ድረስ ባለበት የቆየ ሲሆን ከወራት በፊት ካፍ የባለቤትነት መብት እንዲሰጥ ለፌዴሬሽኑ ደብዳቤ ጽፎ ነበር። በዚህም መሰረት የሰነድ ርክክቡ ተጠናቆ የውልና ማስረጃ ስራዎች በመከናወን ላይ እያለ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በመከሰቱ ሊቋረጥ ችሏል። ወደፊት ከኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በመተባበርና ሂደቱን በማጠናቀቅ ህጋዊ ይሆናል ተብሎም ይጠበቃል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ይህን እያደረገ በነበረበት ወቅትም ጎን ለጎን ዘርፈ ብዙ ስራዎችን ሲያከናውን እንደነበረ ፕሬዚዳንቱ አቶ ኢሳያስ ያስታውሳሉ። የጀርመኑ ክለብ ባየርሙኒክ የአካዳሚውን ሜዳ እንዲያሰራ፣ ጂአይዜድ ደግሞ ሁለት የተፈጥሮና አንድ የሰው ስራሽ ሜዳዎችን ለመስራት ቃል መግባታቸውን ጠቁመዋል።
በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድኖችን ለተለያዩ ጨዋታዎች ለማዘጋጀት በሆቴሎች እንዲያርፉ ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ እንደሚደረግ ይታወቃል። ከዚህ በኋላ ግን በዚህ አካዳሚ በማሳረፍ ዝግጅታቸውን እንዲያደርጉ ማድረግ እንደሚቻል አቶ ኢሳያስ ተናግረዋል። ከእግር ኳስ ባሻገር ያሉ ስፖርቶችም ብሄራዊ ቡድናቸውን ማሳረፍ የሚችሉበት አጋጣሚ እንዳለ ተገልጿል። ከዚህ ባሻገር በኢትዮጵያ አርፈው ወደ ሌሎች አገራት የሚጓዙ ብሄራዊ ቡድኖች በአካዳሚው እንዲያርፉ በማድረግ ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት እንደሚቻልም ጠቁመዋል። ይህንን ለማድረግ ግን የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት ያስፈልጋል። ይኸውም የልምምድ ሜዳ እና የጉድጓድ ውሃ መሆኑን ለመንግስት ጥሪ ተደርጓል። ይህ ሲሆንም የፌዴሬሽኑን ጽህፈት ቤት አካዳሚው ወዳለበት ስፍራ ለማዘዋወር እንደሚያመች አቶ ኢሳያስ አብራርተዋል።
የቀድሞውም ሆነ የአሁኑ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት የሚገኝበት አካባቢ መሐል ከተማ እንደመሆኑ የእግር ኳስ እንቅስቃሴ ለማድረግ አይታሰብም። አፍሪካን ጨምሮ በሌሎች አገራት ስፖርቱ ሙሉ በሙሉ የሚንቀሳቀሰው በአንድ አካባቢ በተገነባ ዘመናዊ የስፖርት ማዕከል ነው። ይህ አካዳሚ እያለ ግን አገልግሎት መስጠት ሳይጀምር የመፍረስ አደጋ ተጋርጦበት ነበር። የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ባደረገው ጥረትና በመደበው 2 ሚሊዮን ብር ግን በድጋሚ ሊታደስችሏል። በቀጣይም መንግስታዊ አካላት ለትውልድ ሊተላለፍ የሚችለውን አካዳሚ ሊጠብቁ እንደሚገባ አቶ ኢሳያስ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ በበኩላቸው፤ የአካዳሚው ግንባታ የተጀመረው እርሳቸው የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ እያሉ መሆኑን አስታውሰው፣ ለዓመታት በዚህ ሁኔታ ውስጥ አልፎ አሁን እድሳት ሲደረግለትም በስፖርቱ ውስጥ መሆናቸውን ተናግረዋል። በመሆኑም ይህ ለእግር ኳስ እድገት እንዲሁም ስፖርተኞችን ለሚያፈራ አካዳሚ ኮሚቴው የሚጠበቅበትን የሚወጣ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነሩ ዱቤ ጂሎ፤ ከወራት በፊት አካዳሚውን በጎበኙበት ወቅት አሳዛኝ ሁኔታ መመልከታቸውን ያስታውሳሉ። በወቅቱም ከፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ጋር በመሆን ወደ ስራ መግባት እንደሚኖርበት ተነጋግረዋል። በተከናወነው ስራም አሁን የተሻለ ሁኔታ ላይ ሊገኝ ችሏል። ስለ ስፖርት ሲታሰብ ዋናው ጉዳይ የማዘውተሪያ ስፍራዎች በመሆናቸው ኃላፊነት ያለበት ኮሚሽኑ አካዳሚው ስልጠና እንዲጀምር በትኩረት በመስራት ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል። አካዳሚው እንዲገነባ ያደረጉ አካላት ምስጋና የሚገባቸው ቢሆንም ለ15 ዓመታት ያለ ስራ መቀመጡ ግን ጥፋት ነው ሲሉም አቶ ዱቤ ተናግረዋል። በመሆኑም ይህንን ለማረም በቁርጠኝነት መነሳታቸውን አረጋግጠዋል። አካዳሚውን ለማፍረስ ሙከራ ያደረጉትንም የሚቃወሙና ማስተካከያ ማድረግ የሚያስፈልግ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በእርሳቸው ሃሳብ ላይ ያከሉት የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽነር አቶ ኤሊያስ ሽኩር በበኩላቸው፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ማዕከላትን መንከባከብ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል። ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ለስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች መሬት ከመስጠት ባሻገር በቀጣይነት አብሮ መስራት አስፈላጊ ነው። የተገነቡና እየተገነቡ ያሉ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችና የስልጠና ማዕከላት ከተልእኳቸው አንጻር በሙሉ ኃይላቸው እየሰሩ አይደለም። በሌላ መልኩ በየአካባቢው የተገነቡት ማዕከላት ለማህበረሰቡ ተገቢውን አገልግሎት መስጠት አለባቸው። በመሆኑም በየአካባቢው ያሉ የስልጠና ማዕከላትና አካዳሚዎች ተገቢውን ግልጋሎት እንዲሰጡ ማድረግ ተገቢ ነው። በተለያዩ አካባቢዎች ውድ የሆነው መሬት ለስፖርት እንዲውል ቢሰጥም እንደ ካፍ አካዳሚ ሁሉ ለዓመታት ታጥረው መቀመጥ የለበትም። መንግስት፣ ህብረተሰብ እንዲሁም የስፖርት ቤተሰቡም በስፖርት ስም የተቀመጡ መሬቶችንና ግንባታዎችን ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው በበኩላቸው፤ አካዳሚው የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ብቻም ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ሀብት መሆኑን ጠቁመዋል። የአካባቢውን ማህበረሰብም ተጠቃሚ በማድረግ ገቢ ማስገኘት የሚቻልም ይሆናል። እስካሁን አካዳሚውን አለመጠቀም ‹‹ምን ዓይነት እንደሆን ያሳያል›› ያሉት ሚኒስትሯ፤ መንግስት ቦታውን ሰጥቶ መስራት ያለበት አካል በሚገባው ቦታ አለመገኘቱ አሳዛኝ መሆኑን ይገልጻሉ። ቦታውን ከተረሳበትና ከተጎዳበት በማስተካከል አሁን ያለበት ላደረሱ አካላትም ምስጋና ይገባል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 22/2012
ብርሃን ፈይሳ