እናትነት በርህራሄ ያጌጠ፣ በልዩ ደግነት የተኳሸ፣ በፍቅር የደመቀ ውድ ማንነት ነው። ለዚህ ማንነት ቁብ ያልሰጠ ህብረተሰብ ለእናቱ ክብር የሌለው ትውልድ በእርግጥም ታላቅነት ላይ መድረሱ የማይታለም ነው። በአለም ላይ ካሉ ስጦታዎች ሁሉ የከበረ ሴትነት ክብር መንሳት ከክብር ይርቃል። ስለ ሴት ልጅ መጠቃት በሰማ ጊዜ ለምን? ብሎ የማይጠይቅ ትውልድ፤ ቀጣይ ለሚተካው የሰው ዘር ግድ የሌለው ወደ ፊት ለሚመጣው ትውልድ የማይጨንቀው የተሻለ ፍሬ ማፍራት የማይችል ግለባ የበዛበት ምርት፤ ውጤት አልባ ግኝት ነው።
ለዚህ ትውልድ መግሪያው ሁለት መንገድ ይታየኛል። ከጅምሩ ስለ ሴት ያን አመለካከት መቀየር ለሴት ልጅ የሚገባት ታላቅ ቦታ ማመን ሲሆን ሁለተኛው ሴት የሚበድል ሴትን የሚጨቁን ስለ ሄዋን ህይወት መቃናት እንቅፋት የሚሆን ባደናቀፈው ልክ መቅጣት በበደለው ልክ አስተማሪ ቅጣት ለእርሱ መስጠት። የህግ መላላት ጥፋቶችን ያበራክታል የእኩይ ተግባር ማስቆሚያ ሁነኛ ልጓም አለማበጀት ተግባሩን እንዲሰፋ ምክንያት ይሆናል።
እንደ ህብረተሰብ ሴትን ልጅ የሚበድል በአካልና በአዕምሮዋ ላይ የማይሽር ጠባሳን ያሳረፈ የሴትን ልጅ ክብር ያዋረደ የሄዋንን ማንነት ያሳደፈ የሚመጥን ቅጣት አስተማሪ የሆነ ፍርድ ሊሰጠው ይገባል። ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰማን ያለነው የሴት ልጅ ጥቃት ማስቆምን ስናስብ ቀድመን በምን መልክ የሚለው ላይ መግባባት ያሻናል። የጠነከረ ህግ የማያወላዳ እርምጃ ለተግባር ሲነሱ ያስቡታል።
ማህበረሰባዊ ልማዳችን በሴት ልጅ ላይ ያለው አተያይ ገና አልተስተካከለም። ሴት ልጅ እያበረከተችው ያለውን ትልቅ ጠቀሜታ ገና አልገባውም። ቤተሰብ የማነጽ ጎጆን የማቃናት ተግባርዋ የማህበረሰቡ አይን እስካሁን አልተመለከተውም። እንደ እድል ኢኮኖሚውን በበላይነት ተቆጣጥሮ ዱቄት መግዣ የሚሆን ሳንቲም የሰጠ አባት ውሃ ቀድታ አቡክታ ቀምማ ፣መጥና አብስላና ለምግብነት አጣፍጣ የምታቀርበዋን ሚስቱ እጆች በእርሱ የሚተዳደሩ ስራ ፈት አድርጎ ይቆጥራቸዋል። ምናልባትም ለልጆቹ የትምህርት ወጪያቸውን ስለሸፈነ በየእለቱ ለለውጣቸው እየተጋች ለምቾታቸው የምትጨነቀዋን እናት ለውጣቸውን እየተከታተለች ምታንጸዋ ሴት በሱ አይን ምንም አይደለችም።
ስለምን የሴት ልጅ ፈተና መቆሚያ አጣ? ስለምን እናትነት የታላቅነቱ ያህል ከፍታ ራቀው? ተንበርክካ አምጣ ፍሬዋን የምትቸር እናት ለልጅዋ ህይወት ሰጥታ ህይወትዋን የምትገብር እንስት ዓለም ምቹ ሆና አልጠበቀቻትም። ይህች የፍቅር መለኪያ የደግነት ጥግ የሆነችው እናት በ21ኛ ዘመን ላይ የሚገባትን ክብር ተነፍጋለች። በየአቅጣጫው ዋይታዋ በየሸንጎው ብሶትዋ ይሰማል።
የሴትን ልጅ ታላቅነት ስለእናት ያለው የገዘፈ ሚና የተረዳ ትውልድ ለእርሷ ክብር ይዋደቃል።ይህ ትውልድ ፍሬው ያማረ መድረሻው የተገራ ነውና ሀገር በእርሱ ትለመልማለች። ሌላ የጠለሸ ገፅ ደግሞ ባልተገራው ትውልድ ማህደር ላይ ይነበባል። ወንዱ ለእንስትዋ ውድቀት ምክንያት ለሰቆቃዋ ዋነኛ ምክንያት ሆኖ ይገኛል። ያኔ ፍትህ ተዛብቶ ሴትነት ያለ አግባብ ተጨቁኖ እናትነት ክብር አጥቶ ይገኛል።
ሴትነት ልኬት የሌለው ውብ ማንነት ነው። ስለዚህም ነው ፍቅር በእናት ጥበብን በሴት መመሰል የተላመድነው። ፍሬን ሰጥታ ትውልድን የምትቀጥለዋ ሄዋን፤ የሰው ልጅ ገና ከመነሻው እንደ እርሳስ ከስር የምትቀርጸው እንስት ስብዕናውን ከማንም ቀድማ የምታንጸው እናት ህመም እና ጉዳት የማይሰማው ግድ የለሽ ትውልድ ዛሬ ላይ ተገኘ?
በዚህ ሰልጥኗል፤ የሰው ልጅ ትልቅ ደረጃ ደርሷል በሚባልበት ዘመን ስለ ሴት ልጅ መብት መነጠቅ ፣ መበደል፣ አካላዊና ስነ ልቦናዊ ጥቃት መባባስ ተደጋግሞ ከአለም የተለያዩ ማዕዘናት በየዕለቱ ይደመጣል። ይህች ሰለጠንኩ ባይዋ ዓለም ለዘመናት ከተኛችበት እንቅልፍ መንቃትዋን ብታውጅም አንገትዋን የሚያሰብራት የሄዋን ሰቆቃ ግን አሁንም አልራቃትም።
ዛሬ ድረስ የሄዋና ስቃይ ማቆሚያው ርቋል። የሴት ልጅን ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ማስቆም ወደ ኋላ አቀበት የመውጣትን ያህል ሆኖባት ትግል ላይ ትገኛለች። የመጪው ትውልድ ፍሬ አብቃይ ለሆኑት ሴቶች ዛሬም አለም ምቹ አይደለችም።
በኢኮኖሚያቸው አድገዋል፤በስልጣኔ ወደ ፊት ተራምደዋል የሚባሉት ሀገራት እንኳን የሴት ልጅን መብት በማስከበሩ ሂደት ከታዳጊ ሀገራት የተሻሉ ቢሆኑም ለወንዶች የሰጡትን እድል ለሴቶች በእኩል ማጋራት ዛሬ ድረስ አልተቻላቸውም።ድምፃቸውን ከፍ አድርገው የሴት ልጅ መብት ማክበራቸውን ቢለፍፉም እውነታው የተገላቢጦሽ ነው። የሄዋንን መብት ቀጥተኛ ባልሆነ መልኩ ይደፈጥጡታል ፤ይከሰክሱታልም።
መብትዋን እንዳታይ አድርገው ይነጥቋታል። ሴትዋን አስጊጠው የወንዱ አጃቢ ከማድረግ ባለፈ እራስዋን ችላ በጎ ተጽዕኖ መፍጠር እንድትችል ሁኔታዎች ምቹ እንዳይሆንላት ይደረጋል። ባደጉት አገራት አሁንም ሴት ልጅ ለእኩል ስራ እኩል ደመወዝ የማታገኝበት ሁኔታ መመልከት አይደንቅም።
በሌላም መልክ አሁን ድረስ በሄዋን ላይ ወሲባዊ ትንኮሳዎችና ጥቃቶች ይደርሳሉ።በማታለያዎች የሰውነት ክብርዋን ዝቅ ያደርጉባታል። ማታለያዎችን እንደ ጭንብል አጥልቀው መጠቀሚያ ያደርጓታል። ሰለጠንኩ የሚለው የአለም ክፍል የሰለጠኑ ግፎችን በሴቶች ላይ ማድረሱን ቀጥሏል።
በታዳጊው የአለም ክፍል ደግሞ ይህ ገፅታ ይበልጥ ይከፋል። በሚፈጠሩ የስራ እድሎች ከወንዶች እኩል ተሳትፎ እንዳይኖራቸው፣ ትምህርት እንዳያገኙ ተደርገው፣ ስለ እራሳቸው የመወያየት ስለ መብታቸው የመጠየቅና በውሳኔ ሰጪነት የመሳተፍ መብታቸው ተጥሶ፣ በማህበራዊ ኢኮኖሚውና በፖለቲካው ሁኔታዎች ሊኖራቸው የሚገባውን ተሳትፎና መፍጠር የሚችሉት በጎ ተጽዕኖ መወጣት እንዳይችሉ መብት ተነፍገው፣ ለአካላዊና ስነ- ልቦናዊ ጥቃት ሰለባ ሆነው ይገኛሉ ።
እነዚህ ጫናዎች ሴቶች በተለያዩ መስኮች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ከወንዶች ጋር ሲነጻጸር በጣም ዝቅተኛ እንዲሆን አድርጓቸዋል። የአለምን ህዝብ ግማሽ ያህል ቁጥር የሚሸፍኑት ሴቶች በተነፈጋቸው እድል ምክንያት ውጤታማ ሳይሆኑ ቀርተዋል። ያላቸውን አቅም ተጠቅመው ለማህበረሰቡ ሊፈጥሩት የሚችሉት ትልቅ ለውጥ እንዳይታይ አድርጎታል።
ለሴት ልጅ ክብር መስጠት ገና ያለመደ፤ለዓለም ያበረከቱትን የላቀ አስተዋፅኦ አምኖ ያልተቀበለ ማህበረሰብ ባላበት አለም የሴት ልጅን በደል ማስቆምና ተጠቃሚነትዋን ማረጋገጥ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ትግል መጠየቁ የማይቀር ነው። በሴቶች ዙሪያ የሚሰሩ ተቋማት ቢበራከቱም የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት አልቻሉም። ስለ ሴቶች መብት ተሟጋቾች ቢበረክቱም ትግላቸው ውጤቱ አላረካም።
እነዚህ ከላይ የተቀመጡ ተግዳሮቶች የሴት ልጅ መብት በተገቢው ሁኔታ ላለመከበሩ ምክንያት ተደርገው ቢታዩም ዋንኛው የመፍትሄ ቁልፍ ግን ማህበረሰቡ የሴቶችን መብት በማስከበሩ በኩል ተገቢውን ተሳትፎ ማድረግ እንዲችል ስለ ሴቶች መብት የሚያሳውቁና ግንዛቤውን ሊያሳድጉለት የሚችሉ የተጠናከሩ ስራዎች መስራት ወሳኙ ጉዳይ ነው። ከዚህም ጋር በሴት ልጅ ላይ የሚፈጸሙ ግፎችን ተገቢ በሆነ መልኩ ምላሽ የሚሰጥ የህግ ማዕቀፍ ሊበጅና ሊተገበር ይገባል።
ለሄዋን መብት መከበር ደጀን የሚሆን ማህበረሰብ ለመፍጠር ስለ ሴት ልጅ መብት ግንዛቤውን ማስፋትና ለሴት ልጅ ትልቅ ክብርና ቦታ መስጠት ተገቢነትን ማስረዳትና የመብታቸው መከበር ያለውን ጠቀሜታ አጉልቶ ማሳየት ተገቢ ነው። ለማህበረሰቡ ስለ ሴት ልጅ መብት በማሳወቁ በኩል ትልቅ ጥረት ሊደረግ ይገባል። የሴትን ልጅ በደል ለማስቆም ልጓም ማበጀት ግድ ይላል። ቸር ይግጠመን።
አዲስ ዘመን ሰኔ 7/2012
ተገኝ ብሩ