8ኛው የኢትዮጵያ የከተሞች ፎረም በጂግጂጋ ከተማ ከየካቲት 9 እስከ 14 ድረስ ‹‹መደመር ለኢትዮጵያ ከተሞች ብልጽግና›› በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር ተገለጸ።
የከተሞች ፎረም አብይ ኮሚቴ ሰብሳቢና የፌዴራል ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚንስቴር ሚንስትር ዴኤታ አቶ ካሣሁን ጎፌ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ የ8ኛው ከተሞች ፎረም ዝግጅት መከበር ዋና አላማው የከተማ ነዋሪዎችን፣ የመንግስትና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎና ትብብር በማጠናከር የከተሞች ልማት እንዲፋጠን ማስቻል ነው፡፡
ከተሞች ያላቸውን እምቅ አቅም በኢንቨስትመንት፣ በንግድ፣ በቱሪዝም፣ በታሪካዊ፣ በባህላዊና በማህበራዊ እሴቶቻቸው ዙሪያ የማስተዋወቅ አጋጣሚን ያሰፋል፡፡ በልማት የተሻሉ ከተሞች እውቅና እና ምስጋና ይቸራቸዋል፡፡ አዳዲሲ የፈጠራ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ብርታትን መስጠቱ ተጠቃሾች ናቸው ብለዋል ሚንስትር ዴኤታው፡፡
በተመሳሳይ የከተሞች ልማት በአስተማማኝ ሁኔታ የሚረጋገጠው እና ለአገር አቀፍ እድገት የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ በአግባቡ ማበርካት ያስችላቸዋል፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም እንዲከበር ከተወሰነበት ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ሰባት ዙሮች ተግባራዊ ተደርጓል ብለዋል አቶ ካሳሁን ጎፌ፡፡
የሶማሌ ክልል የከተማ ልማትና ቤቶች ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አብዱል ፈታህ ሸህ ቢሂ በበኩላቸው፤ በክልሉ የጸጥታ ሁኔታ ማንኛውም ተሳታፊ ምንም ዓይነት ሥጋት ሊያድርበት አይገባም፡፡ አስፈላጊው ዝግጅት ከህዝቡ፣ ከጸጥታ መዋቅሩ፣ ከእምነት አባቶችና ከአገር ሽማግሌዎች ጋር መደረጉን ገልጸዋል፡፡
በሙሀመድ ሁሴን