ጤንነቱ የተጠበቀ የስራ ፍላጎቱ እና ታታሪነቱ የተረጋገጠ በቂ ትምህርት እና ስልጠና ያለው እርሶ አደር መፍጠር ለግብርና ልማት ወሳኝ ነው። ታዲያ የዚህን ሀይል ምርታማነቱን ለማሳደግ የሚያስችለው የቴክኖሎጂ አቅርቦት ካላገኘ፣ ቴክኖሎጂው በሚፈለገው መጠን ካልተባዛ እና በአግባቡ ወደ አምራቹ ካልተሰራጨ የሚፈለገው እድገት ሊገኝ አይችልም። በመሆኑም የቴክኖሎጂ አቅርቦት የብዜት ስርጭትን የማሻሻል ጉዳይ የህዝቡን የማምረት አቅም ከማጎልበት ተግባር ተነጥሎ የማይታይ ጉዳይ ይሆናል።
እንደሚታወቀው በአገራችን እጅግ በርካታ የተለያዩ የአግሮ ኢኮሎጂ ዞኖች አሉ፤በሁሉም አካባቢዎች አንድ ዓይነት ቴክኖሎጂ መጠቀም አይገባም። በአንድ አካባቢ የሚሰራ ቴክኖሎጂ ማለትም በቂ ዝናብ ባላቸው አካባቢዎች ፈጽሞ በሌላ ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎች አይሰራም፤ ቢሰራም ተፈላጊውን ውጤት አያስገኝም። እያንዳንዱ አካባቢ በግብርና ልማት ረገድ ሊያስገኝ የሚችለውን የላቀ ዕድገት እንዲያስገኝ ለማድረግ ከአካባቢው ሁኔታ ጋር የተጣጣመ ቴክኖሎጂ መቅረብ አለበት። በመሆኑም ለተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች የሚስማሙ መላውን የአገራችንን የአግሮ ኢኮሎጂ ዞኖች ፍላጎት የሚያረኩ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ማቅረብና ይህንኑ በቀጣይ ማሻሻል ያስፈልጋል። የግብርና ቴክኖሎጂ አቅርቦቶችም ይህንን ለማድረግ የሚያስችል ባህሪ ሊኖረው ይገባል።
የሚቀርበው የግብርና ቴክኖሎጂ አርሶ አደሩ በማምረት እንቅስቃሴው ሂደት የሚያጋጥሙትን ምርታማነቱንና ገቢውን የሚጎዱ ችግሮችን በመፍታት የግብረና ልማትን ለማፋጠንና የአርሶ አደሩን ህይወት መለወጥ የሚያስችሉ መሆን አለባቸው። ስለሆነም የሚቀርበው ግብርና ቴክኖሎጂ ከአርሶ አደሩ ተጨባጭ ችግር የሚነሳ መሆን አለበት። አርሶ አደሩም የማምረት ስራ ከሚጀምርበት፣ አምርቶ እስከሚሸጥበት ድረስ ያሉትን እጅግ በርካታ ስራዎች በሚገባና በዝርዝር በማጥናት ችግሮቹን ለይቶ በማውጣት ለመፋታት የሚያስችል መሆን አለበት።
ታዲያ የአካባቢውን ሁኔታ ያገናዘበ ምርታማነት ሊጨምሩ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ አርሶ አደሩ ምርታማነቱ እንዲጨምር እየሰሩ ካሉት የምርምር ተቋም አንዱ የሆነው የአምቦ የግብርና ምርምር ተቋም ነው። በተቋሙ ውስጥ የግብርና ኤክስቴሽን ባለሙያ እና የኮሚኒኬሽን ቡድን መሪ የሆኑት ወይዘሮ አዜብ በቀለ ተቋማቸው አርሶ እና አርብቶ አደሩን እንዴት እያገዘ እንዳለ እና ተቋሙ የአርሶ አደሩን ምርታማነትን የተሻሻለ ቴክኖሎጂ በማቅረብ እንዴት እየጨመረው እንዳለ ነግረውናል።
በግብርና ኤክስቴንሽን የተሰሩ ስራዎች
የአምቦ ግብርና ምርምር በአገር አቀፍ ደረጃ የእጽዋት ጥበቃ ስራዎችን እና የደጋ በቆሎ ምርምሮችን በአገር አቀፍ ደረጃ እያስተባበረ የሚገኝ ተቋም መሆኑን የአምቦ ግብርና ኤክስቴንሽንና ኮሙኒኬሽን የቡድን መሪ የሆኑት ወይዘሮ አዜብ በቀለ ይናገራሉ።
እንደ ወይዘሮ አዜብ ገለጻ የአምቦ ግብርና ምርምር በኦሮሚያ ምዕራብ እና ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን፤ ከማዕከሉ ሆነ ከሌሎች ማዕከላት የሚወጡ ቴክኖሎጂዎችን ፣ምክረ ሀሳቦችን በማዕከሉ በተለያዩ አግሮ ኢኮሎጂ የማላመድ ስራ እና የቅድመ ማስተዋወቅ ስራዎችን በግብርና ኤክስቴንሽን በኩል ይሰራል። እንደባለሙያዋ ገለጻ ይህ የቴክኖሎጂ ውጤት ወደ አርሶ አደሩ የሚመጣው በየወረዳዎች የሚከሰቱትን የተለያዩ ችግሮች በመለየትና በአካባቢው በሚዘራ ዋና የሰብል ዓይነቶችን መሰረት በማድረግ የፍላጎት ጥናት ተሰርቶ ነው።
ለደጋው ተስማሚ የሆነ የበቆሎ ዝርያ ጂባት ”Jibat” የተሰኘው እና የፕሮቲን ይዘታቸው ከፍተኛ የሆኑና ለደጋው አየር ንብረት ተስማሚና ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የበቆሎ ዝርያዎችን በሳይንሳዊ ስማቸው “ኤ ኤም ኤች 760 ፣ኤ ኤም ኤች 852 …” የተባሉ የቴክኖሎጂ
ዝርያዎችን በተለያዩ የዞኑ ወረዳዎች በማስተዋወቅ በስፋት እንዲመረቱ መደረጉን ወይዘሮ አዜብ ገልጸዋል። እንዲህ ያሉ በየዓመቱ የሚወጡ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሮች፣ ለግብርና ባለሞያዎች የማስተዋወቅ እና የመስክ ላይ ስልጠና እና ትውውቅም በተቋማቸው በኩል እንደሚሠት ይናገራሉ።
ከዚህም ባለፈ የሰርቶ ማሳያ ስራዎችን መስራት ብቻ ሳይሆን የምግብ አሰራሩንም በአራት የምግብ አይነት በዳቦ፣ በገንፎ፣ በቅንጨ እና አነባበሮ መልክ በማዘጋጀት እናቶች ልጆቻቸውን እንዲመግቡ ትምህርት እንደሚሰጥ፣ ሴቶችን በስልጠናው እንዲሳተፍ ክትትልና የቤት ለቤት ቅስቀሳና ትምህርት እንደሚሰጡ ባለሙያዋ አስረድተዋል።
በኩታ ገጠም በማረስ የተገኘ ውጤት
እንደ ወይዘሮ አዜብ ገለጻ፣ ከቅድመ ማስተዋወቅ ስራ በተጨማሪ አርሶ አደሩን በፍቃደኝነት በማደራጀት በኩታ ገጠም ሠፋፊ እርሻዎች ላይ ጤፍ፣ ስንዴና፣ በቆሎ እና ማሽላ በማልማት ሰፋፊ ስራዎች ተሰርተዋል፣ በዚህም የአርሶ አደሩ ህይወት እንዲለወጥ ተደርጓል። ይህ የጋራ አሰራር ለማስተማርና ለአርሶ አደሩ ግበአቶችን በወቅቱ ለማቅረብና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በተጨማሪም ለአግሮ ኢንዲስትሪው በጥራትም ሆነ በብዛት የሰብል ምርት ግብአቶችን ለማቅረብ ስለሚረዳ ከባለፈው ዓመት ጀምር ልዩ ትኩረት ተሰጦት እየተሰራ ይገኛል። በዚህም መሰረት በ2011 በ316 ሄክታር ማሳ ላይ በቆሎ ጅባት፣ BH 661, 546, 547 ጤፍ፣ ኮራና፣ዳግም፣ ቁንጮ ፤ስንዴ ኪንግ ፣በርድ፣ ዋኔና ሊሙ፤ ማሽላ መልካም የተባሉ ዝርያዎችን በስፋት የማስተዋወቅ ስራ መሰራቱን ወይዘሮ አዜብ ተናግረዋል። ተቋሙ ለስራው ስራም የምስጋና ባህላዊ አልባሳትና እንዲሁም የምስክት ወረቀቶች ከወረዳውና ከዞኑ ተበርክቶለታል። በዘንድሮም ዓመት ሰፋፊ የኩታ ገጠም ስራዎችን በ11 ወረዳ ላይና በ500 ሄክታር መሬት ላይ በተደራጁ አርሶ አደሮች መሬት ላይ ተግባራዊ ለማድረግ አቅደው እየሰሩ እንደሆነ ወይዘሮ አዜብ ተናግረዋል።
የስራ እድል ፈጠራ ላይ የተሰሩ ስራዎችን አስመልክቶም፣ ከወረዳ ጋር በመሆን መሬት የሌላቸውን ወጣት አርሶ አደሮችን በሶስት ማህበር በማደራጀት የተሻሻሉ የጤፍ ዝርያዎችንና የሞያ ድጋፍ በመስጠት ከፍተኛ ምርት አግኝተዋል። በአምቦ ወረዳ ስራ አጥ ወጣት አርሶ አደሮች በማህበር ተደራጅተው ወረዳው በሰጣቸው መሬት ላይ በተቀናጀ ዘመናዊ የአመራረት
ዘዴ ምርጥ ዘር እና ጤፍ ሙሉ ፓኬጆችን ተጠቅመው እንዲዘሩ ተደርጓል።
በስራቸው ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ወጣት አርሶ አደሮች ለጀቤና ማዕበር 15 ዘመናዊ የእህል ጎተራ እና አንድ የጤፍ መውቂ ማሽን ተሰቷቸዋል። መንግስት ትኩረት በሰጠው መሰረት የቴክኖሎጂ ፍላጎት ጥናት ተደርጎ ግንደበረት እና አቡና ግንደበረት ወረዳዎች ምንም አይነት የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ አለመሆናቸውና ለመኪና አመቺ ያልሆነ ቦታ መሆኑን የዳሰሣ ጥናት በማድረግ የአጭር ጊዜና የረጅም ጊዜ እቅድ በማውጣት በቆሎ፣ አሲዳማ አፈርን በኖራ በማከም ስንዴ እንዲያመርቱ ድጋፍ እንደተደረገላቸው ወይዘሮ አዜብ ያስረዳሉ።
በጤፍ እና ማሽላ የተሻሻሉ የሰብል አይነቶች ላይ በሳለፍነው ዓመት በዘንድሮም የቀጠለ ሰፊ ስራ መሰራቱን የሚጠቅሱት ባለሙያዋ፣ በስራውም አበረታታች ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል። እንደዚሁም በኢልፈታ ወረዳ በዚሁ በጀት ዓመት በቀረበላቸው የደግፉን ጥያቄ መሰረት የዳሰሳ ጥናት ተደርጎ ሰፋፊ ሰርቶ ማሳያ ስራዎችን ለመስራት ስልት እየተነደፈ መሆንኑን ወይዘሮ አዜብ ገልጸው በቆሎ የኩታገጠም የማረስ ስራም በሰፊው እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ያጋጠሙ ተግዳሮቶች
የመጀመሪያው ተግዳሮት የአርሶ አደሩ ለውጥ በቶሎ ያለመቀበል ችግር ነው። ይህም በብዙ ትምህርቶች እና ሰርቶ በማሳያ ዘዴዎች አርሶ አደሩ በቴክኖሎጂዎቹ አምኖበት ወደስራ እንዲገባ ማድረግ መቻሉን ወይዘሮ አዜብ ያስረዳሉ። ሌላኛው ሁሉም ገበሬ ማህበር እና ቦታዎች ለመድረስ የመንገድ አለመመቻቸት ሌላኛው ተግዳሮት ነው። የእውቀቱን ክፈተት እየሞላን ሳይማር ያስተማረንን ይህንን ደግ ህዝብ ለመርዳት እንደባለሙያ እኔ እና የስራ ባለደረቦቼ ዝግጁ ነን ያሉት ወይዘሮ አዜብ ፣ የሚመለከተው አካል የመሰረተ ልማቶችን በተለይ ደግሞ መንገድ፣ ቢያንስ ደግሞ የውስጥ ለውስጥ ጥርጊያ መንገድ እንዲሰራ ጥሪያቸውንም አስተላልፈዋል።
መልዕክት
የቴክኖሎጂ አቅርቦት ብዜትና ስርጭት ስርዓት ተፈጥሮ እና ቀልጣፋነቱም ተረጋግጦ ቢሆን ዞሮ ዞሮ ይህንኑ ተቀብሎ ተግባራዊ የሚያደርገው አምራቹ አርሶ አደር ነው። ስለሆነም የሚቀርበውን ቴክኖሎጂ ከአርሶ አደሩ አቅም ጋር እንዲመጥን ተደርጎ መቅረብ ይኖርበታል። አርሶ አደሩ ሊጠቀምበት የማይችላቸውን የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎች እድገት ከማፋጠን አንጻር
ምንም ፋይዳ እንደማይኖራቸው ባለሙያዋ ያስረዳሉ። በሌላ በኩል ደግሞ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በተከታታይ ያለማቋረጥ ማቅረብ ያስፈልጋል። ይህን ማድረግ የምንፈልገውን ፈጣንና ቀጣይነት ያለው እድገት ሊያረጋግጥ እንደማይችልም አስገንዝበዋል።
ቴክኖሎጂው ከተጠቃሚው አቅም ጋር መመጣጠን አለበት ሲባል ከኤክስቴንሽን አገልግሎታችን ተጠቃሚ መሆን የሚችሉት እና የሚገባቸው ሶስት የተለያየ አቅም ያላቸው አምራቾች እንደሚኖሩ ታሳቢ መደረግ አለበት። በመጀመሪያ ደረጃ እና በዋነኛነት ያልተማረው አርሶ አደር አለ። በሂደት እየጨመረ ዋናው ክፍል እየሆነ የሚሂደው የተማረ እና የሰለጠነ አርሶ አደርም ሌላው ነው። ሁለቱ አንድ ዓይነት ቴክኖሎጂ መጠቀም አይችሉም፣ ስለዚህም ካልተማረው አርሶ አደር አቅም ጋር የሚመጣጠን የዝቅተኛ ቴክኖሎጂ ፓኬጅ እየተዘጋጀ መሰራጨት ይኖርበታል።
አሁን ካለንበት ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ ሲታይም ዋናው ጉዳይ ይህ ነው። ከዚህ ጎን ለጎን በሂደት በከፍተኛ ፍጥነት ይጨምራል ተብሎ የሚታሰበው የተማረ አርሶ አደር ነው፤ ለእንደዚህ ዓይነቱ አርሶ አደር የሚቀርበው ቴክኖሎጂ የላቀና ላልተማረው ከሚቀርበው የተለየ መሆን አለበት። ሁሉም እንደየ አቅማቸው የሚመጥናቸውን የቴክኖሎጂ አቅርቦት ማግኘታቸውን ማረጋገጥ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው።
በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ አቅም ያላቸው ናቸው ባይባልም በሰፋፊ እርሻዎች ሆነ በውስን መሬት በላቀ ቴክኖሎጂ በመጠቀም በግብርና ስራ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች አሉ። ወደፊት ቁጥራቸው እና በግብርናው ኢኮኖሚ የሚኖራቸው ድርሻ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ እንደሚሄድ ይገመታል።
በአጠቃላይ አርሶ አደሩን የስራ ፍላጎት እና ተነሳሽነት ከጠበቅንና ከአሻሻልን፣ ጤንነቱን ከአረጋገጥን የትምህርትና ስልጠና ደረጃውን ከፍ ካደረግን፤ ከዚህ ጎን ለጎን አምራቹ ምርቱን እንዲያሳድግ የሚያስችለው ከአቅሙ ጋር የሚመጥን የቴክኖሎጂ አቅርቦት በቀጣይነት እንዲኖር ካስቻልን፤ ይህንኑ ለማድረግ የሚያስችል ቀልጣፋ የቴክኖሎጂ አቅርቦት ፣የብዜትና እና የስርጭት ስርዓት ከፈጠርን ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የግብርና ልማት ለማረጋገጥ የሚያስፈልገንን ወሳኝ ስራ ሰራን ማለት ነው። የግብርና ልማት ግን በዚህ ብቻ የታጠረ አይደለም። የሰው ሃይል ብቻ ሳይሆን መሬትንም በአግባቡ መጠቀም ይጠይቃል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 8/2012
አብርሃም ተወልደ