ትምባሆ ሳይንሳዊ ስሙ ኒኮቴና ታባከም(Nicotiana tabacum) ሲሆን በዓለማችን በስፋት የሚበቅል እፅ ነው፤ በትምባሆ ውስጥ የሚገኘው ኒኮቲን በፈረንሳዊው ዢየን ኒኮት የተሰየመ ሲሆን ኒኮት በ(1530-1600) እ.ኤ.አ የኖረና ለአውሮፓ ትምባሆን ማጨስ ያስተማረ እንደሆነ ታሪኩ ያሳያል:: ትምባሆ በአላካሎይድ ኒኮቲን ቅመም የበለፀገ ሲሆን ከጥንት ጀምሮ ለመድኃኒትነትና ለማነቃቂያነት ሲያገለግል የኖረ ነው፤ ይህ ተክል በጥንት ሰዎች በጉንጭ በመያዝ የሚዘወተር የነበረ ቢሆንም በምንገኝበት ዘመን ግን በሲጋራ መልክ እየተዘጋጀ የደራ የሚባል ገበያ አለው፤
ተክሉ ዓለማችንን ተቆጣጥሯል ማለት ይቻላል፤ ምክንያቱም በኢኮኖሚ ውስጥ ያለው ድርሻ ቀላል የሚባል አይደለም:: አመታዊ የሲጋራ ሽያጭ ትርፍ 35 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር እንደሆነና ትምባሆ በማጨስ በዓመት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 6 ሚሊየን እንደሚደርስ የገበያና የጤና መረጃዎች ያሳያሉ:: ይህም በመሆኑ በዓለም እንደዚህ ተክል የሰዎችን ህይወት ያጠፋ የለም ለማለት ይቻላል::
አመታዊ የሲጋራ ሽያጭ ትርፍ 35 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር እንደሆነና ትምባሆ በማጨስ በዓመት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ደግሞ 6 ሚሊየን እንደሚደርስ የገበያና የጤና መረጃዎች ያሳያሉ።
በትምባሆ ውስጥ የሚገኘው እጅግ ሱስ አስያዥ ቅመም አልካሎይድ ኒኮቲን(alkaloid nicotine) ሲሆን ተክሉ መርዛማ ከሚባሉ እፅዋት የሚመደብ ነው:: ይህንን ተክል በአንድ ጊዜ ከልክ በላይ መውሰድ ተቅማጥ፣ የመጫጫን ስሜት፣ ማስመለስ፣ የትንፋሽ ማጠር፣ የልብ በዝግታ መምታትና አቅልን ለመሳት ሊዳርግ ይችላል:: የትምባሆ ልማት በአብዛኛው የሚካሄደው ለቅጠሉ ሲባል ነው::
ትምባሆ በሕክምናው መስክ
ትምባሆ በታሪክ ውስጥ ለረዥም ጊዜ እንደ መድኃኒት ሲወሰድ የቆየ እፅ ነው፤ የትምባሆ ቅጠል አሻኝ(diuretic)፣ በሰውነት ውስጥ የጓጎለን ነገር የሚበትን(discutient)፣ ሰውነትን ሰከን አድርጎ የሚያረጋጋ ነገር ግን ሱስ አስያዥ(narcotic)፣ የምራቅ ምርት የሚጨምር(sialagogue)፣ እንቅልፍ የሚያመጣ(sedative)፣ የማስመልስ ባሕሪ ያለው(emetic)፣ ፀረ ወናጊ (antispasmodic) እንዲሁም በባሕል ሕክምና በጉበት ውስጥ ያለውን የሃሞት ፍሰት ለማስተካከል ይወሰዳል::
ትምባሆ በውጭ አካል ላይ ለቆዳ በሽታዎችና ለጊንጥ ንድፊያ የሚወሰድ ሲሆን፤ እብጠት ላላቸው ቁርጥማቶችም ይወሰዳል:: ለጊንጥ ንድፊያ ለጋ ቅጠሉን በተነደፍነው ቦታ ላይ አሻሽቶ ማድረግ ሕመሙን ያስታግሳል:: በቆዳ ላይ እንደኪንታሮት ያሉ ሕመም ያላቸውን እብጠቶች ህመማቸውን ለመቀነስ ወይም ለማዳን ጥቅም ላይ ይውላል፤ የተጨቀጨቀ ቅጠሉን በራስ ላይ ማድረግ ከፍተኛ ራስ ምታትን ያሽላል፤ ከዚህ በተጨማሪም ከደረቀ ቅጠሉ በመኪና ጉዞ ወቅት ለሚያጋጥም የማስመለስ ሁኔታ መመለሻ ማዘጋጀት ይቻላል::ይህ ሁሉ ጥቅም ይኑረው እንጂ፣ ትምባሆ በጣም አደገኛ የሚባል ተክል ነው፤ ምክንያቱ ደግሞ በፍጥነት ሱስ የማስያዝ ባሕሪ ስላለው ነው፤ በእፁ ውስጥ የሚገኘው ኒኮቲን በቆዳችን በኩል ጭምር ወደ አካላችን መግባት የሚችልና ሱስ ሊያሲዝ የሚችል ነው::
ትምባሆ ለምግብነት
ከትምባሆ ቅጠል ፕሮቲን ማግኘት ይቻላል፤ ፕሮቲኑ ምንም ሽታና ጣዕም የሌለው ነጭ ዱቄት ሲሆን ከሌሎች ምግቦችና መጠጦች ጋር በመቀላቀል ሊወሰድ ይችላል፤ ይህ ፕሮቲን 99.5 የፕሮቲን ይዘት ያለው ሲሆን ምንም ጨው፣ ቅባትና ኮሌስትሮል የለውም:: ከትምባሆ ዘር ፍሬ ደግሞ ለምግብ የሚሆን ዘይት ማውጣት ይቻላል:: የተክሉ የሁሉም ክፍል ኒኮቲን አለው:: በመሆኑም ተክሉ የፀረ ነፍሳት(insecticide) መድኃኒቶችን ለመስራት ይውላል፤ የደረቀው ቅጠሉ እስከ 6 ወር ድረስ ጥቅም ሊሰጥ ይችላል፤ ከቅጠሉ የሚጨመቅ ፈሳሽ ሰውነትን በመቀባት ነፍሳትን ከአካባቢያችን ማራቅ ይቻላል::
አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2012