
በየትኛውም የለውጥ መንገድ አባጣ ጎርባጣና አንገራጋጭ ነገር አይጠፋም፡፡ አዲስ ነገር እንዲሁ ያለችግር አይመጣም፡፡ አይለመድምም፡፡ ከግርታ አንስቶ እስከ ተቃውሞ የሚያደርሱ አስቸጋሪ ምላሾች በየጊዜውና በየቦታው ያጋጥማሉ፡፡ በእኛ ሀገር የሆነው ይኼው ነው፡፡ በህዝባዊ እምቢተኝነት የተጀመረው ለውጥ በመሪው ድርጅት ተቀጣጥሎና ግዘፍ ነስቶ ተመልሶ ወደ ህዝቡ ሲገባ አቀባበሉ በሁሉም አካባቢና የህብረተሰብ ክፍል ዘንድ እኩልና ተመሳሳይ አልነበረም፤ እስካሁንም አይደለም፡፡ ግማሹ ተሸቀዳድሞ የለውጡ ደጋፊና ጋሻ ጃግሬ ሆኗል፤ ከፊሉ በጥርጣሬ አይን እየተመለከተ ዘጠኝ ወራት ያህል ተጉዟል፡፡ በጣም ጥቂቱ ደግሞ ይህ አጋጣሚ ለእኔ ብቻ መሆን አለበት ባይ ሆኗል፡፡
በለውጡ ከተገኙ አገራዊ ትሩፋቶች መካከል፤ የፖለቲካ እስረኞች መፈታት፤ የሰብአዊ መብት መከበር ጭላንጭል መታየት መጀመር፤ አገርን የበዘበዙ ሙሰኞችና ተጠርጣሪዎች በህግ ፊት መቅረባቸው የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በተለይ፣ በፖለቲካ አቋማቸውና የትግል መስመራቸው ወይ መርጠው አሊያም ተፈርጀውና ተገፍተው በውጭ ይኖሩ የነበሩ ተቃዋሚዎች ወደ አገር እንዲገቡ መደረጉ ትልቁ ድል ነው፡፡
እነዚህ ሁሉ ሆነው ግን አሁንም በመንግሥትና በአንዳንዶች መካከል መግባባትና መተማመን አልተቻለም፡፡ በየስርቻው የራስ ፍላጎትና ጥቅም እያስቀደመ፤ የአገርን ተስፋና ሕልም እያጨለመ የሚቀጥል እኩይ ተግባር እዚህም እዚያም ይስተዋላል፡፡ በተለይ ባለፉት ወራት ከኦነግ ታጣቂዎች ጋር በተያያዘ በምዕራብ ኦሮሚያና በደቡብ በጉጂ ዞን አካባቢ ነፍጥ አውርጄ ገባሁ ያለው ታጣቂ ኃይል አገር ውስጥ ከገባ በኋላ አካባቢውንና ማህበረሰቡን ሲያስቸግር ከርሟል፡፡
ደጋግሞ እንደተባለው ከውጭ ሲገቡ ቄጠማ ጎዝጉዞ እንኳን ደህና መጣችሁ ብሎ የተቀበለን ሰላም ናፋቂ ወገን ሰላም መንሳት ለህሊና የሚቆረቁር፤ ለፍርድም የሚያስጨክን ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ ለኦሮሞ ሕዝብ ጥቅም ሲሉ በውጭ ሆነው ሲታገሉ የነበሩ ኃይሎች በተገኘው ሰላም ተጠቅመው ወደ አገር ገብተው አብዛኞቹ በሕዝባቸው መካከል ተገኝተው በሰላም ለዘላቂ የሕዝብ ጥቅም በሰላማዊ መንገድ ሲታገሉ ዳግም ነፍጥ ያነሱትና ጫካ የገቡት የኦነግ ኃይሎች ዛሬም ተሳስተዋል ማለት ይቻላል፡፡
መቼም ሽማግሌ አይጥፋ ነውና እስካሁን የደረሰው ጉዳት ቀላል ነው ባይባልም ከመነጋገርና ከመወያየት የሚያመልጥ ጉዳይ ባለመኖሩ በሽምግልና ነገሮች በርደዋል፡፡ ጫካ የገባውም ትጥቁን ፈትቶ በሰላማዊ መንገድ ለመቀጠል መስማማቱ የባህልና የትውፊት ባለሀብቶች መሆናችንን በድጋሚ አሳይቷል፡፡ የኦሮሞ አባገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎችና የአገር ሽማግሌዎች ጫካ የገባውን የኦነግ ታጣቂ ጨምሮ ወደ አገር የገቡትን ለኦሮሞ ሕዝብ እንታገላለን የሚሉትን የፖለቲካ ድርጅቶች በአንድ አገናኝተው ማወያየታቸው፤ ማወያየት ብቻም ሳይሆን ማስማማታቸው በአንድ በኩል መንግስት በሆደ ሰፊነት የሄደው ረጅም ርቀት ፍሬ ማፍራቱን ያሳየ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ጋሞዎች ሁሉ የኦሮሞ ባህልም አኩሪ፤ ችግር ፈቺ ሥርዓትና ሥርዓቱን የሚያስከብሩ አባቶች እንዳሉት በገሀድ ያመላከተ ነው፡፡
አዎን እኛ ኢትዮጵያውያን በችግሮቻችን ዙሪያ ተቀምጠን ከተወያየን ወደ ፍርድ ቤት ከመሄድና በችሎት ፊት ከመቆም በላይ የሚመረጡ መፍትሔ የሚገኙባቸው ትውፊቶች ባለቤቶች መሆናችን እርግጥ ነው፡፡ ይህም በኦሮሞ አባገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎችና ሽማግሌዎች ተግባር ተገልጿል፡፡ መንግስትም “በትዕግስት ለጠበቀ ዓለሙ ሁሉ ወደርሱ ይጓዛል” እንዲሉ፣ የትዕግስቱን ትሩፋት አግኝቷል፡፡ ሁሉም ግን መልካም ነው ተብሎ ብቻ የሚታለፍ አይደለም፡፡ ይልቁንም፤ ባለፉት የችግር ወራት ብዙ ሰቆቃ ደርሷል፡፡ ችግር ተፈጥሮ ንጹሀን ተጎድተዋል፤ ህፃናት ተሰቃይተዋል፤ የመንግስትና የሕዝብ ሀብት ተዘርፏል፤ ባጠቃላይ አገሪቱ እንደ አገር ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ፤ እንዲሁም ፖለቲካዊ ክስረት ደርሶባታል፡፡ ይህ የጠቅላላው ሕዝብም ኪሳራ ነው፡፡ በእያንዳንዱ ስህተታችን አገር ትጎዳለች፡፡ እናም እንማራለን፡፡ አሁን ግን መማር ብቻ አይበቃም፡፡ ጥፋተኝነት ተሰምቶን አገራችንንና ሕዝባችንን ልንክስ ይገባል፡፡ ሁልጊዜ ከጥፋት መማር ብቻም ግን አይገባም፡፡ ሁሉም ወገን መከባበርን አስፍኖ መነጋገርን ባህል አድርጎ ለሀገር ግንባታ መነሳት አለበት፡፡
የኦሮሞ አባገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎችና የአገር ሽማግሌዎች ለሰላም ያደረጉት ጥረት ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም ወገን መትጋት አለበት፡፡ የፖለቲካ ሃይሎችም ለግጭት መፍትሄ በሆኑ ባህላዊ እሴቶቻችን ታግዘው ከራስ ይልቅ ለህዝብ ሰላም መስራት ይገባቸዋል፡፡ ይህን በማድረግም ኢትዮጵያ የባህልና የትውፊት ባለሀብት መሆኗን ለዓለም ማሳየት ተችሏል።
አዲስ ዘመን ጥር 15/2011