በንጉሣዊ ሥርዓቱ ዘመን ‹‹እረኛ ምን አለ?›› ይባል ነበር አሉ:: በዘመንኛው ‹‹ዓለም እንዴት ውላ አደረች›› ብለን የሚዲያ ዳሰሳ (ሞኒተሪንግ) እንደምናደርገው ማለት ነው:: እርግጥ ነው በዚህኛው ዘመን የመረጃ ዳሰሳ ሲደረግ በ24 ሰዓታት ውስጥ ብቻ ሳይሆን በየሰዓቱና በየደቂቃው የሚፈጠሩ ክስተቶችን ለመቃኘት ያስችላል:: ይህ ዕድል ባልነበረበት ዘመን ግን ‹‹ከእረኛ ምን አለ?›› የሚገኘው መረጃ የወራት ርዝማኔ ያለው ሊሆን ይችላል::
በዘመኑ ‹‹እረኛ ምን አለ?›› የሚባለው፤ የአካባቢው ሰው ምን እያለ እንደሆነ ለማወቅ ነው:: የህዝብ አስተያየት እያሰባሰቡ ነው ማለት ነው:: ንጉሡም እረኛ ምን እያለ እንደሆነ ለማወቅ ባለሟሎቻቸውን ይልካሉ (በዘመንኛው ስንተረጉመው ደህንነት መሆናቸው ነው):: እረኞች በሚሉት ነገር የህዝቡ የልብ ትርታ ይታወቃል ማለት ነው::
‹‹እረኛ ምን አለ?›› የተባለው በምክንያት ነው፤ ለምን ‹‹ህዝብ ምን አለ?›› አልተባለም? ህዝብ አዋቂ ስለሆነ እውነቱን ስለማይናገር፤ ይሉኝታና አስመሳይነት ስላለበት ወይም ስለሚፈራ ነው:: ልጆች ግን የዋህ ስለሆ ያዩትንና የሰሙትን በቀጥታ ይናገራሉ:: ‹‹ልጅ ምን ያወራል ቢሉ የምድጃ ሰሙን›› የሚባል አባባልም አለ፤ የምድጃ ሰሙን ማለት ምድጃ (የእሳት ዳር ጨዋታ) የሚሰማውን ለማለት ነው:: ንፁህ ሰሌዳ ስለሆኑ የተጻፈባቸውን ነው በደማቁ የሚናገሩት::
ወላጆች ማታ ማታ ምድጃ (እሳት ዳር) ቁጭ ብለው ብዙ ነገር ያወራሉ:: በዚህ የእሳት ዳር ጨዋታ መንግሥት ይታማል፤ ይወቀሳል:: የሥርዓቱ ምንነት በዚህ የህዝብ እንጉርጉሮ ይታወቃል::
እረኞች ደግሞ ልጆች ስለሆኑ የዋህ ናቸው:: ምድጃ ዳር የሰሙትን ነገር በግጥም ይጫወቱታል:: ጨዋታዎቻቸው የወቅቱን ሁኔታ የሚገልፁ ይሆናሉ:: ብሶታቸውን፣ ደስታቸውን… ሁሉ ይገልፃሉ:: በዚህ የእረኞች እንጉርጉሮ መንግሥት የህዝቡን ሁኔታ በቀላሉ ያውቃል ማለት ነው:: ለዚህ ነው ‹‹እረኛ ምን አለ?›› የሚባለው::
አሁን ወቅቱ የእረኛ ነው:: እረኛ እንጉርጉሮ የሚያበዛው በክረምት ወራት ነው:: ምክንያቱም የሚጠበቁ ነገሮች ሁሉ የሚበዙት በክረምት ስለሆነ ነው:: በበልግ ወቅት የተዘሩ የሰብል አይነቶች የቤት እንስሳት ከበሏቸው ይሞታሉ:: ምክንያቱም በቂ ዝናብ ስለማያገኙ ውስጣቸው መርዛማ ነው:: ምናልባት ከአካባቢ አካባቢ ሊለያይ ቢችልም እኔ በማውቀው አካባቢ (ሰሜን ሸዋ እና ደቡብ ወሎ) ‹‹አንጣቆ›› ይባላል:: መርሐቤቴ አካባቢ ደግሞ ‹‹አጣብቆ›› ይሉታል:: በማሽላ ቡቃያ (አዲስ ብቃይ) ውስጥ የሚገኝ መርዝ ነው:: በተለይም ላም እና በሬ አጥብቆ ይገላል:: በዚህ ወቅት ጠባቂዎች ባለማሽላዎች ሳይሆኑ ባለከብቶች ናቸው::
ከሰኔ ወር መጨረሻ አካባቢ ጀምሮ ግን መርዛማነቱ ይቀራል፤ ያኔ ጥበቃ የሚደረገው ለከብቶቹ ሳይሆን ሰብሉ በከብቶች እንዳይበላ ነው:: ጠባቂዎችም ባለከብቶች ብቻ ሳይሆኑ ባለሰብሎችም ይሆናሉ:: የሁሉም ጠባቂዎች እረኛ ነው የሚባሉት (በብዛት ግን እረኛ የሚባለው ለከብትና ፍየል ጠባዊዎች ነው)::
የእረኛን የክረምት እንጉርጉሮ አስመልክቶ የሚባሉ የሥነ ቃል ግጥሞችን እናስቃኛችኋለን:: እነዚህ የሥነ ቃል ግጥሞች የጥበብ ሀሳብ ናቸው፤ እንደማንኛውም የኪነ ጥበብ ሥራ ስሜት ገላጭ ናቸው::
እረኞች ውሏቸው በውጭ (በመስክ) በመሆኑ ኃይለኛ ዝናብ በመጣ ጊዜ ዛፍ ሥር የሚቆሙ ቢሆንም በይበልጥ ሊያድናቸው የሚችል ከቄጤማ የተሠራ «ገሣ» እንዲሁም አሮጌ ጃንጥላ ያዘጋጃሉ:: እያንዳንዱ እረኛ ከብቶችን ሲያግድ ከለስላሳ የባህር ዛፍ ቅርፊት (አልፎ አልፎ) እና ከቃጫ ገመድ (በብዛት) የተገመደ ጅራፍ ይኖረዋል:: የጅራፉ ጫፍ ደግሞ ድምጽ እንዲኖረው በፈረስ ጭራ ይገመዳል:: አሁን አሁን ግን በማዳበሪያ ቃጫ እየተተካ ይገኛል:: በክረምት ጊዜ እረኝነት ከበጋው የበለጠ ጥንካሬ ይጠይቃል::
እረኞች ከሚጠቀሙባቸው ሥነቃሎች አንዱ የጅራፍ ግጥም ነው። ጅራፍ ማጮህ በእረኞች ዘንድ የሚዘወተር የጨዋታ ዓይነት ነው:: ጅራፍ በቡሄ ወቅት ይበልጥ ቢዘወተርም የአካባቢው እረኞች ከበልግ ወቅት ጀምሮ በብዛት ከብቶቻቸውን ለማገድ ጅራፋቸውን ይዘው ይወጣሉ። ከብቶችን ሜዳ ላይ በማሠማራት ጅራፍ ይዘው በማጮህ ይወዳደራሉ:: አንደኛው ወገን የሌላኛውን ወገን «ከአንተ ጅራፍ የእኔ ጅራፍ ጩኸት ይልቃል» በማለት እያንዳንዱ የራሱን ከፍ የሌላውን ዝቅ በማድረግ ይፎካከሩበታል። ሆኖም እረኞች በጅራፍ ጩኸት ውድድር ጊዜ ያሸነፈው ቡድን ተሸናፊውን ለማናደድ ይዘፍናል:: ተሸናፊውም ቢሆን ራሱን ለማጠናከርና ለማበረታታትና ሌላ ጊዜ ለማሸነፍ የራሱን የመልስ ዘፈን ይዘፍናል:: ይህን የጅራፍ ውድድር ሁለትና ከዚያ በላይ እረኛች ሊጫወቱት ይችላሉ::
የአንተ ጅራፍ ለከስካሳ
የኔ ጅራፍ አንበሳ
ስማው ስማው ሲያገሳ::
የአንተ ጅራፍ ስትቆረጥ፣
በኔ ለመድረስ ወገብህ አይቆረጥ
እየተባባሉ በልጦ መገኘትን ይለማመዳሉ።
በሌላ በኩል አንድ በሰው ቤት ተቀጥሮ ሠርቶ የሚበላ እረኛ እና ሌላው በወላጆቹ ቤት እንደልቡ የሚኖር እረኛ በአንድ ሜዳ ከብት ሲያግዱ በሚገናኙበት ወቅት የሚጫወቱት ጨዋታ አለ:: በሰው ቤት ተቀጥሮ ቢሠራም ስንፍናው ያስቸገረ፤ ሁሌም ከአሠሪዎች ቤት የማይለምድ በየጊዜው በተለያዩ ሰዎች ቤት እየዞረ የሚቀጠርን እረኛ ይተረባል። እንዲሁም በእናት እና በአባቱ ቤት እያለ ከብቶቹን የማይቆጣጠር እና አብዛኛውን ጊዜ ቤት ውስጥ የሚውል እረኛ ብዙ ጊዜ ተረቡ ከሚያርፍባቸው መካከል አንዱ ነው። በጧት የማይነሳ ሰነፍ፣ እንቅልፋምን ደግሞ በአካባቢው ያሉ የጓደኞቹ ከብቶች በጠዋት ሲወጡ «የእርሱማ ከብቶች ፀሐይ እስክትወጣ ድረስ ከቤት አይወጡም» እየተባለ ይዜምበታል።
እነዚህ እረኞች የሚጫወቱት ምሽት አካባቢ ከብቶችን ወደ መንደር ካስጠጉ በኋላ ነው። ጓደኞች ስንፍናውን ለመግለጽና ከአንዱ ቤት ሌላ ቤት የሚቀያይር መሆኑን በጅራፍ ውድድር ጨዋታቸው ላይ እንዲህ እያሉ ይገልፁለታል:: ከብቶቻቸውን ወደ በረት ሳያስገቡ ተራርቀው ኮረብታ ላይ በመቆም ጅራፍ እያጮሁ ምልልስ ያደርጋሉ።
ንሳ ተቀበል የጅራፌን መልዕክት
መስከረም ጠባ ስትዞር ለከት
ብታስታውሰው አበቧ ልሙጃ
እንግዲህ ይብቃህ ያለው ምድጃ
ሲል አንደኛው ሌላኛው እረኛ ደግሞ መልስ ለመስጠት
ንሳ ተቀበል የጅራፌን ጩኸት
ቡሃቃውን አምጣ ከትንሿ ማጀት
ታች ምድጃ ስጣት ለናትህ
ስታነኳኩር እንድታጐርስህ
እያለ ይተርበዋል ሰነፉን እረኛ።
ሌላኛው የእረኞች ጨዋታ ደግሞ ‹‹አህያ መጣች›› በሚል አዝማች የሚጫወቱት ነው:: ‹‹አህያ መጣች ተጭና….›› በማለት የሚፈልጉትን ሀሳብ ይገልፃሉ::
በአህያ መጣች ጨዋታ ብዙ ጊዜ የሚመላለሱት እርስ በርስ መተራረብ (በዘመነኛው ትርጉም መፎጋገር) ነው:: ጀግንነታቸው፣ አዋቂነታቸው፣ ብልህነታቸው… ሁሉ የሚገለፀው በሚፈጥሩት የግጥም ሃይል ይመስላቸዋል::
በነገራችን ላይ የአህያ መጣች ጨዋታ ብዙ ጊዜ የእረኞች ይሁን እንጂ አዋቂዎችም እርስ በርስ ይተራረቡበታል:: አህያን የተጠቀሙበት ምክንያት በግልጽ ባይታወቅም፤ ምናልባት ግን አህያ በገጠሩ የአገሪቱ ክፍል የዕለት ከዕለት የሥራ መንቀሳቀሻ ስለሆነች ነው:: ገበሬውም ነጋዴውም ያለ አህያ አይንቀሳቀሱም:: በአህያ የጭነት እንቅስቃሴ ደግሞ ረጅም ርቀት ይኬዳል:: አህያ ጭኖ የሄደ ሰው ሲመለስ አዲስ ነገር ይዞ ይመጣል:: በድሮ ጊዜ ንግድ የገንዘብ ማግኛ ብቻ ሳይሆን የኮምኒኬሽን መረብ በመሆን የመረጃ ማግኛም ነበር:: ከአካባቢው ርቆ የሄደ ሰው ሲመለስ አዲስ ወሬ ይዞ ይመጣል:: አህያዋ ከፊት ስለምትሆን የሰውየው መምጣት የሚታወቀው ደግሞ በአህያዋ ነው:: ለዚህም ነው ‹‹አህያ መጣች›› የሚለው ጨዋታ የተፈጠረው:: አህያዋ ጭነት ብቻ ሳይሆን መረጃም ይዛ ትመጣለች::
አህያ መጣች ተጭና ወንበር
እጣን አሮጌው ይቀጠፍ ጀመር
‹‹እረኛ ምን አለ?›› ማለት ይሄ ነው እንግዲህ:: በዘመኑ የነበሩ መንግሥታት መረጃ ይደብቁ ነበር:: ድርቅ ወይም ሌላ አስከፊ ወረርሽኝ (እንደ ዘንድሮው ኮሮና ማለት ነው) ሲከሰት ጉዳቱን አይናገሩም ነበር:: ዛሬ የኮሮና ቫይረስ የያዛቸውን ሰዎች እና ህይወታቸው ያለፈም ካለ በየዕለቱ እንሰማለን:: ለዚያውም ከነ ዝርዝር ጉዳዩ:: እንዲህም ሆኖ ግን ህዝብ አያርፍም! አሁንም እኮ መንግሥት የደበቀን መረጃ አለ እየተባለ ነው:: ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ‹‹ምንም የደበቅነው ነገር የለም›› ብለዋል::
የኪነ ጥበብ ሥራዎች (በተለይም ሥነ ቃል) እንዲህ የዘመንን ባህሪ ያሳያሉ:: ልጆች ደግሞ የዋህ ናቸውና በቀጥታ ይናገራሉ:: ‹‹ዕጣን አሮጌው ይቀጠፍ ጀመር›› የሚለው የአህያ መጣች የእረኞች ዘፈን በዚያን ዘመን ከህፃን እስከ አዋቂ ድረስ ለሞት ያበቃ አደጋ ተክስቶ እንደነበር ይነግረናል::
አህያ መጣች ተጭና ገብስ
ምን የሚሉት ነው መሬት ማውረስ
ተትቶ መሬት የት ሊደረስ
የ‹‹መሬት ለአራሹ›› ተቃውሞ በእረኞች ነበር የተጀመረ ማለት ነው:: እረኞች ቤት ውስጥ ሲወራ የሚሰሙትን ነው መስክ ላይ የተናገሩት:: ‹‹እረኛ ምን አለ?›› የሚለውን ለመስማት የሚላከው የንጉሡ ጆሮ ጠቢ ይሄን ሲሰማ እንግዲህ የህዝቡን የልብ ትርታ አወቀው ማለት ነው:: መሬት ‹‹ባላባት›› በሚል ዘውዳዊ ልማድ የአንድ ወገን መጠቀሚያ ሳይሆን ሁሉም ድሃ እኩል የሚያገኘው መሆን አለበት የሚል መልዕክት የያዘ ነው::
በእረኞች የአህያ መጣች ጨዋታ ውስጥ ፖለቲካዊም ሆነ ማህበራዊ ሂስ ይሰነዘራል:: በማህበራዊ ህይወት ውስጥ ነውር የሆኑ ነገሮችን የሚያወግዝ መልዕክት ያለው ጨዋታ ይጫወታሉ::
ለምሳሌ በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ከባሏ ውጭ ሌላ ወንድ ጋር ግንኙነት ያላት ሴት የተጠላች ናት::ይች ሴት ብዙ ጊዜ የባሏን ቤት ትታ ውሽማዋን ወደምታገኝበት ቦታ ስትሄድ ከታየች ወይም ወሬ ከተሰማባት በእረኞች ትሰደባለች:: ከዚህ በተጨማሪ ሚስቱ ከሌላ ወንድ ጋር ግንኙነት እንዳላት የሚጠረጥር ባል በማህበረሰቡ ዘንድ ዝቅተኛ ግምት ይሰጠዋል። ምክንያቱም ሚስቱን መቆጣጠር አይችልም ተብሎ ስለሚታሰብ ክብር አይሰጠውም:: ነገር ግን አጥፊዎቹን ለማረም ደግሞ እረኞች ከመንደር የቃረሙትን ወይም ያዩት ጉዳይ ላይ ተመስርተው ይገጥማሉ።
አህያ መጣች ተጭና ዳባ
እገሊት ሄደች ጉድባ ለጉድባ
አንተ አያ እገሌ የእንትና ባል
ምሽትህን ጠብቅ አትበል ቸል::
እንዲህ ተሆነ የባል ሥራቱ
ቶሎ ቶሎ በል ይቅረብ እራቱ::
እግሯንም አጥበህ አደስ ቀብተህ
ላክለት እንጅ ላያ ውሽሜ
ለሜዳ አህያ ለአያ ሸምሽሜ
በሌላ በኩል የአካባቢው እረኞች ሌብነት የተጠላ ሥነ ምግባር መሆኑን ያውቃሉ:: በአካባቢው እንስሳትን እና የቤት ዕቃዎችን ጨለማን ተገን በማድረግ የሚሠርቅ ሌባን ፊት ለፊት በግጥም ይሰድቡታል። ቤተሰቦቻቸው በሌቦች ሲማረሩ ያደመጡ እና በሬ ሊሰርቅ በጨለማ የመጣው ሌባ በድንጋይ መመታቱን እንዲሁም ጉድጓዶች ውስጥ መግባቱን የተረዱ እረኞች በአንድ ወቅት ሌባውን ሲያዩ እንደሚከተለው ተናግረውታል::
አህያ መጣች ተጭና ሙሬ
አያ እገሌ ገባ በጉድጓድ ሲሰርቅ በሬ
በሰው ቤት ተቀጥረው የሚሠሩ እረኞች ደግሞ የኑሯቸውን ሁኔታ በሰው ቤት የሚንከራተቱት፣ በተጐሳቆለ ኑሮ ያሉ፣ የሚራቡ፣ የሚገፉ ሆነው ግን የተለያየ ባህሪ ያላቸው ይሆናሉ:: አንደኛው ሰነፍ፣ ሌላኛው ሌባ፣ አንዱ በሆዱ የሚታማ እንዲሁም የራሱንና የከብቶችን ደህንነት የማይጠብቅ ይሆናል:: በዚህ ጊዜ እረኞች በአህያ መጣች ግጥም እየተቀባበሉ እንደሚከተለው ይተራረባሉ::
አህያ መጣች ተጭና ኮርቻ
ያ ጓደኛዬ መተኛት ብቻ
አህያ መጣች ተጭና ለምድ
ያ ጓደኛዬ ማዞርያ ሆድ
አህያ መጣች ተጭና ድስት
የእግሩ ቅርጭጭት ያለው ብዛት
እረኞች በጓደኛቸው ያጋጠማቸውን ያለመታመን ችግር በቀልድ መልክ በላሜ ቦራ ግጥም ይገልፁታል::
ላሜ ቦራ
እንች እንጀራ
የዳጉሣ
ቢያንቀኝሳ
እግዜርሳ
እግዜርማ ቆላ ወርዶ
ተወራርዶ
ላሚቷ ጥቁር ወተቷ ነጭ
የዘንድሮ ሰው ተገላባጭ
ይህን የቀልድ ግጥም ሲዘፍኑ እርስ በርስ እየተቀባበሉ ነው:: እረኞች በመካከላቸው እንደዚህ አይነት ባህሪ ያለበትን ልጅ በግጥም መልክ ይነግሩታል::
እረኞች ሆድ ሲብሳቸው የሚናገሩትን፣ ሲጎረምሱ የሚዘፍኑትን እና በሰውኛ ዘይቤ ጦጣ እና ዝንጀሮዎችን የሚያናግሩባቸውን የሥነ ቃል ግጥሞች በሌላ ክፍል ይዘን እንመለሳለን፤ መልካም ሳምንት!
አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2012
ዋለልኝ አየለ