የርዕሴ የሽክርክሪት ዐውድ፤
ደረጃ የወጣላቸውን የሀገራችንን ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ከመዘርዘር ይልቅ ደረጃ ያልወጣላቸውን ማሰቡ ይቀል ይመስለኛል። በአጭሩ ለመግለጽ ያህል ለመኖር ከምንደገፋባቸው መሠረታዊ የሕይወት ማቆያዎቻችን እና አገልግሎት ሰጭዎችንና መስጫዎችን ደምረን ብንመረምር እንደ “ፕሮቶኮላቸው” ብቃት በደረጃ እየመደብን ያልከፋፈልናቸው ጉዳዮች ስለመኖራቸው እርግጠኛ አይደለሁም። ሆቴሎች ከሚበላለጡብት የኮከብ ዋጋ ባልተናነሰ ሁኔታ የዕለት መገልገያዎቻችንና ቁሳቁሶቻችን ሁሉ ማዕረግ በሰጠናቸው ልዩነቶች የተበላለጡ ናቸው።
የዕለት ቀለባችን ጤፍ ሳይቀር ወደፊት በአልማዝ፣ በወርቅና በብር እየተመዘነ ደረጃ ሳይወጣለት እንደማይቀር ከአያያዙ መገመት አይከብድም። ቡናችን፣ ምግባችንን የምናጣፍጥበት ሽንኩርት፣ እንጀራችንን የምንጠቅስበት ሽሮና በርበሬ ዕድሜውን የሚያድለን ከሆነ ከጥቂት ዓመታት በኋላ የባለጠግነት አንዱ መስፈርት ተደርገው ሽቅብ መስፈንጠራቸው እንደማይቀር ያበደው ገበያችንና ያሳበዱን ነጋዴዎች ምልክቱን ከጠቆሙን ቆይተዋል። “ኮሮና ደጉ!” የገበያው እብደት ከህመሙ እኩል እያሳሰበን እህህ በማለት ስናጉተመትም እንድንውል “ሕዝባዊ አጀንዳ” ሰጥቶናል።
ደረጃ የወጣላቸውና የሰጠናቸው ጉዳዮቻችን ምግብና መጠጦቻችን፣ አልባሳትና ማጌጫዎቻችን፣ መኪናዎቻችንና መኖሪያ ሕንፃዎቻችን፣ ትምህርት ቤቶቻችንና የጤና ተቋሞቻችን ብቻም አይደሉም። ለድህነታችንም የጎላ ደረጃ ሰጥተነው ማሕበራዊ ክፍሉን እያደመቅን ስለሆነ ለጉዳዩ ባዕድ የምንሆን አይመስለኝም። የድህነታችን “ደረጃ” በማለት ስያሜ የሰጠሁትን “የመደብ” መለያና መታወቂያችንን ደጋግሜ ብሰማውም መስፈርቱ እና ጽንሰ ሃሳቡ ሊገባኝ ያልቻለው “የድሃ ድሃ” የሚለው መግለጫ ነው።
በሀገራችን ዐውድ “ድሃ ማነው? የድሃ ድሃስ የትኛው የማሕበረሰብ ክፍል ነው?” የሚሉት ጽንሰ ሃሳቦች ለክርክር ቢቀርቡ ይህ ነው መልሳቸው የሚባልላቸው ዓይነት አይደሉም። “መልስ አለኝ” ባይም የሚኖር አይመስለኝም። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ “የድሃ ድሃ” የሚለውን መጠሪያ አልሰማሁም የሚል ሰው ከተገኘ እርሱ “ዕድለኛ ጆሮ የታደለ” መሆን ይኖርበታል። ከከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ “ከመካከለኛና” እስከ ታችኛው የሥልጣን ተዋረድ “አንቱ” የተባሉና የከፍታ ወንበር ላይ የተቀመጡ አለቆች “የድሃ ድሃ”ን ገናና ሐረግ በአፋቸው ሲያላምጡ የሚውሉ እስኪመስል ድረስ ደጋግመው እየተጠቀሙበት እንዳሉ እየተመለከትን ነው። “ዘመነ ኮሮና” ካገነናቸው ቃላትና ሀረጋት መካከል (ከእነ ሳኒታይዘር፣ ፌስ ማስክና ማሕበራዊ ርቀት) እኩል “የድሃ ድሃ” የሚለው መገለጫም በስፋት ለጆሯችን ጥጋብ ከሆነ ሰነባብቷል። ነዋይ ደበበ “የእኔ ድሃ” የሚለውን አራራይ ሙዚቃውን በዚህ ወቅት ሪሚክስ አድርጎ እንደገና ቢያንጎራጉረው ብዙ አድማጭ የሚያገኝ ይመስለኛል።
የአካባቢያቸውን ማሕበረሰብ ለመደገፍ በበጎ ዓለማ የተነሳሱ ወጣቶቻችን ባለማወቅ፣ የዕለት ማዕዳቸውን ለማጋራት የተጉ ዜጎች፣ ከሀብታቸው ቆንጥረው ለመስጠት ንፍገትን የተጠየፉ “ብፁዓን” በየአካባቢው ለሚገኙ አቅመ ውስን ዜጎች የመሠረታዊ ሸቀጦች ድጋፍ ለማድረግ እጃቸውን ከመዘርጋታቸው አስቀድሞ በሚዲያዎች ማይክራፎን ፊት ቆመውና ከሹሞች ጋር ተቀምጠው “ይህንን ዕርዳታና ድጋፍ የምንለግሰው ከማሕበረሰቡ ውስጥ “የድሃ ድሃ” ተብለው ለተለዩ
ወገኖች ነው” በሚል የመክፈቻ ንግግር ሃሳባቸውን መግለጫቸውን አንባቢያንን “አልሰማችሁም፣ አላያችሁም” ብዬ ለመጠየቅ አልደፍርም። የየዕለቱ ክስተት ስለሆነ። አንጋፋው አዲስ ዘመን ጋዜጣም በሰኔ 11 ዕትሙ የድሃ ድሃ የሆኑ ዜጎችን የሚጠቅም ፕሮጀክት መነደፉን ያበሰረን ይህንኑ ቃል እንዳለ በመጠቀም ነው።
ሩዝ፣ ዱቄት፣ ዘይትና ማኮሮኒ የሚታደለው “ለድሃ ድሃ” መባሉ፣ የሚያንጠበጥብ የጣሪያ ቆርቆሮ መጠገኑና ያዘመመ ጎጆ ተቃንቶ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች መበርከቱ እጅግ የሚያስመሰግንና የህሊና እርካታ መስጠቱ ባይካድም “የድሃ ድሃ ስለሆኑ ነው” ተብሎ መስፈርቱ በየሚዲያው ተጋኖ እንዲነገር መደረጉ ግን ስሜትን ማወክ ብቻ ሳይሆን ሰብዓዊነትን የሚፈታተን ጭምር መሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። “ዕድሜ መንግሥታዊ ላልሆኑ የሀገራችን የተራድኦ ድርጅቶች” ይሁንና እነሆ ዘጠኝ ክረምት የማይነቅለውን ክፉ መገለጫ በአንድ ክረምት ተክለውብን አልፈዋል።
ደግመን እንጠያየቅና ለመሆኑ “ድሃ” እና “የድሃ ድሃ” የልዩነቱ መስፈርትና መስመሩ ምንድን ነው? “ድሃ” የሚሰኘው በምን ወንጠፍት ተለይቶና ፀድቆ ነው? “የድሃ ድሃስ” ከድህነት ውስጥ ተፈልቅቆ የወጣው የትኛው የኑሯችን ዲ.ኤን.ኤ ተመርምሮ ነው? ከማኅበረሰቡ ውስጥ “የድሃ ድሃ” ተብለው ለርዳታና ለድጋፍ የተለዩ ወገኖች በሥነ ልቦናቸው ላይ ምን ዓይነት ጫና ሊፈጥር እንደሚችል ታስቦበትስ ይሆን? ለወደፊቱ ኑሮ ሲሰምርላቸው እነዚህ “የድሃ ድሃ” ዜጎች ወደ ድህነት “የክብር ማማ” ከፍ የሚሉት ምን ምን ሁኔታዎች ሲሟሉላቸው ነው። ደፍረንና ጀግነን ለድህነትስ ደረጃ አወጣን ደግ፤ ለመሆኑ ባለጠጎችን “የባለጠጋ ባለጠጋ”፣ ዝነኞችን “የዝነኛ ዝነኛ”፣ ሀብታሞችን “የሀብታም ሀብታም” ወዘተ. በሚለው ማነጻጻሪያ በደረጃ መከፋፈል ሊኖርብን ይሆን? ጥያቄዎቹ ኮርኳሪ ብቻ ሳይሆኑ ሞጋችም ጭምር ስለሆኑ ልብ ተቀልብ ሆነን ልናስብበት ይገባ ይመስለኛል። የዕለት ጉርስና መገልገያ ቁሳቁስ የሌላቸውን “ድሆች”፣ “ይህንንና ያንን” ለማግኘት ያልቻሉትንና ቀን የከፋባቸውን ደግሞ “የድሃ ድሃ” አድርገን በመፈረጅ ተስፋቸው እስትንፋሳቸው ብቻ እንዲሆን መወሰናችን በእጅጉ የበደል በደል ይመስለኛል። መርዳት ከተፈለገ “መረዳት የሚገባቸውን ብቻ ረዳን” ማለቱ በቂ ይመስለኛል።
ሀገሬና ድህነታችን፤
የሠፈሬን እውነታ፣ የአካባቢዬን ሐቅ፣ የማሕበረሰቡን ውሎ አምሽቶ ከመቃኘት ዘልዬ ዓለም አቀፍ ሪፖርቶችና ጥናቶች የሀገሬን ድህነት በምን ደረጃ አስቀምጠውት ይሆን ብዬ ለመመርመር ሞክሬ ነበር። ደግነቱ እጅግም በንባቤ ሳልገፋ ቃል በቃልም ባይሆን በገደምዳሜ ገለጻ ዓለም አቀፍ ተቋማቱ ሀገሬን ለመመደብ የሚሞክሩት “የድሃ ድሃ” (Poorest of Poor) ወይንም (Destitute) ወደሚለው ደረጃ በማስጠጋት እንደሆነ ለመረዳት ችያለሁ። የመስፈርታቸው ሦስት ፅኑ አእማድ ተደርገው የተወሰዱት መመዘኛዎች ደግሞ ጤና፣ ትምህርት፣ የኑሮ ደረጃዎች ናቸው። መገለጫቸው ደግሞ የተራዘመ ድርቅ፣ የተራቆተ ግጦሽ፣ የመሬት መሸርሸርና በአጠቃላይም የሀገራችን ገበሬዎች ለሺህ ዘመናት እንደ ቅርስ እየጠበቁ የሚከውኑትንና በጥንድ በሬዎች የሚጎተተውን የሞፈርና ቀንበር የአስተራረስ ዘዴ በምሳሌነት በመጥቀስ ነው።
ስለዚህም ስድስቱን የድህነት አንጓዎች ማለትም፤ ሰው ሠራሽና ተፈጥሮ ወለድ (Situational)፣ ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣውን (Genera¬tional)፣ የዕለት ምግብና መጠለያ ችግራችንን (Ab¬solute)፣ በአንጻራዊነት ከድህነት ወለል ከፍ ብለን መገኘታችንን (Relative)፣ የከተማ ድህነትና ጉስቁልና
ስፋትን (Urban) በመዘርዘር ከዓለም ሀገራት መካከል ከመጨረሻዎቹ ሃያ ያህል ዝርዝሮች ውስጥ ኢትዮጵያን ያስቀምጧታል። ምናልባትም “የድሃ ድሃ” በማለት ሰድቦ ለሰዳቢ የሰጠነው ራሳችን እንሆንን? ብዬም ራሴን በራሴ የጠየቅሁት በዚሁ ምክንያት ነው።
አንድ ተያያዥ ጉዳይ እግረ መንገዴን አስታውሼ ልለፍ። የሀገራችንን ኢንቬስትመንት የሚመራውና የሚቆጣጠረው ተቋምና አብዛኞቹ ዲፕሎማቶቻችን እስከ ቅርብ ጊዜያት ድረስ ሀገራችን ሙዓለ ነዋያቸውን ለሚያፈሱ ባለጠጋ ባዕዳን ምቹና አዋጭ መሆኗን ሲያስተዋውቁ ከሚጠቀሙባቸው ዋና ዋና መቀስቀሻዎች መካከል፤ ድንግል የተፈጥሮ ሀብት ባለቤቶች መሆናችንን፣ በተፈጥሮ የዓየር ንብረት የተባረክን መሆናችንን እና “እርካሽ የሰው ጉልበት” የተትረፈረፈባት ምድር እንደሆነች ጮክ እያሉና የአዋጅ ያህል እያስተጋቡ ነበር።
ስለ ሁለቱ ቀዳሚ መቀስቀሻ እውነታዎች በአምስት ጣቶቼ ፈርሜ አውነትነቱን አረጋግጣለሁ። “እርካሽ የሰው ጉልበት” የሚለው የስድብ ታርጋና ማስተዋወቂያ ግን እንደምን ሰብዓዊና ሀገራዊ ክብርን ጨፍልቆ ዝቅ እንደሚያደርግ ለመረዳት ለማንም የሚከብድ አይመስለኝም። ይሄው ሀገራዊ “የመለያ ሰንደቃችን” ብሔራዊ መገለጫችን ሆኖ በርካታ የውጭ ሀገራት ባለሀብቶች ቀጥረው በሚያሠሯቸው ዜጎቻችን ላይ ይፈጽሙት የነበረው ግፍ በይፋ የታወቀ ነበር። ዛሬም ቢሆን “እርካሽ የሰው ጉልበት” የሚለው መታወቂያችን “በቂ የሰው ኃይል” በሚል የተተካ ቢሆንም “የርካሽ ጉልበቱ ብዝበዛ ቀርቷል ወይ?” ለሚለው ሞጋች ጥያቄ ግን መልሴ “ሆድ ይፍጀው” የሚል ይሆናል። ”
“የድሃ ድሃ” ሌላው ቅቡል መልክ፤
የቁስ እጥረትና የዕለት እንጀራ እጦትን መስፈርት አድርገን “የድሃ ድሃ” እያልን ከድህነት ወለል በታች እንደሆንን በመቁጠር በንግግር ራሳችንን በራሳችን ባንፈጠፍጥ በግሌ በእጅጉ እመርጣለሁ። ስያሜው ብቻም ሳይሆን የተዋረድንበት ድህነታችንና ኑሯችንን በየዕለቱ ተግባራችንም ሆነ በባዕዳን ቀረርቶ እንዳይጎላም ጭምር ምኞቴ ነው። የጠገብነው “የድህነት” ስድብ የታሪክነት ክብር ተነፍጎት እንደ ተረት ሲወራ ማድመጥና ማየት ህልሜም ቅዠቴም ነው። ገለጻው ራሱ ከአንደበታችን ብቻ ሳይሆን ከመዛግብተ ቃላቶቻችን ሳይቀር ሙሉ ለሙሉ ተወገዶ ለማየትም ጉጉቴንና ጸሎቴን ጠንከር አድርጌ ተያይዤዋለሁ። ሕዝባችን ወደ ተሻለ ከፍታ ወጥቶ ድህነትን ራሱን ቁልቁል እየተመለከተ የሚሳለቅበት ዘመን እየቀረበ መምጣቱን ሳስብ አንዳች የደስታ መንፈስ ውስጤን ሲያረሰርስ ይሰማኛል።
ለበርካታ ዓመታት “የሀገራችን ዋናው ጠላት ድህነት ነው” ብለው ያወጁትና እኛን ዜጎችንም ጮክ አድርገው ያዘመሩን ሟቹ የሀገራችን አለቃ ድህነትን አግዝፈውልን የነበረው በገበሬ ማሳ ውስጥ እንደሚቆም ባዕድ አካል ወይንም የወፎች ማስፈራሪያ አውከሬ (በጉራጊኛ) መሰል ሰብዓዊ ፍጡር ስለውልን ነበር። ድህነትን አፋፍተን ያሳደግነው እኛው ራሳችን እንዳልሆንን ሁሉ አግዝፈን ስንረግመው መኖራችን በራሱ እንቆቅልሽ ነበር ማለት ይቻላል። “እናንተ ኢትዮጵያዊያን ለድክመታችሁ ሰበብ አታጡም” የሚሉት የውጭ ሀገር ዜግነት የነበራቸው የሥራ ባልደረቦቼ ሁሌም ትዝ የሚሉኝ ገበናችንን ተረድተውት ይመስለኛል። “ሰዓቴን ሰበርኩት” ከማለት ይልቅ “ሰዓቴ ተሰበረ” እያላችሁ በግዑዝ ቁሶች ማመካኘት ትወዳላችሁ እያሉ የሚያሳጡን በአንድ በኩል እውነትነት አይታጣበትም።
“ራሳችንን ሰድበን ለተሳዳቢ፣ ራሳችንን ረግመን
ለተራጋሚ” ያስተላለፍናቸው በርካታ ሀገራዊ መርገምቶቻችን በቅርብ ዓመታት ውስጥ በነገይቱ ኢትዮጵያ እንደማይኖሩ ተስፋ ብሰንቅም “የድሃ ድሃ” የሚለው መታወቂያ ግን ሙሉ ለሙሉ ከሚወገድ ወደሌላ ጉዳይ ተሸጋግሮ ዕድሜው ቢረዝም የምመኝባቸው በርካታ ጉዳዮችም አልጠፉም። ይህንን ማሰቤ ራሴን በራሴ እየተቃረንኩ ከራሴ ጋር በመላተም እንደሆን ልብ ይሏል።
“የብልጽግና” ፓርቲውንና የሀገሪቱን መሪነት ደርበው የያዙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) “ብልጽግና” የሚለውን ቃል ደጋግመው የሚያውጁትና መርሐቸው አድረገው “እመኑልኝ” የሚሉት ምናልባትም የድህነት ጥዩፍነት ባህርያቸው አስገድዷቸው ይሆንን እያልኩ መጠየቄ አልቀረም። የሌት ተቀን ጥረታቸውን በለውጥ ዓላማ ላይ ማዋላቸው፣ “ዋናው ጠላታችን” ድህነት ነው የሚለውን ማሳበቢያ ለመሰባበርና “የድህነታችንን የሰበብ ቀስት ወደ ራሳችን” መልሰን “ከራሳችን ጋር እንታገል” ማለታቸው ስለዚሁ ይሆንን? እያልኩም እጠይቃለሁ። በንግግራቸው ውስጥ “ወደ ብልጽግና ለምናደርገው ጉዞ” የሚለው አባባል ይበልጥ ቀልቤን ስለሚስበው አክብሮቴ ከፍ ያለ ነው።
“የድሃ ድሃ” የሚለው ሀረግ ሙሉ ለሙሉ እንዳይጠፋ “ከራሴ ድምዳሜ ጋር ያቃረነኝ” ዋነኛው ምክንያት የሚከተለው ነው። በአስተሳሰብ፣ በአመለካከት፣ በተግባር፣ በርእይ፣ በማስፈጸምና በመፈጸም አቅምና በቅንነት ማጣት ተኮንነው በሕዝብና በሀገር ላይ እንክርዳድ በመዝራት ሊያሳክሩን ቀን ከሌት የሚጥሩትን ብኩኖች በቁስ ድህነት ሳይሆን በኅሊና ባዶነት “የድሃ ድሃ” ብለን ብንጠየፋቸው ያጸድቃል እንጂ አያስኮንንም። አባባሉን የተዋስኩት ከወላጅ እናቴ ከወይዘሮ ወሰኔ ነው። “የበጎነት ድህነት” የሚሉት የተዘወተረ አባባል ነበራት።
መልካም ሀገራዊ ርእዮችና ጅምሮች የማይጥማቸው፣ ውጪያቸው በሱፍና በከረቫት ሽክ ብሎ ውስጣቸው በክፋትና በቅንዓት የተበከለ “የበጎነት ድሆችን” ደረጃቸውን ከፍ አድርገን “የድሃ ድሃ” ብንላቸው ያንስባቸው ካልሆነ በስተቀር በዛብን ብለው ስሞታ እንደማያቀርቡ እገምታለሁ። ሰላማዊ ዜጎች የሰላም እንቅልፍ እንዳያገኙ አመጽ ሲያውጠነጥኑ አድረው ማለዳ ላይ “የሞት መርዶ” ለማወጅ ምላሳቸውን የሚያሾሉት እኩያን “የድሃ ድሃ” ስያሜ በሚገባ ይገልጻቸው ይመስለኛል። ሀገራዊ ተስፋን ለሚገሉ፣ ሕዝብ ተረጋግቶ ውሎ እንዳያድር የሚተጉ፣ የመልካም ነገር ፀርነታቸውን በንግግርና በተግባር የምንመሰክርላቸውን ኃይላት በሙሉ ጠቅልለንና ደማምረን “የድሃ ድሃ” ብለን ብናውጅላቸው ክፋቱ አይታየኝም።
ከዚህ በተረፈ ግን በቁሳቁስ እጥረትና በዕለት እንጀራ እጦት ለሚፈተነው ወገናችን የርህራሄ እጃችንን ዘርግተን ጉድለቱን ስንሞላለት ንግግር ለማሳመርና ውለታ ለማስቆጠር በማሰብ ብቻ “የድሃ ድሃ” እያልን “በአፍ እላፊ” ባንሳለቅባቸው መልካም ይሆናል። ለመታረም መፍጠኑም አይከፋም። እነርሱ “የድሃ ድሃ” ሳይሆኑ የኑሮ እጥረት ሰለባ ኩሩ ዜጎቻችን ናቸውና። ሰላም ይሁን
አዲስ ዘመን ሰኔ 13/2012
(ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com