የ75 ዓመት ጎልማሳ ናቸው:: የተወለዱት በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን ቸሃ ወረዳ የግወግቢ በሚባል ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነው:: አንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በዛው ወረዳ በሚገኝ የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል:: ስምንተኛ ክፍል ከጨረሱ በኋላ ግን በአካባቢያቸው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ምክንያት ደብረብርሃን በሚገኘው ኃይለማርያም ማሞ ትምህርት ቤት አቅንተዋል:: የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ውጤታቸው ወደ ዩኒቨርስቲ የሚያስገባ ባለመሆኑ ኢትዮጵያ ሆቴል በተከፈተበት ዓመት በሆቴሉ በሂሳብ ሰራተኝነት ተቀጥረው መስራት ጀመሩ:: ሁለት አመት ካገለገሉ በኋላ የመስተንግዶ ኃላፊ ሆነው ተመደቡ:: ይሁንና ብዙም ሳይቆዩ የዋቢ ሸበሌ ሆቴል ይከፈትና ደመወዝ ጭማሪ ተደርጎላቸው በዝውውር ለጥቂት ወራት ሰሩ::
በአለቆቻቸው ጥያቄ ዳግመኛ ወደ ኢትዮጵያ ሆቴል ተመልሰው መስራት ቀጠሉ፤ ብዙም አልቆዩ የ1966ቱ የመንግስት ለውጥ መጣና የፍልውሃ ሆቴሎች ምክትል ሥራአስኪያጅ ሆነው ተሾሙ:: በግለሰቡ ታታሪነትና ስራ ወዳድነት ይደነቁ የነበሩ ኃላፊዎች ግን በሾሟቸው ቦታ እንዲቆዩ አላደረጓቸውም፤ ይልቁንም የዋቢ ሸበሌ ሆቴል በወቅቱ የነበረውን የገበያ ችግር ይፈታሉ የሚል እምነት ጣሉባቸውና በተመሳሳይ ደመወዝ በሕዝብ ግንኙነት ተመልሰው እንዲሰሩ አደረጉ:: ከአየር መንገድ ኃላፊዎች ጋር ቅርበት በመፍጠር በትራንዚት የኢትዮጵያን መሬት የሚረግጡትን መንገደኞች ሳይቀር በአውቶብስ በማስጫንና በማምጣት የሆቴሉ ደንበኞች እንዲበራከቱ አደረጉ፤ በዚህም ከፍተኛ ገቢ ማስገባት ቻሉ::
በከፍታቸውም ሆነ በዝቅታቸው «ለምን?» ብለው የማይጠይቁ እኚሁ ስራ ወዳድ ሰው ታዲያ በተመደቡበት ስፍራ ሁሉ ውጤት በማምጣት አንቱታን አገኙ::በዚህም የዋቢ ሸበሌ ሆቴል ምክትል ስራ አስኪያጅ ሆነው ተሾሙ:: ይሁንና ወቅቱ የለውጥ ጊዜ በመሆኑ ችግሮች እዚያም እዚያም መታየት ጀመሩ::ከእነዚህም መካከል በእቴጌ ጣይቱ ሆቴል በአንድ ግለሰብ ምክንያት የሰራተኞች አመፅ ይነሳል:: ቀድሞውንም በተፈጥሮ የተጣላን ማስታረቅና ማስማማት የሚወዱት እኝሁ የዛሬ እንግዳችን በሆቴሉ የተፈጠረውን ችግር ይፈቱ ዘንድ የሰራተኛ ማህበርና የውይይት ሊቀመንበር ሆነው ተላኩ:: እንደታሰበው ግጭቱ እንዲረግብ በማድረግ ሆቴሉ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አወንታዊ ሚና እንዲጫወት የበኩላቸውን ጣሩ:: ተሳካላቸውም::
የግለሰቡን የፖለቲካ ንቃት ያዩት የመንግስት ኃላፊዎች ከተቀጠሩበት ሙያ ጎን ለጎን የካቲት 12 በተባለ የፖለቲካ ትምህርት ቤት ገብተው እንዲሰለጥኑ አደረጉ:: ከፖለቲካ ትምህርት ቤቱ እንደወጡም የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ሆነው ተሾሙና የሰራተኛና የወጣቶችን ማህበራትን በማደራጀት ረገድ የበኩላቸውን ሚና ተወጡ:: በዚህ ሂደትም የነበሩ ችግሮችን በድፍረት በመናገርና የማያምኑበትን በመቃወም ረገድ መታወቅ ጀመሩ:: ይህ አዝማሚያቸው ግን የነበሩት ባለስልጣናት አላስደሰተም፤አንዳንዶቹም የግለሰቡ ግትር ባህሪ ስጋት ጫረባቸውና ከፖለቲካ ሹመታቸው ተነስተው ወደ ተቀጠሩበት የሆቴልና ቱሪዝም ኮሚሽን እንዲመለሱ አደረጉ::
የተመደቡበት ቦታ ግን እንደቀድሞው ስራ የሚበዛበት ባለመሆኑ ተሰላቹ፤ ያለስራ የመንግስትን ደመወዝ መቀበል አንገሸገሻቸው:: ስለሆነም እንደእሳቸው በሁኔታው የተሰላቹ ጥቂት ሰዎችን አሰባስበው በራሳቸው ተነሳሽነት እየተዘዋወሩ የሆቴሎችን ስራ መከታተል ያዙ:: ይህን ጥረታቸውን ያዩ የኮሚሽኑ ሥራአስኪያጅም በአዳማ ራስ ሆቴል ሥራ አስኪያጅ ሆነው እንዲሰሩ አደረጓቸው:: በመቀጠልም አስመራ በሚገኘው 11 ሆቴሎች በሚያስተዳድረው አምባይስራ ሆቴሎች አስተዳደር ሥራ አስኪያጅ ሆነው ተመደቡ:: ወቅቱ ሻቢያና ህውሃት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር አለመግባባት ላይ በመሆናቸው ወደአስመራ ላለመሄድ አመንትተው ነበር:: ይሁንና ከባለቤታቸው ጋር ተማክረው ወደ አስመራ ለመሄድ ወሰኑ:: አስመራ እንደሄዱ ግን በነበረው ጦርነት ምክንያት አብዛኞቹ ሆቴሎች ገበያ ተቀዛቅዞ ስለነበር እንደሌሎቹ ሆቴሎች ገቢ ማስገባት ቀርቶ ለሰራተኞችም
ከማዕከላዊ መንግስት በሚላክ ገንዘብ ነበር ደመወዝ ይከፈል የነበረው:: ይህንን ሁኔታ ለመቀየርም ብዙ ጥረት አደረጉ:: በዚህም ሆቴሎቹ ራሳቸውን እንዲችሉ ከማድረግ ያለፈ ስኬታማ ስራ መስራት ቻሉ::
ይሁንና የነበረው ጦርነት እየተባባሰ በመምጣቱ ደርግም በመውደቁ ሸሽተው ሱዳን ገቡ:: ብዙም ሳይቆዩ ወደአገራቸው ተመለሱ:: ይሁንና የሆቴሎች ኮርፖሬሽን በመፍረሱ ሁኔታዎች መቀያየር ጀመሩ፤ ስልጣኑን የተረከበው ኃይል እንደተራ አዲስ ሰራተኛ እንዲሰሩ በማድረጉ አልዋጥ ይላቸዋል:: በወቅቱ ደግሞ ከ25 ዓመት በላይ ያገለገለ ጡረታ መውጣት ይችል ስለነበር በገዛ ፍቃዳቸው ጡረታቸውን አስከበሩ:: በአምስት የሆቴል ዘርፎች ከአቬየሽን ኮሌጅ ዲፕሎማቸውን ያገኙት እኚሁ ሰው ከመንግስት ስራ ራሳቸውን ካገለሉ በኋላ እጃቸውን አጣጥፈው አልተቀመጡም:: በተለያዩ የግል ሆቴሎች ተዘዋውረው በሥራአስኪያጅነት አገለገሉ:: ከዚሁ ጎን ለጎንም የኢህአዴግን ስርዓት በመቃወም ቀስተዳመና፥ ቅንጅት፥ አንድነትና ሰማያዊ ፓርቲዎች ውስጥ በመግባት ሲታገሉ ቆይተዋል:: በአሁኑ ወቅትም በኢዜማ ፓርቲ ውስጥ በአባልነት እየተሳተፉ ይገኛሉ:: ከዛሬው እንግዳችን ከአቶ ድንቁ ወልደማርያም ጋር በተለየዩ ወቅታዊና አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገናል:: እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል::
አዲስ ዘመን፡– አብዛኛውን የሕይወት ጊዜዎትን በሆቴል ሙያ ነው ያሳለፉት፤ ወደ ፖለቲካው አለም የገቡበት የተለየ ምክንያት ይኖርዎት ይሆን?
አቶ ድንቁ፡- እንዳልሽው አብዛኛውን ጊዜዬን ያሳለፍኩት በሆቴልና ቱሪዝም ሙያ ቢሆንም ጎን ለጎን የፖለቲካ ትምህርት በመማሬ እንዲሁም ከመሰረቱም ለፖለቲካ ፍላጎት የነበረኝ በመሆኑ የተለያዩ ፓርቲዎችን መስርቻለሁ:: ኢህአዴግንም በመቃወም ንቁ ተሳትፎ ሳደርግ ቆይቻለሁ:: በነገራችን ላይ ከሆቴል ስራ ከመውጣቴ በፊት ነው ቀስተደመና ፓርቲን ከአንዳንድ ሰዎች ጋር በመሆን የመሰረት ነው::
ግን ለዚህች አገር አንድ ፓርቲ የትም የማያደርስ በመሆኑ መድብለ ፓርቲ ስርዓት መምጣት አለበት በሚል በሕብረት ለመስራት ያሉትን አራት ድርጅቶች በማሰባሰብ ቅንጅት ተፈጠረና እኔም የቅንጅት አባል ሆኜ በምርጫ 97 ተወዳደርኩ:: እኔን ወደ ተቃውሞው ጎራ ያስገባኝ የብሶት ጉዳይ ብቻ አይደለም:: በደል ቢኖርብኝም ብሶት ያላቸውን እየፈለኩ በብሶት መንፈስ ፓርቲ ውስጥ አልገባሁም:: ይልቁኑ የፖለቲካ አቋምና ፍላጎት ስለነበረኝ ነው:: ደግሞም ከፖለቲካ ህይወት ውጭ መውጣት የለብኝም የሚል አላማ ነበረኝ:: በተለይም በዚህች አገር ውስጥ ዲሞክራሲና እኩልነት መስፈን አለበት የሚል አቋም ስለነበረኝም ጭምር ነው::
በነገራችን ላይ በምርጫ 97 ወረዳ 23 በተወዳደርኩበት ጊዜ በከፍተኛ ድምፅ ነው ያለፍኩት:: ይሁንና ሕወሓት ይህንን ሁኔታ መቀበል ባለመቻሉ ያለምንም በደል በምርጫው በማሸነፌ ብቻ ለእስር ዳርጎኝ ነበር:: የሚገርምሽ ከሌሎቹ የቅንጅት አባላት በተለየ ሲፈታኝም ሆነ ሲያስረኝ ይሄነው የሚለው የክስ መዝገብ አልተከፈተብኝም ነበር:: መጀመሪያ እንዳልወዳደር ማድረግ ይችሉ ነበር፤ ከተወዳደርኩና ካሸነፍኩ በኋላ ማሰር ግን ተገቢ አልነበረም:: ምክንያቱም ስልጣን ወይም የምክር ቤት መቀመጫ ውርስ አይደለምና ነው:: ከእስር ከተፈታሁ በኋላም መሪዎቻችን ታስረው እኛ ዝም ብለን መቀመጥ ስላልቻልን አንድነትን መሰረትን:: በወቅቱ ከነበሩት ድርጅቶች መካከል የተሻለ ጥንካሬ የነበረው ፓርቲ አንድነት ነበር:: በዚህ ምክንያት ሕወሓት ኢህአዴግ አሁንም ይገዳደረኛል ብሎ ስላሰበ አንድነት እንዲፈርስ አደረገና ለሌላ አካል ሰጠ:: እኛም ወጣን:: ከዚያ በኋላ አስቀድሞም ሰማያዊ ፓርቲ የአንድነት አንጃ ስለነበር እነየሽዋስ አሰፋ ከስር ተፈትተው እንድንገባ ሲጋብዙን ምንም ሳናንገራግር ተቀላቀልናቸው:: አንድ አመት ያህል እያደራጀን ከቆየን በኋላ ኢዜማ ተመሰረተ ወዲያውም ወደ ኢዜማ ገባን::
አዲስ ዘመን፡– ወደ ኢንተርቪው ስንገባ ባለፉት 27 ዓመታት ዜግነታችንን አጥተን ነው የኖር ነው የሚል ሃሳብ ሰንዝረውልኝ ነበር፤ ይህን ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
አቶ ድንቁ፡– ይህንን ያልኩሽ እንደምታስታውሽው ባለፉት 27 ዓመታት ብዙዎቻችን በትውልድ መንደራችን ስያሜ እንጂ ኢትዮጵያዊ ዜግነታችን እንድንተዋወቅ አልተፈቀደለንም ነበር:: ኢትዮጵያ ብለን ደፍረን እንዳንናገር ጫና ተደርጎብን በመኖራችን ምክንያት ብዙዎቻችን ዛሬም የሌላ አገር ዜጋ የሆንን ያህል ስሜት ይሰማናል:: በመታወቂያችን ሳይቀር የብሄር ማንነት ማንጠልጠያ ተሰጥቶን እንጂ በድፍረት በኢትዮጵያዊነታችን ኮርተን እንድኖር አልተደረግንም ነበር:: ኢትዮጵያዊነት ጨርሶ ቦታ አልነበረውም ::
አዲስ ዘመን፡–ብዙውን ጊዜ ጉራጌ ለመብቱ የማይታገልና የፖለቲካ ንቃተህሊና የለውም ብለው በድፍረት የሚናገሩ ሰዎች አሉ፤ በእርሶ አስተሰሳብ የጉራጌ ማህበረሰብ የፖለቲካ ንቃተ ህሊና የለውም ብለው ያምናሉ? ከሆነስ ለምን?
አቶ ድንቁ፡– እርግጥ ነው አብዛኛው የጉራጌ ማህበረሰብ አጠቃላይ ሁኔታው ወደ ንግድ ያመዝናል፤ ግን ማንም ሰው ከፖለቲካ ውጭ መሆን አይችልም:: ተወደደም ተጠላም ፖለቲካው በአንድም በሌላ ይነካዋል:: ፖለቲካ በእያንዳንዱ ሰው ልቦና ውስጥ ያለ ጉዳይ ነው:: ፖለቲካ ማለት እኮ አስተዳደር ማለት ነው:: ጉራጌም ሆነ ሌላው ከዚህ አስተዳደር ማምለጥ አይችልም:: በሌላ በኩል ግን ማንኛውም ሰው በህይወቱ የሚያዋጣውን ይመርጣል፤ አንዳንዶች ባለው ነገር ሊረኩ ይችላሉ፤ ሌሎች ደግሞ አይበቃኝም ብለው የሚተጉ ሊሆኑ ይችላሉ:: ስለዚህ የትልም ጉዳይ ይመስለኛል:: በአጠቃላይ የፖለቲካ ባህላችን ከነበረው ሁኔታ አንፃር ሲታይ ሁሉም ፖለቲከኛ ሊሆን አይችልም:: ጉራጌን እንደማህበረሰብ ስታይው በንግድ ዘርፍ ላይ ብቻ እንዲያተኩር ያደረገው ምክንያት ሊኖር ይችላል:: ለምሳሌ የጉራጌ ህብረተሰብ የሚኖርበት አካበቢ የመሬት ጥበት አለ:: አርሶ ለመኖር የሚያስችል የእርሻ መሬትም የለውም:: ስለዚህ የሚያዋጣው ንግዱ ይመስለኛል:: ለዚህ ነው እንጂ ንግድ ብቻ ነው የአንተ ስራ ተብሎ የተሰጠው አይደለም:: ይሁንእንጂ የጉራጌ ማህበረሰብ ወደ ንግድ ማድላቱ የፖለቲካ አቋም የለውም ለማለት አያስደፍርም:: ወታደራዊ ሞራልና ጀብዱ የለውም ማለትም አይደለም:: በእርግጥ ይህ ማህበረሰብ ሰላማዊ ህዝብ ነው፤ ከሁሉም ጋር ተቻችሎ መኖር የሚወድ ነው፤ ደፍሮ ከገባበት ግን ውጤታማ ነው:: ምንአልባት በፖለቲካው ዘርፍ ገብቶም እንደሙያ አድርጎ አይወስደው እንጂ ከማንም ያላነሰ ጠንካራ ህዝብ እንደሆነ አውቃለሁ::
በሌላ በኩል ያነሳሽው የንቃተ ህሊና ጉዳይ ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ነው ባይ ነኝ:: ምክንያቱም ንቃተ ህሊናው የሚዳብረው ከባህሉም ጋር የሚተሳሰር ሊሆን ስለሚችል ነው:: ከዚህ አኳያ ወደ ሰሜን አካባቢ ያሉ ማህበረሰቦች ጋር ማነፃፀር አይቻልም:: ምክንያቱም ገዢው መደብ ከሰሜን አካባቢ የመጣ እንደመሆኑ ትምህርትም የተስፋፋው ከላይ ወደታች በመሆኑ ወደታች ስትወርጂ ንቃተህሊናው የዳበረ ህዝብ ማግኘት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል:: ምክንያቱም ንቃተህሊና በትምህርት የሚዳብር በመሆኑ ነው:: ይህም ቢሆን ግን የንቃተ ህሊና ችግር ስላለ ነው ብዙውን ጊዜ ጉራጌ ፖለቲካ ውስጥ የማይገባው ብሎ መደምደም አይቻልም::
አዲስ ዘመን፡– አንዳንድ ሰዎች የጉራጌ ማህበረሰብ ብሔርተኝነት የሚያቀነቅን ፓርቲ በስሙ የሌለ መሆኑ እንደሌላው ብሔረሰብ ተጠቃሚ አልሆነም ብለው ያምናሉ፤ እርሶ በዚህ ሀሳብ ይስማማሉ?
አቶ ድንቁ፡– እኔ እንደማምንበት ተቆርቋሪነት የማጣት ችግር ብቻ አይመስለኝም:: ምክንያቱም ጉራጌ በታሪኩ እስካሁንም ከህዝብ ጋር አብሮ የሚኖር፤ የትም ቦታ ሄዶ የሚሰራ፤ ራሱን በአንድ ቦታ አጥሮ የማያስቀምጥ ህብረተሰብ ነው:: ሁሉም ጋር በጉልበቱ፤ በእውቀቱና በችሎታው ሰርቶ መኖር የሚችል ህዝብ ነው:: ስለዚህ ያ የሰራበት ቦታ ሁሉ የእኔ ነው ብሎ ስለሚያምን ከማንም በላይ ኢትዮጵያዊ መሆንን ምርጫው ያደረገ ማህበረሰብ ነው:: አስቀድሜ እንደነገርኩሽ የመሬት ጥበት መኖሩ፥ አካባቢው የሚያፈራው ሃብት ውስን በመሆኑ ወደተለየዩ አካባቢዎች በመሄድ በታታሪነትና ስራ ሳይንቅ ይሰራል:: ስለዚህ ጉራጌ በሰራበት ቦታ ሁሉ አገሬ ብሎ የሚኖር ሕዝብ ነው:: እኔ አጠንክሬ መናገር የምፈልገው ነገር ጉራጌ እኔ ብቻ ነኝ ባይ አለመሆኑንና ሁሉም የእኔ፤ እኔም የሁሉም ነኝ ባይ መሆኑን ነው:: በስሙ የተመሰረተ ፓርቲ ባለመኖሩ ከሌላው ህዝብ በተለየ በደል ደርሶበታል ብዬ አላምንም:: በነገራችን ላይ በርካታ ፓርቲ ያላቸው ብሔረሰቦችም የተለየ ተጠቃሚ ሆነዋል ብዬ አላምንም::
አዲስ ዘመን፡–እንደሚያውቁት ከለውጡ በኋላ ደቡብ ክልል ስር ያሉ የተለያዩ ዞኖች የክልል ጥያቄ አቅርበው ሲዳማ ፍቃድ ሲያገኝ ሌሎቹ ደግሞ አለመፈቀዱ ቅሬታ መፍጠሩ ይሰማል፤ እርስዎ ይህንን ጉዳይ እንዴት ያዩታል?
አቶ ድንቁ፡– እኔ ሌላው ክልል ስለሆነ እኔም ክልል መሆን አለብኝ የሚለው አስተሳሰብ ጠቃሚ አይደለም ብዬ ነው የማስበው:: ከማንአንሼ የሚባለው አስተሳሰብ ጥሩ ውጤት ያመጣል ብዬ አላምንም:: ላለፉት 27 ዓመታት በብሔር ተለያይተን መኖራችን በራሱ በአገር ደረጃ መከፋፈል እንዳመጣብን እሙን ነው:: በነገራችን ላይ ብሔርተኛ የሚለው ቃል በራሱ ትክክለኛ ትርጓሜ አለው ብዬ አላምንም:: ከዛ ይልቅ ጎሰኝነት ብለው እመርጣለሁ:: ብሔርተኝነት የሚለው አስተሳሰብ ለስልጣን እንዲያመችና ይህች አገር እንደአገር ቀጥላ እንዳትሄድ በዘውጌ ወይም በጎሰኝነት ለመለያየት የተሸረበ ሴራ ነው:: ከልለው የተለያየ አገር ፈጠሩብን:: ይህ አስተሳሰብ አገር የማሳጣት ዓላማ ያዘለ ነው:: ከ 27 ዓመታት በላይ የዘሩትና ስር የሰደደ አጥፊ አስተሳሰብ በመሆኑ ነው አገሪቱ በሚገባት ልክ ልታድግ ያልቻለችው:: በእርግጥ እንዲያድጉ የተፈለጉ አካበቢዎች አድገዋል፤ ዘረፋም ተፈፅሟል:: አንድ ወገን ተጠቃሚ ሌላው ተበዳይ ሆኖ ቆይቷል::
በመሆኑም ይህ የፌደራሊዝም ስርዓት ውጥንቅጣችንን አውጥቶን ኢትዮጵያዊ ማንነታችን አሳጥቶን ሳለ እንደጥንታችን ወደአንድነታችን ተመልሰን ማምጣት አለብን ማለት ሲገባን ዛሬ ላይም እነሱ በቀደዱልን ቦይ መፍሰስ አለብን ብዬ አላምንም:: እኔ እንዳውም ክልል የሚለው አስተሳሰብ ራሱ መቅረት አለበት ባይ ነኝ:: ወደትናንትናው ስርዓት መመለስ ካልሆነብን ክልል የሚለውን ቃል ራሱ በሌላ ስያሜ ብንቀይረው ደስ ይለኛል:: በእኔ እምነት ክልል ሰጪም ሆነ ነሺ የሚሆን አካል ሊኖር አይገባም:: እኔ በኢትዮጵያዊነቴ ነው የማምነው፤ ጉራጌ ክልል ይሁን ካልኩ ተበትኖ ያለው የጉራጌ ተወላጅ ምን ሊሆን ይችላል? ሁሉም ህዝብ የየራሱ ዋሻ ውስጥ ሲገባ መሬቱ ምን ሊሆን ይችላል?:: ሀገራችንን ባለችበት ሁኔታ የክልል እንሁን ጥያቄ መነሳት አልነበረበትም ባይ ነኝ:: እንደእኔ እምነት ደቡብ ክልል ባለበት ቆይቶ ህዝብ የሚሻለውን እንዲመርጥና ወደ አንዲት ኢትዮጵያ ለመምጣት ወቅቱን መጠበቅ ነበረብን::
አዲስ ዘመን፡– ይህን ሲሉ በዚህ ወቅት ለሲዳማም ቢሆን የክልልነት መብት መሰጠት አልነበረበትም ለማለት ፈልገው ነው?
አቶ ድንቁ፡– አዎ፤ እሱ አንድ ነገር ነው፤ ደቡብ በጠቅላላ አራትና አምስት ድሪቶ ማልበስ አያስፈልግም::እያወራን ያለነው ስለኢትዮጵያዊነትና ስለአንድነት ነው:: ምርጫ ከተካሄደ በኋላ ዋናው ችግራችንን የሆነውን ሕገመንግስት ማሻሻል ሊቀድም ይገባ ነበር:: በሕገመንግስቱ ውስጥ የተሸነቀሩ ነገሮች ናቸው ችግር የፈጠሩብን:: እንደአገር ሁሉም በየራሱ በደል ደርሶበታል:: ስለዚህ ዲሞክራሲን የምናመጣው በተናጠል አይደለም:: ከዚያ ለመላቀቅ ተብሎ ክልል እንሁን ካልን ከአንድ አገር ወደ ብዙ አገሮች እንሸጋገራለን ማለት ነው:: በመሆኑም አገር እንዳለ ሆኖ ለአስተዳደር እንዲመች አድርጎ መቅረፅ ይቻላል፤ በዚህ መልኩ መከፋፈሉ ከቀጠለ ኢትዮጵያ የምትባለውም አገር ላትኖር ትችላለች:: በእርግጥ አሁን ባለው ሕገመንግስት መሰረት ለሲዳማ መሰጠቱ ልንቀበለው እንችል ይሆናል፤ ግን በዚህ ሁኔታ መቀጠል የለበትም:: አስቀድመን ህገመንግስቱን ማሻሻል አለብን፤ ለዚህ ደግሞ በህዝብ የተመረጠ የህዝብ ተወካይ ሊኖረን ይገባል:: አሁን ባለው ሁኔታ ሕገመንግስቱ ቀድሞውንም የተቀረፀው አገር ለማፍረስ ስለሆነ ይህን አፍራሽ ሕገመንግስት ማሻሻል ይገባናል::
አዲስ ዘመን፡– እርሶ ይህንን ቢሉም እንደደቡብ በአንድ መጨፍለቅ የሌላውን ያህል ተጠቃሚ አልሆንኩም፤ ተበድያለሁ የሚል ማህበረሰብ አለ፤ በሌላ በኩል እርሶ የሚሉትን መዋቅር እውን ማድረግ ማለት አሀዳዊ ስርዓትን መመለስ ነው ብለው የሚከራከሩ አሉ፤ እነዚህን ጥያቄዎች በምን መልኩ ነው ማስተናገድ የሚቻለው ይላሉ?
አቶ ድንቁ፡– እውነት ነው፤ ይሄ ግን በአባባል ደረጃ ነው:: ግን ደግሞ የነበረው ስርዓት እኮ እንድንከፋፋል ያደረገ ነው፤ ለተመረጡ ብሄረሰቦች ክልል የመሰጠቱ ጉዳይ አንዱን ወዳጅ ሌላውን ጠላት ከማድረግም የመነጨ ነው:: በነገራችን ላይ አሀዳዊነት ቢኖርም ችግር አልነበረውም፤ ልክ እንደ ትልቅ ኃጥያት ልንቆጥረው አይገባም::ምክንያቱም አሀዳዊ ሆነው የበለፀጉ ብዙ አገሮች በአለም ላይ በመኖራቸው ነው:: በመሆኑም ዲሞክራሲውን ማስፋት ነው እንጂ በድፍኑ አያስፈልግም ማለት ውሃ አያነሳም:: ይሁንና እኛ አገር ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር የፌደራል ስርዓቱ እንዳለ ሆኖ ለአስተዳደር በሚመች ሁኔታ መቅረፅ ያስፈልጋል ባይነኝ:: ትናንት የነበረው ስርዓት አድሎ ስላለበት እኮ ነው ወደአንድነታችን እንመለስ የምንለው:: የተጠቀሙ እንዳሉ ሆነው ትናንትም ዛሬም እየተበደሉ ያሉ ህዝቦች አሉ::
ስለዚህ በደሉን ሊያስቀረው የሚችለው ፍትሃዊ ምርጫ ተካሂዶ ህዝባዊ መንግስት ሲኖር ነው:: ዲሞክራሲ ይኑር ነው እየተባለ ያለው እንጂ ትናንት ተበድያለሁ፤ ዛሬም ራሴን ችዬ ልውጣ ማለት አይቻልም:: አስተዳደሩ እኩልና ፍትሐዊ ክፍፍል ኖሮ በህግና በደንብ የተጠበቀች አገር እንድትኖረን ማድረግ እንችላለን:: እንዳውም መገንጠል የሚለው ሃሳብ በሕገመንግስቱ ውስጥ የሰነቀሩት በእውነት ለጠየቀው ሁሉ ለመስጠት ሳይሆን የሕዝብን ስሜት ለማማለልና ለመከፋፈል እንዲመቻቸው ነው:: በዚህ አገር ያለው ሃብት የሁሉም ነው ሊሆን የሚገባው:: ደግሞም እኔ የጉራጌ ተወላጅ በመሆኔ ብቻ ሕዝቡን ወክዬ ክልል እንሁን ማለት አልችልም:: የህዝቡን ፍላጎት ገና አልተረዳሁትም፤ እኔ የምነግርሽ የራሴን ስሜት ብቻ ነው:: እንደምታውቂው ደግሞ ባለፉት ዓመታት በሕዝብ ስም ሲነገድ ነው የተኖረው::
አዲስ ዘመን፡– ሰሞኑን በህወሓትና በብልፅግና መካከል ያለውን አለመግባባት ለመፍታት የአገር ሽማግሌዎች የጀመሩት ጥረት እንዴት ያዩታል?
አቶ ድንቁ፡– እርቅ የሚመጣው ከሁለቱም ወገን ፍላጎት ሲኖር ነው:: ግን አንዱ እሺ አይልም ተብሎ መተውም አለበት ብዬም አላምንም:: ለምሳሌ እኔ ካሉኝ ልጆች መካከል አንዱ በእኔም ሆነ እርሱ ጥፋት ከቤት ቢወጣና ጎዳና ተዳዳሪ ቢሆን እመክራለሁ፤ አስመክራለሁ እንጂ ይህን በማድረጉ ልጅነቱን ልነፍገው አልችልም:: ምክንያቱም እውነታው እሱ በመሆኑ ነው:: ብሔራዊ እርቅ ማለት የግለሰቦች ጉዳይ ሳይሆን የአገር ጉዳይ ነው:: በዚህች አገር ላይ በእኩልነት፥ በዲሞክራሲና በሰላም ለመኖር አገሪቱ የሁላችንም እንድትሆን መግባባት መቻል አለብን:: ከተግባቡ በኋላ ነው እርቅ የሚመጣው:: ዛሬ ላይ አንደኛው ወገን እሺ ባይልም ሁኔታው ሲገባውና ሲረዳ ወይም አቅም ሲያንሰው ሊመጣ ይችላል:: በብዙ ምክንያት ከትናንት ዛሬ ይሻላል:: አሁን ስለወያኔ ስናስብ የዚህ አገር ምስቅልቅል የመጣው እሱ አገሪቱን ተረክቦ ማስተዳደር ከጀመረ ወዲህ እንደሆነ ይታወቃል:: ይህን ሁሉ አድርጎ ግን የበደለው ሁሉ ይቅር ተብሎ ወደ ሰላም ለመምጣት ፍላጎት ላይኖረው ይችላል:: ይሁንና አሁን አሁን ከራሱ የወጡ ሰዎች ፈንቅለው ሊጥሉ ጊዜያቸው ደርሷል:: ይህ ሁኔታ ሲያይል በሰላም ለመኖር አቅሙ ሲከዳው፤ እንደትናንት መኖር ሳይችል ሲቀር መለወጡ አይቀርም::
ስለዚህ ይህች አገር እንድትቀጥል ከተፈለገ በቀልና ቂማችንን እርግፍ አድርገን መተው አለብን:: በመንፈሳዊውም አለም ሆነ በሳይንሱ ረገድ ትናንት ላይመለስ ሄዷልና ዛሬን በዛሬ መነፅር ቃኝተን ለነገ ጥሩ ነገር ለማምጣት መትጋት ነው ያለብን:: በነገራችን ላይ በሰላም አብሮ መኖር እሴታችን የኖርንበት እንጂ አዲስ ነገር አይደለም:: ቂምና በቀል መቆም አለበት ማለት ስንጀምር ውስጣችን ንፁህ መሆን አለበት:: ጠላት የሚለው አስተሳሰብ መጥፋት ይገባል:: ወያኔ ጠላታችን አይደለም፤ ወንድማችን እንጂ!:: እንደአገር ዜጋ ነው:: ሊያጭበረብረን ይችላል እንጂ ልንክደው አንችልም:: ይህም ሲባል እኛም በደል የለም ማለት አይደለም:: ሁላችንም ጋር ያለው በጠረጴዛ ዙሪያ መፈተሽና መዳኘት አለበት:: ሁልጊዜ በጠላትነት ተፈራርጀን እንኪያሰላምታችንን የምንቀጥል ከሆነ ለዚህች አገር ጥሩ ነገር ልናመጣ አንችልም::
በእርግጥ ግፍ ከተሰራ ቁጭትና ሃዘኑ እንዲሁ ይጠፋል ማለት አይደለም:: በህግ መጠየቅ የሚገባው ጉዳይ ለህግ ማቅረብ ይገባል:: የእኛ ዋነኛ ችግር ገንዘብ አይደለም:: እነሱ የዘረፉት አምጡ ብንላቸው አሁን ላይ ከየትም ሊያመጡት አይችሉም፤ አሽሽተውታል:: ስለዚህ ሆደ ሰፊ ሆነን ነገሮችን ማየት ይገባናል:: የባይተዋርነት ጥያቄ ሊነሳም አይገባም:: በዚህ ረገድ በመንግስት በኩል የተያዘው ነገር ጥሩ ይመስለኛል:: እለት በእለት የሚደረጉትን ነገሮች ፈልገን አይደለም የምንደግፈው:: የእኛ አላማነው ብለን የተነሳንበትን ጉዳይ በመንግስት ሲተገበር በማየታችን ነው:: በምንስማማበት ጉዳይ ላይ ተቃዋሚ ስለሆንን ብቻ መቃወም አይገባንም:: ሲጣመም ማቅናትም ይገባናል:: ልዩነቶቻችንን እያጎሉ እለት በእለት የሚያጋጩን ሰዎች ወንበር ናፋቂዎች እንጂ የእኛ ተቆርቋሪዎች አለመሆናቸውን ጠንቅቀን እናውቃለን:: በህዝብ ስም እየነገዱ ነው:: ለዚህች አገር የፈሰሰ ውሃ ያላቀኑ ፖለቲከኞች ከውጭ በሚያገኙት ድጎማ ህዝብ እያጋጩ ለህዝብ ቆሜያለሁ ሊሉን አይችሉም:: እርቅ የሚመጣው በመቻቸል በመተሳሰብ ቁጭ ብሎ በመወያየት ብቻ ነው:: የተበላሸውን ግንኙነት ማደስ ይገባናል:: ቀና ነገር በመነጋገር ቁጭ ብሎ በመወያየት ሊፈታ ይችላል:: ምክንያቱም ችግሩ ያለው ግንኙነታችን በመበላሸቱ ነው:: የሚያገናኘን ድልድይ ተሰብሯል፤ እንጠግነው:: ወይም እንቀይረው::
አዲስ ዘመን፡– ስለዚህ ሽምግልናው ተስፋ ይኖረዋል የሚል አቋም ነው ያለዎት?
አቶ ድንቁ፡– እንዳልሽው እኔ የተወሰነ ጥርጣሬው አለኝ:: ነገር ግን ተስፋ ይኖራል ብዬ አምናለሁ:: እዛ አካባቢ ያለው ህብረተሰብ የመብት ተቆርቋሪ ሲሆን፤ ነፃነቱን ሲፈልግ ሕወሓትን ዳር አውጥቶ ያቆማዋል የሚል እምነት አለኝ:: ሕወሓትም አቅም ሲያንሰውና ከሕዝብ ሲነጠል የግድ መታረቁ አይቀርም:: ሕወሓት ሕገመንግስቱን የቀረፀው፥ በመንግስት የአስተዳደር ስልጣን ላይ የበላይነቱን ይዞ የቆየ በመሆኑ ዛሬ ፈልጎ እኮ አይደለም እዛ የተወሸቀው:: ይታረቃሉ፤ አይታረቁም የሚለውን ነገር ምንአልባት በሂደት የምናየው ነገር ቢሆንም አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ግን ሕወሓትን እንደነበረው ሊያቆየው የሚችለው አይደለም:: ለምሳሌ መዋቅሩን ብንመለከት ቅድመ ኢህአዴግና ድህረ ኢህአዴግ ሁለቱም አንድ ናቸው፤ የስም ቅያሬ ነው የተደረገው:: ብልፅግና ኢህአዴግ ላይ የተመሰረተ ፓርቲ ነው:: መዋቅሩ ገና አልተነካም፤ ስለዚህ እንደብልፅግና ካድሬዎቹን መለወጥና መታረቅ አለባቸው:: ጥንካሬው እያየለ ሲመጣ፤ የቀድሞው መዋቅር እየከሰመ ሲሄድ እዛ ያለው ኃይል መዳከሙ አይቀርም:: መንግስት ምንአልባት ይህንን ስራ በውስጥ እየሰራ ሊሆን ይችላል:: እሱን ሆኜ መናገር አልችልም::
በሌላ በኩል ግን ሕወሓቶች ዛሬም በመንግስት መዋቅር ውስጥ ብዙ ሰዎች እንዳሏቸው ይታወቃል:: እነዚህ ሰዎች ዋና አላማቸው መቀሌ ያለውን ተቃዋሚ ኃይል እዚህ ሆኖ መደገፍ ነው:: ስለሆነም እነሱን እየደጎምን ለሆቴል መክፈያ መቀሌ መላክ የለብንም ባይ ነኝ:: ወደእዛ የሚላከው ሃብት መታየት መፈተሽ አለበት:: ለዚህ ደግሞ ምሰሶውን ማፍረስ ያስፈልጋል:: ግን ይህ ሲሆን በጥላቻ ላይ ተመስርተን መሆን አይገባም:: እነሱን ለምን ይህን ያህል እሹሩሩ ማለት ያስፈልጋል የሚል ነገር ከብዙዎች አንደበት ሲነገር እሰማለሁ:: በእኔ እምነት ግን የለውጡ ኃይል በመጀመሪያ አቅም አልነበረውም:: ደግሞም የወጣው ከኢህአዴግ ውስጥ ስለነበርም ውስጣዊ ትግል ነበረበት የሚል እምነት አለኝ:: እንዲያውም መፈንቅለ መንግስትም ለማካሄድም ተሞክሮ እንደነበር እናውቃለን:: ይህ ሁሉ ችግር ባለበት ቶሎ እርምጃ መወሰድ አለበት ብዬ አላምንም:: ይልቁንም ሁሉም ወደ ልቦናው መመለሱ ስለማይቀር ወደሰላም የሚመጣበትን መንገድ ማፋጠን አስፈላጊ እንደሆነ ነው የማምነው::
አዲስ ዘመን፡– በሌላ በኩል ከፍተኛ ወንጀል የሰሩ ሰዎችንም ይቅርታ ማድረግ የህግ የበላይነት ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ያስገባል ሲሉ የሚከራከሩ አሉ፤ በዚህ ረገድ የእርሶ ምላሽ ምንድን ነው?
አቶ ድንቁ፡- እውነት ነው፤ አሁን ባለው ሁኔታ ሕገመንግስቱና የወጡት አዋጆች የማስፈፀም ጉዳይ መኖር አለበት:: ነገር ግን የህግ የበላይነት የሚመጣው በአዲስ መልክ ከምንቀርፅበት ህገመንግስት ነው ባይ ነኝ:: ወደዚያ ለመሸጋገር አሁን ያሉትን ደንቦችና አዋጆችን የማስከበር ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል:: ማስከበር ማለት ደግሞ ማሰር ብቻ ማለት አይደለም:: መግደል ማለትም አይደለም:: እሱማ ትናንት ወያኔን ስንረግም የነበረበት ጉዳይ ነው፤ ዛሬ ደግሞ እኛም ወደእዛ እንመለስ እያልን እንዳይሆን ስጋት አለኝ:: አስቀድሜ ሆደ ሰፊ እንሁን ያልኩት ይህንንም ጭምር ታሳቢ በማድረግ ነው:: ለእነዚህ ወገኖችም የይቅርባይነት መንገድ ማሳየት ነው:: ለምሳሌ እኔ አሁን ያለው መንግስት በተለይም ዶክተር አብይ የሚከተሉት የይቅር ባይነት መንገድ አደንቃለሁ:: እኔ የእሳቸው ተከታይ አይደለሁም፤ የራሴ አቋም ያለኝ ሰው ነኝ:: ዶክተር አብይን የማደንቅበት፤ የምከተልበትና የማመሰግንበት ምክንያት ከዚያ አገር ግንጠላ፤ ከዚያ ከመበታተን አዳኑን ከምንላቸው ሰዎች ዋነኛው በመሆናቸውና ነው::
በተግባርም እያሳዩን በመሆኑ በንግግራቸውም እየገለፁልን በመሆኑ ነው:: ለምሳሌ ልጥቀስልሽ፤ ምክር ቤት ቃለመሓላ በፈፀሙበት ጊዜ ባደረጉት ንግግር 38 ጊዜ ኢትዮጵያዊነትን ያነሱ የመጀመሪያው መሪ ናቸው:: እኛ ከዚህ ወዲያ ምን እንፈልጋለን!?:: እንደአንድ አገር፤ እንደአንድ ህዝብ የምንኖርበትን መንገድ የሚያመቻችልን ከሆነ ምን ያስፈልገናል?::
አንድ ህዝብ ሲባል ግን የሁሉንም ማንነት ለመጨፍለቅና በአንድ ቋት ውስጥ ይገባል ማለት እንዳልሆነ ልብ እንዲባል እፈልጋለሁ:: ዛሬ እዚህ ሜዳ ላይ ቁጭ ብለን በነፃነት የምንናገርበትን ሁኔታ መፍጠሩ በራሱ ትልቅ ነገር ነው:: ግን ስላልገደለ፥ ስላላሰረ፥ ህግ ማስከበር አቅቶታል ሊባል አይቻልም:: ይህቺ የፖለቲካ ሽወዳ ነች:: ደግሞም ስም ማጥፋት ነው:: ይህንን የሚሉ ሰዎች ሞክረው አማካሪ ልሆን ብለው ያልተሳካላቸው ሰዎች ናቸው:: ከእኔ ወዲያ ሌላ ሰው የለም ባዮች ናቸው:: ውጭ አገር ተቀምጠው ገንዘብ ብቻ በመስጠት የሌላውን ወገን የሚያስገድሉ፤ ፅንፈኞች ናቸው:: ሰዎችን እየማገዱ እነሱ በተመቻቸ ኑሮ የሚኖሩ ሰዎች የሚያደርጉት ሴራ ነው:: ግን ከእሱ ጋር ቆመው ዋጋ ሲከፍሉ አንድም ቀን አላየናቸውም፤ ይልቁኑ ያሳደጉትንና በፈለጉበት ጊዜ ሁሉ ጃስ የሚሉት ውሻ ሲለቁ ነው የሚታዩት:: ይህ ግን አያዋጣም:: ውሻ መብላት ያለበት ሊሰርቅ የመጣውን ብቻ ነው:: ጤናማውን ሰው ከበላና መንደርተኛው በገዛ ሰፈሩ መኖር የማይችል ከሆነ ግን ሊገደል ወይም ሊወገድ ነው የሚገባው:: ስለዚህ ለዚህች አገር በባይተዋርነት የምናየው ህዝብ አይኑር:: በጥላቻ የምናየው ወገን ሊኖረን አይገባም:: በመጀመሪያ እያንዳንዳችን ከራሳችን መግባባት ስንችል ነው ሌላውን ማግባባት የምንችለው::
አዲስ ዘመን፡- በአጠቃላይ በአገሪቱ ላይ ያሉ የፖለቲካ ችግሮች በምን መልኩ መፈታት አለበት ይላሉ?
አቶ ድንቁ፡- ዶክተር አብይ ያለበት ችግር «ላም እሳት ወለደች እንዳትልሰው ፈጃት እንዳትተወው ልጅ ሆነባት» እንደሚባለው አይነት ነው:: በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ ያለው የጸጥታ ሁኔታ አሳሳቢ ነው::አብይ የመጣው ከኦሮሚያ ክልል መሆኑ ሰላም የማስከበር ስራ በሚሰራበት ጊዜ «ወንድሞችን እያስጨረሰነው» የሚባል ሃሜት አለበት:: በእኔ እምነት ግን እስከዛሬ ድረስ ሽማግሌ ተልኳል:: ትግዕስት ተደርጓል ባይ ነኝ:: ባይሳካለትም በእርቅ ለመፍታት ያደረገው ጥረት የሚናቅ አይደለም:: እነዚህ ሰዎች አሁን የገዛ ወገናቸውን በሽፍትነት እየገደሉ ነው፤ ሽፍትነት ደግሞ በሽምግልና ይፈታል ተብሎ የሚታሰብ ጉዳይ አይደለም:: ምንም እንኳን መግደል ከአንድ መንግስት የሚጠበቅ የመጀመሪያው ተግባር ባይሆንም ህዝብን ወደማጣት ሲመጣ ግን ጸጥታን ማስከበር ይገባል:: ከዚህ አኳያ እነ ዶክተር አብይ ይህንን ጉዳይ በጥንቃቄ የያዙት ይመስለኛል:: በዘላቂነት ግን ይህ ሃይል ትንኮሳውን የሚያቆምበትን መንገድ መቀየስና ማዳከም ያስፈልጋል:: የዚህን ኃይል ደጋፊ ኃይሎች ከፖለቲካው ማራቅም ይገባል:: የሚገርመው አስቀድሜ እንዳልኩሽ በአንድ በኩል እርምጃ ሲወስድ ነፍጠኛ ይሉታል፤ እርምጃ ሳይወስድ ሲቀር ህግ ማስከበር አቅቶታል የሚል ስሞታ ያሰማሉ:: እሱ የፈላ ውሃ ውስጥ እንዳለ መረዳት ይገባናል፤ ማገዝ ይገባናል:: አሁን ያገኘነውን ሁኔታ ማጣት የለብንም፤ አንዴ ካጣነው መቼም ይህች አገር አገር አትሆንም:: እስኪ ይታይሽ በአደባባይ በሚዲያ የሚሰደብ መንግስት የት ነበር? ይህ ሁኔታ ፍራቻ አይደለም ሰብዓዊነት ነው፤ ዲሞክራሲም ነው:: እኛ ወደዚያ ጎዳና ይወስደናል ብለን ስለምናስብ ነው ከጎኑ የቆምነው::
አዲስ ዘመን፡– ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ::
አቶ ድንቁ፡– እኔም እንግዳችሁ ስላደረጋችሁኝ አመሰግናለሁ::
አዲስ ዘመን ሰኔ 20/2012
ማህሌት አብዱል