‹‹የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበር›› የሚል ማህበር ተቋቁሞ እውቅና በማግኘት ባለፈው ሳምንት የምስክር ወረቀቱን ተቀብሏል:: ይሄ ማህበር የመጀመሪያ የምስረታ ጉባኤውን ሲያካሂድ በቦታው ነበርኩ:: ለረጅም ጊዜ ሲያከራክር የነበረው የስያሜው ነገር ነው:: ገላጭ የሆኑ ስሞችን ከዚህ በፊት የተቋቋሙ ማህበራት ይዘውታል:: ለምሳሌ ‹‹የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማህበር›› ጥሩ ስያሜ ነው፤ ግን በዚህ ስም ማህበር እያለ ድጋሚ ፈቃድ አይሰጥም:: አንድ ማህበር ሲቋቋም በሙያው ስም ነው መሆን ያለበት:: ሙያውን የሚገልጽ መሆን አለበት::
የብዙዎች ጥያቄ የሚሆነው እንግዲህ ‹‹በሙያው ስም ማህበር ካለ ለምን ሌላ ማህበር አስፈለገ?›› የሚል ነው:: ትክክለኛ ጥያቄ ነው:: ይግረማችሁ ሌላም ማህበር አለ:: የኢትዮጵያ ነፃ ጋዜጠኞች ማህበር:: ይሄኛውም ማህበር የተቋቋመው የመጀመሪያው ማህበር ሙያውን በሚያስጠብቅ መንገድ አልሰራም በሚል ነው::
እነሆ አሁን ደግሞ ሦስተኛ ማህበር (ምናልባት ሌላ የማላውቀው ከሌለ) ተመስርቷል:: ይሄም የተመሰረተው ሙያውን ለማስጠበቅና በአገሪቱ የጋዜጠኝነትን ሙያ ለማሳደግ፣ መብታቸውንም ለማስከበር ነው:: የተመሰረተውም የመጀመሪያዎቹ በሚፈለገው ልክ ስላልሰሩ ነው:: እንኳን በሚፈለገው ልክ መሥራት እስከመኖራቸውም አይታወቁም:: የጋዜጠኞች ማህበር ባለፈው ዓመት 50ኛ ዓመቱን ሲያከብር እስከመኖሩም ሳይታወቅ ነው:: በሚያውቁት ጥቂት ሰዎችም መንግስት ያቋቋመውና ለመንግስት የሚወግን ገለልተኛ ያልሆነ ማህበር ነው እየተባለ ሲታማ ቆይቷል:: ‹‹ነፃ›› የሚል ቅጽል ስም ይዞ የመጣው የኋለኛው ማህበርም እነሆ እስከመኖሩም አይታወቅም::
ለመሆኑ የአሁኑስ ምን ይዞ መጥቶ ይሆን? ከእነዚያ ያልተሻለ ከሆነ ተወቃሽነቱ ከቀድሞዎቹ በብዙ እጥፍ ይጨምራል፤ ምክንያቱም እነዚያ ስላልሰሩበት እኛ የተሻለ እንሰራለን በሚል ስሜት የተመሰረተ ነው:: ይሄኛው ከከሸፈ በዚህ ሙያ ድጋሚ ፈቃድ ማግኘት ራሱ የሚቻል አይመስልም፤ የትዝብት ትዝብት ነው:: ቀጣይ በሚመጣው ትውልድ ተወቃሽ ይሆናል:: በዚህ ሙያ ማህበር እንዳናቋቁም አደረጉን ማለታቸው አይቀርም:: በመንግስትም ሆነ በህዝብ ላይ አመኔታ ያሳጣል::
አዲሱ ማህበር ስያሜው አካታች ይመስላል:: የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ከተባለ እንግዲህ የካሜራ ባለሙያዎችንም ይጨምራል ማለት ነው:: ዝርዝር አሰራሩን በሚያወጣው የመተዳደሪያ ደንብና መመሪያ ላይ ይወስናል:: ዋናው ነገር ዓላማና ተግባሩ ነው::
ከዚህ ማህበር የሚጠበቀው የሙያውን ክብር ማስጠበቅ ነው:: በአገሪቱ ደብዛው የጠፋውን የጋዜጠኝነት ሳይንስ ማሳወቅ ነው:: ማንም እንደፈለገው የሚደነፋባቸውን ጋዜጠኞች ለመብታቸው መከራከር ነው:: ከባለሥልጣን እስከ ሀብታም፣ ከአርቲስት እስከ አክቲቪስት ‹‹እሽ አትበሉኝ የሹም ዶሮ›› በሚሉ ሁሉ ማስፈራራትና ማሳቀቅ ሊደርስባቸው አይገባም:: ለጋዜጠኞች መብት ጠያቂ አካል መኖር አለበት:: ጋዜጠኛ ለብዙ ነገር ተጋላጭ ስለሆነ የሙያው ክብር መታወቅ አለበት::
በሌላ በኩል፤ ማህበሩ ሥርዓት ያጣውን የአገሪቱን የመገናኛ ብዙኃን ጠብ አጫሪነት ከባለሙያዎቹ ጋር በመመካከር ሙያውን የሚያስከብር መሆን አለበት:: የመንግስትም ይሁኑ የግል መገናኛ ብዙኃን የአንድ ወገን ልሳን ሲሆኑ ሙያውን ያሰድባል:: ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መነጋገር ያስፈልጋል:: መድረኮች እያዘጋጀ ውይይት ማካሄድ አለበት:: የሙያ ማህበር ነውና ለሙያው በሚወጡ ደንብና መመሪያዎች ላይ መሳተፍ አለበት:: በውስጡ ያሉት ሰዎች ባለሙያ ናቸውና ከመንግስት ጋር ተቀራርበው ይነጋገሩ:: መንግስት የሚያወጣው ደንብና ፖሊሲ ከሙያው ጋር የሚኖረውን ግንኙነት ማጥናትና ማጤን ይጠበቅባቸዋል:: ሙያውን የሚፃረር አሰራር ካለም መሞገት አለባቸው:: አለበለዚያ ‹‹አልሰሩበትም›› ብለው ከታዘቧቸው ማህበራት አይሻሉም ማለት ነው::
የአገራችን መገናኛ ብዙኃን የፖለቲካ ትግል ላይ ናቸው:: ስለዚህ የሙያ ሳይሆኑ የፖለቲካ ትግል ማሳለጫ ናቸው ማለት ነው:: በዚህ ሁኔታ ደግሞ የሙያው መርሆዎች ይጣሳሉ:: የማጥቃት እና የመከላከል ሥራ ነው የሚሰሩት፤ የተቋቋሙበትን የፖለቲካ ዓላማ የሚደግፉትን ያቆለጳጵሳሉ፤ የእነርሱን ሃሳብ የሚቃረኑትን ደግሞ ያለምንም ይሉኝታ ያወግዛሉ:: ማህበሩ እንዲህ አይነት አይን ያወጡ ሙያዊ ግድፈቶችን ሊሞግት ይገባል::
አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2012
ዋለልኝ አየለ