የመስኖ መሠረተ ልማቶችን የማስተዳደር ሥራ ትኩረት ይፈልጋል!

ግብርናውን ከዝናብ ጥገኝነት ለማውጣት፣ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ፣ የምግብ ዋስትናንና ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ከተቀየሱ ስትራቲጂዎች መካከል የመስኖ ልማት አንዱ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በእዚህ መነሻነትም የበርካታ ትላልቅ፣ መለስተኛና አነስተኛ ግድቦች ግንባታ ተካሂዷል፤ እየተካሄደም ይገኛል፡፡ ከእዚሁ ጎን ለጎን ለእዚሁ ዓላማ የሚውሉ ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች ተቆፍረዋል፡፡

በመስኖ መሠረተ ልማቶቹ ስንዴን ጨምሮ የተለያዩ የሰብል፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ዓይነቶችን በመስኖ የማልማት ሥራ እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ የተገነቡ ግድቦች ቀደም ሲል ለስኳር እና ለአትክልትና ፍራፍሬ ልማት የዋሉበት ሁኔታ እንዳለ ሆኖ እንደ ስንዴ ላሉት ሰብሎች የመስኖ ልማትም የሚውሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

ይህን ሁሉ ተከትሎም በልማቱ እመርታዊ ለውጦች ተመዝግበዋል፡፡ ለእዚህም የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን በአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ በሀገሪቱ በስንዴ ልማት እየተመዘገበ ላለው ውጤት የመስኖ ልማቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ ባለፈው ዓመት በመኸር፣ በበጋ ስንዴ ልማትና በበልግ 300 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ የተመረተ ሲሆን፤ ከእዚህ ውስጥ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ሚና ከፍተኛ ነበር፡፡

የመስኖ ልማቱ በእዚህ ልክ እየተካሄደ ባለበት በእዚህ ዘመን ለመስኖ አገልግሎት የተገነቡት የከሰምና ተንዳሆ ግዙፍ ግድቦች ለታለመላቸው ዓላማ ያልዋሉበት ሁኔታ እንዳለ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ በቅርቡ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ይፋ ያደረገው ጥናት እንዳመለከተውም፤ በግድቦቹ ሲለማ የነበረው በጣም ውስን እዚህ ግባ የማይባል ሄክታር መሬት ብቻ ነበር፡፡ ይህም ይባስ ብሎ የመስኖ ልማቱ በተለያዩ ምክንያቶች ቆሟል፡፡

ሀገሪቱ እነዚህ ግድቦች የጀመሩትን ልማት በማቋረጣቸው ወይም ወደ ልማቱ በሚጠበቀው ልክ ባለመግባታቸው ሳቢያ ሀገሪቱ ለኪሳራ እየተዳረገች ትገኛለች፡፡ የከሰም ግድብ በሚፈለገው ልክ ወደ ሥራ ባለመግባቱ ሳቢያ በዓመት 10 ቢሊዮን ብር እንዲሁም የተንዳሆ ግድብም እንዲሁ በሚፈለገው መልኩ ሥራ ላይ ባለመዋሉ ሳቢያ በዓመት 33 ቢሊዮን ብር እያጣች መሆኑን ጥናቱ አመላክቷል፡፡

ይህ እየሆነ ያለው መስኖ ልማት ላይ በስፋት መሥራት በጀመረች፤ በእዚህም ውጤታማ እየሆነች በምትገኘዋ ኢትዮጵያ ነው፡፡ በሌሎች አካባቢዎች ሌሎች የመስኖ መሠረተ ልማቶች እየተገነቡ ባለበት ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች የመስኖ መሠረተ ልማት ካልተገነባልን፣ የተጀመረው ግንባታ ዘገየ እየተባለ በሚጠይቅበት በአሁኑ ወቅት እነዚህ ብዙ ሀብት ወጥቶባቸው በተገነቡ የመስኖ መሠረተ ልማቶች መጠቀም አለመቻል ተገቢ አይሆንም፡፡ ለመፍትሔውም ፈጥኖ መንቀሳቀስም ይጠይቃል፡፡

ለመስኖ መሠረተ ልማቶቹ በሚፈለገው ልክ ሥራ ላይ አለመዋልም ሆነ ጨርሶ ወደ ሥራ አለመግባት ምክንያት ተደርገው ከቀረቡት መካከል የመስኖ መሠረተ ልማት ማስተዳደር አቅም ውስንነት አንዱ መሆኑም በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡

በርግጥ ግድብ መገንባትና የመስኖ አውታሮችን መዘርጋት ትልቅ ነገር ነው፡፡ በእዚህ መሠረትም በሀገሪቱ ባለፉት ዓመታት በርካታ ትላልቅ የመስኖ ግድቦች ተገንብተዋል፡፡ ይህ አንድ ስኬት ነው፡፡ የመጨረሻው ግብ ግን በመሠረተ ልማቶቹ የመስኖ ልማቱ ተካሂዶ የሚፈለገውን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ነው፤ በእዚህ በኩል መፈጸም ያለበት ሊፈጸም አልቻለም፡፡

ከባዱ የግንባታ ሥራ ተካሂዶ እያለ በማስተዳደር ውስንነት ሳቢያ ሀገር በመሠረተ ልማቶቹ ማግኘት የሚገባትን ሳታገኝ መቅረቷ በእጅጉ ማስቆጨት ይኖርበታል፤ ይህ ብቻም ሳይሆን ይህን ሀብት በሚገባ ጥቅም ላይ በማዋል የታለመለትን እንዲያሳካ ለማድረግ በፍጥነት መንቀሳቀስ ይገባል፡፡

መንግሥት ግብርናውን ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅ ቆርጦ እየሠራ ባለበት ሁኔታ እነዚህ ግዙፍ የመስኖ መሠረተ ልማቶች በእዚህ ደረጃ ከልማቱ ውጪ መሆናቸው በእጅጉ ያሳስባል፡፡ የሚመለከታቸው አካላት በእዚህ ላይ ተነጋግረው መፍትሔ ማስቀመጥ ባለባቸው ወሳኝ ወቅት ላይ መሆናቸው ሊታወቅ ይገባል፡፡

በጥናቱ መሠረት የችግሩ ምንጭ ከሆኑት መካከል የመስኖ መሠረተ ልማቱን ማስተዳደርና መጠገን ችግሮች ታይተዋል፡፡ ችግሮቹ ከተለዩ በፍጥነት ወደ መፍትሔው መግባት ክፍተቱን ለመሙላት ይረዳል፡፡ ጥናቱ ያመላከታቸው መፍትሔዎች አሉ፤ ሌሎች መፍትሔዎችንም አዘጋጅቶ መሠረተ ልማቶቹ ሙሉ ለሙሉ ወደ ልማቱ እንዲገቡ ማድረግ ላይ መሥራት የመጪው ጊዜ ሥራ ሊሆን ይገባል፡፡

መሠረተ ልማቶቹን ማስተዳደር የሚያስችሉ አሠራሮችን ቀይሶ በመተግበር ዘላቂ መፍትሔ ማስቀመጥም ያስፈልጋል፡፡ እነዚህን ችግሮች መፍታት ላይ በሚገባ ከተሠራ እየተገነቡ ባሉና በቀጣይ በሚገነቡ ተመሳሳይ መሠረተ ልማቶች ሊገጥሙ ለሚችሉ ችግሮችም ከወዲሁ መፍትሔን ያመላከተ አሠራር ለማስቀመጥ ይጠቅማል!

አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You