ሐሜት ጠባያዊ ነጸብራቅ ነው። ሐሜት የሚያማውን ሰው እያዋራ ታሚው ሰው መልስ በማይሰጥበት ርቀት ላይ የሚገኝበት አንድ ወይም ከአንድ በላይ የሆኑ ሰዎች፣ በሹክሹክታ የሚከውኑት የአፍ ሥራ ነው። አዎ አፋቸው ነው፤ ሥራውን የሚሰራው፤ መቆያ ሆኖ የሌላውን ሰው ማንነት የሚያምሰው። ለዚህ ነው፤ “ያውሩ ሥራቸው ነው”፤ ያለው አንድ ወዳጄ።
ስሙን መጥቀስ ያልፈለገ አንድ ወዳጄ በአንድ የግጥም ሥራው ላይ ፡-
“ራሱን ማዳን ያልቻለ ትናንሽ ዓሳ ሁላ፣
የሚሸሸግበት ቢያጣ ቢጠፋበት የባህር ጥላ፣
ዓሣ ነባሪው ሳያየው ከጀርባው ይሆንና ፣
“አማረብኝ ብሎ እኮ ነው፤” ብሎ ለብጤው ያማዋል፣
ዓመል ሆኖበት እንጂ፤ ለ”አቅመ-ቢስ” ምን ይነግሯል። ”
(ያልታተመ ትርጉም)
ሐሜት እግረኛ ነው፤ መዋያ ቢኖረውም ማደሪያ ስፍራ የለውም። ከተናጋሪው ተነስቶ ወደነጋሪው በሄደበት እግር ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ወደሚሰማው ይነጉዳል። ሐሜት በባለአክናፍ ፈረስ መንግስተ ሰማያት ሄደ እንደተባለ ሆኖ፣ ሲበርር አያርፍም ይሄዳል፤ እዛም መላእክቱ ካላበረሩት። ሐሜት ደንባራ በቅሎ ነው፤ ከነጋሪው ወደሰሚው ሲያልፍ “ወደቀ ተሰበረ ነው፤ ተሰበረ ሽባ ሆነ ነው፤ ሽባ ሆነ መተት ይጠራል፤ መተቱ ፀበል ያጠጣል፤ ፀበሉ ካላዳነውም ከንፈር መጣጩን ይሰበስባል፤” ሐሜት የማይናቅ አፍራሽ ጉልበት አለው፤ ቢችል የሚታማውን ሰው አንጠልጥሎ ወደመቃብር አፍ ይወስዳል።
የ7ኛ ክፍል ተማሪና የ13 ዓመት ልጅ የሆነችውን ልጁን፣ ደም መቷት ያገኘ አባት፣ ልጁን በጋቢው ጠቅልሎ ወደሆስፒታል ይዟት ሲበርር ያዩ ሰዎች፣ ከሆስፒታል እስኪመለስ ቤቱን በጠያቂ ሞልተው ሌላውን ልጁን ሲያጽናኑ ደረሰ።
እንደገባም አላመነታም፤ ስለተቆረቆራችሁልኝ አመሰግናለሁ። አሁን ደህና ናት፤ ብሎ ምስጋና ማቅረብ ሲጀምር በእሜድ ጠና ያሉ እናት ተነስተው፤ “አንተ ምን ሰይጣን ቢሰርርህ ነው፤ ይቺን እንቦቃቅላ ህጻን ተነስተህ የምትደፍረው….. ብለው ከመናገራቸው እዚያ የነበረው ሰው ሁሉ በተወዛገበና ግራ በሚያጋባ ድምጽ መንጫጫት ፣ ሲጀምር በገዛ ቤቱና በገዛ ጊቢው ያልጠበቀውን “ውርደት የቀመሰው” አባት፣ በረንዳው ላይ በድንጋጤ ዘርፈጥ ከማለት ውጭ ያደረገው ነገር አልነበረም ።
ፈንጠር ፈንጠር ብለው ተቀምጠው የነበሩ ጎበዛዝትም ጠጋ ብለው “ይሄንን እንስሳዊ ባህሪ ከየት አመጣኸው?”፤ አሁኑኑ ፖሊስ ጣቢያ እንሂድ ብለው ሲያንገራግሩ እንደምንም አቅሟን ሰብስባ የተነሳችው ታማሚ ልጁ በሃይለኛ ድምጽ “አባቴን ተዉት እንጂ የምን ድፍረት፣ ስለምን ግፍ ነው፤ ስትል አባትየውን “ለጥብስ አድርሶ”፣ የነበረው የሐሜት ሰራዊት ነፋስ እንደገባው ውሃ ተገምሶ ከቤቱ ውልቅ ውልቅ እያለ ተነስቶ መሄድ ጀመረ። እማማ አስካለ እማማ…ብሎ ተጣራና ፣ “ማነው እንዲህ አደረገ ያላችሁ?” ሲል ይጠይቃቸዋል።
ትንሹዋ ልጅህ ስታለቅስ ሰምቶ፣ ግርማ ባለሱቁ ሲያናግራት “አባባ ደም በደም አርጓት ይዟት ሄደ፤ ያለችው እርሷ ናት ፤ ብሎኛል። የ8 ዓመት ልጅ ምስክርነት፤ ያስከተለውን የተዛባ መልእክት ለማጣራት እንኳን ሳትፈልጉ፣ ምነው ወነጀላችሁኝ ?.ይ…ሄ ደግ ነው እማማ አስካለ…” ሲል የተደናገጡት አስካለ ታዲያ ምን ሆና ደማች ሲሉት ፤ ኪንታሮት ነበረባትና የባህል መድሃኒት ተቀብታ ነበረ፤ እርሱ መሰለኝ፣ የችግሩ ምንጭ። የሆነው ሆኖ ግን ታክማ ተሽሏት መጥታለች። እማማ አስካለ… አልሰሙትም ። መስማት የፈለጉት እንደ መንደሩ ሰው ሁሉ “ጉድ ጉድ” የሚሉበትን ወሬ ነበረና አልሰሙትም።
ሐሜተኛ ሰው መስማት የሚፈልገውን ክፉ እንጂ፣ ደግነትማ ወሬ የሚነሳ ከንፈር የሚያስመጥጥ አይደለም፣
መልካምነት ለሐሜት አይመችም፣ ቸርነት የሰው ሥጋ ለማንኮር አያገልግልም። እናም ሐሜተኞች ስለሰው ደግ ስትነግሯቸው ይታመማሉ። ባለፈው ለታመመው እግር ኳስ ተጫዋች እኮ የህክምናውን እና የትራንስፖርቱን ወጪ እገሌ የተባሉት ሀብታም ለገሱት ፤ ሲባል የሰማ ሐሜተኛ ድንቅ ነው – እፁብ ነው – የሚል ቃል ከአፉ አይወጣም። “የ… ደላው … ይላል፤ ቃሉን ለጥጦ ከአፉ ላይ፤ እያወጣ፣ “እርሱማ ምን አለበት፤ የደሃን ላብ አሟጥጦ እየበላ ቆንጥሮ የኳስ ተጫዋች ኩላሊት፣ የዘፋኝ ጉበት ያሳክም። ይገርማል ፤ ባለፈውም በተመሳሳይ ኩላሊት የታመመ ልጅ አሳከመ አሉ፤ እርሱ ከኩላሊት ህክምና ምን የሚያዛምደው ነገር አለ? ሲል ትርተራውን ይጀምራል። አንድ አራት ኩላሊታቸውን የታመሙ ልጆችን ህንድና ባንግላዴሽ ነው፤ ወስዶ ያሳከመው። ”
“እናስ?” አትበሉት፤ ካላችሁት ግን ያለጥርጥር ኦርጂናሉን ኩላሊት አስወግዶ አርተፊሻል ሊያስገጥምላቸው መሆኑን ከውስጥ አዋቂ ሰምቻለሁ”፤ ብሎ የዚያን ሰው የተባረከ ስም አውርዶ መሬት ለመሬት ይጎትተዋል። ደግነት በእርሱ መዝገበ-ቃላት ውስጥ ሸፍጥ ተብሎ ነው፤ የተተረጎመዋ።
ሐሜተኞች ስለሌሎች ደግ ያልሆኑ ነገሮችን በመናገር የሚዝናኑ ስለሰውየው አወቅን የሚሉትን ሲያወሩ የደስታ እና የጭንቀት ቅልቅል ሆርሞን የሚረጩ ግብዞች ናቸው። ስለዚያ ሰውም በዝርዝር ባወሩ ቁጥር ቁጣቸው ውስጣዊ መፍነክነካቸው፣ እየጨመረና እየበረታ፣ ሣቅ በቀላቀለ ድብልቅ ስሜት እየተናጡ ነው፤ የሚቀጥሉት። ምስኪኖች!!
በዚህ ሂደትም ፣ ራሳቸውን እንደተጎዱና የበደል አሳር እንደተቀበሉ በማስመሰል ተውኔቱን የሚጫወቱ ቆሻሻቸውን ሌላውን በማሳደፍ ማጠብ የሚፈልጉ “ጉዶች” ናቸው። አንድ ሰው ስለሌላው ሰው በፊትህ ሲያማ ሁለት ሶስት ገራሚ ነገሮች እየፈጸመ መሆኑን ልብ በል። አንደኛው ነገር ስሌላኛው ሰው ጉድፍ ሲያወራ የራሱን ንጽህና ለገበያ እያቀረበ ነው። ሁለተኛ ደግሞ፣ ላንተ ስለሌላው ሰው ሲያወራ ሐሜት የሚሰማ ጆሮ እንዳለህ ገምቶና አሳንሶህ መሆኑን ተገንዘብ። ሶስተኛ፣ አንተም ተከተለኝና ይህንን ሰው በሐሜት አለንጋ እና ስለት እንቆራርጠው ብሎ ቡድን እየሰራ ነው። ስለዚህ አንተ ሶስቱንም አለመሆንህን ማሳየት አለብህ።
በዚህ ጊዜ ስልክህን አውጣና ለብቻችን ስለእርሱ ከምናወራ ልጥራውና ፊት ለፊት ያደረሰውን በደል እንንገረው ትለዋለህ (እድሜ ለቴክኖሎጂ) ያኔ ዝም ካለህ የሆነ እውነት ከእርሱ ጋር እንዳለ መገመት ትችላለህ፤ መቀበጣጠርና መዛለፍ ከጀመረ ግን ዋሾ ቀጣፊና አስመሳይ መሆኑን አውቀህ ትሰናበተዋለህ።
ሌላ ደግሞ በቁርጥ ቃል ሰው በሌለበት ወሬ ማውራት ይሸክከኛል ፤ ሰውየውን ነገ ማለዳ ወይም ከሰዓት በኋላ ሳየው መድረሻ ነው የማጣው፣ ስለዚህ ተወኝ አትንገረኝ፤ ካወራኸኝ ግን ፣ ሄጄ ነግረዋለሁ፤ በለው። በዚህ ጊዜ “ሂድና ንገረው” ካለ ግን፤ እርሱ ፊት ለፊት ሊያወራው የፈራውን ሰው፤ አንተ እንድትሰድብለት ተላላኪው ሊያደርግህ አቅዶ ነው፤ የሚነግርህ ማለት ነው። ስለዚህ እንደሱ ከሆነ “ጆሮዬ የኔ ነው – አልሰማም” በልና አሳፍረው። እንዲህ ኣይነት ሰዎች በአለባበሳቸው “ቂቅ ያሉ” ፣ ሸሚዞች የሚለዋውጡ፣ ሲያዩዋቸው ትልቅ ሰው የሚመስሉ ትናንሾች ናቸው። ልብሳቸው ልባቸው አይደለምና አትፍሯቸው ወይም አትፈሯቸው።
ሐሜተኞች ፣ ስለሚያሙት ሰው አወቅን ከሚሉት ነገር ለአንዱም በቂ ወይም ግማሽ ማስረጃ እንኳን ማቅረብ የማይችሉ ወሬውን ከእነርሱ ከባሱ ወሬኞች የለቃቀሙት የተራ ሐሜት ጥርቅም ነው። የሚያሙትን ሐሜት ከመለማመዳቸው የተነሳ ደንቀፍ እንኳን ባያደርጋቸው
አይድነቃችሁ፤ ፈሪዎች ስለሆኑ ግን፤ በሰውየው ፊት አያወሩትም፤ እንዲያውም ሰውየው ድንገት ቢከሰት በፊቱ ሲሽቆጠቆጡና አቅፈው ጉንጩን ወይም ትከሻውን ሲስሙ ብታዩዋቸው እንዳይገርሟችሁ። የቆሙበት ብካይ ያለበሳቸው አመዳም ጠባይ ውጤት ነውና።
“ሐሜት ቃር መሆኑን እያወቀው ትርፉ፣
ሰው ለምን ይሆናል እያደረ ክፉ ። ” የሚል ቆየት ያለ የሀገራችንን ግጥም አስታውሳለሁ።
“ሐሜት ሰው መብላት ነው፤ ያለጨው አዋዜ፣
እያደር ይቆጫል ሲያልፍ ይኼ ጊዜ።
ስለዚህ ሲታማ ፤ ለእኔ ብለህ ስማ፣
ነውና ነገሩ ፤ ያም ሲያማ ያም ሲያማ!!” (ያልታተመ)
በተለይ በቤተ-ዕምነት ውስጥ እንዲህ አይነት ሰዎች ሲያጋጥሟችሁ፣ አትደናገጡ። ሰንበላጦች የትም አሉ፤ ዲያብሎስም እኮ ከክብሩ የተነሳ በአምላኩ ፊት ከእርሱ የሚቀድም ያልነበረው፣ በውበቱ ያማረና እንከን የማይወጣለት እንደንጋት ኮከብ የሚያበራ ባለፀዳል እኮ ነው፤ እና አትደናገጡ። ድምጻቸውን ከሰው በላይ ከፍ አድርገው “ተመስገን” ሲሉ ብታይዋቸው እንዳትደናገጡ። ሰይጣንም ወደሲዖል ሲወስድ ታላቁን የገነት በር አሳይቶ ነው!!
ሐሜተኞች ደግ የሚመስሉ ክፉዎች፤ ትሁታን የሚመስሉ፣ ትዕቢተኞች ናቸው። ሊነግሯችሁ ሲነሱ፣ ጨዋ የሚመስል ነገራቸውን አስቀድመው ነው፤ ወደ ነውረኛ ጉዳያቸው የሚሸጋገሩት። ስለዚህ በትሁት አቀራረባቸው እንዳትሸወዱ፣ ደግ በሚመስለው ቃላቸው እንዳትበለጡ።
ማማት የለመደ አፍ ወዳጁን ብቻ ሳይሆን ወላጁንም ያማል፣ ማማት የለመደ አፍ አለቃውን ፣ ጓደኛውን ወንድምና እህቱን ከማማት ወደ ኋላ አይመለስም። ውግዘትና ግዝት ልማዱ ነው። ስለዚህም ነው፡-
“ማማት የለመደ አፍ ሙት እናቱን ያማል፣
ወልዳኝ ሳትወደኝ ነው፤ የሞተችው ይላል። ” ተብሎ የተገጠመው። (ያልታተመ)
አዎ፣ ከቶውንም የማይጠቅመንን ዝባዝንኬ ወሬ ሲጠቀጥቁብን በዝምታ አንሞላላቸው። የማይመለከተኝን ላለመስማት መብት አለኝ ማለትን እወቁበት።
እና ምን ለማለት ነው? በየቤተ ዕምነቱ፣ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ሲዘምሩ፣ ተመስጠው እንዳይመስላችሁ ዓይናቸው “የእንትና ምንነት ላይ”፣ እንጂ ወደአምላክ አይደለም። “ይህንን ስልህ አንተ በጣም መጎዳትህን ሳይ አሳዝነኸኝ ነው፤ እኛ፣ ስንት ነገር ችለን ነው፤ የቆምነው፣” ሊሉህ ይችላሉና ሐረጋማ በሆነው ወጥመዳቸው ውስጥ እንዳትገቡ ተጠንቀቁ። በፍጹም አልሰማም እንኳን ማለት ቢያቅትህ፣ ማማሟቂያ ድምጸትም ሆነ ቃል ከቶውንም አታበድራቸው። እዚያው ማስተዋል ለጎደለው ጠባያቸው ትተሃቸው ዞር በል። ጎንዶሮ ለእነዚህ ፣ የአስመሳይነት ባለሰንደቆችና የበድን ቃል አመንጪዎች፤ ምክንያቱም የእነርሱ ቃል ሞት እንጂ ህይወት ፣ ጥላቻ እንጂ ፍቅር ፣ መለያየት እንጂ ህብረትን የሚያመጣ አይደለም።
እኛ ደግሞ በእጅጉ ህብረት ፣ መከባበር፣ ፍቅርና ጽኑ መደማመጥ ያስፈልገናል። ከእነአሉብን ጉድለቶች የሚያስተሳስረንና የሚያመሳስለን ነገር እጅግ ብዙ ነው። ብዙውን መልካም ይዘን፣ ጥቃቅኑን አረም ነቅሰን እያወጣን ወደፊት መጓዝ አለብን። ይህም ለቤት፣ ለመ/ ቤት እንዲሁም ለሐገር ይበጃልና!!
አዲስ ዘመን ሰኔ 13/2012
አገልጋይ ዮናታን አክሊሉ