– አመራሩ በጣልቃ ገብነት ይመራ ነበር
አዲስ አበባ፡-ባለፉት ጊዜያት በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከፍተኛ የመሬት ዘረፋ መካሄዱንና በአመራሩ ላይም ጣለቃ ገብነት እንደነበር ርዕሰ መስተዳድሩ ገለጹ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ አሻድሊ ሀሰን በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፣መንግስታዊ መዋቅሮችንና የኃላፊነት ቦታዎችን በመጠቀም በክልሉ መሬትና ሀብት ላይ ቀጥተኛ ለግለሰቦች ስጡ የሚል ትእዛዝ ይሰጥ ነበር፡፡
ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚታወቀው በተፈጥሮ ሀብቱ ሆኖ ዋናው ደግሞ የመሬት ጉዳይ ነው ያሉት አቶ አሻዲሊ፣ ለም የሆነው ሰፊ መሬት በተገቢው መንገድ ቢሰራበት ከክልሉም በላይ ለኢትዮጵያ የሚበቃ መሆኑን ገልጸው፣ አሰራሩ ልቅ ስለነበረ በርካታ ሰዎች ክልሉ ውስጥ ገብተው መሬት ዘርፈዋል ብለዋል፡፡
እንደ አቶ አሻዲሊ ሀሰን ገለጻ፣ በእርሻ ላይ ብቻ ከ600 በላይ የሚሆኑ ኢንቨስተሮች የተባሉ መሬት መውሰዳቸውን ከዚያ ውስጥ 20 በመቶ የሚሆኑት እንኳን መሬቱን ለማልማት አለመቻላቸውን ጠቅሰው ሰፊ ጥናት ከተደረገ በኋላ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል፡፡
በኢንቨስተርነት ስም የተሰማሩት መሬት ዘራፊዎች የዘረፋ ስልታቸው ያነጣጠረው በመጀመሪያ መሬቱን ተረክበው የባለቤትነት ካርታ ካወጡ በኋላ ካርታውን በማስያዝ ከባንክ ከፍተኛ የገንዘብ ብድር እንደሚወስዱ ነገር ግን ምንም አይነት የልማት ስራ እንደማይሰሩ ጠቁመው፣ይህንን ድርጊት የመሬት ዘረፋ ከማለት ውጪ ሌላ ትርጉም እንደሌለው ጉዳቱም ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመሬት ወረራ ብቻ የተሰማሩት ኢንቨስተሮች በእርሻ ስም ብቻ የወሰዱ መሆናቸውን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ ያለአግባብ በዘረፋ የተወሰደውን መሬት ለማስመለስ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ተድርጎ በስኬት ተጠናቋል፡፡ በርካቶች ፈቃዳቸው ተሰርዞ ካርታቸው እንዲመክን ሲደረብ ሌሎች ደግሞ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፡፡
ቀደም ሲል በነበረው ሁኔታ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ አመራሮች በስውር በሌሎች አመራሮች ጣልቃ ገብነት ይመሩ ስለነበር አሁን ነጻ የወጣንበት ወቅት ነው ብሎ መወሰድ ይቻላል ሲሉ የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ እንደ አጋርም እንደ ታዳጊ ክልልም አመራሩ በቀድሞው ጊዜ ሙሉ እምነት ኖሮት፣በክልሉ ጉዳዮች ላይ ነጻ ሆኖ የሚወስን አመራር ነበር ብሎ መውሰድ ይቸግራል ብለዋል፡፡
በተለያየ መንገድ ውሳኔዎችን በጋራ ወይም በጫና ለማስወሰን መሯሯጦች እንደነበሩ አስታውሰው፣ ለምሳሌ በመሬት ጉዳይ ‹‹በትእዛዝ ለእነ እከሌ እከሌ ስጥ ትባላለህ፡፡ እንግዲህ ለእነዛ ካልሰጠህ ሌላ ነገር ነው የሚሆነው›› ሲሉም አመልክተዋል፡፡
በሌሎችም በመሰረተ ልማቶች፣ በፖለቲካዊ ውሳኔዎች ጉዳይም ቢሆን ፓርቲው ነጻ ሆኖ እየሰራ አልነበረም፡፡አመራርን የመመደብ ሁኔታዎች ነበሩ፤ ስለዚህ ከጣልቃ ገብነት ነጻ አልነበሩም በማለትም ገልጸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 16/2011
ወንድወሰን መኮንን