የተወለዱት ኤርትራ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ በነበረችበት በ1950ዎቹ አጋማሽ አስመራ ከተማ ሲሆን እድገታቸውም ደግሞ ደቀመሃሪ በተባለ አካበቢ ነው:: በዚህም ምክንያት አማርኛንም ሆነ ትግርኛን አቀላጥፈው መናገር ይችላሉ:: የልጅነትም ሆነ የጎርምሳና እድሚያቸው በኤርትራውያን መሃል ሆነው በማሳለፋቸው በተለይ ደግሞ የትግርኛ ተናጋሪውን ማህበረሰብ ስነልቦና ተገንዘበው እንዲያድጉ ምክንያት ሆኗቸዋል:: ደቀ መሃሪ አስኳላ ሃዋርያት እና ደቀ መሃሪ አስኳላ ሀበሻ ትምህርት ቤቶች እስከ አምስተኛ ክፍል ድረስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ሲሆን ከስድስተኛ ክፍል እስከ አስረኛ ክፍል ደግሞ ጎንደር አዲስ ዘመን ከተማ ከተማሩ በኋላ ወደ አስመራ ተመለሱ:: ለመመለሳቸው ምክንያት ደግሞ ገና በ12 ዓመት እድሜ ሳሉ በኢህአፓ ተመልምለው ወደ ፖለቲካ ተቃውሞ መግባታቸው ቤተሰቦቻቸውን ባለማስደሰቱና ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ በመፈለጋቸው ነው:: በዚህም መሰረት ወደ ተወለዱባት ከተማ ተመልሰው 11ኛ እና 12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ተከታትለው አጠናቀቁ::
ይሁንና የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ማምጣት ባለመቻላቸው ዩኒቨርሲቲ የመግባት እድል ሳያገኙ ይቀራሉ:: በአጋጣሚ ግን ነፃ የትምህርት እድል ያገኙና ወደ ህንድ ይሄዳሉ፤ በእዚያም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በማርኬቲንግ ይሰራሉ:: ቀጠሉናም ሌላ ዲግሪ በሶሾሎጂ ( በማህበረሰብ ጥናት) እንዲሁም በጋዜጠኝነት የማስተርስ ዲግሪ አግኝተው ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ:: ኢትዮጵያ እንደመጡም እነ አቶ እቁባይ በርሄ ባቋቋሙት ደብረያሬድ የስነጥበብ ትምህርት ቤት መስራት ጀመሩ:: ብዙም ሳይቆዩ ፋና ሬድዮ ገብተው ማገልገል ጀመሩ:: ይሁንና በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ጦርነት በመጀመሩ ኤርትራውያንን ከሥራ ማባረር ይጀመራል:: የዛሬው የዘመን እንግዳች ምንም እንኳን ኢትዮጵያዊ ቢሆኑም ኤርትራ በመወለዳቸው ምክንያት ኤርትራውያን በተባረሩ ማግስት ያለአንዳች የቃልና የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ሰበብ ተፈልጎ ከሥራ እንዲሰናበቱ ተደረገ:: በገዛ አገራቸው ያለበቂ ምክንያት ከሥራ የተሰናበቱት እኚሁ ሰው ታዲያ በወቅቱ የነዋሪነት መታወቂያ የሌላቸው መሆኑ ደግሞ የራሳቸውን ሥራ ለመስራት እንኳ ፈተና ገጠማቸው:: ከአንድ ዓመት ልፋት በኋላ በአንዲት በጎ ሴት ድጋፍ ንግድ ፍቃድ አውጥተው የቢዝነስ ጋዜጣ ማዘጋጀት ጀመሩ:: ግና ጊዜው የጦርነት በመሆኑ የንግዷ ጋዜጣቸው ብዙ ርቀት መጓዝ አልቻለችም:: የአቅም ውስንነትም ፈተናቸውና ህትመቱን አቋረጡ::
በዚህም ግን ተስፋ አልቆረጡም፤ የተለያዩ ድርጅቶችን በማማከር አገልግሎት መስጠት ጀመሩ:: በተለይም ከተሞች የኢንቨስትመንት መቃብር የመሆናቸው ጉዳይ ያሳሰባቸው ስለነበርም በከተሞች ልማት ዙሪያ ለመስራት አቀዱ:: የከተሞች ቀን የሚል ፕሮግራም በማዘጋጀት ኢንቨስትመንት እንዲነቃቃ የማድረግና የማስተዋወቅ ሥራ ይጀምራሉ:: ይህንን ፅንሰ ሃሳብ መንግሥት ተረክቦ ማስኬድ ሲጀምር ደግሞ ትተውት ወደ ነበረው የህትመት ሥራ ገቡ:: «ንዋይ ስትሪት» የተባለ ጋዜጣ ማዘጋጀት ጀመሩ:: ይህም አስር ወራት ያህል ለህትመት ከበቃ በኋላ በፋይናንስ እጥረት ምክንያት ተገታ:: በአሁኑ ወቅት የተለያዩ ሚዲያዎችን የማማከር ሥራ የሚሰራ ድርጅት አቋቁመው ከማማከሩ ባሻገር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ዶክመንተሪዎችን ያዘጋጃሉ:: ለተለያዩ ድርጅቶች መጽሄት ያሳትማሉ:: ኩነቶችን ያዘጋጃሉ፤ ያስተባብራሉ:: በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን እየተጋበዙም በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ትንታኔ ይሰጣሉ:: አዲስ ዘመን ጋዜጣ ባለትዳርና የሶስት ልጆች አባት ከሆኑት ከአቶ ኦሃድ ቤናሚ ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ቃለመጠይቅ አድርጓል:: እንደሚከተለው ይቀርባል::
አዲስ ዘመን፡- ቃለ መጠይቃችንን እስቲ ከስምዎት ትርጓሜ ይጀምሩልንና ቀጥለውም የኢትዮ- ኤርትራ ዳግም ወደ ሰላም መምጣት የፈጠረበዎትን ስሜት ይግለፁልን?
አቶ ኦሃድ፡- ኦሃድ ማለት በእብራይስጥ ቋንቋ ምስጋና ማለት ነው:: ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወሰደ ቃል ነው:: ለእኔ የኢትዮጵያና የኤርትራ እርቅ ትልቅ እፎይታ ነው ። በቀደሙት ዘመን ኤርትራውያን ወንድሞቻችን እንደሆኑ፤ ኢትዮጵያም አገራቸው እንደሆነች አሰማኝ ነገር አልተሰራም:: ከመልካም እሴቱ ይልቅ ጠንክሮ የሄደው ወታደራዊ እርምጃው ነበር :: ያ አካሄድ ኤርትራውያንን የተለየ አመለካከት እና የከረረ ስሜት እንዲኖራቸው አድርጓል:: ያ የከረረ አመለካከትና ስሜት ግን ዶክተር አብይ ከመጡ ወዲህ እየረገበ ነው የመጣው:: ይህም ኤርትራውያን ለእኛ ጥሩ ስሜት ብሎም ለዘመናት ያልተፋቀ ፍቅር እንዳላቸው ለማየት ያስችላል:: ኤርትራውያን ጠላቶቻችን አይደሉም:: እንዳውም በአካባቢው ካሉ አጎራባች አገራት የተሻለ የማንነት አንድነት ያለን ከኤርትራ ጋር ነው:: ባለፉት 30 ዓመታት ግን የኤርትራና የኢትዮጵያ ህዝቦች ትልቅ አላስፈላጊ ዋጋ ከፍሏል:: ብዙ ወንድሞቻችንን አጥተናል ፤ ብዙ ሃብት ባክኗል፤ ኢኮኖሚያችን ደቋል::
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ ሰዎች ባለፉት ሁለት ዓመት ሁለቱ አገራት ሰላም ፈጠሩ ቢባልም ከመሬዎች ግንኙነት ያለፈ አይደለም ሲሉ ይከራከራሉ:: እርሶ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
አቶ ኦሃድ፡- ይሄ አስተሳሰብ ፖለቲካን ካለመገንዘብ የተፈጠረ ነው የሚመስለኝ:: ይሄ ሂደት በጣም ትልቅ ትርጉም ያለው ነው:: በሁለቱ አገሮች መካከል ተኩስ አቁም ስምምነት መኖሩ ራሱ ትልቅ እፎይታ ነው:: ከዚህ ባሻገር ደግሞ ድርድር ነው:: መንግሥትም በአልጀርሱ ስምምነት ተቀብሏል:: እርግጥ ነው እኛ በወቅቱ የተነገረን እውነታ ሌላ ነው:: በወቅቱ የነበሩ ባለስልጣናት ዋሽተውናል:: ስለሆነም ለአልጀርሱ ስምምነት መገዛት ይገባናል ተብሏል :: ዶክተር አብይ ይህንን እናከብራለን ሲሉ በኤርትራ በኩል ጥሩ ተቀባይነት አገኙ:: በታሪክ ለመጀመሪያ በሚባል ደረጃ አንድ ኢትዮጵያዊ በዚያ ደረጃ ኤርትራ ውስጥ ተቀባይነት አገኘ:: እኔ በህይወት ዘመኔ ይህንን አያለሁ ብዬ አልገምትም ነበር:: ምክንያቱም በጣም የመረረ ሃዘንና ቅሬታ እንደነበረባቸው አውቅ ስለነበር ነው:: አስቀድሜ እንዳልኩሽ ኤርትራውያን ክፉ ህዝቦች አይደሉም:: ለእኛ የሚያስቡ ስለኛ የሚጨነቁ የእኛን ጉዳይ የሚከታተሉ ብዙ ኤርትራውያን አሉ:: የኢትዮጵያን ክፉ ነገር አይፈልጉም:: ፖለቲካው ላይ ሲመጣ ነገሮች የተለያዩ ናቸው:: ስለዚህ በዶክተር አብይና በፕሬዚዳንት ኢሳያስ መካከል የተፈጠረው ስምምነት የግለሰብ ስምምነት አይደለም:: ሁለቱም የሚወክሉት ተቋማዊ አካል አለ:: አገሮችን የሚወክሉ ሰዎች ናቸው:: ለእኔ እነዚህ ሰዎች በጋራ ሆነን የፖለቲካ ችግሮቻችን እንፍታ ብለው መቀራረባቸው ትልቅ እምርታ ነው::
አዲስ ዘመን፡- ግን እኮ ዛሬም ድረስ ወደብ አልባ የመሆን ጉዳይ የሚያንገበግበው ህዝብ በሌላ በኩል አለ፤ ይህስ ጥያቄ በአግባቡ አልተመለስም በሚል ቅሬታ ያለው አካላት አሉ? እርቁ ጥቅምን አሳልፎ ይሰጣል የሚል ስጋትም አላቸው?
አቶ ኦሃድ፡- የኢትዮጵያ ጥያቄ ሌላ ጉዳይ ነው፤ በእኔ እምነት እርቁ ጥቅም አሳልፎ ይሰጣል የሚለው አስተያየት የተሳሳተ ነው:: የወደብን ጉዳይ በሚመለከት መስራት የነበረበት የኢትዮጵያ መንግስት ነበር:: በወቅቱ ሥራውን አልሰራም:: ማንኛውም አገር የባህር በር ያስፈልገዋል:: አሁን የተጀመረው ሂደት ወደብ እንዴት መጠቀም እንችላለን? ወደ ሚለው መፍትሄ ያስኬዳል:: እንደምታውቂው አቶ ስዩም መስፍን የኢትዮጵያን ህዝብ ዋሽተዋል::
እውነቱን ለመናገር የባድመ ጦርነት የመሬት ጥያቄ አልነበረም:: ኢሳያስን የማደከምና ኤርትራን የመምታት ፍላጎት ስለነበር ነው:: የኢትዮጵያን ህዝብ በኤርትራ ላይ ማስነሳት የምትችይው «መሬትህ ተወረረ» ስትዪው ብቻ ነው:: በወቅቱ ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ በሻቢያ ላይ ትንሽ ቅሬታ ነበረበት:: ይህም ሆኖ ግን በሰላም መፈታት የሚችል ነገር ነበር:: ወደ ጦርነት መኬዱ ይህችን አገር ወደ ኋላ አስቀርቷታል:: አገሪቱን ይመራው የነበረው ህውሃት በወቅቱ ኤርትራ ላይ የተጠቀመው የጦርነት ፖሊሲ ነው:: በወቅቱ የመሪና የአመራር ችግር ነበር::
ላለፉት 20 ዓመታት ጦርነትም ሆነ ሰላም ሳይኖር የተቆየበት ዓመታት በተለይ የትግራይን ህዝብ የጎዳበት ሁኔታ እንደነበር እሙን ነው:: ይህንን ሁኔታ ማስቀረት የቻለው የአብይ አስተዳደር ነው፤ ህውሃት20 ዓመት ሙሉ ችግሩን ታቅፎት ከመኖር ውጭ መፍትሄ ማምጣት አልቻለም:: ስለዚህ በዶክተር አብይ ትልቅ ለውጥ መጥቷል ብሎ በሙሉ ልብ መናገር ይቻላል::
ዛሬ በየመንገዱ ላይ ኤርትራውያንን ታያለሽ:: ይህንን እንደለውጥ አለመቁጠር የዋህነት ነው:: ደግሞም ይህንን ሁሉ ዓመት የከረመ ቁርሾ እያለ ከኤርትራ ጋር ሙሉ ለሙሉ መተማመን በአንድ ቀን አይመጣም:: ምክንያቱም ታሪካችን ጦርነትንና የግጭት በመሆኑ ነው:: የተጀመረውን ሰላማዊ ግንኙነት ካጣጣልነው እንዴት አድርገን ነው ለውጥ የምናመጣው?:: ያኛውንስ ምን ልንል ነው?:: በአጠቃላይ ይህንን አይነት ሃሳብ የሚያቀርቡ ሰዎች የፖለቲካ ግንዛቤ የሌላቸው ሰዎች ናቸው ባይ ነኝ::
አዲስ ዘመን፡- ወደ አገራዊ ጉዳዮች እንመለስ፤ እንደሚታወቀው በአገሪቱ ካሉት የፖለቲካ ትኩሳቶች በዋናነት የሚጠቀሰው በህወሓትና በፌዴራል መንግስቱ መካከል ያለው ግጭት ነው፤ በእርሶ እይታ የዚህ የግጭት መንስኤና መዳረሻ ምንድን ነው?
አቶ ኦሃድ፡- እንደምታስታውሽው ኢህአዴግ ከለውጡ በፊት በነበሩት ዓመታት በጥልቅ መታደስ እያለ ራሱን ለማሻሻል ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፤ ከብዙ መገማገም በኋላ የእነ ዶክተር አብይ ቡድን መጣ:: የዚህ ቡድን ስልጣን የተረከቡበት አካሄድ ህገመንግስታዊ ነው:: ስለዚህ ቤተመንግስት ከገቡ በኋላ ማስተካከል ነበረባቸው፤ የገቡትም የተበላሸ ነገር ስላለ ነው:: እነሱ ችግሩን ለማስተካከል ሲሞክሩ ህወሓት ማጉረምረምና ቅሬታ ማሰማት ጀመረ::
አዲስ ዘመን፡- የቅሬታው ዋነኛ ምንጭ ምንድን ነው ይላሉ?
አቶ ኦሃድ፡- ዋነኛው ጉዳይ የሚመስለኝ
የስልጣንና የሃይል ማጣት ጉዳይ ነው:: ሃያል ሆኖ የመቀጠል ፍላጎት ስላላቸው ነው:: ይህ አይነቱ አካሄዳቸው የፖለቲካ ችግር እንዲፈጠር አድርጓል:: ህወሓት ያንን ሃይልና ስልጣኑን ያጣበትን መንገድ መቀበል አልፈለገም:: በእኔ እምነት ህወሓት ላይ ስህተት አለ:: ለውጥም የመጣው ችግር በመኖሩ ነው:: አይተሽ እንደሆነ ከ20 ዓመታት በላይ የመሩት የሱዳን፣ ግብፅ፣ ቱኒዚያ፣ የሊቢያና የሌሎችም አረብ አገራት መሪዎች የተወገዱት በጦርነትና በአመፅ ነው:: በዚህ ቀጠና በሰላም የወረደው ህወሃት ብቻ ነው፤ በሰላም ወርዶ በሰላም እንዲኖር እድል የተሰጠው ህወሃት ብቻ ነው:: መግለፅ የምፈልገው አንድ ነገር በዘመናት ሂደት ውስጥ ህዝቦች መሪዎቻቸውን የሚታገሱበት ዓመት እያጠረ ነው የሚመጣው:: አሁን ያለው ትውልድ አንድ መሪ ከሁለት የምርጫ ዘመን በላይ እንዲቀጥል አይፈልግም:: ከ25 ዓመታት በላይ የኖሩ መንግሥታት እየተዋረዱ፤ እየተገፉ የወረዱበት እውነታ ዓለም አቀፋዊ ክስተት ነው:: እኔ ህወሓት ምን እንደሚፈልግ አላውቅም::
ህወሓቶች «አብይ አምባገነን ነው፤ ›ተጋሩ› እየተገደለ ነው» የሚሉት ነገር ሁሉ ውሸት ነው:: አንድ ነገር ልንገርሽ ፤ ህወሓት ከስልጣን ከተወገደ በኋላ እየተገደሉ፤ እየታፈኑ ያሉት የትግራይ ተወላጆች አይደሉም፤ የአማራና የኦሮሞ ተወላጆች ናቸው:: በየዩኒቨርሲቲውና በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ተፅዕኖ ሲደርስባቸው ያየነው አማራና የኦሮሞ ተማሪዎችን ነው:: እኔና አንቺ በምንኖርባት አዲስ አበባ እንኳን 1ነጥብ 2 ሚሊዮን የትግራይ ክልል ተወላጅ በሰላም እየኖሩ ነው ያሉት:: እኔ የማውቃቸው በርካታ የትግራይ ባለሃብቶች ጨረታዎችን አሸንፈው ስራቸውን እየሰሩ ነው ያሉት:: ህወሓት ምን እንደሚፈልግ ግልፅ አይደለም:: እዚህ አካባቢ በሰላም እንዲቀጥል የተፈቀደለት ብቸኛው መንግስት ህወሃት ብቻ ነው፤ ግን እየበጠበጠ ያለው ራሱ ነው::
በእኔ እምነት የዶክተር አብይ መንግስት ሁሉንም ጥያቄ የሚመልስ ሳይሆን ጥያቄ መመለስ የሚያስችል ስርዓት አመቻችቶ የሚያልፍ ነው:: ብዙዎቻችን ተስፋ ያደረግነውም እዚህ ላይ ነው:: ደግሞም ለማድረግ የሚሞክሩትና የሚታዩት ነገሮች ከሚያወሩት ጋር የሚቀራረብ ነው:: አንዳንዴ ላይሳካ ይችላል፤ ነገር ግን የሁሉንም ጥያቄ ለማስተናገድ ጥረት እያደረጉ፤ እያባበሉ ጠመንጃ እያስጣሉ የመጡ ብቸኛው መሪ ዶክተር አብይ ናቸው:: ስለዚህ ይህ መንግስት እድል ሊሰጠው ይገባል፤ ህዝቡ በመረጠው እስኪተዳደር ድረስ ዶክተር አብይን ከመደገፍ በስተቀር ሌላ ምርጫ የለንም::
አዲስ ዘመን፡- በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የዶክተር አብይ የኖቬል ሽልማት ተመልሶ መውጊያ እንዳይሆንባቸው ስጋት እንዳሎት ተናግረው ነበር፤ አሁን ላይ ከዚሁ ጉዳይ ጋር ተያይዞ የፈጠረው ችግር አስቀድመው ተረድተውት ነበር ማለት ነው?
አቶ ኦሃድ፡- እኔ ሰሞኑን ከዶክተር አብይ የኖቬል ሽልማት ጋር ተያይዞ አቶ ስዩም መስፍን የሰጡትን ሃሳብ አልቀበለውም፤ አልምሰማማበትም፤ ዶክተር አብይ የተረከቧት ኢትዮጵያ አቶ ሃይለማርያም ከተረከቧት ኢትዮጵያ ጋር አትነፃፀርም::
በሀገሪቱ ሁከትና ብጥብጥ የተነሳው ኢህአዴግ ተመረጥኩ ባለ በሶስተኛው ወር ነው:: ሙሉ ለሙሉ አሸንፊያለው ባለበት ምርጫ ነው አዲስ ሃይል የመጣው:: ስለዚህ ችግር ነበር:: ይህንን መቀበል መቻል አለብን:: የኢህአዴግ መንግስት ያለጦርነት በድንጋይ የወረደ መንግስት ነው:: ይህ ትልቅ ስልጣኔ ነው:: ግን ለምንድን ነው የወረደው? ብለን መጠየቅ ይገባናል:: እነሱ በሚመሩበት ጊዜ ፍትህ አልነበረም፤ የሰብአዊ መብት ጥሰት በርካታ ነው፤ ሙስናው በቀላሉ የሚገለፅ አይደለም:: ስለዚህ እነዚህ ችግሮችን ነው የዶክተር አብይ መንግስት የተረከበው:: ከዚያ በኋላ ለሁሉም በር ከፍቷል:: አንዳንዱ ክርስትና ተነስቶ የሚገባ አለ፤ አንዳንዱ ከነመሳሪያው የገባና ከገባ በኋላ ካልተታኮስኩ የሚልም አለ:: ይህንን ሁሉ ውጥንቅጥ መቆጣጠር ሂደታዊ ነው:: በአንድ ቀን የምታስወግጂው አይደለም:: ዶክተር አብይ እንዳሉትም ገደብ የሌለው ትዕግስት ያስፈልጋል:: እሳቸው ይህንን ነው በተግባር ያሳዩን:: ግን ደግሞ ገደብ በሌለው ትዕግስታቸው ገብተው የጨፈሩ ሰዎች አሉ:: ገጀራ የሚያነሳ አለ፤ ክላሽ የሚጎትት፣ በረባ ባረባ ዘራፍ የሚል፣ ፌስቡክ ከፍቶ ጥላቻ ሲነዛ የሚውል አለ::
ይህም እያለም ዶክተር አብይ ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ ቅራኔው እየረገፈ ነው የመጣው:: ሰላማዊ ትዕግስት ቱሩፋቱን እያሳየን ነው ያለው:: በእውነቱ አቶ ስዩም በተናገሩት ነገር በጣም ነው የማዝነው፤አሳፋሪም ነው:: ምክንያቱም እሳቸው አንጋፋ የዲፕሎማሲ ሰው ናቸው:: ለምንድንነው በዶክተር አብይ ላይ ይህን ያህል ጥላቻ የሚያራምዱት? ዶክተር አብይ ወታደር ልከው «ግደሉ፤ ጨፍጭፉ» ብለው ያየዙበት አጋጣሚ የለም:: ምንአልባት ይሄ አጋጣሚ ኖሮ ቢሆን ኖሮ የኖቬል ሽልማቱ ጥያቄ ውስጥ ሊገባ ይችል ነበር:: ልንገነዘብ የሚገባን ይህ ሽልማት ትልቅ ትርጉም ያለው ነው:: እነ አቶ ስዩም ከእዚህ እውነታ ጋር የመኖር ግዴታ አለባቸው:: በእርግጥ አቶ ስዩም ይህን ነገር የተናገሩት የህወሓት ፍላጎት ውስጥ ሆነው ነው::
አዲስ ዘመን፡- ከለውጡ ወዲህ በትግራይ ክልል ተወላጆች ላይ የተለየ በደል እንደደረሰ ነው ብለው ያምናሉ?
አቶ ኦሃድ፡- በነገራችን ላይ ከዚህ ጋር ተያይዞ በትግራይ ሚዲያዎች አካባቢ ያሉት ያልተቋረጡ ፕሮፖጋንዳዎች ግለሰብ ላይ ያተኮረ የኮምዩኒኬሽን ስትራቴጂ ነው:: መሪውን በመምታት ከጣሉት በኋላ ታች ያለው እንደሚረግፍ በማሰብ የተቀየሰ የኮምዩኒኬሽን አቅጣጫ ነው:: በእኔ እምነት ይህ ስትራቴጂያቸው ግን እየሰራ አይደለም:: ህወሓት ዶክተር አብይን በነካ ቁጥር እዚህ ያለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ደጋፊ እየጨመረ ነው የመጣው:: እነሱ እንደሚሉት በዘሩ የተነሳ ጥቃት የደረሰበት የለም:: ምናልባት በሁለት ግለሰቦች መካከል የተፈጠረ ግጭት ሊኖር ይችላል:: በዓለምም ተመሳሳይ ሁኔታ አለ:: ይህንን የሁለት ግለሰቦች ግጭት ወስደሽ ለፖለቲካ አጀንዳ ማስፈፀሚያ ማድረግ አይገባም:: አሁን ላይ በትግራይ ተወላጆች ላይ በደል እንደደረሰ ተደርጎ እየተነገረ ያለው ወሬ በጣም አሳፋሪና ከእውነት የራቀ ነው:: እርግጠኛ ነኝ የትግራይ ህዝብ እንደእነሱ አያስብም:: በአገሩ አንድነት ላይ የሚደራደር ህዝብም አይደለም:: ህወሓት ጠላታዊ አስተሳሰቡን ወደ ህዝብ ማውረድ የለበትም:: አሁን ያለው መንግስት ለትግራይ ህዝብ የተለየ ነገር አያደርግም፤ የሚያጎለውም የለም:: በእርግጥ እኔ የመንግስት ተወካይ አይደለሁም፤ ነፃ ዜጋ ነኝ:: ግን አስተውላለሁ:: የአብይ አስተዳደር በይቅርታና በመደመር የተመሰረተ ፍልስፍና የሚያራምድ ባይሆን ኖሮ ብዙ ውጥንቅጥ ውስጥ እንገባ ነበር::
እርግጥ ነው ስርዓቱን ተጠቅመው ሲበዘብዙ የነበሩ በርካቶች ናቸው:: የመንግስትን መዋቅር ተጠግተው በተዛባ ሁኔታ ሙስና ውስጥ የተዘፈቁ ነበሩ:: ይሄ ግን መቀሌ ካለው ትግሬ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም:: ምንአልባት አንዳንዱ ባለስልጣን ዘመዱን ጠቅሞ ሊሆን ይችላል፤ ነፃ የውጭ የትምህርት እድል ለራሱ ወገን ሰጥቶ ሊሆን ይችላል፤ የመሬት ድልድል ላይ መጠቀም አለ:: ይህ ሁሉ ሲሆን ህወሓት ፈልጎት ይሁን ወይም ሳይፈልገው የተደረገ መሆኑን አናውቅም:: በእሱ ጊዜ ግን ይህ ሆኗል:: ይህ ሲባል ግን ህወሓት ሙስናን ሆነ ብሎ አውቆ ነው የፈቀደው ለማለት አይቻልም:: ነገር ግን እነዚያ ማፊያዎች የፈጠሩት ችግር የትግራይ ህዝብ ሊሆን አይችልም:: ይህንን ማስተካከል ሲገባ «ዶክተር አብይ የትግሬዎች ጠላት ነው» ማለት ተገቢ አይመስለኝም:: ከአቶ ስዩምም የሚጠበቅ አይመስለኝም:: እስካሁን ድረስ ዶክተር አብይ የኖቬል ሽልማቱን የሚያስነጥቅ ነገር አላየሁባቸውም::
አዲስ ዘመን፡- ህወሃት እንደሚለው የትግራይ ህዝብና ህወሃት አንድ ናቸው?
አቶ ኦሃድ፡- እኔ የትግራይ ህዝብ ጋር በተወሰነ መልኩም ቢሆን አብሬ ኖሪያለሁ:: ጨዋ ህዝብ ነው:: ግን አንድ የፖለቲካ ስትራቴጂ አለ:: እያስደነገጡና እያስበረገጉ ህዝቡን የእጅ ጥምዘዛ ህይወት እንዲኖር እያደረጉት ነው:: ህወሓት ስህተት ሰርቷል፣ የማይሳሳት ፓርቲም የለም:: ምክንያቱም የቅዱሳን ስብስብ አይደለም:: ጊዜው በረዘመ ቁጥር ደግሞ ስህተቶቹ እየበዙ ነው የሚመጡት:: ያ ስህተት ግን የትግራይ ህዝብ ስህተት አይደለም:: የሃይለስላሴ ስህተት የኢትዮጵያ ህዝብ አይደለም:: የአብይ ስህተት የኦሮሞ ህዝብ ስህተት አይደለም:: ይህንን ማወቅ አለብን:: አንዳንድ የህወሓት አባላት ይህንን ፖለቲካ በማጦዝ የመገንጠል አዝማሚያ እያሳዩ እንደሆነ ይታወቃል:: እኔ ግን በደንብ አስበውበታል ብዬ አላምንም:: ይህ አካሄዳቸው ለትግራይ ህዝብ ሊያመጣ የሚችለውን ጉዳት የተገነዘቡት አይመስለኝም::
እኔ አንድ ተራ ዜጋ ነኝ፤ ግን ህዝቡ ውስጥ ብዙ ጥያቄ አለ:: ከተራ ዜጋ የሚወጣው አስተያየት ሊያሳስበው ይገባል:: ይህንን ማድረግ ካልቻለ የሰው ልጅ ጭንቀት የማይገባው ፓርቲ መሆኑን ያመላክታል:: እኔ እንደ ማህበረሰብ ጥናት(ሶሾሎጂ) ተማሪነቴ ህዝብ ህዝብ ተሳስተሃል አይባልም፤ በህወሓት ሀጥያት የትግራይ ህዝብ አይፈረድበትም:: የትግራይ ህዝብ ጥሩ ልብ ያለው ህዝብ ነው:: መገንጠል ማለት ይህን ህዝብ ማጣት ነው:: ከዚህም በላይ ክፉ ጎረቤቶች ልንሆንም እንችላለን:: ስለዚህ መገንጠል የሚለው ሃሳብ ብዙ የሚያስኬድ አይደለም፤ በመሆኑም እኔ ህወሓቶችን ለማለት የምፈልገው ጥሩ አጀንዳ ይዛችሁ ኑ እና ለሳሞራ እንዳጨበጨብነው ለእናንተም እናጨበጭባለን ::
የግጭት አጀንዳቸው ይጣሉትና ልዩነቶቻችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት እናድርግ:: የኢትዮጵያ ህዝብ ከህወሓት የሚፈልገው ሰላም ብቻ ነው:: የተጣለ አስተሳሰብ( አይዶሎጂ) ይዘህ፤ የ60ዎቹ የሁለተኛ ዓመት ተማሪዎች የቀረፀልንን አጀንዳ በ2012 ላለው ትልውድ ልታቀርበው አትችልም:: ዘመኑን የሚመጥን ሃሳብ ይዘህ መምጣት ይገባሃል የሚል መልዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ::
በሌላ በኩል አንቀፅ 39 ላለፉት 27 ዓመታት ተነስቶ አያውቅም፤ አሁን ለምንድንው በትግራይ አካባቢ የሚነሳው? ህወሓት ከስልጣኑ ስለተባረረ ነው? በትግራይ ህዝብ ላይ ቅሬታ በተፈጠረ ቁጥር ለዶክተር አብይ ከሚጠበቀው በላይ የፖለቲካ ቱሩፋት እያመጣላቸው ነው:: የህወሓት እንዲህ መሆን ህዝቡ ለዶክተር አብይ ያለው ድጋፍ እንዲጨምር አድርጎታል:: ስለዚህ የፖለቲካ ኪሳራ እያጋጠማቸው ነው:: ዶክተር አብይ እኮ በእሳቸውም ሆነ በቤተሰባቸው ላይ ተደጋጋሚ የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸዋል፤ መፈንቅለ መንግስትና ሌሎችም ችግሮች ተቃጥቶባቸዋል:: አንድም ቀን ግን ስለራሳቸው አንስተው አያውቁም:: ይህ ሆኖ ሳለ ተበድለናልና የእንግንጠል ሃሳብ የሚመጣው ከህወሃት ነው:: ይህ የሚያስኬድ አይደለም::
አዲስ ዘመን፡- ትግራይን ስለመገንጠል ማሰቡ ፋይዳው ምንድን ነው?
አቶ ኦሃድ፡- በእኔ እምነት ፋይዳው አይታየኝም:: በእኔ አስታሳሰብ ትግራይ ብትገነጠል መጀመሪያ የምትጎዳው ኢትዮጵያ ናት የምትመስለኝ:: ምክንያቱም ከአምስት ሚሊዮን በላይ የሚሆን ህዝብ ትግራይ ውስጥ አለ:: እሱን እናጣለን:: ምክንያቱም ቁጥራችን የሚጀመርው ከህዝብ ነው:: ስለመሬት፣ ስለማዕድንና ስለሃብት ከማውራታችን በፊት ልናጣ የምንችለውን ህዝብ ነው ማሰብ የሚገባን:: በሁለተኛ ደረጃ በምትቀጥለዋ ትግራይ ምን ሊፈጠር ይችላል? ብዬ ሳስብ ደግሞ እሰጋለሁ:: ምክንያቱም በአንድ በኩል በጣም የመረረ ጥያቄ የሚያነሱ የአማራ ክልል ሰዎች አሉ:: ጅምላ የዘር ማጥፋት ዘመቻ ተፈፅሞብናል የሚሉ አሉ:: በኤርትራ በኩል ያለውም ስሜት ጥሩ አይደለም:: በታሪክ በተደጋጋሚ ከህወሓት ዘላቂ ግንኙነት ሊኖር እንደማይችል ኤርትራውያን ጠንቅቀው ያውቃሉ:: በምትገነጠል ትግራይ ውስጥ ኤርትራውያን በጣም ነቅተው የሚጠብቋት አገር ነው የምትሆነው:: ለኢትዮጵያም ጠንቅ ሊሆን የሚችል የፖለቲካ መዋቅር ሊፈጠር ይችላል:: ስለዚህ የትግራይ መገንጠል ለኢትዮጵያ ችግር የሚሆነው በዚያ መልኩ ነው:: ይህንን ችግር ሊያስተናግድ የሚችል መንግስት ደግሞ ላይኖር ይችላል:: ማንም አትራፊ አይደለም::
አዲስ ዘመን፡- ከዚሁ ጋር ተያይዞ የተለያዩ ችግሮችን ባሉታዊ መልኩ እያራገቡ ያሉ ሚዲያዎች ጉዳይ በምን ሊቃኝ ይገባል ይላሉ?
አቶ ኦሃድ፡- የሚዲያው ባህል አሳዛኝ ሁኔታ ላይ ነው ያለው:: ሚዲያው ኃላፊነቱን በትክክል እየተወጣ አይደለም:: አንዳንድ የሚዲያ ዘገባዎች በእውቀትም በእድሜም የበሰለውን ሰው ሳይቀር የሚፈታተኑ ናቸው:: አሁን እየተለቀቀ ያለውን የጥላቻ ዘመቻ የአገሪቱ ህዝብ የማስተናገድ አቅም የለውም:: ሚዲያዎች ይህንን ተገንዝበው በህግና በመርህ ሊንቀሳቀሱ ይገባል:: በሌላ በኩል በተደጋጋሚ ስልጣና መስጠት ይገባል:: በተለይ የክልል ሚዲያዎች በስነምግባር ረገድ ዳግመኛ መቅረፅና ማስተካከል ያስፈልጋል ባይ ነኝ::
አዲስ ዘመን፡- ሰሞኑን የአገር ሽማግሌዎች ባህላዊውን የእርቅ እሴታችንን መሰረት አድርገው አገራዊውን ችግር በሽምግልና ለመፍታት ወደ መቀሌ ሄደዋል፤ ይህ ጉዳይ ምን ያህል ጠቃሚ ነው ብለው ያምናሉ? ውጤታማስ ይሆናል?
አቶ ኦሃድ፡- በመጀመሪያ እንደዚህ አይነት ዜጎች መኖራቸው በራሱ በጣም ደስ የሚል ነው:: ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት ይቻላል ብለው የሚያምኑ ኢትዮጵያውያን መኖራቸው በጣም የሚያስደስት ነው:: እርግጠኛ ነኝ ይህን የዜጎች ተነሳሽነት መንግስት አያውቀውም:: ሆኖም ይህ ጥረት የሚመሰገን ነው:: በሌላ በኩል ግን ሽምግልናው የመጣው ከማሃል አገር ወደ ህወሃት ነው:: ይህንን ጉዳይ በተለያየ መልኩ ሊታይ ይችላል፤ አንደኛው መንግስት ራሱን ደብቆ ራሱ እንደላካቸው አድርጎ የማብጠልጠል ነገር ሊኖር ይችላል:: በእርግጠኝነት ዶክተር ደብረፂዮን ሰው አክባሪ ናቸው:: ግን አጀንዳው ያለው የፖለቲካ ሚዛኑ ላይ ነው:: አሁን ያለው የፖለቲካ መዋቅር ህወሃት ተመልሶ እንዲመጣ የሚፈቅድ አይመስለኝም::
ምንአልባት ህወሃት ብልፅግና ውስጥ ሆኖ ቢሆን የራሱ ድርሻ ይኖረው ይችላል:: ከብልፅግና ውጭ ሆኖ የብልፅግናን እድልና ጥቅም ሊያገኝ አይችልም:: ምክንያቱም አካሄዱ አይፈቅድም:: አንዳንድ ጊዜ ህወሃቶች ምን እንደሚያስቡ አይታወቅም:: አብዛኛውን ጊዜ በስሜት ተነሳስተው ነው የሚንቀሳቀሱት:: ለምሳሌ በቅርቡ ምክርቤቱ ምርጫ እናካሂዳለን ብሎ የወሰነው በስሜት ተነሳሽነት እንደሆነ ነው የምረዳው:: ትግራይ ውስጥ ተቃዋሚዎች ይወዳደራሉ፤ አይወዳደሩም የሚለው ነገር ሌላ ጉዳይ ሆኖ በዚህ ሰዓት ለህወሓት ምርጫ ማካሄድ አንገብጋቢ ጉዳዩ ነው ወይ?::
በተለይ ደግሞ በፌዴራል ደረጃ በኮረና ምክንያት ምርጫ በተራዘመበት ጊዜ፤ ኮረና ራሱ ያመጣብን የኢኮኖሚ ቀውስ ባልተፈታበት ሁኔታ፤ የአባይ ጉዳይ አሳሳቢ በሆነበት ወቅት ምርጫ ማካሄድ ያንያህል አስፈላጊ ነው ብዬ አላምንም:: ይህን ስታይ የህወሓት ነገር ለሽምግልና የማይመች መሆኑን ማሳያ ነው:: ለምሳሌ የካቲት 11 በዓላቸውን ሲያከብሩ አይተሽ እንደሆነ ህፃናትን መሳሪያ አሲይዘው የተሳተፉበት ሁኔታ ነበር:: ህፃናትን ማሳሪያ ማስታጠቅ ቀርቶ የጉልበት ሥራ ማሰራት በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ህግ በወንጀልነት ነው የተደነገገው:: ህፃናት በዚህ እድሜያቸው ስለጦርነት ማሰብ አይገባቸውም:: ከዚያ ይልቅ ስለልማትና ስለአገር ፍቅር አስተምረው ቢያንጽዋቸው ለሁሉም ጠቃሚ ይሆን ነበር::
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ህዝብ በህወሓት ላይ ቅሬታ አለው:: 27 ዓመታት ለአንድ አስተዳደር በቂ ነው:: የአብይ መንግስት የራሱ የሆነ አካሄድ አለው:: ህዝብ ከፈለገውና ከተቀበለው ደግሞ ህወሃት ሊቃወመው የሚችልበት ምክንያት የለም:: ይልቁንም ህወሓት ህዝብ የሚቀበለው ከሆነ አጀንዳ ይዞ መምጣት ይችላል:: ለምሳሌ ሰሞኑን ጀነራል ሳሞራ የሰጡት ቃለ መጠይቅ አብዛኛውን ነገር ምንም አዲስ ሃሳብ ባያነሱም ጦር መማዛዝ አያስፈልግም፤ ይልቁንም ማገዝ እንደሚገባ የገለጽዋት አንዲት ሃሳብ ግን የብዙዎችን ልብ ነካች:: ይህም የሚያሳየው የኢትዮጵያ ህዝብ ምንም እንኳን ቢበደል ተመልሶ ህወሓትን ለማቀፍ ዝግጁ መሆኑን ነው:: ጀነራል ሳሞራ የስርዓቱ አካል የነበሩ ሰው ናቸው:: ተቋማቸው ሙስና የሌለበት እንደሆነ ተናግረዋል፤ እርግጥነው እሳቸው እየመሩት የነበረው ተቋም «የኔ መስሪያ ቤት በሙስና ተጨማልቆ ነበር» ማለት አይጠበቅባቸውም፤ ግን ሁላችንም እንደምናውቀው መከላከያ ብዙ ጥያቄ የነበረበት ተቋም ነው::
በከፍተኛ ደረጃ ሪፎርም የተካሄደውም እዛ ተቋም ውስጥ ነው:: የመከላከያ መኪኖች መርካቶ መጥተው ቴሌቪዥን ያራግፉ እንደነበር ይታወቃል፤ ምንም ጥያቄ የለውም:: በዚህ ላይ መከራከር አያስፈልግም፤ ግን እሳቸው አንዲት ጥሩ ነገር ስለተናገሩ ህዝብ ልቡ ምን ያህል ዝግጁ እንደሆነ ያስረዳል:: ይህንን ህዝብ በቃላሉ ማሸነፍ አልቻሉም:: ህወሃቶች ተራራ ያንቀጠቀጠ ትውልድ ይሉናል፤ ግን ህዝቡን በፍቅር ማንቀጥቀጥ አልቻሉም::
ህወሓቶች ጥሩ አጀንዳ ይዘው ከመጡ ህዝቡ ቅርብ መሆኑን የሚያሳይ ነው:: የኢትዮጵያ ህዝብ «አሀዳዊ መንግስት ያስፈልገኛል» ካለ መቀበል ያለብን የኢትዮጵያን ህዝብ ነው:: ህዝቡ ይወስን:: እኛ ለምን ህዝቡን እናባርረዋለን?:: አቶ ስብሃት ነጋ አንድ ወቅት ላይ « እኛ የ1960ዎቹ የሁለተኛ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የቀረፁልንን ነው የምንኖረው» ብለው እንደጀብድ ተናግረው ነበር:: ግን ይህ ለእኔ አሳፋሪ ነው:: አዲስ ትውልድ ሲመጣ እውቀት ማደግ አለበት:: በኢዛና ዘመን እውቀት ነበረ፣ በእነ አፄ ቴድሮስ ዘመን፣ በእነ አፄ ምኒልክ ዘመንም እውቀት ነበር:: ሁሉም በራሱ ዘመን እውቀት ነበረው:: አሁንም ህወሓት አጀንዳ ካለው ህዝቡ ጋር ችግር የለበትም:: ለዚህ ደግሞ የጀኔራል ሳሞራ ቃለመጠይቅ ይህንን ማሳያ ነው:: ህወሓት አንድ አቋም ይዞ የሚንቀሳቀስና በሰጥቶ መቀበል መርህ የማያምን ስለሆነ ለሽምግልና ዝግጁ ነው ብዬ አላስብም:: በእርግጥ መሞከሩ ጥሩ ነው፤ ቢያነስ ሞክረን ነበር ለማለት ያስችላል:: ግን ህወሓት በሽምግልና የሚያምንና የሚመለስ ፓርቲ አይደለም::
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግኖታለሁ::
አቶ ኦሃድ፡- እኔም የዘመን እንዳችሁ ስላደረጋችሁኝ ከልብ አመሰግናለሁ::
አዲስ ዘመን ሰኔ 13/2012
ማህሌት አብዱል