አዲስ አበባ፦ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በሰራተኛ ፍልሰት መቸገራቸውን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ትናንት በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ፓርኮችን የማልማት እና የማስተዳደር ስራዎች አፈፃፀም በተመለከተ የፌዴራል ኦዲተር የክዋኔ ኦዲት ውጤትና አስተያየት ላይ ለቀረቡ ጥያቄዎች የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ሌሊሳ ነሜ እንዳሉት፤ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ዓላማ ለዜጎች የሥራ ዕድል ማመቻቸትና የሥራ ዕድል መፍጠር ነው፡፡ ፓርኮች የሚገነቡት በከተሞች ዳርቻዎች ላይ እንደመሆኑ ወደ አካባቢዎቹ የሚደርስ ትራንስፖርት እና በአካባቢዎቹ የመኖሪያ ቤት እጥረት የተነሳ ሠራተኞች የዋጋ ንረት እየጋጠማቸው በተደጋጋሚ የሥራ ፍልሰት እየተከሰተ ነው።
ለዚህም የቦሌ ለሚ ቁጥር 1 እና ሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን በዋቢነት በመጥቀስ ዋና ስራ አስፈጻሚዋ አስረድተዋል፡፡ በቦሌ ለሚ ቁጥር 1 አሥር ሺህ ሠራተኞች ተቀጥረው በትራንስፖርትና በመኖሪያ ቤት እጥረት 8ሺህ ሠራተኞች መልቀቃቸውን ጠቁመው፣ በምትካቸውም አዲስ ሠራተኞች መቀጠራቸውን ገልጸዋል፡፡
በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ አቅራቢያ የሚገኙ የመኖሪያ ቤቶች ፓርኩ ሥራ ሲጀምር ኪራያቸው ሦስት መቶ ብር እንደነበር አስታውሰው፣ይህ ዋጋ በአሁኑ ወቅት 1ሺህ 100 ብር መድረሱን አስረድተዋል። ችግሩን ለመቅረፍ መንግሥትና የከተማ አስተዳደሮችና ባለሀብቶች በጋራ በመረባረብ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ መሐመድ የሱፍ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለሚሠሩ ዜጎች መጠለያ ባጭር ጊዜ እንዲገነባ መንግሥትን መጠየቅ፣ በቦሌ ለሚና ሐዋሳ የሚታዩ ችግሮችን መፍታት የመረጃ አያያዝን ማስተካከል እንደሚገባ ተናግረዋል ።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ እንደገለጹት፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ ማልማትና ማስተዳደር ዋና ዓላማ ባለሀብቶች ገብተው ሠራተኞች የሥራ ዕድል አግኝተው የውጪ ምንዛሪ ቢያመነጭ የተሻለ መሆኑን እና እንደ ሀገር ለመወዳደር የቤት ችግር መፍታት አለበት፡፡ ባለሀብቶችም መሬት በተመጣጣኝ ዋጋ አግኝተው ቤቶች ቢሠሩ ችግሮቹን እንፈታለን ብለዋል።
አዲስ ዘመን ጥር 16/2011
ኃይለማርያም ወንድሙ