በዚህ ሳምንት ለሦስት አዳዲስ የኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች ፈቃድ ተሰጥቷል:: አዲስ የሬዲዮ ጣቢያ ተከፈተ በተባለ ቁጥር ጉጉት ያድርብኛል (ከልጅነቴ ጀምሮ ሬዲዮ ስለምወድ ሳይሆን አይቀርም):: ሬዲዮ ጣቢያው የሙከራ ሥርጭት ጨርሶ መደበኛ ሥርጭት እስከሚጀምር ድረስ እቸኩላለሁ:: የሚኖሯቸውን ፕሮግራሞች ሲያስተዋውቁ እስከሚጀመሩ ያስቸኩላል::
ዘመኑ ፈጣን የመረጃ አማራጮች ያሉበት መሆኑ እንደ ምክንያት ቢቆጠርም አሁን አሁን ግን የሬዲዮ ጣቢያ ላይ ያለው ጉጉት የቀዘቀዘ ይመስላል:: የሬዲዮ ማድመጫ ፀጉር ቤት እና ታክሲ ብቻ ይመስል ሌላ ቦታ ብዙም አይሰማም:: በተለይ ቤት ውስጥ ቁጭ ብሎ ሬዲዮ ማድመጥ ብዙም የሚስተዋል አይደለም::
በመዲናችን አዲስ አበባ በርካታ የኤፍ ኤም ጣቢያዎች አሉ፤ አሁንም አዳዲስ እየተጨመሩ ነው:: እነዚህ የኤፍ ኤም ጣቢያዎች በየመድረኩ የሚወቀሱበት ነገር ተመሳሳይ የፕሮግራም ይዘት ያላቸው መሆኑ ነው:: ሰዎች በሚፈልጉት አይነት ይዘት አማራጭ ያላቸው አለመሆኑ ነው:: ሙዚቃ ሙዚቃ ሙዚቃ፣ ስፖርት ስፖርት ስፖርት… ተመሳሳይ ፕሮግራም::
‹‹በእገሌ ሬዲዮ ጣቢያ የተላለፈ›› ተብሎ አጀንዳ የሆነ ትልቅ ጉዳይ እምብዛም አይሰማም:: በጋዜጣ እና በቴሌቪዥን የተላለፉ ግን ብዙ ጉዳዮች አጀንዳ የመሆን ዕድል አግኝተዋል:: ለምን ይሆን? ትልልቅ ፖለቲከኞች እና ባለሥልጣናት ጋዜጣ እና ቴሌቪዥን ላይ ነው ሲቀርቡ የምመለከተው:: ትልልቅ ፖለቲከኞች የሚቀርቡበት የሬዲዮ ጣቢያ አንድ ወይም ሁለት መጥቀስ ቢቻል ነው:: ከብዛታቸው አንፃር በጣም አነስተኛ ነው:: ይህ የሆነበት ምክንያት የኤፍ ኤም ጣቢያዎች መዝናኛ ላይ ስለሚያተኩሩ ይመስለኛል::
በሌላ በኩል ደግሞ በታዳሚው በኩልም ችግር አለ:: የተወራለት ፕሮግራም ብቻ እንመርጣለን፤ ሲባል ሰምተን ነው ወደዚያ ነገር የምንሄድ:: እንዲያውም ቴሌቪዥን ጣቢያዎች እና ጋዜጦች ላይ የሌለ ሬዲዮ ጣቢያዎች ላይ ብዙ ነገር አለ:: በተለይም አንድ ሙያ ላይ በማተኮር ጥልቀት ሰጥቶ በስፋት ለአድማጭ ግንዛቤ የመስጠቱ ጉዳይ ከሌሎች ይልቅ በኤፍኤም ሬዲዮኖች ላይ በስፋት ይስተዋላል:: በዚህ በኩል የበለጠ መመስገን ያለባቸው የሬዲዮ ጣቢያዎች ናቸው::
ውበትን ብቻ የተመለከቱ ፕሮግራሞች አሉ:: የህክምና፣ የህግ፣ የምህንድስና፣ የአርክቴክት፣ የቱሪዝም፣ የትራፊክ፣ የተሽከርካሪ ባህሪያት (ሳይንስ)፣ የአካል ጉዳተኛ፣…. በአጠቃላይ አንድ ጉዳይ ላይ ብቻ የሚያተኩሩ በርካታ ፕሮግራሞች አሉ:: እንዲህ አይነት ፕሮግራም የሚበረታታ ነው:: አንድን ሙያ በጥልቀት እንዲታይና እንዲተነተን ያደርጋል:: በዚያ ዘርፍ ውስጥ ያሉ ሰዎች እውቀት እንዲያገኙ ያደርጋል:: ለምሳሌ ስለተሽከርካሪ ባህሪያትና መገጣጠሚያዎች የሚሰራ ፕሮግራም ከዩኒቨርሲቲ ጀምሮ በዚያ ዘርፍ ለሚማሩ እና ለሚሰሩ ሁሉ ራሱን የቻለ ትምህርት ነው:: ህግ ላይ፣ ህክምና ላይ፣ ቱሪዝም ላይ፣ ውበት ላይ.. በየዘርፉ ያሉ ሙያዎች የራሳቸው ታዳሚ አላቸው:: በባለሙያ ሲብራሩና ሲተነተኑ ብዙ ዕውቀት ያስይዛሉ:: የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ቁጥራቸውም አነስተኛ ስለሆነ ብዙም የዚህ አይነት ፕሮግራም የላቸውም፤ ያሉትም መዝናኛ እና የውጭ አገር ስልት ያለው ይዘት ላይ የሚያተኩሩ ናቸው:: አገርኛ ፕሮግራሞችም እንዳሉ ሳንዘነጋ ማለት ነው::
የኤፍ ኤም ጣቢያዎችን በጣም የታዘብኳቸው ዜና ላይ ነው:: የአንድ መገናኛ ብዙኃን ተቀዳሚ ሚናው ዜና ነው:: ሬዲዮ ሲባል ለማንም ቀድሞ ትዝ የሚለው ዜናው ነው:: ሬዲዮ ደግሞ በባህሪው ከየትኛውም የመገናኛ ብዙኃን በተሻለ ቀዳሚ መሆን አለበት:: እየሆነ ያለው ግን በተቃራኒው ነው:: በቴሌቪዥን (ይባስ ብሎም በጋዜጣ) እየተቀደሙ ነው:: ሬዲዮ በባህሪው በደቂቃ ልዩነት ውስጥ የተፈጠሩ ክስተቶችን ለመዘገብ ሰፊ ዕድል ያለው ነው:: ቴሌቪዥን ይሄን ዕድል ማግኘት አይችልም:: እርግጥ ነው ቀረፃ ባይኖረውም ጉዳዩን ብቻ ዜና አንባቢው ማሳወቅ ይችላል (ሰበር ሲሆን እንዲያ ነው እየሆነ ያለውም):: በሬዲዮ ግን ሰበር ዜና መስማት ብዙም አያጋጥመንም:: ውሎውን ሲራገብ የዋለ ክስተት ነው ምሽት ላይ ዜና ተብሎ የሚቀርበው::
ሌላው ችግራቸው ምንጭ ሳይጠቅሱ (ሁሉንም ማለቴ አይደለም) ሌላ መገናኛ ብዙኃን የሰራውን ዜና ማንበብ ነው:: በአንድ የሬዲዮ ጣቢያ ላይ በተደጋጋሚ የምሰማው ነገር ሁልጊዜም ግርምትም ትዝብትም ይፈጥርብኛል:: ቃል በቃል ሙሉውን አንብበው የሪፖርተሩ ስም ላይ ሲደርሱ ‹‹ዘገባው የእገሌ›› ነው ብለው የራሳቸውን ሪፖርተር ስም በመጥቀስ ይደመድሙታል:: እንግዲህ ያ ሪፖርተራቸው ዋሽቷቸዋል ማለት ነው፤ ወይም ራሳቸው ሆን ብለው አድርገውታል ማለት ነው:: እንደ አርታኢ መገናኛ ብዙኃንን አለመዳሰሳቸውና አለማስተካከላቸውም ስህተት ነው:: እርግጥ ነው አንድ አርታኢ የእያንዳንዱን መገናኛ ብዙኃን ዜና ሁሉ አያይም፤ ግን የዕቅድ ዜና ሲሆን በቤቱ ሪፖርተሮች የተሰራ መሆን አለመሆኑን ማወቅ ነበረበት:: ደግሞ ለምን እንደሆነ አላውቅም ብዙ ጊዜ ምንጭ የማይጠቅሱት ከመንግስት መገናኛ ብዙኃን ሲወስዱ ነው:: በአይናቸው ካስተዋሉ ሰዎች እንደሰማሁት የሌላ መገናኛ ብዙኃን ድረ ገጽ ከፍተው ቀጥታ ከዚያው ላይ የሚያነቡ የሬዲዮ ጋዜጠኞች አሉ:: ይሄን ማድረጋቸው ጥሩ ነበር፤ ችግሩ ግን ራሳቸው የሰሩት ዘገባ አድርገው ማቅረባቸው ነው::
በኢትዮጵያ ፍቃድ አግኝተው የሚንቀሳቀሱ በርካታ ንግድና የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች ይገኛሉ:: የማህበረሰብ ሬዲዮ ብዛትን ስንመለከተው በአሁኑ ወቅት 72 ደርሷል:: የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ ማለት ስሙ እንደሚገልጸው የማህበረሰብ ነው:: የማህበረሰብ ነው ማለት የአካባቢውን ማህበረሰብ ታሪክ፣ ወግና ባህል የሚያስተዋውቅ መሆን አለበት ማለት ነው:: በአካባቢው የመግባቢያ ቋንቋ፣ ለአካባቢው ሰዎች የሚሆን መሆን አለበት:: የምንሰማው ግን ከኢንተርኔት ላይ የውጭ አገር ጥናትን ሲያነቡ ነው::
አንድ ነገር ግን ከግምት ውስጥ መግባት አለበት:: የሰው ሃይል እጥረት አለባቸው:: የሰው ሃይል እጥረት ብቻ ሳይሆን የሙያ ብቃትም የለም፤ የሙያ ብቃትና ልምድ ሲኖራቸው ወደ አገር አቀፍ ጣቢያዎች ይሄዳሉ:: የብሮድካስት ባለሥልጣን ለማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች በተደጋጋሚ ሥልጠና ይሰጣል፤ በየሥልጠናው የሚነሳው ግን ተመሳሳይ ችግር ነው::
እነዚህ የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች ብቃት ያለው በቂ ባለሙያ ቢኖራቸው ለአገር አቀፍ ጣቢያዎች ትልቅ የመረጃ ምንጭ የሚሆኑ ናቸው:: ዳሩ ግን ‹‹እገሌ የማህበረሰብ ሬዲዮ እንደዘገበው›› ሲባል ሰምተን አናውቅም:: ቢሰራባቸው ግን የአካባቢውን ሁኔታ በቅርበት የሚያውቁት እነርሱ ነበሩ:: ለምሳሌ የጉራጌ ማህበረብ ሬዲዮ ጣቢያ አለ እንበል:: አዲስ አበባ፣ መቀሌ ወይም ባህር ዳር ሆኖ ስለጉራጌ በስልክ ከመጠየቅ ከዚህ ሬዲዮ ጣቢያ መረጃ መውሰድ የበለጠ ቅርብ ይሆን ነበር:: እርግጥ ነው የማህበረሰብ ሬዲዮ እነዚህ አካባቢዎች አይደርስም፤ ዳሩ ግን የቴክኖሎጂ ዘመን መሆኑን አንርሳ:: የተደራጀ ድረ ገጽ ካላቸው እዚያ ላይ በመጫን በየትኛውም አካባቢ በቀላሉ ተደራሽ መሆን ይችላሉ::
የሬዲዮ ጣቢያዎች በበዙ ቁጥር ተጨማሪ አዳዲስ ሃሳቦችና ፈጠራዎችም አብረው እንዲበዙ ይጠበቃል:: በተለይም የማህበረሰብ ሬዲዮኖች በኤፍኤሞቻችን ላይ የሚስተዋለውን ተመሳስሎሽ በማስወገድ ለአድማጭ አማራጭ ሆነው እንዲቀርቡ ከብሮድካስት ባለስልጣን ጀምሮ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል:: ከአዳዲሶቹ የሬዲዮ ጣቢያዎች አዲስ ነገር እንጠብቃለን!
አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2012
ዋለልኝ አየለ