አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ለውጥ በመደመር ፍልስፍና ላይ በመመርኮዝ የፖለቲካ ማሻሻያዎችን ያደረገና የንግድ ልውውጥን ለማገዝ የሚያስችል መሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሲውዘርላንድ ዳቮስ በመካሄድ ላይ ባለው 49ኛው የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም ላይ በመገኘት ወቅታዊ የሀገሪቱን ፖለቲካና ኢኮኖሚ አመልክተው በአደረጉት ንግግር፣ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ለውጥ የመደመር እሳቤን የያዘና በሦስት ምሶሶዎች የተመሰረተ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ከምሰሶዎቹ ቀዳሚው የዲሞክራሲ ምህዳሩን ማስፋት የሚለው ሲሆን፤ በዚህም የፖለቲካ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ወደሀገራቸው ገብተው በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ የማበረታታት እና የፖለቲካ እስረኞች የመፍታት ተግባራት የተከናወኑበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ማሳደግ ሁለተኛው ጉዳይ እንደሆነ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት የሀገሪቱን ዜጎች በተለይም ወጣቶችንና ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ዛሬ በዓለም ላይ ፈጣን ኢኮኖሚ እያስመዘገቡ ካሉ ሀገራት መካከል አንዷ እንደሆነች በመጥቀስ፣ ባለፉት አስር ዓመታት በአማካኝ ዘጠኝ በመቶ ዕድገት እንዳስመዘገበች አውስተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አሁን በሀገሪቱ እየተካሄደ ያለው የለውጥ ሂደት ኢኮኖሚውን የበለጠ ከማሳደግ አንጻር ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው በመግለጽ፤ ሴቶች ወደ አመራርነት መጥተው ሀገራዊ ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ የማድረግ ሥራ መሠራቱን አስታውሰዋል፡፡ በመንግሥት የካቢኔ አወቃቀር ውስጥ ሴቶችን በውሳኔ ሰጭነት በማሳተፍ ለውጡን ለማስቀጠል የሚያስችሉ እርምጃዎች መወሰዳቸውንም ገልጸዋል፡፡
ቁልፍ ቁልፍ ቦታዎችን ይዘው እየሰሩ እንዳሉ ለማሳየትም የመከላከያ ሚኒስቴርን ጨምሮ የንግድና ኢንዱስትሪ፣ የትራንስፖርት እና አዲስ የተቋቋመውን የሰላም ሚኒስቴር እየመሩ መሆናቸውን በመግለጽ፤ በአገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት ርዕሰ ብሄርና ሴት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት በሥራ ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
የምሥራቅ አፍሪካንና የአካባቢውን ሀገራት ትስስር ማጠናከር ሶስተኛው ምሰሶ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ትስስሩና ትብብሩ ለልማት ካለው አስተዋጽኦ በተጨማሪ የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ ረገድ ጉልህ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡
የንግድ ልውውጥ ማድረግን በመተመለከተ፣ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት ጽህፈት ቤት መገኛ እንደመሆኗ ከኢትዮጵያ ጋር የንግድ ልውውጥ ማድረግ ከፍ ያለ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ባለፉት አመታት ላስመዘገበቻቸው ኢኮኖሚያዊ ዕድገቶች የውጭ ባለሀብቶች ሚና ቀላል እንዳልነበረ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አሁን እየተደረገ ያለው የፖለቲካ ማሻሻያና የጠበቀ የንግድ ግንኙነት በሀገሪቱ እድገት የተሻለ ተስፋ መኖሩን የሚያመላክት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንትና አብሮ ለመስራት ምቹ ሁኔታዎች ያሉባት ሀገር በመሆኗም፣ ባለሃብቶች አጋጣሚውን እንዲጠቀሙበት ጠቅላይ ሚንስትሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 16/2011
ኢያሱ መሰለ