ኮቪድ 19 ወረርሽኝ በኢትዮጵያ የምርጫ ሥራን አደናቅፏል። ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም ሊካሄድ ቀን ተቆርጦለት የነበረው ሀገር አቀፍ ምርጫ ማራዘም የግድ ሆኗል። ወረርሽኙ በዓለም አቀፍ ደረጃም ቢሆን በ53 አገራት ምርጫ ነክ ሒደቶችን እንዲራዘሙ ማስገደዱ እውነት ነው። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ የምርጫ ጉዳይ የሕገመንግሥት ጥያቄ ማስነሳቱ ከሌሎች ለየት አድርጎታል። በተለይም በኢትዮጵያ በሚገኙ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል በጋራ ጉዳዮች ላይ ተቀራርቦ የመሥራትና ብሔራዊ ጥቅምን በማስቀደም ረገድ ቀደም ሲል ጀምሮም የጋራ መግባባት አለመኖሩ በአጀንዳው አፈታት ዙሪያ ልዩነትን ፈጥሯል። የአለመግባባት፣ የንትርክ አጀንዳም ሆኖ ከርሟል።
በኮቪድ 19 ውጥረት ውስጥ ተሆኖም የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጉዳዩን በመገምገም “በወረሽኙ ውስጥ ምርጫ ለማስፈጸም እቸገራለሁ” ማለቱን ተከትሎ መንግሥት ሌሎች አማራጮችን ወደመፈለግ ፊቱን እንዲያዞር አስገድዷል። በዚህም መሠረት የተለያዩ የሕግ አማራጮች ከተፈተሹ በኋላ የሕገመንግስት ትርጉም ማድረግን በመመረጡ ወደዚህ ሥራ መገባቱም የምናስታውሰው ነው።
ከምርጫ ቦርድ የአልችልም ሪፖርት የቀረበለት የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በወቅቱ መካሄድ ካለመቻሉ ጋር ተያይዞ ጉዳዩ የሕገ መንግሥት ትርጉም እንዲሰጥበት ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ግንቦት 28 ቀን 2012 በይፋ ጥያቄ አቀረበ።
ጉባዔውም ጥያቄውን ከተቀበለ በኋላ በጉዳዩ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚመለከታቸውን አካላትና ባለሙያዎችን በመጋበዝ አስተያየት ሲሰማና ግብዓት ሲሰበስብ ቆየ። ሒደቱም ግልፅ በሆነ መንገድ በመገናኛ ብዙኃን እንዲተላለፍ በማድረግ መላው ሕዝብ እንዲከታተለውም ሁኔታዎችን አመቻቸ። በአጭር ጊዜም የውሳኔ ሃሳቡንም ለፌዴሬሽን ምክርቤት ላከ።
የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ጉዳዩን ከመረመረና በምክር ቤቱ አባላት ሰፊ ውይይት ካካሄደበት በኋላ፣ ሰኔ 03 ቀን 2012 የጉባዔውን የውሳኔ ሃሳብ በማፅደቅ በጉዳዩ ላይ የሕገ መንግሥት ትርጉም ሰጠ።
የፓርላማው ሁለት አንኳር ጥያቄዎች ምን ነበሩ? አንደኛው በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ምርጫ ማካሄድ ስላልተቻለ ሕገ መንግሥቱ ደግሞ ዋና ዋና የመንግሥት ሥልጣን አካላት (ሕግ አውጪና ህግ አስፈጻሚ) በየአምስት ዓመቱ በሚደረግ ሃገር አቀፍ ምርጫ መሠረት በሚደረግ የሥልጣን ርክክብ ላይ የሚመሰረት በመሆኑ፣ አሁን ሀገሪቱን በመምራት ላይ የሚገኙት የመንግሥት አካላት የሥልጣን ዘመን ላይ ሁኔታው ምን አንደምታ አለው?
ሁለተኛው፤ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ለሕዝብ ጤና ሥጋት መሆን ካቆመበት ጊዜ ጀምሮ ምርጫው መከናወን ያለበት በስንት ጊዜ ውስጥ ነው የሚል ነው።
አጣሪ ጉባዔው ጉዳዩን እንዴት መረመረው?
ከሕገመንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔው ጽ/ቤት ባገኘሁት መረጃ መሠረት፤ አጣሪ ጉባዔው ጉዳዩን መርመር ከመጀመሩ አስቀድሞ ጉዳዩን ተቀብሎ የማየት ሥልጣን አለው ወይንስ የለውም፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትስ እንዲህ ያለውን ጉዳይ ወደ ጉባኤው እንዲልክ ሥርዓቱ ይፈቅዳል ወይንስ አይፈቅድም የሚሉ ሁለት ጥያቄዎችን መርምሯል። ሁለቱም ጥቄዎች ላይ ጉባዔው በዚህ የውሳኔ ሃሳብ ሐተታ በተለገጹት ምክንያቶች አዎንታዊ መልስ በመስጠት ብይን ከሰጠ በኋላ ጉዳዩን ወደመርመር ዘልቋል። ብይኑ ዋና ይዘትም ጉባዔው በሕገመንግሥቱ
አንቀጽ 84(1) መሰረት ጉዳዩን የመቀበልና የመመርመር ሥልጣን አለው የሚል ነው። በተጨማሪም ጉባዔው ሕገመንግሥቱን መሠረት በማድረግ የፍርድ ቤት ክርክር አስታከው የሚመጡ ሕገመንግስታዊ ጉዳዮችን ወይንም ሕገመንግሥቱን የሚጋፉ አዋጆች መመልከት ብቻ ሳይሆን፣ ሕገመንግሥታዊ የትርጉም ሥርዓትን ሊያሰፉ የሚችሉ አንኳር ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ትንተና እና የውሳኔ ሃሳብ በመስጠት ጉባዔው ሆነ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሕገመንግስቱ ቀድሞ ታሳቢ እንዳደረገው የሕገመንግሥት ትርጉም ሥርዓትን ማሳደግ ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን ጭምር ከግምት ያስገባ ነው። የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት የትርጉም ጥያቄውን ለማቅረብ የሚችል መሆኑን በተመለከተም በአዋጅ ቁጥር 798/2005 አንቀጽ 3(2) (ሐ) መሠረት የሕገመንግሥት ትርጉም ጥያቄውን ለማቅረብ ይችላል የሚል ብይን አጣሪ ጉባዔው ሰጥቷል።
አጣሪ ጉባዔው በሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት የተነሳውን ጥያቄ ከመመለሱ አስቀድሞ ከሕገመንግሥት የትምህርት ዘርፍ ባለሙያዎች፣ ከሕግ ባለሙዎች፣ ሕገመንግሥቱን በማርቀቅ ሒደት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተካፋይ ከነበሩ ግለሰቦች እንዲሁም፣ ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው ሶስት የመንግስት ተቋማት ማለትም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በቴሌቪዥን ቀጥታ ስርጭት የተላለፈ የመስማት ሒደት (Hearing) አካሂዶ ነበር። ይህ ሒደት በጉባዔው ይሁን በፍርድ ቤት ደረጃም ቢሆን በሀገሪቱ የመጀመሪያው ግልጽ ታሪካዊ ሂደት ነበር። ከዚህ በተጓዳኝ ጉባዔው ባደረገው ጥሪ መሰረት ከ34 ግለሰቦችና ተቋማት የሙያ አስተያቶችን በጹሑፍ ተቀበሎ ጽሑፎቹን በመዳሰስ በግብአትነት ተጠቅሟል። ከዚህ ሒደት ጎን ለጎን ጉባዔው በበኩሉ በዋና ዋና ጭብጦች እና በተዛማጅ ጥያቄዎች ዙሪያ በርካታ ውይይቶች እና ክርክሮች ለሁለት ሳምታት ሲያደርግ መቆየቱን በይፋ ገልጿል።
ጉባዔው የተከተለው የሕገመንግሥት አተረጓጎም መርሆዎች የጉባዔ አባላት የቀረበውን ጥያቄ ለመመርመር የተሻለ ሆኖ ያገኙት የትርጉም ዘዴ ዓላማ ተኮር ወይም መዋቅራዊ (Purposive/ structural) የሚባለውን ነው።
የሕገመንግሥት ባለሙያዎች እንደሚገልጹት እና የጉባኤው አባላት እንደሚያምኑበት ለጉባዔው ለቀረበለት ጉዳይ መፍትሔ ለመስጠት እድል ወይም የተወሰኑ ግልጽ ድንጋጌዎች ባለመኖራቸው ከሕገመንግሥት ጠቅላላ ዓላማ እና ሊያሳካቸው ካሰባቸው ግቦች አኳያ ምክንያታዊ መልስ ሊገኝ የሚችለው ከሕገመንግሥት መግቢያ ጀምሮ ከጉዳዩ ጋር ቀጥተኛ ወይንም ትስስር ያላቸውን የሕገመንግሥቱን አንቀጾች በመመርመር ነው የሚል ግምት ተወስዷል።
በሌላ በኩል እንዲተረጎሙ የተጠየቁት ሶስቱ የሕገመንግሥት አንቀጾች 549(1)፣ 58(3) እና 93 በጣምራ ቃል በቃል (textual) በሆነ አተረጓጎም እንኳን ቢተረጎሙ ለጥያቄው ግልጽ መፍትሄ ሊሰጡ ይችላሉ የሚሉ አስተየቶችም ተንጸባርቀዋል። ምክንያቱም በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 58(3) በሥልጣን ላይ ያለው የሕግ አውጪ አካል የሥራ ዘመን ለአምስት ዓመታት ነው የሚለው ድንጋጌ መሰረት ያደረገው በአንቀጽ 54(1) መሠረት የምክር ቤቱ አባላት በአዲስ ምርጫ መተካታቸውን ከግምት አስገብቶ ነው። በኮቪድ 19 ወረርሽኝ እና በወረርሽኙ ምክንያት በወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት አገር አቀፍ ምርጫን ለማከናወን አስፈላጊ የሆኑ የህዝብ ግንኙነት እና ሰፊ እንቅስቃሴ የሚጠይቁ ተግባራትን ማከናወን ስላልተቻለ ምርጫውን
ማካሄድ አይቻልም። ስለዚህም ምርጫ ካልተካሄደ ምክር ቤቶቹም ይሁኑ በምክርቤቶቹ የሚሰየሙ የአስፈጻሚ አካላት የሚሰየመው አስፈጻሚ አካል ሥልጣን ጊዜ ይቀጥሏል ብሎ መተርጎም ይቻላል የሚል ነው።
ጉባዔው ይህንን የትርጉም አቅጣጫ እንደአንድ አማራጭ በመመልከት ያስተናገደ ቢሆንም በዋናነት ግን በውሳኔ ሃሳብ ሃተታው እንደተመለከተው ጥያቄውን ለመመለስ በሶስቱ አንቀጾች አልተገደበም። ጉባዔው የሕገመንግሥቱን መንፈስ እና ሙሉ ዓላማ ባገናዘበ መልኩ ሕገመንግሥቱን የፓርላሜንታዊ ሥርዓተ መንግሥት እሳቤዎች ላይ የተመሰረተ፣ ሥልጣን ክፍተት የማያስተናግድ፣ የመንግስተ ቀጣይነትን የሚመርጥ፣ የመንግስት ግልጽነት እና የመንግስት ተጠያቂነት ሃሳቦች የሚያስተናግድ መሆኑን በምርመራ ሒደቱ ተገንዝቧል። አሁን በቀረበ ጥያቄም የፌዴራልም ሆነ የክልል የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲሁም ፌዴራሉ እና ክልል ሥራ አስፈጻሚ አካላት በሕገመንግሥት በተቀመጠው የሥልጣን እና ሥራ ኃላፊነት ገደቦች መሠረት አዲስ ምርጫ ተከናውኖ መንግሥት እስኪመሰረት ድረስ ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ጉባዔው የውሳኔ ሃሳብ አቅርቧል።
የሥልጣን አካላቱ በሥራው ላይ የሚቀጥሉት የኮቪድ 19 ወረርሽኝን የሕዝብ የጤና ሥጋት መሆኑ በሚመለከታቸው የጤና እና ሌሎች የውሳኔ ሰጪ አካላት ከተረጋገጠበት ጊዜ ጀምሮ ከ9 – 12 ባሉት ወራቶች ውስጥ 6ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ተከናውኖ እስኪተኩ እንደሆነ ጉባዔው የውሳኔ ሃሳብ ሰጥቷል።
ጉባዔው የሕገመንግሥት አንቀጾች ትርጉም መሠረት ያደረገ የትርጉም መርሆ በተወሰነ ደረጃ ከግንዛቤ ያስገባ ቢሆንም በዚህ ረገድ እጅግ የጠበበውን በተናጠል በእያንዳንዱ አንቀጽ ውስን ቃላቶች ላይ ብቻ የሚመሰረተውን የትርጉም አቅጣጫ መፍትሄ ሰጪ ባለመሆኑ ይሄን የአተረጓጎም አቅጣጫ አልተቀበለውም።
ጉባዔው ይህንን ጠባብ የትርጉም አቅጣጫ ያልመረጠበት ምክንያት ይህ የትርጉም አቅጣጫ ሕገመንግሥቱ ምንም አስቸኳይ ሁኔታ ቢፈጠር (ወረርሽኝ ይሁን ጦርነት ወይንም የተፈጥሮ አደጋ) ምርጫው በአምስት ዓመት ተከናውኖ የአዲስ መንግሥት የሥልጣን ርክክብ መደረግ አለበት የሚል መደምደሚያ ላይ ስለሚያደርስ ነው። እንዲህ ያለው የትርጉም አካሄድ አሁን ባለንበት እውነታ የሕዝቡን ጤና አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ አጣሪ ጉባዔው የሚያስኬድ ሆኖ አላገኘውም። እንዲህ ያለው አተረጓጎም ተጨባጭ ሁኔታን ያላገናዘበ፣ ለተነሳው ጥያቄ ምክንያታዊ ትርጉምም ሆነ ኃላፊነት የተሞላበት መልስ የሚሰጥ ሆኖ አልተገኘም።
ከማሻሻያ ሥራዎቹ እና በተግባር እየተፍታቱ ከሚመጡ የሕገ መንግሥት ድንጋጌዎች ሌላ በዋናነት ሕገመንግሥታዊ ሥርዓት በዳበረ የሕገመንግሥት ትርጉም በተከታታይ ትውልዶች እየደረጀ የሚሄድ በመሆኑ ቀጣይነት ያለው ተከታታይ እና እያደገ የሚሄድ ሥራ ሊሆን ይገባል።
የተቃዋሚዎች የልዩነት ሃሳብ
የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሰሞኑን ከሕገመንግሥት አጣሪ ጉባዔ የቀረበለትን የሕገመንግሥት ትርጉም ጉዳይ ላይ ተወያይቶ የመጨረሻ ውሳኔውን አሳርፏል። በዚህ ውሳኔ መሠረት 6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ እንዲራዘም ተወስኗል። በዚህ የምክር ቤቱ ውሳኔ መሠረት አሁን በሥራ ላይ የሚገኘው መንግሥት የኮቪድ 19 ወረርሽኝን የሕዝብ የጤና ሥጋት አለመሆኑ በሚመለከታቸው የጤና እና ሌሎች የውሳኔ ሰጪ አካላት ከተረጋገጠበት ጊዜ ጀምሮ ከ9 – 12 ባሉት ወራቶች ውስጥ
6ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ተከናውኖ እስኪተካ ድረስ በሥራ ላይ ይቆያል።
ይህ ውሳኔ እንደተሰማ አንዳንድ ፖለቲካ ፓርቲዎች ቅሬታቸውን ወዲውኑ ባወጡት መግለጫዎች አንጸባርቀዋል። አንዳንድ ኢትዮጵያውያንም በማህበራዊ ድረገጾች ሀሳባቸውንና ሥጋታቸውን አጋርተዋል። በስፋት ከተነሱት ቅሬታዎችና ትችቶች ሚዛን የሚደፋው “የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ቀጣዩ ምርጫ ያለገደብ እንዲተላለፍ መወሰኑ ትክክል አይደለም” የሚል ነው። “ኮቪድ 19 የሕዝብ ጤና ሥጋት አለመሆኑ ሲረጋገጥ” የሚለው ለገዥው ፓርቲ ልቅ የሥልጣን ጊዜ የሚሰጥ ነው በማለት አምርረው ተቃውመዋል።
አንዳንዶች የሕገመንግሥት አጣሪ ጉባዔው ባለሙያዎችን ያሳተፈበት መንገድ አግላይ ነበር ሲሉ ሞግተዋል። በእነሱ መከራከሪያ መሠረት በሕግ እና በሕገመንግሥት ጥናት ሁለተኛ ዲግሪና ከዚያ በላይ ያላቸው ብቻ እንዲሳተፉ የተደረገበት አግባብ ትክክለኝነት ላይ ጥያቄ ያነሳሉ። በአገራዊ ጉዳይ ላይ ዲግሪ ያለው፣ የሌለው በሚል መከፋፈል አግላይነት ነው ያሉ ሲሆን እንደምርጫ ቦርድና እንደጤና ሚኒስቴር ያሉ ተቋማት ተጋብዘው ሃሳባቸው እንደሰጡት ሁሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጉዳዩ ላይ ሃሳብ እንዲሰጡ አለመደረጉን በጉድለትነት ይነቅፋሉ።
እንደማሳረጊያ
ኮቪድ 19 ወረርሽን ተክትሎ ዘንድሮ ሊካሄድ የነበረው ምርጫ የተሸጋገረበት ብቸኛ ምክንያቱ ከሕዝብ ጤና ጥበቃ ጋር የተቆራኘ ነው። የምርጫ ሒደቶች ሰፊ የህዝብ ተሳትፎን የሚፈልጉ ናቸው። የምርጫ ማእከላት ማደራጀት፣ ባልሳሳት ከ250 ሺ በላይ ምርጫ አስፈጻሚዎችን መመልመልና ሥልጠና መስጠት፣ 50 ሚሊዮን መራጮችን መመዝገብ፣ የእጩዎች፣ የጋዜጠኞች፣ የታዛቢዎች ምዝገባና እንቅስቃሴ፣ የምረጡኝ ቅስቀሳ፣ የምርጫ ቁሳቁሶችን ከቦታ ቦታ ማንቀሳቀስና ማሰራጨት፣ የድምጽ መስጫ እለት ግርግሮች ለኮቪድ 19 ስርጭት ምቹ መሆናቸው የተረጋገጠ ነው። ይህም ሆኖ ግን ሁሉንም ነገር ከሕዝብ ሳይሆን ከፖለቲካ ጥቅማቸው አንጻር ብቻ በማየትና በማስላት ምርጫው መካሄድ አለበት የሚል ግትር አቋም በመያዝ የሕዝብን ጤና ጉዳይ በካልቾ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖር እንደአንድ ትልቅ ተግዳሮት ማየት ይቻላል።
ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች እንደሚሉት፤ በእንዲህ አይነት ለአገራችንም አዲስ በሆነ የሕገመንግሥት ትርጉም ክስተት መሰል ቅሬታዎችና ተግዳሮቶች መኖራቸው የሚጠበቅ ነው። ተቃውሞንም በሰለጠነ መንገድ ማቅረብና ማንሸራሸርም ሕገመንግሥታዊ አካሄድ ነው። ከዚህ በተቃራኒው ግን ከመስከረም ወር 2013 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ “መንግሥት የለም” በሚል ለአመጽና ብጥብጥ ከወዲሁ መዘጋጀት በመንግሥትና በሠላማዊ ሕዝብ ላይ ግልጽ ጦርነት ማወጅ ይሆናል። እንዲህ ዓይነቱን አካሄድ መንግሥት እንደማይታገስ በተደጋጋሚ ያስጠነቀቀውም ከምርጫ ውጪ መንግሥታዊ ሥልጣንን በኃይልና በጉልበት ለማግኘት መሞከር ኢ- ሕገመንግሥታዊ በመሆኑ ጭምር ነውና የሚደገፍ ነው
አዲስ ዘመን ሰኔ 13/2012
ፍሬው አበበ