የሰው ልጅ በህይወት ዘመኑ ሶስት መሰረታዊ ፍላጎቶች እንደሚያስፈልጉት ይነገራል፤ ምግብ፣ መጠለያና ልብስ፡፡ ከነዚህ ሶስት ዋና ዋና ጉዳዮች ውስጥ ደግሞ ምግብ ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ ምክንያቱም የሰው ልጅም ሆነ ህይወት ያላቸው ነገሮች በሙሉ ያለምግብ ምንም ናቸውና፡፡
በዚህ የተነሳም ምግብ ለሰው ልጆች የሁሉም ነገር መሰረት ነው፡፡ ምንም እንኳ የበለፀጉ አገራት የምግብ ፍላጎታቸውን በማሟላታቸው ዋነኛ ጉዳያቸው መሆን ቢያቆምም በማደግ ላይ ላሉና ለደሃ አገራት ግን የምግብ ጥያቄ መሰረታዊ ነው፡፡ የምግብ ጥያቄ የሰላም እጦት ምንጭ ይሆናል፤ የፖለቲካ ፍላጎት ማራመጃም ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ የአፍሪካ አገራት ደግሞ ምግብ ከምንም ነገር በላይ የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም የምግብን እጥረትና ችግር በቅርበት ያውቁታልና፡፡
እንዳለመታደል ሆኖ ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብቷ የታደለች አገር ብትሆንም ከዚህ ሃብት ግን ተጠቃሚ አይደለችም፡፡ ለግብርና ምቹ የሆነ የአየር ፀባይና ለም አፈር ቢኖራትም የምግብ ፍጆታዋን ለመሸፈን አላስቻላትም፡፡ በዚህ የተነሳ ድህነትና ረሃብ መገለጫዋ ሆኖ ኖሯል፡፡
አገሪቱ ከድህነት ለመውጣት ከምታደርገው ጥረት ይበልጥ በውስጥ ሽኩቻ ውስጥ ሆና አንዴ ለልማት፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ለጥፋት በሚሰለፉ ሃይሎች መካከል በሚከሰቱ ግጭቶች ድህነትን ድል ማድረግ ተስኗት ቆይታለች፡፡ ከውጭ ወራሪ ሃይል ጋር የተደረጉ ጦርነቶች ሁሉ በድል ቢጠናቀቁም በድህነት ላይ የተደረጉ ጦርነቶች ግን እዚህ ግባ የሚባል ለውጥ አላመጡም፡፡
ወደኋላ መለስ ብለን የቅርብ ጊዜውን ታሪክ እንኳን ብንቃኝ የእርስ በርስ ግጭቶችና በየመካከሉ የተከሰቱ የድርቅና የረሃብ ትውስታዎች የዛሬ ዘመን ትውልድ ጭምር የሚያስታውሳቸው ናቸው፡፡ ለምሳሌ በ1966 እና በ1977 የተከሰቱ የድርቅ ችግሮች ያረገፉት የሰው ህይወት በዓለም ማህበረሰብ ጭምር መጥፎ ትውስታን ጥለው ያለፉ የታሪክ ጠባሳዎች ናቸው፡፡
በኢህአዴግ ዘመንም በርካታ የልማት ስራዎች መከናወናቸው የሚታወስ ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን በእነዚህ አመታትም ቢሆን በተለይ የምግብ ዋስትናችንን ለማረጋገጥ ሳንችል ኖረናል፡፡ በተለይ በመሰረተ ልማትና በማህበራዊ ዘርፎች በርካታ ስራዎችን እንደሰራ የሚመሰከርለት ኢህአዴግ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ አልቻለም፡፡ በዚህ የተነሳ በቀን ሶስት ጊዜ መብላት ቀርቶ አንድ ጊዜም መብላት የተሳናቸው
ዜጎች ቁጥር ቀላል እንዳልሆነ በተለያዩ አጋጣዎች የሚወጡ መረጃዎች ማሳያዎች ናቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ አፋቸው ከእህል ሳይገናኝ ወደትምህርት ቤት የሚሄዱ ተማሪዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በአዲስ አበባ በዚህ ችግር ውስጥ የነበሩና ብዙ ችግሮችን የተጋፈጡ ተማሪዎችና ወላጆች እንደነበሩ የምናስታውሰው እውነታ ነው፡፡
ከአምስት ሚሊየን በላይ ዜጎች እንዳሏት የሚታመነው አዲስ አበባ አብዛኞቹ ከእጅ ወደአፍ የሚኖሩ ናቸው፡፡ ከተማዋ የአገሪቱ ርዕሰ ከተማና የበርካታ ዓለምአቀፍ ተቋማት መቀመጫ እንዲሁም ከአንድ መቶ በላይ የሆኑ ኤምባሲዎች የሚገኙባት ከተማም ናት፡፡ ከዚህ አልፎ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ፣ የአውሮፓ ኮሚሽን ማዕከልና የተለያዩ ዓለምአቀፍ ተቋማት መቀመጫ በመሆን ትታወቃለች፡፡
እነዚህና መሰል ትላልቅ ተቋማትና ህዝብ ያለባት ከተማ የመሆኗን ያህል ግን በርካታ ትችቶች ይቀርቡባታል፡፡ በተለይ ለመኖሪያ ምቹ ያልሆኑ መኖሪያ ቤቶች እና ከ50 ሺ በላይ የጎዳና ተዳዳሪዎች እንዲሁም በልመና የሚተዳደሩ በርካታ ዜጎችና በእለት ገቢ ብቻ በርካታ ቤተሰብ የሚያስተዳድሩ ነዋሪዎች መኖሪያ መሆኗ የከተማዋ መገለጫ ነው፡፡
በከተማዋ ባለፉት 15 አመታት በመሰረተ ልማት እና በቤት ልማት ዘርፍ በርካታ ስራዎች ቢከናወኑም የበርካታ ዜጎች ዋነኛ ችግር የሆነውን ድህነት ከመቅረፍ አንጻር ግን አጥጋቢ አልነበሩም፡፡ ይልቁንም የመልሶ ማልማት ስራዎቹ በድህነት ውስጥ ሆነው ስራና መኖሪያቸውን በአንድ ላይ ላደረጉ የመሃል ከተማ ነዋሪዎች የስራ አጥነት ምንጮች መሆናቸውን በምሬት ይገልጻሉ፡፡ በዚህ የተነሳ ኢትዮጵያ በሁለት ዲጂት እድገት አሳይታለች ሲባል ብዙዎች በምፀት ሊመለከቱት ግድ ሆኖባቸዋል፡፡ ወደሰዎች ኪስ ያልገባ የቁጥር እድገት ለህዝብ ምንም አልነበረምና፡፡
ከሁለት አመት በፊት ወደስልጣን የመጣው የለውጥ ሃይል ታዲያ እነዚህን የህዝብ ችግሮች ለመቅረፍ በተለያዩ ዘርፎች ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህዝብን መሰረታዊ ፍላጎቶች ያገናዘቡ በርካታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ አንዱ ባለፈው አመት በአዲስ አበባ የተጀመረው የወላጅን ሸክም የመጋራትና የተማሪዎችን ችግሮች የመቅረፍ ስራ ነው፡፡
አስተዳደሩ የህዝቡን የኑሮ ሁኔታ ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የተማሪዎችን ሙሉ የመማሪያ ቁሳቁስና ዩኒፎርም የሸፈነበት ስራ ፤ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ለበርካታ ተማሪዎች ተደራሽ የነበረው የተማሪዎች ምገባ መርሃግብር ሌላው ተጠቃሽ ተግባር ነው፡፡
እነሆ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጀመረውን የፀረ ድህነት ተግባሩን አጠናክሮ በመቀጠል በተለይ ለችግረኛ ቤተሰብ ትልቅ ፋይዳ ያላቸው የልማት ስራዎችን ቀጥሎበታል፡፡ ከነዚህ ስራዎች አንዱ ደግሞ ትናንት ለምረቃ የበቃውና በሰዓት 80 ሺ ዳቦ የመጋገር አቅም ያለው ሸገር የዳቦ ፋብሪካ ነው፡፡
ዳቦ መሰረታዊ የሰዎች ፍላጎት ማሳያ ነው፡፡ በተለይ ልጆች ባሉበት ቤት ማለዳ ተነስቶ ዳቦ አለማቅረብ ድህነት ካልሆነ ሌላ ምንም ሊባል አይችልም፡፡ አብዛኛው የመዲናዋ ነዋሪዎችም ዳቦ መሰረታዊ ፍጆታቸው ነው፡፡ በዚህ የተነሳ በአማካይ ለአንድ ሰው አንድ ዳቦ ያስፈልጋል ብንል እንኳ በቀን አምስት ሚሊየን የሚጠጋ የዳቦ ፍላጎት እንደሚኖር መገመት ይቻላል፡፡ ነገር ግን በከተማዋ ይህንን ፍላጎት በአግባቡ ለማሟላት የሚያስችል በቂ ዳቦ ቤቶች አልነበሩም፡፡
ከዚያ አልፎ ደግሞ ያሉትም ዳቦ ቤቶች አንዳንዶቹ ከሚዛን በታች በማቅረብ፤ ከፊሎቹም በየጊዜው ዋጋ በመጨመር ህብረተሰቡን ሲያማርሩ ኖረዋል፡፡ ህብረተሰቡም እነዚህ ዳቦ ቤቶች ባማረሩት ቁጥር መንግስትን ሲያማርር ቆይቷል፡፡ ይህንን የህብረተሰቡን የዳቦ ፍላጎት ከመሰረቱ ለማሟላት ታዲያ የከተማ አስተዳደሩ በኢትዮጵያ የኢንቨስመንት ታሪክ ውስጥ ትልቅ አሻራ ከጣለው ሚዲሮክ ኩባንያ ጋር በመተባበር በሰዓት 80 ሺ ዳቦ መጋገር የሚያስችል ዳቦ ፋብሪካ ገንብቶ እነሆ ለ ምረቃ አብቅቷል፡፡
ይህን ዳቦ ቤት ለየት የሚያደርገው ደግሞ ለዳቦ ግብአት የሚሆነውን የስንዴ ምርት በአገር ውስጥ በማምረት አቅርቦቱን ለማሳደግና ከዚያም አልፎ የውጭ ምንዛሪን በማስቀረት መንግስት እያደረገ ያለው የፀረ ድህነት ዘመቻ ይበልጥ ለማቀጣጠል የሚያስችል መሆኑ ነው፡፡ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ከመሰረታዊ ፍላጎት መጀመር ሁሉንም ያማከለ እድገት ለማምጣት ወሳኝ ነውና መልካም ስራ እላለሁ፡፡
ይህ የዳቦ ፋብሪካ ለአዲስ አበባ ህዝብና ለአካባቢው ነዋሪዎች እንዲሁም ለከተማ አስተዳደሩም ልዩ ትርጉም ያለው ነው፡፡ በአንድ በኩል አስተዳደሩ በዚህ ደረጃ ለህዝቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ዳቦ ማቅረቡ ለህዝቡ በተለይ ዝቅተኛ የገቢ ምንጭ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ያለው ፋይዳ የላቀ ሲሆን፤ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይም የሚያሳድረው አወንታዊ ሚና የላቀ ነው፡፡ በመሆኑም እንዲህ አይነት የህዝብ መሰረታዊ ፍላጎቶች መሰረት ያደረጉ የልማት ስራዎች ወደፊትም ተጠናክረው ቢቀጥሉ ከድህነት ለመውጣት የተጀመረው ሩጫ አጭር እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 19/2012
ውቤ ከልደታ