የልጆች አስተዳደግ ጥበብ ደራሲ አቶ ሽመልስ ፋንታሁነኝ የልጆችን አስተዳደግን በተመለከተ በመፅሐፋቸው ላይ እንደገለፁት ስነምግባር ያለው ልጅ ለማሳደግ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ማውራት፣ መሳቅና፣ መግባባት ያስፈልጋቸዋል። የምርምር ውጤቶችም ይደግፉታል። ህፃናት ስሜታቸውን ለመግለፅ የሚያሳዩትን ምልክት ተረድቶ ምላሽ መስጠት ትልቅ የልጆች የአስተዳደግ ጥበብ ነው። ህፃናት በለጋ እድሜያቸው በቋንቋ ለመግባባት አይችሉም፤ ስለዚህ መግባቢያቸው ለቅሶ ነው። ህፃናት ትኩረት ለማግኘት የሚጠቀሙበት ዋናው መልዕክት ለቅሶ ነው። የሚያለቅሱት አንድ ነገር ሲፈልጉ ብቻ ነው። የተለየ ነገር ሲፈልጉ የተለየ አይነት ለቅሶ ስለሚያለቅሱ ወላጆች ይህን በመረዳት ለችግሮቻቸው መድረስ አለባቸው ሲሉ ይገልፃሉ።
ህፃናት ወላጆቻቸውን ለማበሳጨት አያለቅሱም የሚለው ደራሲው፤ ህፃናት ማሰብ፣ የሚመጣውን ቀድሞ መገመት ወይንም ነገሮችን አዙሮ ማየት አይችሉም። ለቅሷቸው ለሌላው ሰው ምን አይነት ተፅእኖ እንደሚያመጣም አያውቁም። ማልቀሳቸው የፈለጉትን ነገር ለማግኘት እንደሚያስችላቸው ብቻ ነው የሚያስቡት። ይህንን ፍላጎታቸውን ለመግለፅ ብቸኛው መንገድና ትኩረት የሚስቡበት መንገድ ማልቀስ ነው። ስለዚህ ወላጆች ለዚህ ምልክታቸው በፍጥነት ምላሽ መስጠት አለባቸው።
ህፃናት እንደመግባቢያ ቋንቋ የሚጠቀሙባቸው በርካታ መንገዶች አሉ። ከነዚህም ውስጥ የሚፈልጉትን ሰው ፊት በአትኩሮት ማየት ነው። በዚህ ጊዜ ወላጆች ከመረዳት አልፈው የፈለጉትን በመለየት ማድረግ ይኖርባቸዋል። ይህ ደግሞ ልጆች በቀላሉ መግባባትና በወላጆቻቸው ላይ እምነት እንዲያሳድሩ ይገልፃል። ህፃናት ከንፈራቸውን በማጨማደድና ምላሳቸውን በማወዛወዝ እንደመግባቢያነት ይጠቀማሉ። ህፃናት እንደፊታቸው ሁሉ እጃቸውንም ጭምር አንድ ነገር መፈለጋቸውን ለመጠቆምና መራባቸውን ለመግለፅ የሚጠቀሙበት ምልክት ነው። በመላ ሰውነታቸው የተለያዩ ምልክቶችን በማሳየት የሚፈልጉትን ነገር ለወላጆቻው አስቀድመው ለማስጠንቀቅ ይጠቀሙበታል። ብዙ ጊዜም ጀርባቸውን በማዞር የሆነ ነገር መፈለጋቸውን በምልክት ለማሳየት ይጥራሉ።
እንደ ደራሲው ገለፃ ወላጆች ትኩረት ሊሰጡት የሚገባው ነገር ደግሞ ዘወትር አሉታዊ ንግግርን በልጆች ፊት አለማውራት። ከባድ ቃላትን ማለትም ለልጆች አዕምሮ ሊመጥን የማይችል ቃላትን አለመናገር። ልጆችን በጥሩ ስነምግባር ለማሳደግ መልካም ነገርን መናገርና ማድነቅ አስፈላጊ ነው ይላል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 7/2012
ሞገስ ፀጋዬ