…….ዛሬ ላይ ከምንግዜውም በላይ ከተፈጥሮ ሁኔታ ያፈነገጡ ድርጊቶች፣ ጎጂና ሱስ የሚያሲዙ አደንዛዥ እጾች በመላው ዓለም በመንሰራፋት ላይ ይገኛሉ፤ ድርጊቶቹ እየተስፋፉ ሄደው የወደፊት ትውልድ ላይ ጥላ አጥልተው ይገኛሉ። እነኝህ ሁኔታዎች ትውልድን በማሽመድመድ ላይ ይገኛሉ። በፊት እንሰማው ከነበረው ይልቅ ዛሬ ላይ ግብረ ሰዶም ይበልጥ ተቀባይነት እንዳገኘ ማንም አይክድም። ድርጊቱ በአንዳንድ አገሮች ይብስ ብሎ የሕግ ድጋፍ ሁሉ እየተሰጠው ይገኛል። ሁኔታውን ያነሳነው ከስነምግባሩና ሌሎች ጥያቄዎች ውጪ ከሰርቫይቫል ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ስላለው ነው፤ ከተፈጥሮ ህግ ጋርም ተቃርኖ ስላለው ነው። በተፈጥሮ አንድ ዘር ህልውናው ከትውልድ ትውልድ የሚሻገረው ወይም ሊቀጥል የሚችለው በመራባት እንደሆነ የሚታወቅ ነው፤ “ርቢ” ሲባል ደግሞ የሁለት ተቃራኒ ጾታዎችን ግንኙነትና መዋጮ የሚፈልግ የማይሻር ተፈጥሯዊ ሕግ ነው፤ ከዚህ በተቃራኒው የሚጓዝ መጨረሻው ግልጽና አጭር ነው፤ ትውልዱ አይቀጥልም።
በተለያዩ ማማለያዎች የተለወሱ ወጥመዶች ወጣቱን ትውልድ እየተፈታተኑት ይገኛሉ፤ በሥነ ምግባር ረገድ ልቅ የሆነው ይህ ዓለም የሚያሳድረው ተጽዕኖ በርካታ ወጣቶች ግብረ ሰዶም ለመፈጸም እንዲነሳሱ እያደረጋቸው ይገኛል። ከተፈጥሮ ህግ በተቃራኒ ሄዶ ተፈጥሮን ያሸነፈ አንዳች ነገር ማግኘት አይቻልም:: ታዲያ ሰዎች ቀድሞ ተሸናፊነቱ በታወጀ ነገር ላይ ለምን ይሳተፋሉ? ብለን ሁኔታውን ቀርበን ብንመረምረው አብዛኞቹ የግብረሰዶም ግንኙነቶች የሚፈጸሙት ጤናማ ባልሆነ የአኗኗር ዘይቤ ውስጥ ማለትም በአደንዛዥ እጽ፣ በአልኮል መጠጥ፣ ወይም ቅጥ ባጣ ዝግጅት ተጽእኖ ስር ሆኖ እናገኘዋለን። ከሁኔታው ሚስጢራዊነት አንጻር ድርጊቶቹን በቀጥታ መፋለም ባይቻልም ሊጠፉ የተዘጋጁትን ህፃናትና ወጣቶች በማስተማር ልንታደጋቸው ይገባል:: የጠፉትም ላይ ቢሆን በትጋት ለማረም መሞከር አለብን። ውሀ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው እንደሚባለው ሁሉ ይሄም ህይወት ጣፋጭ መስሎ ትውልድ አጥፍቶ የማንወጣው ማጥ ውስጥ ከመግባታችን በፊት በሙሉ ልብ ድርጊቱን መቃወም አለብን።
በተለይ ደግሞ ከተፈጥሮ ውጪ አፈንጋጭ ሁኔታዎችን በመፍጠር የመጥፊያ መንገዶችን የሚያመቻቹ ነገሮችን ነቅሶ በማውጣት ትውልድ ላይ መስራት ያስፈልጋል። እነኝህ የመጥፊያ መንገዶች አደንዛዥ እጾችና የአልኮል መጠጦች ናቸው። አልኮል መጠጣትና ትንባሆ መጠቀም በአብዛኞቹ አገሮች ሕጋዊና የተለመዱ ድርጊቶች ናቸው፤ ነገር ግን ሁለቱም ሱሰኝነትን የሚያመጡ ናቸው። አልኮል መጠጥን ያለ አግባብ መጠቀም በዓለም በርካታ የጤና፣ የቤተሰብ እንዲሁም የማኀበራዊ ችግሮችን እያስከተሉ እንደሆን ግልፅ ነው። ላለፉት በርካታ ዓመታት ሲጋራ ማጤስ በሃብታም አገሮች ጭምር ዋነኛው የሞት ምክንያት ሆኖ ቆይቷል፤ በርግጥ ችግሩ አሁንም አለ፤ እየቀነሰ ቢመጣም። በበለፀጉ አገሮች የሚኖሩ ሰዎች ሲጋራ ማጤስ ወይም ትንባሆን በተለየ መንገድ መጠቀም የሚያስከትለውን ጉዳት በመገንዘብ ሲጋራ ማጤሳቸውን በማቆማቸው ምክንያት የትምባሆ ወይም ሲጋራ አምራች አገሮች አዲስ ገበያ ለማግኘት ስምሪታቸውን ወደ ሦሥተኛው ዓለም ሕዝብ አዙረዋል፤ ይህ ሁኔታም የሚያሳየው ሁኔታው እየጨመረ ሊመጣ እንደሚችል ነው።
በመጪው ትውልድ ላይ የተጋረጡ አደገኛ አደንዛዥ እፆችና መድኃኒቶች
ከአልኮል መጠጥና ከትምባሆ በተጨማሪ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚገኙ የተለያዩ ሰዎች ሕገወጥ አደንዛዥ እጾችንና መድኃኒተቶችን ይጠቀማሉ። እነዚህ ከስፍራ ስፍራ የሚለያዩ ሲሆኑ እነርሱም ማሪዋና (ዊድ፣ፓት፣ ግራስ፣ ሲንሴሚላ፣ ሞታ፣ ሐሽሽ፣ ጋንጃ)፤ ኦፒየም (ሄሮይን፣ ሞርፊን፣ ስማክ) እና ኮኬይን (ክራክ፣ ስኖው፣ ሮክ) የመሳሰሉትን የአደንዛዥ እጽ ዝርዝር ያጠቃልላል።
በተለያየ መንገድ የሚወሰዱ አደንዛዥ እፆች
በከተማ በሚገኙ የጎዳና ተዳዳሪዎች ዘንድ እየታየና እየጨመረ የመጣው ችግር ደግሞ እንደ ሙጫ፣ የቀለም ማቅጠኛ፣ የጫማ ቀለም፣ ነጭ ጋዝና የንፅህና መጠበቂያ ኬሚካሎችን በማሽተት ለሱስ የመጋለጥ ችግር ነው። ከዚህ በተጨማሪ አንዳንድ ሰዎች ጠንካራ የሕመም ማስታገሻዎችን፣ ማነቃቂያ መድኃኒቶችን፣ የምግብ ፍላጎት መድኃኒቶችን ያለ አግባብ ይጠቀማሉ። የዚህ
ሁኔታ ድምር ውጤት ደግሞ አሁን ላይ ባይሰማንም አንድ ቀን ግን ሚዛኑ በዝቶ ተያይዞ መውደቅ የሚያመጣ እንደሚሆን መገመት አይከብድም።
እየጨመረ የመጣው የጎዳና ላይ ህይወት
በተለያዩ ሱሶች ውስጥ የሚገኙ ሰዎች አደንዛዥ እጾችን በመዋጥ፣ በመወጋት፣ በማጤስ፣ በማኘክ ወይም በአፍንጫ በማሽተት ይጠቀማሉ። ይህ ሁኔታም በአካል፣ በአእምሮና ስነልቦና ላይ የተለያዩ ጠንቆችን ያስከትላል። ለምሳሌ ኮኬይን ሰዎች ሲጠቀሙት ለጊዜው ኃይልና ደስታን ይሰጣል። ነገር ግን ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከፍተኛ ድካም፣ ብስጭት፣ ድካምና የመፍዘዝ ስሜትን ያስከትላል። እንደ ኦፒየም፣ ሞርፊንና ሄሮይን የመሳሰሉት አደንዛዥ እጾች ሲወሰዱ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ የዝምታና የመዝናናት ስሜት የሚያሳድሩ ሲሆን ቆይተው ግን ራስን መቆጣጠር አለመቻልና ሕሊናን የመሳት ችግር ሊያስከትሉ ይችላሉ። እንደማሪዋና ያሉት ደግሞ የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ሰዎች በገሃዱ ዓለም
የሌሉ ነገሮችን እንዲያስቡ ወይም የደስታ ስሜት እንዲያድርባቸው፣ በቅዠት ዓለም ውስጥ ገብተው እዲዋዥቁ ያደርጋሉ። ይህ ሁሉ ለምን ? የሰው ልጅ እውነት ምርጫ የለውም ? አስተያየት ስጡበት….
ሰዎች አደንዛዥ እጾችን ለምን ይጠቀማሉ?
በመሰረቱ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ አደንዛዥ እጾችን የሚጠቀሙት አስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታዎች ሲያጋጥማቸው፣ ረሃብና ጥማትን ለመቋቋም፣ አንዳንድ መጥፎ ትውስታዎችን ለመርሳት ወይም በየዕለቱ የሚገጥማቸውን የሕይወት ስቃይ ለማቃለልና ለመርሳት ሲሉ እንደሆነ ይገመታል። ከዚህ ውጪ ያሉት ደግሞ በቅብጠት ነው። ነገር ግን አንድ ጊዜ አደንዛዥ እጽ መጠቀም ከጀመሩ፣ ለሱሰኝነት ስለሚጋለጡ ከዚህ ችግር መላቀቅ ያቅታቸዋል። በመሆኑም ለመተው ሲሞክሩ ከፍተኛ የሰላም ማጣት፣ የጤና መታወክ ወይም አንዳች የኃይል እርምጃ የመውሰድ ባሕሪ ያድርባቸዋል። የሚፈልጉትን አደንዛዥ እጽ ለማግኘት ሲሉም
አብዛኘውን ጊዜ የተለያዩ የወንጀል ድርጊቶችን መፈፀም፣ ምግብ መተው፣ ከቤተሰብ መራቅና ሌሎች ጤናማ ያልሆኑ ድርጊቶች ላይ በሙሉ ይሳተፋሉ፤ በመሆኑም አደንዛዥ እጽን መጠቀም የሚያመጣው ችግር ለመላው ቤተሰብና ለማኀበረሰብ ከፍ ሲልም ለሃገር ጭምር እዳው ይተርፋል።
ሰዎችን አፈንጋጭ ወደ ሆነ ልማድ የሚመራቸው ምንድን ነው?
አንዳንድ አደንዛዥ እጾች፣ ለምሳሌ ኮኬይንና ሄሮይን በከፍተኛ ደረጃ ሱስ የሚያሲዙ ናቸው፤ አንዴ ከተቀመሱ ሳይቋረጥ የመውሰድ ፍላጎት ያሳድራሉ፤ ሌሎች ደግሞ ለረዥም ጊዜ ከተወሰዱ ነው ለሱስ የሚዳርጉት፤ ሱስ ለከፍተኛ የጤና ቀውስ የሚዳርግ ወይም ለሞት የሚያበቃ አደገኛ ወጥመድ ነው። ነገር ግን በቆራጥነትና ከሌሎች ድጋፍ በማግኘት ከሱስ መላቀቅ ይቻላል። አደንዛዥ እጽ መጠቀም የጀመረና ሱስ ያደረበት ሰው እጹን መጠቀም ሲያቋርጥ ከፍተኛ የስነልቦና ችግር ያጋጥመዋል፤ ይህ ሁኔታ ሱስን መቋቋም ያለመቻል ስሜት ነው። በመሆኑም ግለሰቡ የብስጭት፣ የመፍዘዝ ወይም የቁጣ ስሜትና ጠባይ ይታይበታል፤ ከዚህም በላይ ግለሰቡ አደንዛዥ እጹን መውሰድ ካቋረጠ መኖር እንደማይችል ይሰማው ይሆናል።
ወደ አገራችን ስንመለስ ሁኔታው የሚገኝበትን ደረጃ ለመገመት ሰፊ ጥናት የሚያስፈልግ ቢሆንም አእምሮን የሚያነቃቃው ጫት የተባለው አደንዛዥ እጽ ግን በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ ትውልድን እያሽመደመደ እንደሚገኝ ለማየት ብዙ ጥናት የሚፈልግ አይደለም፤ ጫት በኢትየጵያ ያለው የገበያ ድርሻም ሆነ ማህበራዊ ተፅዕኖው ከፍተኛ ነው። ጫት ሱስ የሚያሲዝ በመሆኑ ተጠቃሚዎች በጫት ላይ የስነልቦና ጥገኛ ሆነዋል፤ አስተማሪዎች ሳይቀሩ ተማሪዎቻቸዉን ጫት በጉንጫቸው ይዘው በክፍል ዉስጥ እንደሚያስተምሩ ሲነገር እንሰማለን። ሁኔታው በተለይ በአገሪቱ የምስራቅ ክፍል ተፅእኖው በግልፅ ይታያል። በተለያዩ የማኀበራዊና የፖለቲካ ችግሮች ምክንያት ለሚፈጠሩ ሁኔታዎች ግለሰቦች የሚገጥማቸውን የሞራል ውድቀት ጫት በመቃም እንደመውጫ መንገድ አድርጎ ማየት በስፋት ይታያል።
በኢትዮጵያ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ግለሰቦች በጫት ሱስ ውስጥ ይገኛሉ
ከዚህ ትውልድን ከሚያሽመደምድ ችግር ለመውጣት በተለይ ወጣቱ ትውልድ ላይ ብዙ መሰራት እንዳለበት የሚታይ ነው፤ ሁኔታው ግለሰቦችን የሚመለከት መስሎ ቢታይም ሄዶ ሄዶ በድምር ውጤት የማኀበረሰብና የአገር ውድቀት እንደሚሆን መገንዘብ አይከብድም፤ ሱሰኝነት የሚያስከትሏቸውን ችግሮች ለማቃለል የበኩላችን ማድረግ አለብን፤ የሚጠበቅብንን ተግባራዊ ፍሬ ሃሳቦች ላይ በመንቀሳቀስ የበኩላችንን ልንወጣ ይገባል።
• ከአደንዛዥ እጾች ሱስ ለመላቀቅ ሙከራ በማድረግ ላይ ያለን ሰው በተቻለ መጠን መርዳት፣ ድጋፍ መስጠትና መንከባከብ፤ እነኝህ ሰዎች የሚያሳዩት የባሕሪ ለውጥ ከሱሰኝነት የመነጨ ስለሆነ ችግሩን ተቋቁሞ ሳይሰለቹ መርዳት ያስፈልጋል። • ቀደም ሲል ሱሰኛ ሆነው በጥረታቸው ከችግሩ የተላቀቁ ሰዎችን በማሰባሰብና ድጋፍ ሰጪ ቡድኖችን በማቋቋም ሌሎች ከሁኔታው እንዲላቀቁ መርዳት። • ቤተሰቦች፣ ትምህርት ቤቶችና የጤና ባለሙያዎች ስለአደንዛዥ እጾችና ስለግብረ ሰዶም አደገኛነት በማስተማር ማስገንዘብ ይኖርባቸዋል፤ በወጣቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችንም ለመከላከል፣ ለመዝናናት የሚረዱ ሌሎች ጤናማ መንገዶች መኖራቸውን ማስተማር ተገቢ ነው። • ወጣቶች ለእንዲህ አይነቱ ችግር እንዳይጋለጡ በህብረተሰብ ውስጥ ያሉና ችግሩን ሊያባብሱ የሚችሉ ሁኔታዎችን ማስተካከል ያስፈልጋል፤ ስራ አጥነት፣ ረሃብ፣ የጉልበትና የሃብት ብዝበዛ እንዲሁም ሌሎች ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት መፍታት ያስፈልጋል፤ ጤናማ የሆነ ማኀበረሰብ ጤናማ ባልሆነ ማኀበረሰብ ላይ መገንባት ስለማይቻል ባለሃብቶችም ሰዎችን በማበልፀግ የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል፤ እንዲሁም ኋላ ሄዶ ሄዶ ውድቀት የጋራ ስለሚሆን፣ ነገሩን በጋራ መፍታት ያስፈልጋል። • ሱሪያቸውን ዝቅ ያደረጉ ወጣቶችም ከፍ በማድረግ የአሁንም ሆነ የወደፊት ሕልውናቸውን በሚያረጋግጥ ሁኔታ ስምሪታቸውን ማስተካከል አለባቸው።
ምንጭ ሰርቫይቫል 101
አዲስ ዘመን ሰኔ 13/2012