በልጅነታቸው ብዙ ውጣ ውረዶችን አይተዋል።የቀለም ትምህርትን እንደልባቸው ለማግኘት አልቻሉም።ይሁን እንጂ የሕይወትን ፈተናዎች ተጋፍጠው የአገር ባለውለታ እንዲሆኑ ያስቻሏቸውን ተግባራት አከናውነዋል።ምንም እንኳ በቀለም ትምህርት ብዙ ባይገፉም ከ50 በላይ መጻሕፍትን መጻፍ (በድርሰትና በትርጉም) ችለዋል።ከስነ ጽሑፉ ባሻገር ስለ ሰላምና አብሮነት በተደጋጋሚ ይሰብኩ ነበር … ማሞ ውድነህ።የ81 ዓመታት የሕይወት ጉዟቸውንና አበርክቶዎቻቸውን በአጭሩ እንመለከታለን።
ጥቅምት 12 ቀን 1923 ዓ.ም. ዋግኽምራ ውስጥ ከአቶ ውድነህ ተፈሪና ከወይዘሮ አበበች ወልደየስ የተወለደው ማሞ ውድነህ፣ የልጅነት ጊዜው በአስቸጋሪ ፈተናዎች የተሞላ ነበር።በ1928 ዓ.ም ኢትዮጵያን የወረረው የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር በዓለም አቀፍ ሕግ የተከለከለ የመርዝ ጋዝ በአውሮፕላን በመርጨት በርካታ ሰላማዊ ሰዎችን ገድሏል፤ መንደሮችን በቦምብ አውድሟል።ማሞ የተወለደባት መንደር ደግሞ በፋሺስት የጦር አውሮፕላኖች ከተደበደቡት የኢትዮጵያ አካባቢዎች መካከል አንዷ ነበረች።ሕፃኑ ማሞ በዚህ ድብደባ ወላጆቹን አጣ።
ማሞ የትውልድ መንደሩ የደብር አለቃ ከነበሩት ከየኔታ ትኩ ዘንድ እስከ ዳዊት መድገም ድረስ ተምሮ ዘመናዊ ትምህርት ለመማር ወደ ከተማ ገባ።ይሁን እንጂ በቀለም ትምህርት ረገድ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን ከማጠናቀቅ በዘለለ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን መቀጠል እንዳልቻለ የተለያዩ የታሪክ ማስረጃዎች ያሳያሉ።
በቀለም ትምህርት አለመግፋቱን በብዙ ንባብ ማካካስ የነበረበት ማሞ፣ ብዙ በማንበብና በማሰላሰል ወደ ጽሑፍ መድረክ ወጣ።‹‹ፖሊስና እርምጃው›› የተባለው የፖሊስ ሰራዊት ጋዜጣ በ1952 ዓ.ም. ሲቋቋም የመጀመሪያው አዘጋጅ ሆኖ ለአምስት ዓመታት ያህል አገልግሏል። በ‹‹አዲስ ዘመን›› እና በ‹‹ሰንደቅ ዓላማችን›› ጋዜጦች ላይም ሰርቷል።
በ1952 ዓ.ም. ማሞ ‹‹የት ትገኛለች?›› በሚል ርዕስ በጋዜጣ ላይ ለጻፈው መጣጥፍ እውቁ ደራሲና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ ‹‹እሱስ የት ይገኛል?›› በማለት የሰጠው ምላሽ ሁለቱን የስነ ጽሑፍ ሰዎች ለረጅም ጊዜ አከራክሯቸዋል።
የጽሑፍ እሰጥ አገባው በወንዶችና ሴቶች መካከል ያለውን የወግ ልዩነት አስመልክቶ የተደረገ ሙግት ነበር።ክርክሩ ለብዙ ጊዜያት ቀጥሎ እስከ መንግሥት ባለሥልጣናት ድረስ አነጋጋሪ ለመሆን እንደበቃ ይነገራል።
ክርክሩ የበርካቶችን ቀልብ በመሳቡ የማስታወቂያ ሚኒስትሩ አቶ መኰንን ሀብተ ወልድ ‹‹ጉዳዩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጉዳይ ነው›› በማለት ‹‹መጠናት አለበት›› ብለው አምባሳደር ዘውዴ ረታ ያሉበት ኮሚቴ ተቋቋመ።ኮሚቴው ሁለቱንም ተከራካሪዎች ጠርቶ ባነጋገራቸው ወቅት ‹‹ፊት ለፊት ቢገናኙ ይገዳደላሉ›› ተብሎ በሕዝቡ ይናፈስ በነበረው ወሬ ምክንያት ፖሊስ በመካከላቸው ቢገኝም ባለጉዳዮቹ ማሞ ውድነህና ጳውሎስ ኞኞ ተሳስቀው መሳሳማቸው የኮሚቴውን አባላት ያስደነቀ አጋጣሚ ነበር።
‹‹ብዙ ያነበበ፣ ብዙ ይጽፋል›› እንዲሉ አቶ ማሞ ውድነህ በጋዜጠኝነትና በደራሲነት ያበረከቷቸው ስራዎቻቸው የንባባቸውን ስፋትና ጥልቀት የሚያሳዩ ናቸው።የንባባቸው አድማስ በስራዎቻቸው ፈርጀብዙነት በግልፅ የሚታይ ነው።
ደራሲና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ በበርካቶች ዘንድ የሚታወቁት በተለይ በስለላና በወንጀል ምርመራ ላይ በሚያጠነጥኑ የትርጉም ሥራዎቻቸውና ድርሰቶቻቸው ነው።የታሪክ፣ የልብ ወለድና የተውኔት ስራዎቻቸውም ተወዳጅ ናቸው።በአጠቃላይ ከ50 በላይ የድርሰትና የትርጉም ስራዎችን አሳትመዋል።ከስራዎቻቸው መካከል፡-
•ሁለተኛው የዓለም
•የደቡብ ሱዳን ብጥብጥ
•ብዕር እንደዋዛ
•ፊልድ ማርሻል
ሞንትጐመሪ
•የኤርትራ ታሪክ
•የኛ ሰው በደማስቆ
•የ፪ ዓለም ሰላይ
•ምጽአተ-እሥራኤል
•ሰላዩ ሬሳ
•የ፲፯ቱ ቀን ጦርነት
ጦርነት
•የሴቷ ፈተና
•ከወንጀለኞቹ አንዱ
•ቤኒቶ ሙሶሊኒ
•የገባር ልጅ
•ሁለቱ ጦርነቶች
•አደገኛው ሰላይ
•ዲግሪ ያሳበደው
•ካርቱም ሔዶ ቀረ?
•የ፮ቱ ቀን ጦርነት
•የካይሮው ጆሮ ጠቢ
•ሮሜል – የበረሃው
ተኩላ
•ዘጠና ደቂቃ በኢንተቤ
•ጊለን – የክፍለ ዘመኑ
ሰላይ
•የኦዴሳ ማኅደር
•ከርታታዎቹ
•ከሕይወት
በኋላ ሕይወት
•ስለላና ሰላዮች
•ምርጥ ምርጥ ሰላዮች
•ዕቁብተኞቹ
•አሉላ አባነጋ
•የሰላዩ ካሜራ
•ሰላይ ነኝ
•በዘመናችን
ከታወቁ ሰዎች
•ዕድርተኞቹ
•ሾተላዩ ሰላይ
•ማኅበርተኞቹ
•በረመዳን ዋዜማ
•የበረሃው ማዕበል
•ኬ.ጂ.ቢ. ውስብስቡ
የስለላ መዋቅር
•ሲ.አይ.ኤና ጥልፍልፍ
ስራዎቹ
•ዩፎስ – በራሪ ዲስኮች
•መጭው ጊዜ
•ዮሐንስ
•የአሮጊት አውታታ
•እኔና እኔ
•ኤርትራና ኤርትራውያን
•ሞት የመጨረሻ ነውን?
•የደረስኩበት ፩
•የደረስኩበት ፪
የሚሉት ይጠቀሳሉ።እነዚህ የስለላ፣ የግለሰቦች ታሪክ፣ የሳይንስ፣ የልብ ወለድ፣ የታሪክና የተውኔት ይዘት ያላቸው የድርሰትና የትርጉም ስራዎቻቸው ለኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍ ዘርፍ እድገት ከፍ ያለ አስተዋፅኦ ማበርከት ችለዋል።
ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በአብዛኛው አውሮፓ ውስጥ ይካሄድ እንጂ ውጊያው የተሟሸው በ1928ቱ የጣሊያኖች ወረራ በኢትዮጵያ ነው። ማሞ የተወለዱባት መንደር ደግሞ በፋሺስት ኢጣሊያ የጦር አውሮፕላኖች ስለተደበደበችና በድብደባው ማሞ ወላጆቻቸውን ለጦርነቱ ብዙም ሩቅ አልነበሩም።ይህ ሁኔታም በ1954 ዓ.ም. ለወጣው ‹‹ሁለተኛው የዓለም ጦርነት›› የተሰኘው ስራቸው አጋጣሚን ፈጥሯል።
በ1965 ዓ.ም የታተመውንና ‹‹ምፅዓተ እስራኤል›› የተሰኘውን ስራቸውን ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ 500 ቅጂዎችን (አንዱን በስምንት ብር ሂሳብ) መግዛታቸውን የታሪክ መዛግብት ያመለክታሉ።‹‹አሉላ›› የተሰኘው ድርሰታቸው በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በቴአትር መልክ ተሰርቶ ቀርቧል።
በ1968 ዓ.ም. ከእስራኤል ተነስቶ ወደ ፈረንሳይ ያቀና የነበረው የፈረንሳይ አየር መንገድ (Air France) አውሮፕላን በግሪክ የአየር ክልል ውስጥ ሳለ በፍልስጥኤም ነፃ አውጭ ድርጅት አንጃ ተጠልፎ የኡጋንዳ ሁለተኛ ከተማ በሆነችው ኢንቴቤ አውሮፕላን ጣቢያ እንዲያርፍ ይገደዳል። ጠላፊዎቹ አብዛኛዎቹን መንገደኞች ለቅቀው ወደ መቶ የሚጠጉትን አይሁዳውያንን ለይተው ያግታሉ። የእስራኤል ልዩ ኃይሎች (ኮማንዶዎች) እጅግ በሚያስደንቅ ጀግንነት 90 ደቂቃ ብቻ በፈጀ ግዳጅ ጠላፊዎቹንና ሃምሳ የሚሆኑ የኡጋንዳ ወታደሮችን ገድለው ዜጎቻቸውን ነጻ ያወጡበት ታሪክ ‹‹ዘጠና ደቂቃ በኢንቴቤ›› በሚል ተርጉመውታል። በመጽሐፉ ላይ በወቅቱ ስለነበረው አነጋጋሪው የኡጋንዳው መሪ ኢዲ አሚን ዳዳም ተጠቅሷል።
አቶ ማሞ ከመጽሐፍት በተጨማሪ ጽሑፎቻቸውን በተለያዩ ጋዜጦችና መጽሔቶች ላይም ያሳትሙ ነበር።ታዲያ ጽሑፎቻቸው ጠንከር ያሉና ሹማምንትን ጭምር ሸንቆጥ የሚያደርጉ ነበሩ።በ‹‹የካቲት›› መጽሔት ላይ ፕሬዚደንት መንግሥቱ ኃይለማርያም ‹‹የአገራችንን የባህል ልብስ ለብሰው ቢታዩስ?›› በሚል ርዕስ ያቀረቡት አስተያየት የመጽሔቱ ዋና አዘጋጅ የነበሩት አንጋፋው ጋዜጠኛና ደራሲ ማዕረጉ በዛብህ 150 ብር እንዲቀጡ ምክንያት ሆኗል።
አቶ ማሞ ገጣሚም ነበሩ።በአጠቃላይ ከ200 በላይ ግጥሞችን እንደፃፉ በአንድ ወቅት ተናግረው ነበር።አንዳንድ ግጥሞቻቸው ቀደም ሲል አዲስ አበባና አሥመራ ከተሞች በታተሙ ጋዜጦች ላይ መውጣታቸውና ሌሎቹ ደግሞ እንዳይታተሙ ሳንሱር ከልክሏቸውና ቆራርጧቸው እንደቀሩም ተናግረዋል።
ደራሲና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ የብዕርና ወረቀት ሰው ብቻ አልነበሩም። ተናጋሪ (Public Speaker)ም ናቸው። በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ጥልቅ እውቀት ያላቸውና ከሁሉም በላይ ደግሞ ሀሳባቸውን ለማካፈል ሁሌም ዝግጁ እንደነበሩ የሚያውቋቸው ሁሉ ይመሰክሩላቸዋል። ‹‹ … ብዙ ጊዜ ከአንድ የስልክ ጥሪ በላይ አይፈጁም›› ይሏቸዋል። አቶ ማሞ በርካታ መጻሕፍትን ከማበርከታቸው በተጨማሪም የኢትዮጵያ
ደራሲያን ማህበርን ለ12 ዓመታት በሊቀመንበርነት አገልግለዋል።
አቶ ማሞ ስለ ሰላምና መከባበር ደጋግመው የሚሰብኩ ሰው ነበሩ።ይቅርታ ማድረግም የሁሉም ሰው ባሕል ሊሆን እንደሚገባ አበክረው ሲናገሩ ኖረዋል።እርሳቸው የይቅርታ ልብ ያላቸው ሰው ስለመሆናቸው በኤርትራ የነበራቸው አጋጣሚ ይመሰክራል።አቶ ማሞ በቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በማስታወቂያ ሚኒስቴር የኤርትራ ተጠሪ ሆነው ሲሰሩ የሚያዘወትሩበት ሬስቶራንት ባለቤቶች ጣሊያናውያን ነበሩ።አንድ ቀን የሬስቶራንቱ ባለቤት የሆኑት ጣሊያናዊ ሽማግሌ ከእነ አቶ ማሞ ጋር ቁጭ ብለው ሲያወሩ በፋሺስት ወረራ ወቅት የጦር አውሮፕላን አብራሪ እንደነበሩና ብዙ የኢትዮጵያውያን ቤቶችን እንዳወደሙ ይነግሯቸዋል።ጣሊያናዊው ሰው አቶ ማሞ በፋሺስቶች የአየር ድብደባ ወላጆቻቸውን እንዳጡ አያውቁም ነበር።አቶ ማሞም የሰሙትን ሰምተው በዝምታ ወደ ቤታቸው አመሩ።ከዚያም ሰውየውን ለመበቀል ሲያውጠነጥኑ ከቆዩ በኋላ ‹‹ … ይህን ሰውዬ ብገድለው የሞቱትን ወላጆቼን መልሼ አገኛቸዋለሁ? በቀል ምን ይጠቅመኛል? …›› ብለው በማሰብ የበቀሉን ጉዳይ እርግፍ አድርገው ተውትና ወደ ጣሊያናዊው ሰው ተመልሰው ስለሁኔታው አጫወቷቸው።ጣሊያናዊው ሽማግሌም ስቅስቅ ብለው አልቅሰው አቶ ማሞን ይቅርታ ጠየቋቸው።ስለሁኔታውም ለባለቤታቸው ነገሯቸውና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አቶ ማሞና ጣሊያናውያኑ ጥንዶች የተለየ ቅርበትና ወዳጅነት ፈጠሩ።
አቶ ማሞ በቀድሞው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በሚመራው የእርቅና ሽምግልና ኮሚቴ ውስጥ በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል ሰላምን ለማምጣት ጥረት ካደረጉ ሰዎች መካከልም አንዱ ነበሩ። ከኮሚቴው ባሻገርም በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ሰላም እንዲፈጠር አቶ ማሞ ተደጋጋሚ ጥረቶችን አድርገዋል።
በወታደራዊው መንግሥት የመጨረሻ ቀናት ላይ በአዲስ አበባ ዙሪያ የነበረው የመንግሥትና የአማፅያኑ ኃይሎች ፍጥጫ ያሳሰባቸው አቶ ማሞ በሬዲዮ ቀጥታ ስርጭት ላይ ቀርበው ግጭትና ደም መፋሰስ እንዳይፈጠር፤ ሁሉም ነገር በሰላም እንዲጠናቀቅ መልዕክት አስተላልፈው ከተማዋ ከውድመት ታድገዋታል።
አቶ ማሞ ያመኑበትን ሃሳብ ከመግለፅ ወደኋላ የማይሉ ሰው ነበሩ።በአንድ ወቅት ሊቀ መንበር ሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማሪያም የአፍሪካ አገራት መሪዎችን በጋበዙበት የፓርቲያቸው ስብሰባ ላይ ጎረቤት አገራትን ‹‹ኢምፔሪያሊስቶች››፣ ‹‹አድሃሪያን›› … እያሉ ሲወርፉ አቶ ማሞ የመናገር እድል እንዲሰጣቸው ጠይቀው ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር በባሕል፣ በምጣኔ ሀብትና በታሪክ የተሳሰረች መሆኗን ጠቁመው ጥላቻን ያዘለው የሊቀመንበሩ ንግግር ትክክል እንዳልሆነ ተናገሩ።በጉባዔው ላይ ታድመው የነበሩት የወቅቱ የዛምቢያና የግብጽ ፕሬዚደንቶች የአቶ ማሞ ንግግር ትክክልና በአፍሪካዊነት ስሜት የተቃኘ ተገቢ ሃሳብ እንደሆነ ገልጸዋል።
ከባለቤታቸው ከወይዘሮ አልማዝ ገብሩ ጋር ለ52 ዓመታት ያህል በትዳር ያሳለፉት ደራሲና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ፣ በትዳራቸው ለሌሎች በተለይም አሁን ላለው ትውልድ ትልቅ ተምሳሌት ስለመሆናቸው ይነገርላቸዋል። ‹‹በትዳር ለረዥም ጊዜ ለመኖርዎ ምስጢሩ ምንድነው?›› ተብለው ተጠይቀው ሲመልሱም፣ ‹‹መተማመንና መቻቻል›› በሚል በአጭሩ የገለጹት ደራሲ እና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ፣ ልጆቻቸው አንድም ቀን ጭቅጭቅ ሰምተው እንደማያውቁ ልምዳቸውን አካፍለዋል።‹‹ችግር ሲኖር ቤት ቆልፈን እንነጋገርበታለን›› በማለት ልጆቻቸው ክፉ ቃል ሳይሰሙ ማደጋቸውን ይናገራሉ።ስድስት ልጆችና 10 የልጅ ልጆችን ለማየት የበቁት ደራሲ እና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ ‹‹ሀብታችን ልጆቻችን ናቸው›› በማለት በኩራት የመናገር ልምድ ነበራቸው።
የአቶ ማሞ የትዳር ሕይወት በአርዓያነት የሚጠቀስ እንደሆነ የአቶ ማሞን ቤተሰብ የሚያውቁ ሁሉ ይመሰክራሉ።ለአብነት ያህል አቶ አበራ ሳህሌ የተባሉ ግለሰብ ‹‹ጋሽ ማሞን ሳውቃቸው›› በሚል ርዕስ በጻፉት ጽሑፍ፣ ‹‹ … በ1994 ዓ.ም. ገደማ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ‹አውደሰብ› የተሰኘ ፕሮግራም በተጀመረበት ወቅት ከአዘጋጆች መካከል አንዱ ነበርኩ። እያንዳንዳችን የቡድኑ
አባላት በዝግጅቱ ለመስራት የምናስባቸውን ሰዎች ከአሳማኝ ምክንያት ጋር በጽሑፍ ማቅረብ ነበረብን። እኔ ማሞ ውድነህን ለመስራት ያቀረብኩት ዕቅድ ተቀባይነት በማግኘቱ እሳቸውን በቅርበት ለማወቅ መንገድ ከፍቶልኛል።
የእሳቸውን ታሪክ ለመስራት ከካሜራ ፊትና ኋላ ብዙ አውርተናል። ቤታቸውን አስጎብኝተውኛል። ከቤተሰቦቻቸውም ጋር ለመተዋወቅ ዕድል ገጥሞኛል። የካ ክፍለ ከተማ ቤልጂየም ኤምባሲ አካባቢ ያለው ግቢያቸው አረንጓዴነቱ ከሁሉም ቀድሞ ይታወሰኛል። ቤታቸው ውስጥ ያለው የመጽሐፍ ብዛት ማለቂያ የለውም። የጽሕፈት ጠረጴዛቸው፣ የመብራቱ አቀማመጥ፣ እንዲሁም ፀጥታው ይገርመኛል።
በዚህ ሁሉ መካከል ግን ከማሞ ውድነህና ቤተሰቦቻቸው እስካሁን የማልረሳው እንግዳ ተቀባይነታቸው ነው። የባለቤታቸው የወይዘሮ አልማዝ ገብሩ ሳቅ ከልብ ነው። ከት ብለው ይስቃሉ። ሳቅ ደግሞ ይጋባል። ባለቤታቸውና ልጆቻቸው ያልተዘመረላቸው ጀግኖች ናቸው። ወይዘሮ አልማዝ፣ አቶ ማሞ ሳይረበሹ የሚሰሩበትን ሁኔታ አመቻችተዋል። ልጆቻቸው በትየባና በእርማት (ያውም ኮምፒውተር ባልነበረበት ጊዜ) ትልቅ ውለታ አበርክተዋል። አንዳንዶቹ ከአባታቸው ስራ ጋር የተዋወቁት በዚሁ ሂደት ነው። ነገር ግን ስላበረከቱት ድርሻ ካልተጎተጎቱ በስተቀር ከማናቸውም የሚሰማ ነገር የለም። በሰፊው ሲታይ አባታቸውን ሳይሆን መላውን ኅብረተሰብ ነው ያገለገሉት።
ማሞና ባለቤታቸው በትዳር ህይወት የቆዩት ከአንድ ኢትዮጵያዊ አማካይ የሕይወት ዘመን አይተናነስም። ለሃምሳ ሁለት ዓመታት አብረው በመኖራቸው በርካታ የልጅ ልጆችን ለማየት ታድለዋል። ባለትዳሮቹ ግን ከባልና ሚስትነት ይልቅ ጓደኝነት አልፎ አልፎም የወንድምና እህት ፉክክር ይታይባቸዋል … ›› በማለት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
በአንድ ወቅት ‹‹ቀረኝ የምትለው ነገር አለህ ወይ?›› የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ማሞ ‹‹ … የምችለውን ያህል ወርውሬያለሁ፤ እኮራበታለሁኝ፤ ቀረኝ የምለው ነገር የለኝም›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።ስለስራዎቻው ሕዝባዊነት ሲናገሩም ‹‹ከሕዝብ የወሰድኩትን ነው፤ ወደ ሕዝብ መልሼ የሰጠሁት›› ብለዋል።
ትጉህ አንባቢ፣ የበርካታ መጻሕፍት ደራሲ፣ ጨዋ፣ ባህል አክባሪ፣ የሰላምና የይቅርታ ሰባኪ፣ ደፋርና አንደበተ ርቱዕ የነበሩት አንጋፋው ደራሲና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በተለያዩ ሆስፒታሎች ህክምናቸውን ሲከታተሉ ቆይተው የካቲት 23 ቀን 2004 ዓ.ም ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል።ስርዓተ ቀብራቸውም የሐይማኖት አባቶች፣ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ የጥበብ ሰዎች፣ አድናቂዎቻውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት በአዲስ አበባ መንበረ ፀባዖት ቅድሥት ሥላሴ ካቴድራል ተፈፅሟል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 10/2012
አንተነህ ቸሬ