አዲስ አበባ:- ሰላሳ የሀገር ውስጥና የውጭ የግል ኩባንያዎች ከስኳር ኮርፖሬሽን ጋር ለመስራት ፍላጎት ማሳየታቸውን ኮርፖሬሽኑ አስታወቀ፡፡በስኳር ኮርፖሬሽን ኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ አቶ ጋሻው አይችሉህም እንደተናገሩት፤ ከመስከረም 2009 እስከ ጥር 2011 ባሉት ጊዜያት 30 የሀገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች ከኮርፖሬሽኑ ጋር በሽርክና ለመስራት ማንነታቸውን የሚገልጹ ሰነዶችን አቅርበዋል፡፡ ከአንዳንዶቹ ጋር ውይይቶች ተደርገው የመግባቢያ ሰነድና የጋራ ኮንትራት ውል ተፈርሟል፡፡
ከሰላሳዎቹ ኩባንያዎች ውስጥ አንዳንዶቹ የስኳር ፋብሪካ ሙሉ በሙሉ በመግዛት ስኳር የማልማት ፍላጎት ያላቸው ሲሆን አንዳንዶቹ ደግሞ ከመንግስት ጋር በጆይንት ቬንቸር የማልማት ሀሳብ አላቸው ብለዋል፡፡ ሌሎች ኩባንያዎች ደግሞ የስኳር ፋብሪካዎች ተረፈ ምርቶችን በመጠቀም የተለያዩ ምርቶችን የማምረት ፍላጎት እንዳላቸው መግለጻቸውን ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ጋሻው ማብራሪያ፤ ከስኳር ኮርፖሬሽን ጋር በጋራ ለመስራት ፍላጎት ካሳዩት መካከል ወንጂ ላይ የኢታኖል ፋብሪካ ለመገንባት እንቅስቃሴ የጀመረው የጀርመኑ ሸሚት የተሰኘ ኩባንያ አንዱ ነው፡፡ የስኳር ኮርፖሬሽን መሬትና ሞላሰስ የሚያቀርብ ሲሆን ይህም የፋብሪካው 14 በመቶ ድርሻ ነው፡፡ ሶስት በመቶው በተለያዩ ግለሰቦች የሚያዝ ሲሆን የተቀረውን ድርሻ ሸሚት የሚይዝ ይሆናል፡፡ ኩባንያው በባንክ ማስያዝ ያለበትን ዋስትና አስይዟል፡፡ ለፋብሪካው ግንባታ የሚሆኑ መሳሪያዎችን ከጀርመን ሀገር ለማምጣት እንቅስቃሴ ላይ ነው፡፡
የኮርፖሬሽኑ አንዱ ክፍተት የስኳር ፕሮጀክቶች ወደ ስራ ከገቡ በኋላ የመምራት ችግር ነው ያሉት አቶ ጋሻው፣የግል ኩባንያዎቹ ከሚሳተፉባቸው ዘርፎች አንዱ ወደ ስራ የገቡ ፕሮጀክቶችን የመምራት ስራ ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የግል ባለሃብቶች ፕሮጀክቶችን በመምራት የተሻሉ በመሆናቸው ፕሮጀክቶቹ ትርፋማ እንዲሆኑ ያስችላሉ ተብሎ ተስፋ ተጥሎባቸዋል፡፡ አንዳንድ የግንባታ ስራቸው ያልተጠናቀቁ ፋብሪካዎችን ግንባታውን አጠናቀው እንዲመሩ ለማድረግ ታስቧል፡፡
እንደ አቶ ጋሻው ማብራሪያ፤ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ኮርፖሬሽኑ ከግል ባለሃብቶች ጋር ለመስራት ፍላጎት ነበረው፡፡ መንግስት ባለፈው ዓመት የልማት ድርጅቶችን በከፊል ወይም በሙሉ ወደ ግል ለማዛወር ያስተላለፈው ውሳኔ በዘርፉ ለመሳተፍ የሚፈልጉ ኩባንያዎች ቁጥር እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል፡፡
ሀገሪቱ ለግል ዘርፍ ያላት ምቹ የፖሊሲ፤ የተትረፈረፈ የሰው ሀይልና የተፈጥሮ ሃብት የግል ባለሃብቶቹ በዘርፉ ለመሰማራት ፍላጎት እንዲያሳዩ ምክንያት ሆኗል፡፡
መንግስት የልማት ድርጅቶችን በሙሉ ወይም በከፊል ወደ ግል ለማዛወር መወሰኑን አምና ማሳወቁ ይታወሳል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 16/2011
መላኩ ኤሮሴ