የአሜሪካ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን፣ ኔልሰን ማንዴላ ከእስር ተለቅቀው፣ ፕሬዚዳንት በሆኑበት በዓለ ሲመት ላይ ከተገኙ በኋላ አብረው የሮብን ደሴት እስር-ቤትን ጎብኝተው ነበር:: ለማንዴላ የ27 ዓመት ሙሉ መኖሪያቸው ነበረና ጉብኝት ሳይሆን የመጨረሻ ስንበት ነው ሊባል የሚችለው:: ለቢል ክሊንተን ግን ውጫዊም ውስጣዊም የሆነ ግፊት በተቀላቀለው ስሜት በከባድ ጉጉት ነበር፤ እስር ቤቱን ለመጎብኘት የፈለጉት::
እናም ከደረሱ በኋላ በህንድ ውቅያኖስ ባለችው የሮበን ደሴት ፣ ወደታሰሩበትም ወህኒ እያመሩ ሳለ፣ ማንዴላ ሳያስቡት እንባቸው ከመነጽራቸው አልፎ ፈሰሰ:: ወዲያው ይህንን የታዘቡት ክሊንተን አሁን የሚሰማዎት ስሜት ቁጣ ነው ጥላቻ፣ ወይስ እፎይታ፣ እስቲ ይንገሩኝ ፤ ሲሉ ይጠይቋቸዋል::
ሁለቱንም አይደለም ፤ ዳግመኛ በሀገሬ ምድር ይህንን መሰል ግፍ እንዳይፈጸም የመፈለግ ብርታት ነው ያገኘሁት:: ግፍ ምን እንደሚመስል፣ ጭቆናና ስቃይ ፣ ያለውን መልክ፣ መታጠርና መደብደብ የሚፈጥረውን ውስጣዊ ሞገድ በሚገባ እረዳዋለሁ:: ግን ማንንም አልጠላም :: አየህ፣ ሐገር በጥላቻ አይመራም፤ በሰው ልጅ ላይ ቁጥሩ ይነስም ይብዛ ፣ ቀለሙ ይጥቆርም ይንጣ፣ ቋንቋው ያንተን ይምሰል አይምሰል፤ የሚናገረው ይጣምህም አይጣምህ ፣ መሪ ሆነህ በቡድን ላይም ሆነ በፓርቲ ላይ፣ ክፉ ጥላቻና ቁርሾ ካለህ የምታደርሰው ጥፋት ጥልቅ ነው:: መሪ ስትሆን ሆደ ሰፊነትና ይቅር ባይነት አብረውህ ሊኖሩ ይገባል:: እንባዬ ያመለጠኝ በሁለት ምክንያት ነው፤ አንድም የሰው ልጅ በሰው ላይ የሚጨክንበት አባዜ አልከሰትልህ ስላለኝና እስር ቤት እያለሁ ድንጋይ ያስፈልጡን ስለነበረ ብናኙ ወደዓይኔ እየገባ ለረዥም ጊዜ ያስቸግረኝ ነበረና እርሱ ያስከተለብኝ ጣጣም ነው ይህንን የማልቀስ ጦስ የተወብኝ፤ አይዞህ መድኃኒት ሳደርግበት ይተወኛል:: መልሴ ትክክል ይሁን አይሁን አላውቅም አሉት:: አዎ ለጥላቻ መድኃኒቱ ራስን መግዛት ፣ ለክፋት መድኃኒቱ ምህረት፤ ለዓይን ህመምም ጠብታው ነው::
ቢል ክሊንተን ግን፣ ከዚህ ሁሉ ስቃይ በኋላ ስለበደሉዎት ሰዎች የሚሰማዎት ስሜት አስገራሚ ነው:: የሰው ልጅ የብድሩን ገንዘብ ስለከለከሉት፤ ይበቀላል፤ እርሱ ደልቶት እኔ እየተሰቃየሁ አልኖርም ብሎ በምቀኝነት ሰው ይገድላል፤ ባል ሚስትን ከሌላ ሰው ጋር አየኋት ብሎ በቅናት ስሜት ይገድላል፤ በረባ ባልረባው ጉዳይም ጭምር ሰው ሰውን ይገድላል:: ብቻ ማንኛውም የመበለጥ ስሜት በሰው ልብ ውስጥ ቁጭት ፈጥሮ ሌላኛውን ሰው በማጥፋት ለመበቀል ሁለት ጊዜ አያስብም :: ግን እንዲህ ያለ መጠነ-ሰፊ ጥቃት ተፈጥሮ ሳለ ደግሞ ሁሉን በሰከነ ስሜት በማየት ችግሩን ለመፍታት የሚችል ልብ መፍጠር ሁለት ጊዜ መፈጠርን ሳይጠይቅ አይቀርም ነበረ ያሉት::
በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ ሲያልፉ አደጋውን በፈጠረው ሰው ልብ ውስጥ እንኳን በጎነት አለ፤ ብሎ ማሰብ እጅግ መታደል ነው:: የመላእክት ልብ ሊኖርህ ይገባል፤ ማንዴላ ግን አድርገውታል::
በሒትለራዊት ጀርመን ውስጥ የምድር ፍዳዋን አይታ በ14 አመቷ ወደሞት የተነዳችው አና ፍራንክ የተባለችው ልጅ በተወችው የእስር ቤት ማስታወሻ ውስጥ፣ ሁልጊዜ በልቧ ውስጥ ፣ ተስፋና የማይናወጥ ፍቅር ለሰው ልጅ ነበራት:: ተደብቀው ባሉበት የምድር ቤት ውስጥም ሆነ ከተያዘች በኋላ ይህ ስሜቷ ከእርሷ አልተለየም ነበር::
ቀዳሚው ነገር አይሁድ በመሆኗም ሆነ ከዚያ ቤተሰብ በመፈጠሯ ስህተት እንደሌለ ታምን ነበረ:: እንዲያውም በእዚህ ጥንታዊ ቤተሰብ ውስጥ እንደ እድል መፈጠር የቆየ የአኗኗር ትውፊትን ፣ ልዩ ባህልን፣ የእምነት አስተምህሮና የሰው ለሰው መስተጋብርን ፈጥሮላት ነበረ እንጂ:: አይሁዶች በተሰደዱበት ምድር ሁሉ በታታሪ ሰራተኛነት፣ የሚሰሩትን አድምተው በመስራት እርስ በእርስ በመረዳዳትና ደግ በመተሳሰብ ባህል ያጎለበቱ ሁልጊዜ ወደከነዓን የመመለስና እንደገና አዲስ ህይወት የመምራት ድል ከፊታቸው እንዳለ የሚያምኑና የተሰጣቸውን መክሊት ሳይጥሉ ለመኖር የወሰኑ ህዝቦች ናቸው:: ስለዚህ ልበ-ብርቱነትን ስቃይን ማሸነፍን፣ በስራ ልቆ መገኘትን ከሰው በታች ያለመሆንን ማንነት አጠንክረው መያዝ እንደሚገባቸው የሚያውቁ ነበሩ::
ስለዚህም ነው በተበተኑበት የዓለም ምድር ሁሉ የሥራ ቋንቋቸው የሚኖሩበት ሐገር ቋንቋ ይሁን እንጂ ዕብራይስጥን በተደራቢ ቋንቋነት ለልጆቻቸው የሚያስተምሩት ጽሑፋቸውም ከትውልድ ትውልድ ሳይዛባ የኖረውና የቀጠለው ከዚሁ ጽኑ ማንነታቸው ላይ ቆሞ ነው:: አንድ አይሁዳዊ በጀርመን ሀገር ሲኖር ጀርመንኛ ሊናገር ይገባል ፤ ሒብሩ ግን ከማንነቱ ጋር የተቆራኘ የማይነጠል እውነት ነው:: እንደሚናገሩት ሌላኛው ቋንቋ ተጽእኖ መጠነኛ የዘዬ ልዩነት ሊፈጥር ቢችልም ፤ መሰረታዊው ሒብሩና የአምልኮ ሥርዓቱ አብሮት አለ::
ከእነዚህ የማንነት ማሳያዎች ጋር ለሰው ልጅም ያላቸው ክብር ልዩ ነው:: ለዚህ ነው አና ፍራንክ በምድር ቤት መደበቂያዋም ሆነ፣ በእስር ቤት ማስታወሻዋ ላይ ለሌላው የሰው ልጅ ዘር ጥላቻ ያላንፀባረቀችው:: እንዳንዴ ልብ ብዬ ሳስበው በዚች በእድሜዋ ትንሽ በነበረች ልጅ ልብ ውስጥ፣ የበሰሉ ሰዎች ምክር-ቤት አድርገው የተቀመጡ ይመስለኛል:: ሃዘኗን የምትደብቅበት መንገድ፣ ውጭውን የምትናፍቅበት ዘይቤ፣ ጓደኞቿንና ያሳለፈችውን ደጋግ ጊዜ መልሳ በማሰብ የምትስቀው ነገር፤ ከዚያ ስትወጣ ልታደርጋቸው ስለምታስባቸው ነገሮች የሚሰማት ተስፋ፣ አናዳጆቹን ትውስታዎቿን አስባ የምትስቅበት መንገድና አዋቂዎቹ ጭንቀታቸው ሲገነፍል የሚያሳዩትን መቅበጥበጥ የምትገልጽበት መንገድ ገራሚ ነው::
ዝም ብዬ ሳስብ፣ ሳሰላስለው፣ የሰው ልጅ ራሱን ለመግራት ዝግጁነት ከሌለው፣ ዕድሜ ሰውን ለመግራት አቅም የለውም :: ምክንያቱም ብዙ ሽበታም የሆኑ ያልተረጋጉ ሰዎች ገጥመውኛልና :: ሰውን ከልምዳቸው መምከር ሲገባቸው፣ ተመካሪ የሆኑ የሚቅበጠበጡ፣ (የሚቆጡ አላልኩም ቁጣ በስፍራው ተገቢ ነውና ) ሳያስቡት ትልቅ ቦታ ተቀምጠውም ትላልቅ ስህተት የሚፈጽሙ ትናንሽ ሰዎችም ገጥመውኛል::
በሆኑ አጋጣሚዎች ግጥምጥም የአንድ ወረዳ አስተዳዳሪ መሆን የቻሉ ቀን ቀን ቢሮውን አመሳቅለው ውለው ማታ ቤት ሲገቡ ቤተሰቡን በጌሾ ፈረስ ቁም-ስቅል የሚያሳዩ የቆሙለትን ዓላማ ያልተገነዘቡ በ”ወንበር ፍርሃታቸው” ሳቢያ አስፈሪነትን የፈጠሩ ብዙ ሰዎች አሉ:: (ይችን ሐሳብ ሳፍታታት) ለቦታው ራሳቸውን ሳያዘጋጁ፣ ቦታው ላይ በመቀመጣቸው አልቻልከውም እንዳይባሉ፣ ብቻ ትርምስ የሚፈጥሩ ከችሎታቸው ማነስ የተነሳ በቅጡ ሌላውን የማያስችሉ የክፋት ልጆች ይሆኑና ከአስተዳዳሪነት ይልቅ ገዢነት የሚሰማቸው ፤ ከመሪነት ይልቅ እልቅና የተጠናወታቸው ክፉ ሰዎች ይሆናሉ:: ያኔም ተስተዳዳሪው ሰው ሁሉ በየቤቱ ያለቅሳል:: ታላቁ መጽሐፍም ይህንን በማየት ነው፤ መሳፍንት በከፉ ጊዜ ህዝብ ያለቅሳል ፤ የሚለው::
በአና ፍራንክም ሆነ፣ በኔልሰን ማንዴላ እይታ እነዚህን መሰል ሰዎች የማይችሉት ስፍራ መጥተው ነው እንጂ፤ በተፈጥሯቸው የሚችሉትና የሚገባቸው ስፍራ አለ፤ ነው የሚሉት:: የሚያደርጉትን ክፋት ሁሉ የሚያደርጉት፣ ክፉዎች ስለሆኑ አይደለም፤ ነው የሚሉት:: ደግነትን በቅጡ ስላልተገነዘቡና ያንን ደግነት የሚገልጹበትን ቅጽበት ስለሚስቱት ነው:: እነኚህኑ ክፉ የተባሉ ሰዎች እስቲ ወደልጆቻቸው ዘንድ ውሰዷቸው:: ልጆቻቸውን ሲያቀብጡ፤ (የዝሆን ውሃ አመጣልሃለሁ፤ አውሮፕላን አስነዳሃለሁ፤ ከፈለግክ ቲቪውን ስበረው…እያሉ) ሲያሞላቅቁና አለቅጥ ሲንከባከቡ ልታይዋቸው ትችላላችሁ:: ወድደው አይደለም ደግነታቸውን የሚገልጡበት መንገድ ጠፍቷቸው ነው::
በሌሎች ላይ የሚያደርጉትን ክፉ በማድረጋቸው ከስህተታቸው ያመለጡና ሽንፈታቸውን ድል የነሱ ስለሚመስላቸው ነው፤ ሥራን እንዲህ አድርገው የሚያከናውኑት:: እንዲያውም፣ “ማን መሆኔን አሳየዋለሁ” ሲሉ ሥራውን አከናውኜ የተሰጠኝን ኃላፊነት ተወጥቼ፣ ማለታቸው ሳይሆን፣ አስከፍቶኛል አልታዘዘኝም፣ ንቆኛል ፣ የሚሉትን ሰው፣ ያለበትን ቦታ አስታውቀዋለሁ ማለታቸው ነው::
ትልልቅ ቦታዎች ሰውን ትልቅ አያደርጉም ፤ እንዲያውም የብዙው ሰው ትንሽነት የሚገለጠው ትልቅ ስፍራ ላይ ተቀምጦ እንደ ስፍራው ለመሆን ባለመቻሉ ነው:: ሚዛናዊነት ሲያጣ፣ ራሱን መቆጣጠር ሲሳነው፣ ካለፈው መማር ሲያቅተው፣ እዩኝታ ሲያበዛና በእልህ መመላለስ ሲጀምር ፍትህ ደህና ሰንብች:: ርትዓዊነት ገደል ግቢ የምትባለው ያኔ ነው::
ሰው በእድሜው ታናሽነት ሳቢያ አይናቅም ፤ በቆዳው ቀለም መንጣትና መጥቆር ሊገፋ አይገባም፤ በአስተሳሰቡ ምንምነት ሊነወርም አይገባም :: ተግባሩ የሚያስከትለው አደጋ ግን መመዘን ብልህነትና አርቆ አስተዋይነት ነው:: ስለዚህ ነው በምንም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ኖረው ራሳቸውን ከሚገልጸው ነገር በላይ እጆቻቸውና አንደበቶቻቸው የሚያስከትሏቸውን ጥፋቶች ለይተው የተገነዘቡ ሰዎች መኖርና ራሳቸውንም መግለጽ፣ ለቤት ለማህበረሰብና ለሐገር የሚበጀው::
ክሊንተንን ያስገረማቸው ነገር ይህ ብቻ አልነበረም፤ ከ27 ዓመት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ እስር ቤት ስገባ የያዘኝን የፖሊስ አባል፣ ባገኘው ደስ ይለኛል፤ ያሉትና ለመላው ህዝብ ንግግር ወደሚያደርጉበት አደባባይ መጋበዛቸው ነው:: በስቃይ ላላፈ ሰው እኮ፣ ይኼ ነገር ከቁጣ በስተቀር የሚያተርፈው ነገር የለም፤ እንደ ማንዴላ ላለ ሰው ግን ከሚያስቆጣቸው ነገር መሸሽ ቁጣውን አያስቀርላቸውም፤ ቁጭታቸውን አያሰክነውም :: ከዚያ ይልቅ ካስቆጣቸው ነገር ጋር ፊት ለፊት በመጋፈጥ፣ ቁጣቸውን ራሱን እንዳሸነፉት ማሳየት ይፈልጋሉ፤ በትዕግስትና በብልሀትም አድርገውታልም:: ዕረፍታቸው ያማረውም ለዚህ ይሆን?!!
ድንገት ወደ አንድ ሆቴል ከጠባቂዎቻቸው ጋር ገብተው ፊት ለፊት የተፋጠጡትን የቀድሞ ፖሊስ ወደሚመገቡበት ጠረጴዛ ጋብዘውት አብሯቸው ምግቡን በልቶ ሲነሳ፣ “አይዞህ፣ አትፍራ፤ የታገልኩት አንተም እኔም፤ ልጆቻችንም የልጅ ልጆቻችንም በምንሰራቸው መጥፎ ድርጊቶችና ባህሪያት እንጂ ፣ በቀለማችን በአስተሰባችንና በልዩነቶቻችን ብቻ ሳቢያ በደል በህግ የማይፈፀምባት ደቡብ አፍሪካ እንድትፈጠር ነው፤” ብለውታል::
በአደባባይ ካቀረቡት የእርቅና የይቅር ባይነት ንግግር በኋላም አምስት ሺህ ያህል ነጭ የቦር ፓርቲ (ብሔራዊ ዘረኛ ፓርቲ) አባላት የፓርቲ አባልነት መታወቂያቸውን አቃጥለዋል:: ይህንኑ አስመልክቶ ፣ ጋዜጠኞች ላነሱላቸው ጥያቄም የመለሱት፣ “የጥላቻ ዘንዶን፣ የመከፋፈል አውሬ ሃሳብን፣ በገንዘብ አንደግፍም” ሲሉ ነው፤ የተደመጡት:: አፓርታይድ፣ ማለት “በልዩነት እኩልነት” ማለት ነው:: ልዩነቱ የቆዳ ልዩ መሆን ነው፤ የሃሳብ ልዩ መሆን አይደለም :: እውነት ነው፤ አፓርታይድ እንደ አገዛዝ ያወጣቸው ፖሊሲዎች ፣ የዘረጋቸው የአገዛዝ ስልትና ህግጋት አሉት:: በዚህም ሳቢያ ለነጭ የተፈቀደ ፣ ለነጭ የተከለከለ፣ ለጥቁር የተፈቀደ፣ ለጥቁር የተከለከለ የሚል የቆዳ ቀለም መነሻ ሆኖ ፣ ውገና የተደረገባቸው አገልግሎቶች ፣ ትምህርቶች ፣ ስፍራዎች ነበሩ::
“የነጭ መንገድ ነጭ ባቡር፣
የነጭ ሆቴል ነጭ ሰፈር፣
የነጭ ወይን የነጭ ክብር፤
ይባል ነበር በገዛ ምድር::…
የባንቱስታ መርህ ወና ፤
ሰውን መስፈር በዘር ቁና ፣
ጸንቶ ነበር በምድሪቱ፣
ገንኖ አልቀረም ሆነ ከንቱ፤
ሆኖ አልቀረም እንባ ከንቱ::” (ያልታተመ ግጥም)
ይህም ሁሉ ሆኖ አንድ አስቂኝ ነገር እንደነበረ ልነግራችሁ እወዳለሁ:: ነጮቹ ደቡብ አፍሪካውያን ከጥቁሮቹ አንጻር፣ በቁጥር ትንሽ ናቸው :: ስለዚህ ሚዛን ለመጠበቅ ሲሉ በየአመቱ ፣ ቆዳቸው ቀላ ያሉ ደቡብ አፍሪካውያንና የህንድ ዝርያ ያላቸውን ዜጎች እየለዩ “ነጭ ሆነሃል፤ ክልስ ነህ” የሚል መታወቂያ ይሰጧቸው ነበረ:: አጃኢብ ፤ የሚያሰኘው፣ የዘረኞቹ ስልታዊ ቁጥር ቅነሳና መለያየት ሳይሆን፣ ይህንን ልዩ መብት “ለመጎናጸፍ” ክልሶቹና ህንዶቹ ደቡብ አፍሪካውያን የሚያደርጉት ከሌላው ማህበረሰብ የመለየት ተጋድሎና ያላሰለሰ ጥረት ነበረ:: “ወይኔ ዘንድሮም ጣሉኝ እኮ፤ ብለው ራሳቸውን የሚኮንኑትና የሚያዝኑት ነገር ገራሚ ነበር:: ማን ነበረ፤ አዎ ሚሼል ኦባማ፤ “ጥቁር ሆኜ ለመወለዴ መራጩ እኔ አልነበርኩም ፤ ሆኖም እድለኛ ሆንኩና ጥቁር ሆኜ ተፈጠርኩ” ማለቷ ይነገራል:: የሆናችሁትን ሆናችሁት የተገኛችሁት በዘፍጥረት እንጂ ማን ቀውላላ ፣ ማንስ ጥቁር ማንስ ነጭ ማንስ ድንክ ሆኖ ለመወለድ ይፈልጋል? በቃ ሰው ሆኖ መፈጠር እና እርሱንም ተቀብሎ መኖር ነው:: ይልቅ ከህይወት የምንማረውን እንምረጥ፤ ክፉ ፣ ነገረኛ፣ ጦረኛ፣ ተንኳሸ፣ ሐሜተኛ፣ ነፍሰ-ገዳይ ለመሆን ራሳችንን አንመልምል::
እዚህ እኛም ሐገር በተናገሩት ቋንቋና በድንበርተኛነት አሸናፊ ነው፤ ኃይል አለው፤ ከሚሉት ወገን ራስን ለማካተት የሚደረገው ጥረት አስቂኝም አስተዛዛቢም ነው:: ለዚህ ይመስለኛል፤ የሰው ልጅ ከሚያየውና ከሚያልፍበት መንገድ የሚማር እንጂ በተፈጥሮው ጨካኝም ክፉም አይደለም ሲሉ ሊቃውንት የሚሞግቱት:: ስንማር እንኳን “የሚያበላው የቱ ሙያ ነው?” አይደል የምንለው:: የሚያበላንን እንጂ የሚወድና የምንወደውን የማናውቅ ምስኪኖች እኮ ነን::
ሰው በባህሪው ሲወለድ ጀምሮ ክፉ ሆኖ አይወለድም፤ አዋኪ ሆኖ ወደምድር አይመጣም፤ ፋሽስት ሆኖ አይፈጠርም፤ ክፋትንና ጭካኔን ፣ ከትምህርት ቤት ፣ ከፖለቲከኞች፣ ከማህበረሰብ ፣ ከቤተሰብ (የአዋቂ አጥፊዎች በየቤቱ አሉና) ይማሩትና ሰፈር ውስጥ ከጓደኞቹ ጋር ያፋፋዋል:: ያም ወደማህበረሰብ ያድግና አጥፊ የቀበሌ ሹም፣ አጥፊ የወረዳ አስተዳዳሪ፣ አጥፊ ፖለቲከኛ ይሆናል፤ እርሱ ካልተሳካለት መንደር-ገነን ወሮበላ ይሆንና ለህግም ለሰላምም መስፈን ጠንቅ ይሆናል:: ትምህርት ቤታችን በመልካም ጎኑ፣ ትውልዱን አርሞ ገንቢ መሐንዲስ ያደርገዋል፤ አለዚያም መልምሎ አጥፊ ነፍሰ-ገዳይ ያደርገዋል::
ፋሽስቱ ቤኔቶ ሞሶሎኒ ወደ ስልጣን ከመምጣቱ በፊት የአንድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ነበረ:: ትምህርቱን ሲያስተምር በተመስጦ ይሰሙት የነበሩ ልጆች በውስጡ የተደበቀና እየኮተኮተው ያለው፣ ነፍሰ ገዳይ መንፈስ እንዳለው አያውቁም ነበረ:: በመምህርነት ውስጥ ግን ሁልጊዜ ተማሪዎቹን ስለታላቂቱ ሮምና የአወዳደቋን ምክንያት ሲያብራራ ተጠያቂ የሚያደርጋቸው ማሳበቢያና መጥፋት አለባቸው ብሎ የሚያምናቸው፣ “ወገኖች” ነበሩት:: የፋሽስት ፓርቲ አባል ሆኖ ወደስልጣን ሲመጣ መጀመሪያ የሰየፈው በእርሱ መለኪያ በአስተሳሰብ የሚለዩ ናቸው፤ አንቱ የተባሉ ፈላስፎች፣ የማህበረሰብ አነቃናቂዎች፣ ኮሚኒስቶች፣ የእምነት ሰዎች (ካቶሊክ ቤተክርስቲያንን አልነካትም እንዲያውም ሮም ውስጥ የተለየ የራሷን የቫቲካን ግዛት እንዲኖራት በህግ የደነገገው እርሱ ነው) ናቸው:: ስለጥቁሮችም ሲናገር መገዛት ያለባቸው ፣ ያልሰለጠኑ፣ ደናቁርትና ለመሰልጠንና ለመለወጥ የሮም ስልጡን ክንድ ያስፈልጋቸዋል ብሎ ያምንና ይናገር ነበረ፤ በኋላም ሐገራችን ገብቶ፣ ያደረገውን አድርጎ ተባርሮ ወጣ::
መለየት ጌጥ እንደሆነ እንዳይቀበል ያደረገው የኖረበት ማህበረሰብና አስተሳሰብ ነው:: በራሱ የአስተሳሰብ ግዛት ውስጥ የገነባው እምነቱ፣ በአካባቢው ጉልበት ሲለውጣቸው የታዘባቸው ነገሮቹ፣ ከመሆኑ ሌላ ይህንን ሐሳቡን በፋይናንስ የደገፉት ፣ ያቀነቀኑለት የዘመሩለትና ወደህዝብ ሐሳብነት የቀየሩለት ራሳቸው ሰዎች ናቸው:: ይህንን ሲያይ ልክ ያልነበረው ሐሳቡ ልክ ሆኖ የታየውን ገፋበት :: ጣሊያንንም ከጀርመን ጋር በመተባበር ወደሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከተታት::
በ1922 ወደስልጣን መጥቶ፣ ለ23 አመታት በስልጣን ላይ ቆይቶ በሚያዝያ 28/1945 ዓ.ም. ከሚላን ከተማ ሸሽቶ ሊያመልጥ ሲል ተያዘ ተብሎ ከሚያፈቅራት ሴት (ሚስቱ አይደለችም)፤ ክላራ ፔታቺ እና ሌሎች ሶስት ሰዎች ጋር በማግስቱ ከሰዓት በኋላ ተገደለ:: ግድያውም እውን ሆነ ፣ የፍርድ ሂደቱ ፍጥነት ፋሺስቱ ሞሶሊኒ ያደርገው እንደነበረው በመፈጸሙ ገዳዮቹንም በሰብአዊነት አላሳያቸውም :: ይህም ሆኖ ግን ጭካኔውን ሳይሆን ፍቅሩን ያሰበች፣ ሞቱን ሳይሆን ህይወቷን ከእርሱ ጋር ያቆራኘች ሴት እስከሞት ድረስ አብራው ነበረች:: እርሱም ቢሆን ይላል፤ የታሪኩ ጸሀፊ ቤሊኒ ስቴሌ ሲዘግብ ፣ በሞሶሊኒ ፊት ላይ ፍርሃት አልነበረም ፤ መታከትና ግርጣት ብቻ ነበረ እንጂ:: ይህንንና መሰል ነገሮችን ስናይ ሞሶሊኒም ሰው ነው፤ ሞሶሊኒም አፍቃሪ ልብ ነበረው፤ ሞሶሊኒም በመከራው ሰዓት ተደስቶ አልታየም:: ይህም ሰብአዊ መልካችን ነው እንጂ፤ ሰው ሲፈጠር ክፉ፣ ጨካኝ ፣ ጎበዝ፣ ምርጥ፣ አዋቂ ሆኖ አይወለድም፤ ከቶውንም :: አበቃሁ::
አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2012
አገልጋይ ዮናታን አክሊሉ