‹‹እናት አባት ቢሞት በሀገር ይለቀሳል ፤
ሀገር የሞተ እንደሁ ወዴት ይደረሳል›› ሲሉ ጥንት አያት ቅድመ አያቶቻችን ከራሳቸው ክብር ይልቅ ለሀገር ያላቸውን ፅኑ ፍቅር የሚገልፁበት አባባል አላቸው። የእኔ ዘመን ትውልድ ደግሞ ‹‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል›› አለች እንስሳ የሚለውን ብሂል ያስቀደመ ይመስላል። በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ያለችበት ነባራዊ ሁኔታ ፖለቲከኞቻችን ስልጣን ለመቆናጠጥ ሲሉ እርስ በርሳቸው ለመናቆር የሚጣደፉበት አይደለም። በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ በሀገራችንም ጥላውን አጥልቷል። የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሊጠናቀቅ ጫፍ በደረሰበትና ግብፅ ያስቁሙልኝ ከበሮ የምትደልቅበት፤ የምታየውና የምትሰማው ሁሉ ቅዠት ሆኖ አይሆንም፣ አይደረግም ብላ ያዙኝ ልቀቁኝ እያለች ትገኛለች። ሲያሻት በድርድር አለፍ ሲል በዛቻ መለስ ሲል በመገናኛ ብዙሃኖቿ ጦርነት እያራገበች ባለችበት ወሳኝ ወቅት የእኛዎቹ ፖለቲከኞች ‹‹ምርጫ ካልተደረገ…›› እያሉ መቅበዝበዛቸው አስገራሚ ነው።
ግብፃዊያኑ በአባይ ወንዝ ጉዳይ የትኛውንም ያህል የፖለቲካ ቅራኔ ውስጥ ቢሆኑ ‹‹ኧረ ልጅ ማሰሪያው ኧረ ልጅ ገመዱ…›› እንደሚባለው ዓባይ የእነሱ ማስተሳሰሪያ ቁልፍ ገመዳቸው መሆኑን ጠንቅቀው ስለሚያውቁ በአንድነት ቆመው በሀገራችን ላይ ጫና እያደረጉ ይገኛሉ። ጫናው እስከ አሜሪካ ግምጃ ቤት ዘልቆ ታይቷል። የሀገራችን አንዳንድ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግን በሀገር ሉአላዊነት ላይ የተዳፈረችውን ግብፅ ለመሞገትና ለመመከት ድምፃቸውን ሲያሰሙ አይስተዋልም። ድንቄም ተፎካካሪ የተሰኙና የጠላት ተባባሪ የሆኑም አልጠፉም። እውነተኛ የህዝብ ተቆርቋሪ ከሆኑ ሀገር በአንበጣ ሲወረር፣ ብርቅዬ ሀይቆቻችንና ወንዞቻችን በእምቦጭ አረም የመጥፋት አደጋ ሲጋረጥባቸው፣ ህዝባቸው የድረሱልን ጥሪ ሲያሰማ ያሉበትን ደብዛ አጥፍተው ይቀመጡ ነበርን? ኧረ የት ነው ያላችሁት ማለት ነሸጠኝ።
በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ ከግብፅ የሚሰነዘረውን ጥቃት አንድ ሆኖ በተባበረ ክንድ ከመመከት ይልቅ ሽንቁር በመፈለግ ሀገርን ለማፍረስ የሚዳዳ ባንዳ ፖለቲከኛን ማየት አደባባይ እየወጣ ነው። ይህን ስመለከት ጥይት በግንባሬ ብለው የተዋደቁ ጥንታዊ አርበኞች አጽማቸው ተነስቶ ‹‹የእሳት ልጅ አመድ›› ብለው የሚራገሙ ይመስለኛል። በዚህ ትውልድ የወረደ አስተሳሰብ ሀገርን ለጠላት አሳልፎ መስጠት ታሪክ የማይረሳው ክህደት መሆኑን አለመረዳት ቅድስና ሳይሆን ስይጥንና ነው። ዳሩ ግን ‹‹ ድሮ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ…›› እንዳይሆንብን ቅድሚያ ለሀገር መስራትን ማስቀደም ይገባል። አሁንም ቢሆን ጊዜው አልረፈደምና አስተሳሰባቸው የታወረባቸው፣ ከቅዠታቸው ያልነቁ ፖለቲከኞቻችን ሊያስቡበት ይገባል።
ምርጫ ካልተደረገ ሀገር ትፈርሳለች ሲሉ ጡሩንባቸውን ለሚነፉት ፖለቲከኞቻችን ‹‹ከመጠምጠም መማር ይቅደም›› እንዲሉ አበው ከስልጣን ይልቅ የሀገርና ህዝብ ህልውና ይቅደም ለማለት እወዳለሁ። ‹‹ወገኔ ተበደለ፣ መልካም አስተዳደር የለም፣ የልማት ተጠቃሚ አልሆንም ›› የሚለው ስልጣን ለመያዝ የሚጠቀሙበት የውሸት ጭንብል እንጂ ከልብ የመነጨ ተቆርቋሪ እንዳልሆኑ አሁናዊ አቋማቸው ምስክር ሆኖናል።
በፖለቲካዊ ርዕዮተ አለም ውስጥ ልዩነት አለ፤ ይሄ መኖርም ያለበትና የሚጠበቅም ነው። እንኳን በአንድ ሀገር በአንድ እናት ልጆችም የሀሳብ ልዩነት ይኖራል። ይሄ አይገርምም። በእናትና በእናት ሀገር ላይ ግን ልዩነት የለም። ምክንያቱም እናት እናት ናታ። ያለእሷ፣ያለህዝቧ፣ያለአፈሯ ስልጣን ትርፉ ዘፈን ነው።
የአንዳንድ ፖለቲከኞቻችንን ያልተገባ አካሄድ ስመለከት ድምፃዊ ኤፍሬም ታምሩ ‹‹ ሁሉንም ትተሽ ተመለሽ፤ውብ ዓለም እባክሽ፤ ጎጆሽ ይሻላል ንብረትሽ›› ሲል ያዜመውን ለፖለቲከኞቻችን ማስታወሻ ጋብዛቸው ጋብዛቸው ያሰኘኛል። ሀገርን ለማዳን፣ የሀገርን ጥቅም ለማስከበርና ህዝብን ለመጥቀም ሁሉም አራት ኪሎ መግባት አይጠበቅበትም። ማንነታችሁን ከደጅ አሳይ ታችሁ ህዝቡን ማማለል ደግሞ ብልህነት መሆኑን መምከር አይጠበቅብኝም። ካልሆነም ድንቄም…! መባላችሁ አይቀሬ ነው።
አዲስ ዘመን ሰኔ 21/2012
ሞገስ ተስፋ