እንደምን ከረማችሁ?
ዛሬ አዋጅ አለኝ፣ ስኖር መጠሪያዬ ስሞት መቀበሪያዬ ስለሆነችው፤ አውቃም ይሁን ሳታውቅ ለዘመናት ባይተዋር እንድሆን ስላደረገችኝ እማማ ኢትዮጵያ… በስተመጨረሻም ልጇ መሆኔን አምና በእቅፏ ስላስገባችኝ እና ያንተም የሁሉም ልጆቼ መጠጊያ ደሴት ነኝ ስላለችኝ እናት ሀገር የወጣን አዋጅ ላሰማችሁ መጥቻለሁ።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት የሙስሊም ሀገራት ተብለው ከሚታወቁት ማንኛውም ሀገራት በፊት ለሙስሊሞች መጠጊያ በመሆን በእስልምና ሃይማኖት ታሪክ ውስጥ ግንባር ቀደም ስፍራ የያዘች ሀገር ናት። ይህ ታሪኳ ግን ከጊዜ በኋላ ተረስቶ የአንድ ወቅት የተጨቆኑ ሙስሊሞች መጠጊያ የነበረች፣ የቸር ህዝቦችና ፍትኃዊ መሪዎች አምባ የነበረችው ሀገር የጨቋኞቹን ቦታ ወደ መያዝ ተሸጋገረች።
ይህ ሁኔታ በታሪክ ብቻ ሳይሆን አሁንም የሚስተዋል እውነታ እየሆነ መጣ። ሆኖም ግን ሙስሊሙ ማህበረሰብ ከሌላው የሀገሪቱ ወንድም ህዝቦች ጋር ያለውና የነበረው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ግን የመከባበር የመተዛዘንና የመዋደድ እሴት ላይ የተመሰረተ እንደነበር የማይካድ ሀቅ ነው። ይህ ለዛሬው ማንነታችን እርሾ የሆነን ጠንካራ የማዕዘን ድንጋይ ነው። ነገር ግን “ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ናት” የሚለው ቡርዣዊ አስተሳሰብ ቤተኛን ባይተዋር በማድረግ የሀገሪቱ ግማሽ ጎን የሆነውን ሙስሊም ኢትዮጵያዊ ዘመናትን ላስቆጠረው ህዝባዊና ሰላማዊ ትግል ሳይታክት እንዲሰለፍ አድርጎታል። ሰኔ 4/2012 ዓ.ም ግን የእኒያን ዓመታት የትግል ፍሬ ከአንድ ከፍታ ሆነን በኩራት እንድናይ እድል የሰጠችን ታሪካዊ ቀን ሆና ተመዝግባለች።
ከወደ ኋላ ስላለው ዳራ መለስ ስንል ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በየዘመናቱ በነበሩ ሥርዓቶች ሲደርስባቸው የቆየው የመብት ረገጣና የሃይማኖት ጭቆና ለውስጣዊና ውጫዊ ሃይማኖታዊና ፖሊቲካዊ እንቅስቃሴዎች ምክንያት ሲሆኑ ቆይተዋል። በተለይም በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የተከሰቱ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴዎችና ለውጦች ለኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የዘመናት ችግሮች ወሳኝ የትግል ሂደት ማሳያ መሆናቸውን ማስታወስ ይቻላል።
በዘውዳዊው የአገዛዝ ዘመን በኢትዮጵያ ሃይማኖትና መንግስት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ነበሩ። ለምሳሌ የ1948ቱን ህገ መንግስት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የመንግስት ሃይማኖት መሆኑዋን ይደነግጋል። ምንም እንኳን ለሌሎች ሃይማኖቶችም አንጻራዊ ነጻነትን የሰጠ ቢሆንም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጋር የሚነፃጸር ህጋዊ እውቅና ነበራቸው ለማለት ግን አያስደፍርም። የእስልምና ሃይማኖትን በሚመለከት በ1934 እና 1936 በወጡ የቃዲዎችና የናኢባ ጉባዔ ማቋቋሚያ አዋጆች በልማድ ሲሰሩ ለነበሩት የሸሪዓ ፍ/ቤቶች በግለሰባዊና በቤተሰባዊ ጉዳዮች ላይ የእስልምና ህግ በሚያዘው መልኩ እንዲሰሩ እድሉ ተፈጥሮላቸው ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ህጋዊ እውቅና በኋላ በወጣው በ1952ቱ የፍ/ብሔር ህግ ሳይካተት በመቅረቱ ለሙስሊሞች የተፈቀደው መብት እንደገና ተከልክሏል። በዚህም መሰረት በአዋጅ ቁጥር 165/1952 አንቀጽ 347 ላይ የሰፈረው ድንጋጌ ለሸሪዓ ፍ/ቤቶች ተሰጥቶ የነበረውን እውቅና የነፈገ ነበር፡፡ ምንም እንኳን ይህንን ህግ ተከትሎ በተቀሰቀሰ ህዝባዊ ቁጣ የአፄ ሀይለስላሴ መንግስት የፍትሀ ብሔር ህጉ ቀድሞ የነበሩ ህጎችን አልሻረም ብለው ህዝቡን ለማረጋጋት ቢሞክርም።
የኢትዮጵያዊ ሙስሊም ታሪክ ሲዳሰሰ ሰፊውን ምዕራፍ የሚይዘው ከውጭም ከውስጥም ጠላቶች ጋር የተደረገ ረጅም ትግል ነው። የኢማም አህመድ ሰፊ ትግል፤ የነሸኽ አህመድ ጉራቻ (ዳንዩል አወል)ሸኽ አህመድ ወሎና ጠለሀ ጃዕፈር ከአፄ ዩሀንስ ጋር የተደረገው ትግል፣ የነ ሸኽ መሀመድ ሳዲቅ የአፄሀይለስላሴ ባላባቶች ጋር ያደረጉት ሰላማዊ ትግል፤ የ1966ቱ የሙስሊም ተማሪዎችና ወጣቶች ንቅናቄ፣ የድምፃችን ይሰማ ትግል ወዘተ የሚያመሳስላቸው ከውጭ ሀይላት ጋር ብቻ ሳይሆን ከተላላኪያቸው ጋርም የተደረጉ ውስጣዊ ትግሎች መሆናቸው ነው።
አሁን በመጅሊስ ውስጥ ያለው የለውጥ ትግልም ያላለቀው የትግል ታሪካችን ቀጣይ ምዕራፍ የሆነ የሰለሞናዊው አስተሳሰብ አጋሮችና በዚህ አስተሳሰብ ተቃራኒ የቆመው የሙስሊሙ ማህበረሰብ መካከል የሚደረግ ትግል ነው። ወደ ታሪክ ተመልሶ የመጅሊስን ምስረታ ማየትና ሂደቱን መረዳት ዛሬ ያለውን ተጨባጭ የበለጠ ለመረዳት ያግዛል።
በአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግስት ላይ ሕዝባዊ የተቃውሞ ማዕበል ተጠናክሮ ቀጠለ። ሥርዓቱን ይፈራ የነበረው ሁሉ በድፍረት ለመብቱ መነቃነቅ ቀጠለ። ሕዝባዊው አመፅና ተቃውሞ ከየአቅጣጫው ተጠናክሮ ቀጠለ። ደርግም ሕዝቡ በከፊል ሥልጣኑን የነጠቀውን የአጼ ኃይለ ሥላሴን አስተዳደር ገርስሶ ለመጣል የሙስሊሙ ሰልፍም አጋዥ ሆኖታል። የሕዝቡ ጸረ-ኃይለ ሥላሴ አቋም የልብ ልብ ሰጠው። ጳጉሜን 4 ቀን 1966 ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከዙፋናቸው እንዲወርዱ በደርግ ተወሰነ። ታኅሳስ 14 ቀን 1967 በብሔራዊ ደረጃ ስለሚከበሩ በዓላት ዝርዝር መግለጫ ወጣ። የሙስሊሙ ትግል በከፊል ፍሬ ማፍራት ጀመረ። ኢስላማዊ በዓላትም ብሔራዊ በዓላት ሆነው ተቆጠሩ። “የሕዝብ በዓላት አዋጅ” የተሰኘ አዋጅ ወጣ።
ቀደም ብሎ በ1948 የወጣው አዋጅ ቁጥር ‹‹151/19481/15/9/1948 አ.151›› ተሻረ። በአዋጁ እውቅና ከተሰጣቸው አሥራ ሁለት በዓላት መካካል ሦስቱ የሙስሊሞች በዓላት ነበሩ። እነሱም ዒድ አል ፊጥር፣ ዒድ አል አድሃና የመውሊድ በዓላት ነበሩ። (የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ማኅደር ቁጥር 3432) ታኅሳስ 15 ቀን 1967 የዐረፋ /ዒደል አደሃ/ በዓል የሙስሊሙ የመጀመሪያው በዓል ሆኖ በብሔራዊ ደረጃ ተከበረ።
የአፄው ሥርዓት በሕዝቦች አብዮት ተገርስሶ የደርግ መንግሥት ሥልጣኑን ሙሉ በሙሉ ሲረከብ በ1966ዓ.ም ብሔራዊ ሃይማኖት የሚባል ነገር አከተመ። የመንግሥትና የሃይማኖት የጋብቻ ወረቀትም ተቀደደ። የሙስሊሙ በዓላት በራሱ በሙስሊሙ ትግል እውቅና አግኝተው ብሔራዊ በዓል ሆኑ። “በኢትዮጵያ የሚኖሩ እስላሞች” የሚለው የማግለያ አጠራርም “ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች” በሚለው ተተካ። በዚህም የተወሰኑት የሕዝበ-ሙስሊሙ ጥያቄዎች በትግሉ ተረጋገጡ። ለመጀመሪያ ጊዜ በብሔራዊ ደረጃ የሙስሊሙ በዓል ተከበረ። በሙስሊሙ በዓልም እንደ ክርስቲያኑ በዓል ሥራ ተዘጋ። ተማሪው ዒድን አክብሮ ዋለ። እንደ ከዚህ ቀደሙ በዒድ ቀን ፈተና መሰጠቱ አከተመ።
የመጀመሪያው የደርግ ሊቀመንበር የነበሩት ጄኔራል ሚካኤል አማን አንዶም በዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች ጉባዔ ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የኢትዮጵያ ሙስሊም ኅብረተሰብ ከአጠቃላይ የአገሪቷ ሕዝብ ውስጥ ግማሹን እጅ እንደሚሸፍኑ አምነው ልዩ እንክብካቤ እንደሚያስፈልጋቸው ይፋ ማድረጋቸውን አዲስ ዘመን ጋዜጣ በመስከረም ስድስት 1967 እትሙ ማስፈሩን ሙሐመድ ዩሱፍ ያዕቁብ “የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመከራና የስቃይ ታሪክ” በተሰኘው መጽሐፉ አስፍሯል።
ከደርግ ውድቀት በኋላ በመጣው አዲስ ሥርዓትም በግልጽ እንደሚታወቀውና በኢፌዴሪ ህገ መንግስት ላይ እንደሰፈረው ሁሉም ሃይማኖቶች እኩል ናቸው። የመንግስት የሚባል ወይም በመንግስት ልዩ ድጋፍ የሚደረግለት ሃይማኖት እንደሌለ ያስቀምጣል። መሬት ላይ ባለው አሰራር ግን አሁንም በአዋጅ የተቋቋሙ (ምዝገባና ፈቃድ የማያስፈልጋቸው) እና በምዝገባና ፈቃድ ብቻ ህጋዊ ሰውነታቸውን የሚያገኙ እንዳሉ መረዳት አያዳግትም። ይህ ሁኔታ ደግሞ በአማኞች ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ የፈጠረ ጉዳይ ነው። ለረጅም ዓመታት ህዝበ ሙስሊሙ ተቃውሞውን ሲገልጽ እንደቆየና ለሚመለከታቸው የመንግስት
አካላት ጥያቄዎቹን በተወካዮቹ በኩል ሲያቀርብ እንደነበር ይታወሳል፤ ምንም እንኳን አጥጋቢ ምላሽ ሳይሰጠው ቢቆይም።
ይህ የሙስሊሙ የመብት ትግል የአንድ ጀንበር ብቻም አይደለም። የዘመናት ብሶትና በደል፣ እንዲሁም ማነቃቃት ውጤት ነበር። ምንም እንኳን በወቅቱ የተነሱት ጥያቄዎች ሙሉ ለሙሉ ባይመለሱም ክስተቱ ሙስሊሙ አንገቱን ቀና እንዲያደርግና ለመብቱ መታገል እንዳለበት እንዲያውቅ አድርጓል። ሙስሊም መሆን መዋረድን ያስከትል የነበረው ያኔ አክትሟል። መብትም በትግል እንጂ በልመና እንደማይገኝ አሳይቶ አልፏል።
ከህዝበ ሙስሊሙ የዘመናት ጥያቄ አንዱ የሆነው በአዋጅ መቋቋም ህጋዊ ሰውነትን መላበስ ከፍተኛ መስዋዕቶችን ካስከፈለ በኋላ ምላሹን አግኝቷል። ለህዝበ ሙስሊሙ የዘመናት ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ከቃል የዘለለ በተግባር እንዲተገበር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያበረከቱት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የላቀ ምስጋና ይገባቸዋል።
ነገር ግን ይህ የህጋዊ ማዕቀፍ ድል ትክክለኛ ድል መሆን የሚችለው ድርጅቱን በትክክል ተቋማዊ ኃይል የተላበሰ ማድረግ ስንችል ብቻ እንደሆነ ሊታወስ ይገባል። ህጋዊ ማዕቀፉ መስተካከሉ ብቻ ስኬታማ አያደርገውም። ይልቁንም ብዙ ስራ ይጠብቀናል።
ከድል ወዲያ
በአላህ ፈቃድ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በአዋጅ እንዲቋቋም የተላለፈው ውሳኔ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቋል። ይህ ከ50 ዓመታት በላይ ሕዝበ ሙስሊሙ ሲያቀርበው የቆየው ጥያቄ ብዙ ትግል እና መስዋእትነት የጠየቀ ነበር። ቀደምት አባቶቻችን ሰፊ ልፋት ያደረጉበት፣ ለተለያዩ መንግስታት ጥያቄዎች ያቀረቡበት፣ የህዝበ ሙስሊሙን መሪ ተቋም የማስተካከል ትግል ግብግብ ብዙ ያስከፈለበት፣ በሂደቱም ብዙዎች የደሙለት እና የሞቱለት ህዝባዊ ጥያቄ አካል ነው። የትውልድ የትግል ቅብብሎሽ እና ረጅም ልፋት ውጤትም ነው።
ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ከረጅም ትግል በኋላም ቢሆን መሪ ድርጅታችንን በተራ የበጎ አድራጎት ድርጅት ፍቃድ ከሚተዳደር እና ባዕድ አካላት እንደፈለጉ ከሚጠመዝዙት ድርጅትነት አዋጃዊ ዕውቅና ወዳለው ተቋምነት የማሸጋገሩን ህጋዊ ማዕቀፍ ለማሳካት በመብቃታችን ሁላችንም እንኳን ደስ ያለን ለማለት እወዳለሁ።
መቋጫ
ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች አንገታቸውን ቀና እንዲያደርጉ መስዋዕትነት የከፋላችሁ ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ። ሆኖም ግን የመጅሊስ በአዋጅ መፅደቅ ማለት ሁሉም ነገር አብቅቷል ማለት አይደለም። ከሌሎች ወገኖች ጋር ትከሻ ለትከሻ ሆነን ለመቆም ብዙ ስራዎች ይጠበቁብናል።
በተጨማሪም አገራችን እኛን ትፈልጋለች። እኛም አገራችን ታስፈልገናለች። ተመልካች ሳይሆን ተዋናይ በመሆን ለአገራችን ማበርከት የቻልነውን እያበረከትን መብታችንን እየጠየቅን እያስከበርን መፃኢውን እድላችንን እናሳምራለን።
ድርሻችን የትግል፣ አካሄዳችንና ወቅቱ ቢለያይም አዋጅ ቁጥር 1207/2012 የሁላችንም ትግልና ልፋት ድምር ውጤት ነው። ስለዚህ ውጤት ከመሻማት ተራ ወጥተን መጅሊሱ የተሻለ ዘመናዊ አሰራርና አደረጃጀት ያለው ተቋም እንዲሆን ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል።
በነገራችን ላይ በ1966 ሙስሊም ወገኖቻችን መብታቸውን ለማስከበር ሰላማዊ ሰልፍ ባደረጉበት ወቅት በአንደኛው ምስል ላይ መፈክር ጭምር ይዞ በቀዳሚነት ጥያቄያቸውን አብሮ ሲጠይቅ የነበረ የክርስትና እምነት ተከታይ የነበረው ወጣት፣በዩኒቨርሲቲ ከመለስ ዜናዊ ጋር ለተማሪ ፕሬዚዳንትነት ሲወዳደሩ መለስ ዜናዊ የዚህን ወጣት የመከራከሪያ ጽሁፍ አቀራረብ በመመልከት በፍቃዱ ስፍራውን የለቀቀለት፣ ቀጥሎም የኦሮሞ ነጻነት ግንባር መሪዎች አንዱ የነበረው አቦማ ምትኩ ይገኝበታል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 19/2012
በሐሚልተን አብዱልአዚዝ