በዛሬው የዘመን ጥበብ አምድ ላይ ስለ ‹‹ስነ ጥበባዊ›› ሙያዎችና ስራዎች ለማውራት ወደናል። ለዚህ እንዲያመቸን ደግሞ በቀጥታ ከወቅታዊ ጉዳዮች ጋር ግንኙነት ያለው ተወዳጅ ሰዓሊን እንግዳችን አድርገናል።
አርቲስት ተክለማሪያም ዘውዴ ይባላል። ላለፉት 20 ዓመታት በሙሉ ጊዜ የስቱዲዮ አርቲስት ሆኖ ተወዳጅነት ያተረፉ የስዕል ስራዎችን ለጥበብ አፍቃሪው እነሆ ብሏል። በአሳሳል ጥበብ ወይም ፍልስፍና ‹‹impressionists›› ወይንም ስሜትን መግለፅ ብሎ የሚተረጉመውን ዘዬ ይከተላል። በጥበብ ምጥ ተጨንቆ ወደ እውነታው ዓለም የሚቀላቅላቸውን ስራዎቹ የራሱን ስልት እንዲከተሉና ከየትኛውም ተመሳሳይ ጉዳይ ጋር እንዳይገናኙ ይጥራል። ‹‹የትኛውም ቦታና ዓለም ላይ ስራዎቼን አይቶ ‹ይሄ የተክለማሪያም ስራ ነው› ብሎ አሻራዬን መለየት እንዲችል እፈልጋለሁ›› ይላል ስለ ጉዳዩ ሲጠየቅ።
የተለያዩ ዓለም አቀፍ አውደር ርዕይና የአገር ውስጥ ኤግዚቢሽኖች ተሳትፏል። በጥበቡ ዓለም አባታቸው የሆኑትን የስዕል ስራዎች በግልም ሆነ በቡድን ለእይታ ቀርበው በስነ ጥበብ ወዳጁ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት አስገኝተውለታል። የዓይንና ልቦና ጥማትን ከማርካት ባሻገር በጥበብ ገበያው ላይ የሚቀርቡት የተክለማሪያም እንቁዎች ዋጋቸው እንዲገዝፍና ከአንጋፋዎቹ ተርታ እንዲመደብ መንገዱን ጠርገውለታል። ሰሞኑን ደግሞ ወቅታዊውን የኮሮና ወረርሽኝ በማስመልከት በመኖሪያ ቤት ውስጥ አውደ ርዕይ በማዘጋጀት በማህበራዊ ገፅና በመገናኛ ብዙሃን ላይ አቅርቧል። በወዳጆቹ ደጃፍ ደርሶም ብሩህ ቀን ተመኝቷል። በዛሬው የዘመን ጥበብ አምድ የዚህን አርቲስት የህይወት መንገድ ልናስቃኛችሁ ወደናል።
መክሊት
በስነ ጥበብ ሙያ የሰዓሊነት ተሰጦ እንዳለው የተረዳው ገና በልጅነቱ የአራተኛ ክፍል ተማሪ በነበረበት ወቅት ነው። በይበልጥ ደግሞ የአስተማሪው ‹‹ምን መሆን ትፈልጋለህ›› የሚለው ጥያቄና ማበረታቻ ስሜቱን ፈንቅሎ ተሰጦውን ኮትኩቶ እንዲያሳድገው ገፊ ምክንያት ሆኖታል። ትምህርቱን እስከ 12ተኛ ክፍል ተምሮ ያጠናቀቀው በደጅአዝማች ወንድራድ የመጀመሪያ፣ ሁለተኛና የመሰናዶ ትምህርት ቤት ነበር። በዚያ ተሰጦን ለማዳበር በሚረዳው ማዕከል ውስጥ ክህሎቱን ማዳበር ጀመረ። በተለያዩ ውድድሮች ላይም ይሳተፍና ስኬቶችን ያስመዘግብ ነበር። ከቀለም ትምህርቱ በላይም የስነ ጥበብ ሙያውን አጥብቆ የሚፈልግ ነበር።
‹‹በተለያዩ ልምምዶችና ጥረቶች ሰዓሊ የመሆን ህልሜን ኮትኩቼ አሳደኩት እንጂ በተፈጥሮ የተሰጠኝ አብሮኝ የተወለደ መክሊቴ ነው›› የሚለው አርቲስት ተክለማሪያም አሁን ለደረሰበት ስኬት ተፈጥሮው ወሳኙን ድርሻ እንደሚወስድ ያስረዳል። በዓለም ላይ ታዋቂ የሆኑ የፈጠራ ሰዎችም መሰል መሰጠት የተቸራቸው እንደሆኑ ይናገራል። ነገር ግን ስጦታን የተሻለ ቦታ ለማድረስ ብዙ ልምምዶችና ስራዎች እንደሚጠይቁ ያምናል።
አሁንም ድረስ በልቦናው ውስጥ ተቀርፆ የቆየው የመጀመሪያው የአርቲስት ተክለማሪያም የስዕል ስራ የ10ኛ ክፍል ተማሪ እያለ የሰራው ‹‹በደርግ ጊዜ የነበረውን የኤርትራ ጦርነትና የአንድነት ስጋት›› የሚያንፀባርቅ ነበር። በዚህ ስራው ከትምህርት ቤቱ አንደኛ በመውጣት ሽልማት አግኝቷል።
የሰዓሊው መንገድ
ጊዜው 1983 ዓ.ም ነው። ተክለማሪያም 12ተኛ ክፍል ያጠናቀቀበት ወቅት። በጊዜው የነበረው ጠንካራ ውድድርና ከባድ የማለፊያ ነጥብ ወደ ዩኒቨርሲቲ ሊያስገባው አልቻለም። በወቅቱ 15 የማይደርሱ ተማሪዎች ናቸው እድሉን አግኝተው የነበረው። ‹‹ቤተሰቦቼ ጠንካራና የህይወቴ መሰረት ናቸው›› የሚለው የአሁኑ ተወዳጅ አርቲስት እድሉን እንዳጣ ሲያውቅ በአባቱ አጋዥነት አልባሌ ቦታ እንዳይውል በመካኒክና ብየዳ ሙያ ላይ እንዲሰራ እድሉን አገኘ። ይሄ ደግሞ ስራ ወዳድነትንና ትግስትን አስተማረው።
አባቱ በሚሰራበት መብራት ሃይል እየሰራም ህልሙንና የተፈጥሮ ስጦታው የሆነውን የስዕል ትምህርት ለማጥናት በማታው ክፍለ ጊዜ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ‹‹አርት ስኩል›› ጀመረ። ህይወት በፈለገው ቀና ጎዳና ያለ እንቅፋት እንዲሄድ መንገዱን ጨርቅ ታደርግለት ጀመረች። እርሱ እድሉን ያግኝ እንጂ ከሁለት ሺ ተማሪ 15ቱ ብቻ ነበሩ መሰል እጣ ፈንታ ያገኙት። ለሁለት ዓመታትም ቀን እየሰራ ትምህርቱን በስኬት ማጠናቀቅ ቻለ። ሁለት ጊዜ ተፈትኖም በአንደኛው ስላለፈ በድጋሚ በቀን የመማር እድሉን አግኝቶ የጀመረውን ጉዞ በእጥፍ አስኬደ።
በቀን የአርት ስኩል ትምህርቱን መከታተል የጀመረው አርቲስት ተክለማሪያም ‹‹የፔንቲንግና ስከለፕቸር›› ወይንም የሞኒመንታል ግድግዳ ስዕሎች በአብያተ ክርስቲያናትና በሌሎች ትልልቅ ቦታዎች ላይ የሚሰሩ ግዝፈት ያላቸው የሞዛይክ ስራዎችን የሚያጠና ዲፓርትመንት ውስጥ በምርጫ ገብቶ እውቀቱን አዳብሯል። በቆይታው ትምህር ክፍሉ ጠንካራ፣ በስነምግባር የታነፀና በእውቀት የዳበረ ማንነት ይዞ የእውነታውን ዓለም እንዲቀላቀል እንዳገዘው መለስ ብሎ ጊዜውን እያስታወሰ ይመሰክራል። ለእርሱ ብቻ ሳይሆን ለበርካታ አንጋፋ ሰዓሊያን አርት ስኩል ባለውለታ መሆኑን ከመናገር አልተቆጠበም።
አርቲስት ተክለማሪያም በስራዎቹ ውጤት ማየት የጀመረው ገና ተማሪ በነበረበት ወቅት ነው። በአርት ስኩል በቀን እየተማረ ከጓደኛው ጋር የገና ወቅት የመልካም ምኞት መግለጫ ፖስት ካርዶችን ያሳትም ነበር። እነዚህ ካርዶች ኢትዮጵያዊ ባህልና ወግን የተከተሉ የፈጠራ ስራዎች ነበሩ። በዚህም ትምህርቱን እስከመደጎም ደረጃ ደርሷል። እንዲያውም ከጓደኛው ጋር የስራ ሚኒባስ መኪና እስከመግዛት አድርሶታል። ይሄ ጥረቱና የኢኮኖሚ አቅሙ በአንዳንድ አስተማሪዎች አልተወደደለትም። እንዲያውም ውጤቱን እስከማስቀነስም ደርሶ ነበር። ሆኖም የተሻለ ጥንካሬ አላበሰው እንጂ በሁኔታው ተስፋ እንዲቆርጥ አላደረገውም።
የሙሉ ጊዜ የስነ ጥበብ ባለሙያ
የመጀመሪያውን ኤግዚቢሽን ከሌሎች ሁለት ባልደረቦቹ ጋር በመሆን ያዘጋጀው በአራት ኪሎ ህፃናትና ወጣቶች ቲያትር ቤት ነበር። ጊዜው 1989 ዓ.ም ነው። በልጅነቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ስራዎቹን ሲያርብ በርካታ አድናቆትና አስተያየት አግኝቶበታል።
ከአርት ስኩል ተመርቆ እንደወጣ ብዙም ሳይቆይ ነበር የትዳር ህይወት ውስጥ የገባው። የስዕል ስራዎቹን መስራት ስላለበት በሚኖርበት ኮተቤ አካባቢ በ200 ብር ቤት ተከራየ። ካልወጣን እያሉ የሚያስጨንቁት የጥበብ ስራዎችን ማዋለዱን ተያያዘው። ‹‹የመጀመሪያው የኔ ትልቁ ስኬት ይሄ ነው›› ይላል ግዜውን መለስ ብሎ እያስታወሰ የውሳኔውን ትክክለኛነት እያረጋገጠ።
በስቱዲዮ ውስጥ ነፃነቱን ማንም ሳይጋፋው የስዕል ስራዎቹን መፍጠሩን ተያያዘው። ረጅሙን ጊዜውን በዚሁ በተከራየው ቤት ውስጥ ነበር የሚያሳልፈው። በርካታ ስራዎችን እየሰራ ስራውን ለሚወዱ ሰዎች ማቅረቡን ተያያዘው። የቤት ኪራይ ከመክፈል ጭንቀት ይልቅ ኑሮውንም ሙያውንም ማሳደግ የሚችልበት አጋጣሚውን በጥንካሬው ፈጠረ። ወደ ሙሉነት እየተጠጋ እውቅናውን እየጨመረም ሄደ።
አንድ አጋጣሚ ደግሞ አርቲስት ተክለማሪያምን በስነጥበብ ወዳጁ ዘንድ ይበልጥ እንዲታወቅ አግዞታል። ነገሩ እንዲህ ነው። ጊዜው ደግሞ 1996/7 ዓ.ም አካባቢ። በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የታዋቂው የሬጌ ሙዚቃ አቀንቃኝ ቦብ ማርሌይ ልደት በደማቅ ሁኔታ የቀድሞ ባለቤቱ ሪታ ማርሌ በተገኘችበት የተከበረበት እለት። በዚህ ዝግጅት ላይ የቦብ ልጅ ሴዲላ በማኩሽ ጋለሪ ጉብኝት በምታደርግበት ወቅት የተክለማሪያም ስራ የሆኑትን ሶስት ስእሎች ላይ አይኗን አሳረፈች። ቀልቧ የወደደውን የጥበብ ስራ እንዲያው ተመልክታ ለማለፍ አልፈለገችም ።
ስዕሎቹ የኢትዮጵያውያንንና የጃማይካውያንን ግንኙነት የሚያሳዩ ፈጠራዎች ናቸው። በተለይ ‹‹flying on the sky›› የተሰኘው ርዕስ የጃንሆይን እና የቦብ ማርሌን ምስል በፈረስ ላይ ሆነው የሚያሳይና የእርሳቸውን መሪነትና ታላቅነት፤ የጃማይካውያንን አክብሮት የሚገልፅ ይዘት ነበረው። ሁለተኛው ደግሞ ‹‹mother and child›› የሚል ስያሜ ያለው ሲሆን ኢትዮጵያን የወከለች ሴት ቦብ ማርሌን አቅፋ የሚያሳይ ነው። ይህ ምስል አቀንቃኙ ከሞተ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲቀበር ያሳለፈውን ኑዛዜ እንዲወክል ተደርጎ በአርቲስቱ የተሰራ ነበር። ሶስተኛውና የመጨረሻው ስዕል ደረጃ ላይ ያለው እራሱ ቦብ ማርሌን ካባና ከውስጥ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ለብሶ የሚያሳይ ነው። ይሄ የፈጠራ ስራ እርሱም ሆነ ጃማይካውያን ከኢትዮጵያ ባንዲራ ጋር ምን ያህል ትስስር እንደፈጠሩ ለማሳየት የሰራው ነበር።
የአርቲስት ተክለማርያም ሶስት ስራዎች በጊዜው የቦብ ማርሌ ልጅ ሴዲላ አይን ውስጥ ቀሩ። ተመልክቶ ከማለፍ የራሷ ልታደርጋቸው ከጀለች። ከፍተኛ ዋጋ በማውጣትም የግሏ አደረገቻቸው። ይሄ ክስተት የአርቲስቱን ብቃትና ተወዳጅነት ይበልጥ እንዲፈነጥቅ ያደረገ ነበር። ኢንተርናሽናል ተፈላጊነትንም ጨመረ። ምንም እንኳን ሙሉው የሽያጭ ገቢው በኪሱ ባይገባም የስነ ጥበብ ባለሙያው ሰፊ የእድል በር ተከፈተለት። በእርግጥ እድል ብቻ ሳይሆን የጠንካራ ስራ ውጤትና የብዙ አመታት ልፋቱ ነበር ፍሬ ያፈራው።
ይህ መነሻ ወደፊት ያስፈነጥረው ጀመር። የግል የስዕል አውደ ርዕዮችን ማዘጋጀቱን ቀጠለ። እውቅናውም የዚያኑ ያህል አየለ። በተለይ በሂልተን፣ በማኩሽ ጋለሪና በሌሎች የጥበብ አድባሮች ውስጥ ማሳየት ጀመረ። ይህ ብቻ ሳይሆን ከአርቲስት ያሬድ ወንዶሰን ጋር በሂልተን ሆቴል በርካታ ስዕሎችን በጋራ ለእይታ አቅርበዋል። በአገር ውስጥ ብቻ ሳይገደብም ኢንተርናሽናል ኤግዚብሽኖች ላይ ስራዎቹን በመላክም ሆነ በአካል በመገኘት ማቅረብና ተደናቂነትን ማግኘት ችሏል። በአሜሪካ፣ፈረንሳይ፣ቻይና፣ ዱባይ፣ በኳታር ኢንተርናሽናል አርት ፌስቲቫልና ጅቡቲን የመሳሰሉ አገራት በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው። በተለይ በነዚህ ፌስቲቫሎች ላይ ኢትዮጵያን የማስተዋወቅ አደራውን ከሌሎች ባልደረቦቹ ጋር መወጣት ችሏል።
አሻራ በሚኒሊክ ቤተ መንግስት
አርቲስቱ በቅርብም በማህበራዊ ድረ ገፅና መገናኛ ብዙሃን መነጋገሪያ የነበረ ተወዳጅ የስዕል ስጦታ በቤተ መንግስት ተገኝቶ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ማበርከት ችሏል። ‹‹ኢትዮጵያ ትናንት ዛሬ እና ነገ›› የሚል ርዕስ ያለው ይህ ስራ ለረጅም ዓመት የሰራው እንደሆነ ይናገራል። ለገበያ ላለማውጣት ወስኖ ከበርካታ ፈላጊዎች ጋር እሰጣ ገባ ውስጥ የከተተው ነበር።
ኢትዮጵያ ትናንት በአክሱም ላሊበላ ስልጣኔ፤ ኢትዮጵያ ዛሬ ደግሞ ካለፉት የቅርብ ዘመናት ተጨማሪ አሁን ድረስ የተከሰቱትን ሁነቶች፤ ኢትዮጵያ ነገ ደግሞ በእርሱ እይታ ወደፊት የምንደርስበትን ስፍራ በምናቡ ቀርፆ፤ በብሩሹና ሸራው ላይ ማስፈር ችሏል። ይህን የብዙዎችን ቀልብ የሳበ ስራ ደግሞ ከመቶ ዓመታት በፊት የታሪክ ጎራ ሆኖ የዘለቀው ቤተመንግስት ውስጥ እንዲቀመጥ ሆኗል።
የቤት ውስጥ ኤግዚብሽን
አርቲስት ተክለማሪያም በቦሌ ሩዋንዳ አካባቢ የሙሉ ሰዓት ግዜውን በስራ የሚያጠፋበት ስቱዲዮ አለው። በቤት ውስጥም እንደዛው። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ እየተጠቀመ ያለው የቤት ውስጥ ስቱዲዮውን ነው።
‹‹ሰው በቤቱ ሰርቶ እንዴት በቤቱ ያሳልፋል የሚል እሳቤ ነበረኝ›› የሚለው አርቲስቱ የወቅቱ የኮሮና ወረርሽኝ ጉዳት እንዳለ ሆኖ በቤት ውስጥ መስራት እንዲችል መልካም አጋጣሚ ፈጥሮልኛል ይላል። በዚህም መንፈሳዊ ይዘት የሚያንፀባርቁ፣ ተስፋን የሚጭሩና ነገ እንደሚነጋ የሚናገሩ የሰማያዊ ቀለም ተፅዕኖ ያረፈባቸው ስራዎችን በብዛት ሰራ። 25 ስራዎችንም ለእይታ ለማቅረብ በመወሰንም በመገናኛ ብዙሃን ተቀርፆ በሁሉም የጥበብ አፍቃሪ ደጅ እንዲደርስ አደረገ። ይህን አውደርዕይ የተመለከቱም ከፍተኛ አድናቆታቸውን ቸረውታል።
ሰዓሊው በማጠቃለያችን ላይ ‹‹ተስፋ ማድረግ ዋጋ አለው። ከሳምንት በኋላ ከዚህ ዓለም የምናልፍ ቢሆን እንኳን የቀረውን ጊዜያችንን ተስፋ እያደረግን መኖር አለብን። ይሄ ጠንካራ እምነቴ ነው›› ይለናል፤ አገርም ያው ነው፤ ፖለቲካው ምንም እንኳን ጉድለት ቢኖረው ‹‹ግዴለም ይነጋል፤ ኢትዮጵያም ወደ ቀድሞ ክብሯ ትመለሳለች›› የሚለውን ሃሳብ አጠንክሮ ያነሳል። የተስፋ ማድረግ ሃይልን ነግሮን ልባችንን አሙቆ ሃሳቡን ይቋጫል። ሰላም!
አዲስ ዘመን ሰኔ 7/2012
ዳግም ከበደ