ሀገራችን የምትገኝበት መስቀለኛ መንገድ ከምንጊዜውም በላይ ከመርህ፣ ከንድፍና ጽንሰ ሀሳብ ይልቅ አመክኖዊና ተጠያቂያዊ የሆነ ተግባራዊ እውነትነት / ፕራግማቲዝም / ላይ የተመሰረተ ምልከታንና መላን ይፈልጋል። በነገራችን ላይ ሀገራችን ዛሬ ለምትገኝበት ውጥንቅጥ የዳረጋት አንዱ ምክንያት ይህ ለዘመናት ተጣብቶን የኖረ የንድፈና ጽንሰ ሀሳብ ሱስ ነው ። የሚያሳዝነው ሰሞነኛ የሀገራችንን ሁኔታ ለመበየን እየተሞከረ ያለውም በዚህ ሸውራራ የንድፈ ሀሳብ እይታ ብቻ መሆኑ ነው። ሆኖም ወቅታዊ የሀገራችንን ሁኔታዎችን ስንመረምር፣ መርምረን ድምዳሜ ላይ ለመድረስ፣ አቋም ለመያዝ ቢያንስ የሚከተሉት ነባራዊ ሁኔታዎች ቀድመው ወደ አእምሮአችን ሊመጡ ይገባል። በወረርሽኙ ምክንያት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር መሆናችን፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በወረርሽኙ ምክንያት ዝግጅቴ ስለተስተጓጎለ ቀጣዩን ምርጫ ማካሄድ አልችልም ማለቱ ፤ አደገኛው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከእለት እለት በሀገራችን እንደ ቋያ እሳት በፍጥነት በሕዝቡ ውስጥ በመዛመት እና የዜጎቻችንን ህይወት በመቅጠፍ ላይ መሆኑ፤ ተኝታልን የማታውቀው ግብፅ እንደ ለመደችው የውስጥ ልዩነታችንን ተጠቅማ ሀገራችን ለማተራመስ ከፍ ሲልም የቀጣናውን የመጀመሪያ የውሃ ጦርነት ለማወጅ ነጋሪት እየጎሰመች መሆኑ፤ በሁለት እግሩ ለመቆምና ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ለመመስረት የሚውተረተር ታዳጊ ሽግግር ላይ መሆናችን፤ ከአገዛዝ አስኳልነት በሕዝባዊ ተቃውሞና በለውጥ ኃይሉ ቅንጅት ከመንበሩ የተፈነገለው ትህነግ ለውጡን ለመቀልበስ ሌት ተቀን የሚሸርበውን ሴራ ተከትሎ የተፈጠረው ስጋት ዳመና አለመገፈፉ፤ በአቋራጭ ስልጣን ለመያዝ የሚቋምጡ፣ አሰፍስፈው የሚጠብቁ ኃይሎች መኖራቸው፤ ስልጣን ላይ ያለው መንግስት የስልጣን ዘመን የፊታችን መስከረም 23 የሚያበቃ መሆኑ ተከትሎ የስልጣን ክፍተት ቢፈጠር ሊከተል የሚችለውን ቀውስ፤ ሀገራችን የምትገኝበትን ነባራዊ እውነታን ቁልጭ አርገው ያሳያሉ።
በዚያ ሰሞን የኢፌዲሪ የፌደሬሽን ምክር ቤት፤ የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ በቀረበለት የውሳኔ ሀሳብ መሰረት፤ ” የኮሮና ወረርሽኙ የሕዝብ ጤና ሥጋት ሆኖ ባለበትና የበሽታውን ሥርጭት ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ፀንቶ በሚቆይባቸው ጊዜያትና አዋጁ ከተነሳም በኋላ አዲስ ምርጫ ተካሂዶ የሥልጣን ርክክብ እስኪፈጸም ድረስ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ የክልል ምክር ቤቶችና የፌዴራልና የክልል አስፈጻሚ አካላት የሥራ ዘመን እንዲቀጥል፤ የኮቪድ 19 ሥርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ ምክንያት የሆነው ወረርሽኝ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ የጤና ድርጅቶች የሚያወጡትን መረጃ መሠረት በማድረግ የጤና ሚኒስቴር፣ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና የሳይንሱ ማኅበረሰብ አካላት ወረርሽኙ የሕዝብ ጤና ሥጋት አለመሆኑን ሲያረጋግጡ፣ ይህም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፀደቀበት ቀን ጀምሮ ከዘጠኝ ወራት እስከ አንድ ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ምርጫው እንዲካሄድ ፤ ” የሚል ነው ። ውሳኔው የክልል ምክር ቤቶችንና አስፈጻሚዎችን የስልጣን ዘመን አብሮ ያራዘመበትን ምክንያትም እንዲህ ያትታል ።
” …የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኮቪድ- 19 ወረርሽኝ ምክንያት፣ መጪውን ጠቅላላ ምርጫ ማድረግ አለመቻሉን ሲገልፅ ፤ “ጠቅላላ ምርጫ” ማለት ደግሞ የፌዴራል ምክር ቤቶችን ምርጫ ብቻ ሳይሆን፣ ሁሉንም የክልል ምክር ቤቶች ምርጫ የሚመለከት ነው።
…” እንዲሁም ፣ “… የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ክልሎችንም የሚያካትት መሆኑ ፤ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 102 መሠረት ምርጫ ቦርድ የተቋቋመው በፌዴራልና በክልሎች ነፃና ገለልተኛ ምርጫ ለማካሄድ ስለሆነ ፤ ቦርዱ ጠቅላላ ምርጫ በፌዴራልና በክልሎች ለማካሄድ አቅዶ ዝግጅት ማድረግ ጀምሮ እያለ በወረርሽኙ ምክንያት እንዳልተሳካለት ጉባኤው ባደረገው ምርመራ ማረጋገጥ እንደቻለ አስታውሶ ፤ ቦርዱ ዝግጅት ጀምሮ የነበረው ጠቅላላ ምርጫን ማለትም በፌደራልና በክልሎች ለማካሄድ እንደነበር የሚታወቅ ስለሆነ ፤ የውሳኔ ሐሳቡም በፌዴራሉና በክልሎች የምርጫ ጊዜና በምክር ቤቶችና በአስፈጻሚዎች የሥራ ዘመን ላይ ተፈጻሚነት ሊኖረው ይገባል። ” ሲል የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ውሳኔ ያስረዳል። ይህ ውሳኔ ሕገመንግስታዊም የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታም ከግምት ያስገባ ነው ማለት ይቻላል።
በአንጻሩ በዚህ ውሳኔ ላይ እየተነሱበት ያለው የሕጋዊነትም ሆነ ፖለቲካዊ ጥያቄዎችና ትችቶች መግቢያ ላይ ያነሳሳኋቸውን ነባራዊ እውነታዎች ከግምት ያስገባ አይደለም። ሁሉንም ትችቶች በሶስት ከፍሎ መመልከት ይቻላል። የመጀመሪያው ሕገ መንግስቱ ስልጣን ከምርጫ ውጭ በሌላ መንገድ መያዝ እንደማይቻል በግልጽ የደነገገ ስለሆነ የሚተረጎም ነገር የለውም የሚለው መከራከሪያ የጨዋዎችና ስልጣንን በአቋራጭ ለመቀላወጥ ደጅ ላይ የተለገቡ ኃይሎች ትችት ሲሆን ፤ ሁለተኛው ደግሞ የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የክልል ምክር ቤቶችን እና
የአስፈጻሚዎችን የስልጣን ዘመን ያራዘመው የሕግ ትርጉም ባልተጠየቀበት አግባብ ነው የሚል ሲሆን ሶስተኛው ደግሞ የአስፈጻሚው ስልጣን ሲራዘም ከገደብ ጋር መሆን ነበረበት የሚል ነው። ሕገ መንግስቱ የሚተረጎም ነገር የለውም የሚለው ገልጃጃ መደምደሚያ ከመነሻው ከሕገ መንግስት ባህሪያትና መለያዎች ጋር የሚጣረስ ነው። ከዚህ በፊትም በሕገ መንግስቱ ላይ ከ600 በላይ የትርጉም ጥያቄዎች ለጉባኤው ቀርበው የነበር መሆኑ እንዲሁም የሕገ መንግስት ትርጉም ከነጣላ አንቀፅ ይልቅ አጠቃላይ አውዱንና ዳራውን መመልከት የሚጠይቅ መሆኑ መከራከሪያው ውሃ እንዳያነሳ ያደርገዋል። የክልል ምክር ቤቶችና አስፈጻሚዎች የስልጣን ዘመን የተራዘመበትን ምክንያት ጉባኤው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በላከው የውሳኔ ሀሳብ ላይ በስፋት ያብራራው መሆኑን ከፍ ብዬ ያሳየሁ ስለሆነ አልመለስበትም። ሶስተኛውና የአስፈጻሚው አካል ስልጣን ገደብ ሊጣልበት ይገባ ነበር የሚለው መከራከሪያ በመግቢያ ላይ ያነሳኋቸውን ነባራዊ እውነታዎችን ከግምት ያስገባ ካለመሆኑ ባሻገር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀበትን ገዥ ምክንያት የዘነጋ ነው። አዋጁ አስፈጻሚው አካል በመደበኛው ስልጣኑና እና ኃላፊነቱ ወረርሽኙን ለመከላከል ስለሚቸገር ተጨማሪ ስልጣን የሰጠ ሆኖ እያለ የሕገ መንግስት አጣሪ ጉባኤው ስልጣኑ እንዲራዘም የውሳኔ ሀሳብ ሲያቀርብ ስልጣኑን መወሰን፣ መገደብ ነበረበት የሚለው መከራከሪያ አሳማኝ ካለመሆኑ ባሻገር እርስ በርሱ የሚጋጭ ነው። ከሁሉም በላይ ከወረርሽኙ፣ ከግብፅ እና ለውጡን ለመቀልበስ እና ሀገር ለማተራመስ ከውጭም ከውስጥም ግንባር ፈጥረው ሌት ተቀን ከሚሰሩ ኃይሎች ጋር እየገጠመው ያለ ፈተና እየታወቀ የአስፈጻሚው የስልጣን ወሰን ይገደብ ማለት ከላይ እንደገለጽሁት ነባራዊ እውነትነትን የጎደለው ከመሆኑ ባሻገር ልፍስፍስና ደካማ መንግስት እንዲፈጠረ የሚያደርግ ነው። ይህ አይነቱ መንግስት ደግሞ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ፈተናዎችን መከላከልም ሆነ መጋፈጥ አይችልም። ስለሆነም በዚህ ፈታኝና ቀውጢ ሰዓት ሀገሪቱ የሚያስፈልጋት መንግስት ጠንካራና የመወሰን አቅም ያለው መንግስት ነው።
በኮቪድ 19 ምክንያት ምርጫን ያራዘሙ 55 ሀገራት የአስፈጻሚውን ስልጣን ስለመገደባቸው፤ በዚህ የተነሳ የተቀሰቀሰ ውዝግብና ውርክብ አላየሁም። አልሰማሁም። ይቅርታ ይደረግልኝና የሀገራችን ልሒቃን ትላንት ያሰቃያቸው ከነበረ የቡድን አስተሳሰብ ዛጎል/ሼል/ ዛሬም ሰብረው መውጣት አለመቻላቸው ነው። አንድ ተፅዕኖ ፈጣሪ ምሁር በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ሚዲያ ላይ ቀርቦ የሰጠውን አስተያየት ሌሎች ምሁራን እየተቀባበሉ አንዳንድ ጊዜ ምንም ሳይጨምሩና ሳይቀንሱ ሲያስተጋቡት መስማት የተለመደ ነው። ይህ የማህበራዊ ስነ ልቦናችን ቅርሻ ነው። ሆኖም ከዚህ የቡድን አስተሳሰብ ያፈነገጡና የራሳቸውን አቋም የሚያራምዱ በጣት የሚቆጠሩ የአደባባይ ምሁራን ስላሉን መልሰን እንጽናናለን። ከእዚህ ምሁራን አንዱ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ሬዲዮ “ጥያቄና መልስ “፣ አሁን ላይ “በሸገር ካፌ” በመዓዚ ጠረጴዛ የማይጠፉት፤ የሕግና የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ የሆኑት የሕግ ባለሙያ አቶ አብዱ ዓሊ ሒጅራ፤ ሰሞኑን ከቡድን አስተሳሰብ ወጣ ባለ አግባብ አጣሪ ጉባዔው የክልል መንግሥታትን የሥልጣን ዘመን ማራዘሙ ተገቢ እንደሆነ የተናገሩትን ከአማርኛው ሪፖርተር አንብቢያለሁ።
” …የፖለቲካ ሥልጣን በምርጫ በሚገለጽ የሕዝብ ይሁንታ ብቻ እንደሚያዝ የሚያመለክተው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9 በመላ አገሪቱ ሳይሸራረፍ ተግባራዊ የሚደረግ በመሆኑ፣ ይህንን ምርጫ ደግሞ በአሁኑ ወቅት ማድረግ የማይቻል ስለሆነ የክልል መንግሥታት ሥልጣን
መራዘሙ ሕገ መንግስታዊ ነው። …” በማለት ይሞግታሉ።
እንደ መውጫ
ኮቪድ 19 የሰውን ልጅ ኑሮ ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ ያለ ልዩነት አመሰቃቅሏል። የበለጸገ፣ በመልማት ያለ፤ ጥቁር፣ ነጭ፣ የቀይ ዳማ፣ ቢጫ፤ ክርስቲያን፣ እስላም፣ ሂንዱ፣ ቡድሃ፤ ሴት ፣ ወንድ ፣ ልጅ ፣ አዋቂ ፤ ሳይል። በተወሰኑ አካባቢዎች ወረርሽኙ ከፍተኛ የፓለቲካ ቀውስ ሲፈጥር ፤ መንግስታት የጤና ሊቃውንትን ምክረ ሀሳብ አድምጠው ባስቀመጡት የእንቅስቃሴ ገደብ የተነሳ ዜጎች ለከፋ የጤና፣ የስነ ልቦና፣ የኢኮኖሚ፣ ወዘተረፈ ችግር ተዳርገዋል። ባለፈው ግንቦት መግቢያ ላይ በአለማቀፍና በውጭ ግንኙነት ጉዳዮች ዙሪያ በሚያስነብባቸው ጥልቅና በሳል ትንተናዎቹ የሚመረጠው ” ፎሪን ፖሊሲ ” መፅሔት በጃኮብ ዋለስና ዳርሲ ፓልደር በጋራ ፤ ” The Coronavirus Is Delaying Elections Worldwide ” በሚል ርዕስ ባስነበበው መጣጥፍ ፤ ” …ፖለቲከኞች ለኮቪድ 19 ወረርሽኝ ክትባት እስካልተገኘለት ድረስ ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ በምርጫ እንዲሳተፍ ለመቀስቀስ ድፍረት አይኖራቸውም። ስለሆነም የሕዝብን ጤና ለአደጋ ሳይጋለጥ ማህበራዊ ርቀትን ጠብቆ ነጻና ገለልተኛ ምርጫ ማካሄድ አስቸጋሪ ስለሚሆን ምርጫን ለሌላ ጊዜ ማራዘምን መርጠዋል። ” ከፓርቲና ከስልጣን ሕዝብንና ሀገርን የሚያስቀድሙ ፖለቲከኞች የሚያስጨንቃቸው ወረርሽኙን በመከላከልና በመቆጣጠር የዜጎቻቸውን ህይወትና የሀገርን ህልውና መታደግ ነው። ወረርሽኙን ተከትሎ ሊመጣ የሚችልን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ በጋራ ለመቀነስ ይሰራሉ እንጂ እንደኛ ይህን ክፉ ቀን ለስልጣን መራኮቻ አላዋሉትም። ወረርሽኙን ፖለቲካዊ ነጥብ ለማስቆጠርም አልተጠቀሙበትም። የፖለቲካዊ ጨዋነት አንዱ መገለጫም ይህ ነው። በመላው አለም በዚህ አመት ምርጫ ለማካሄድ ቀጠሮ ይዘው የነበሩ 56 ሀገራት ኢትዮጵያን ጨምሮ ምርጫቸውን ለማራዘም መነሻ የሆናቸው ነባራዊ እውነትነትን ተከትለው መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ገምግመው እንጂ በደመ ነፍስ አይደለም። ለዚህ ነው በአንድም ሀገር በኮቪድ 19 ምክንያት ምርጫ በመራዘሙ ውዝግብ ሲፈጠር ያልሰማነው ። ያላየነው ። እንደኛ ተፎካካሪዎች መፍትሔው ሕገ መንግስታዊነት ሳይሆን እኛን ያሳተፈ ፖለቲካዊ ሽግግር ብቻ ነው ሲሉ ያላደመጥነው። ውረድ እንውረድ ሲባባሉ ያልሰማነው። ምሁራኖቻቸው በቡድን አስተሳሰብ አባዜ ሲንከላወሱ፣ ወዲያና ወዲህ ሲላጉ፣ ጉንጭ አልፋ ሙግት ውስጥ ሲገቡ፣ እሰጥ አገባና ጸጉር ስንጠቃ ላይ ሲጠመዱ ያላስተዋልነው።
የሀገርን ተጨባጭ ሁኔታ ከግምት ያላስገባ እርቃን ንድፍና ጽንሰ ሀሳብ በራሱ ግብ አይደለም። ክፉ ቀንን አሳልፎ ትውልድን አያሻግርም ። ከተደቀነባት አደጋም ሀገርን አያስጥልም ። ስለሆነም ልሒቃኖቻችን ከቡደን አስተሳሰብ ወጥተው እና ነባራዊ እውነትነትን መሰረት ባደረገ አግባብ መደምደሚያ ላይ መድረስን ፣ አቋም መያዝን ሊለማመዱ ይገባል ።
ሀገራችን ኢትዮጵያን እና ሕዝቧን ፈጣሪ አብዝቶ ይጠብቅ !!!
አሜን ።
አዲስ ዘመን ሰኔ 13/2012
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com