ትህነግ/ስብሀታዊያን ( የፓርቲው ሱስሎቭ / አይዶሎግ / የነበረው መለስ ከሞተ በኋላ በጡት አባቱ አቦይ ስብሀት ቤተሰብ ቁጥጥር ስር መዋሉን ለመግለጽ ነው ፤ ) ከፓርቲ ሀገርንና ሕዝብ የሚያስቀድም ቢሆን ኑሮ፣ በሕዝብ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነት፤ በመልካም አስተዳደር ፣ በዴሞክራሲና በሕገ መንግስታዊነት የሚያምን ቢሆን ኖሮ ከአንድም ሁለት ሶስት ጊዜ ከስልጣን የመልቀቅ ግዴታ ተጥሎበት ያውቃል ። የመጀመሪያው ግዴታ የኢትዮ – ኤርትራ ጦርነት ከ70ሺህ በላይ ወጣት መስዋዕት ከሆነ፤ ከዚህ የሚበልጥ ቁጥር ከቆሰለ ፣ አካል ጉዳተኛ ከሆነ ፣ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ሀብት ከወደመ በኋላ መጨረሻው በአልጀርሱ ስምምነት እና በሔጉ የድንበር ኮሚሽን መፈታቱ ላይቀር ወደ ጦርነት መግባቱ፣ ያን ሁሉ መስዋዕትነት ማስከፈሉ ፤ የማታ ማታ በሔጉ የድንበር ኮሚሽን ይግባኝ በሌለው ውሳኔ ለመገዛት የሚስማማ ከሆነ ወደ ጦርነት መግባቱና ያን ሁሉ ዋጋ ሀገርንና ሕዝብ ማስከፈሉ ትልቅ የስትራቴጂያዊ የአመራር ቀውስ ስለሆነ በፈቃዱ ስልጣን ሊያስለቅቀው ይገባ ነበር ። ከዚህ የማይተናነሰው ከባድ ክህደት ደግሞ ሕዝብ ከጦርነቱ እባጭ ፣ ቁስል ሳያገግም መዋሸቱ ነው ። ለጦርነቱ መቀስቀስ ምክንያት የነበረው ባድሜና አካባቢው በሔጉ ችሎት ለኤርትራ ተወስኖ እያለ ፤ የወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስዩም መስፍን ፣ ” ባድመ ብቻ ሳይሆን ፣ ሌሎች በኤርትራ ስር ሰፊ ግዛቶችን ጭምር ያካተተ መሬት ለኢትዮጵያ ተሰጥቷል ። የኢትዮጵያ ሕዝብ በጦር ሜዳ ያስመዘገበውን ድል በዲፕሎማሲውና በሕጉ ሜዳ በማረጋገጡ እንኳን ደሳላችሁ ። ” ሲሉ በአደባባይ ሕዝብን፣ ሀገርን በማታለልና በመዋሸቱ በትህነግ የሚመራው አገዛዝ ሕዝብን ይቅርታ ጠይቆ ስልጣኑን መልቀቅ ነበረበት። ከፓርቲው ውጪ ለሕዝብም ለሀገርም ጥቅም ደንታ ስላልነበረው ስልጣን ላይ ሙጭጭ ብሎ ቀጥሏል ።
ሁለተኛው ስልጣን የመልቀቅ ግዴታ ፦ በ97ቱ ብሔራዊ ምርጫ በቅንጅት በዝረራ መሸነፉ ቀድመው በወጡ መረጃዎች ታውቆ እያለና የምርጫ ቦርድ መግለጫ እየተጠበቀ ሳለ ፤ ትህነግ በማን አለብኝነት ሕገ መንግስቱንና የምርጫ ሕጉን በመጣስ ያሸነፍሁት እኔ ነኝ በማለት ሕዝብ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትና ምንጭ መሆኑን የሚገልጸውን የሕገ መንግስት ምሰሶ በደህንነትና በጸጥታ መዋቅሮች ታግዞ የሕዝብን ድምጽ በመዝረፉ ፤ ይህን ተከትሎ ድምጼ ይከበር በሚል ለተቃውሞ የወጡ ሰላማዊ በሺህዎቹ የሚቆጠሩ ሰልፈኞችን በአዲስ አበባና በክልሎች በመግደሉ ፣ አካል በማጉደሉና በግፍ በማሰሩ ለፈጸመው ግፍ ከስልጣን መልቀቅ ነበረበት ።
ሶስተኛው ስልጣን ለመልቀቅ ግዴታ፦ 5ኛውን ብሔራዊ ምርጫ መቶ በመቶ አሸነፍኩ ባለ ማግስት መጀመሪያ በኦሮሚያ በመቀጠል በአማራና በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ሕዝባዊ ተቃውሞ ሲቀሰቀስበትና ሕዝባዊ አመኔታና ቅቡልነት ሲነፈገው ከስልጣን መልቀቅ ሲገባው በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ገድሏል ። በጅምላ አስሯል ። ሆኖም ሕዝባዊ ቁጣውና ተቃውሞው እየበረታ ሲሄድ ያለ ፍላጎቱ ስልጣኑን ለለውጥ ኃይሉ ለማስረከብ ተገዷል ። አንድም የትህነግ ባለስልጣን ለ27 አመታት ለተፈጸመው ግፍ ፣ ዘረፋና ኢ -ሕገ መንግስታዊነት ተጠያቂ አልሆነም ። አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ ወደ መቀሌ ፣ ወደ መጨረሻ ምሽጉ አፈገፈገ እንጂ ። ሕዝብን ይቅርታ ጠይቆ ከስልጣን የለቀቀ አንድም አመራር የለም ማለት ይቻላል ። ዛሬም አልበቃ ብሎት የትግራይን ሕዝብ የለውጡ ተቋዳሽ እንዳይሆን አፍኖ እየገዛ ይገኛል። ትህነግ ወደ ስልጣን ከመጣ ጊዜ ጀምሮ ሕገ መንግስቱን እንዳሻው ሲጥስ የኖረ ቡድን ነው ። ለሕገ መንግስቱ ምንም ክብር ያልነበረው ከመሆኑ ባሻገር ፤ ይጠቀምበት የነበረው ለራሱ በሚበጅና በሚስማማ መንገድ የስልጣን ዘመኑን ለማስረዘም እንዲሁም የአፈና መዋቅሩን ለመዘርጋት ብቻ ነበር ። ስለሆነም ስለ ሕገ መንግስት ማውራት አይደለም ትንፍሽ የማለት የቅስም ልዕልና የለውም ።
የተከበሩ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሒም የትህነግ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ፤ ከ2010 ዓ.ም አንስቶ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፤ ከዚያ በፊት የትግራይ ክልል ሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊ ፤ የደቡብ ምሥራቅ ዞን አስተዳዳሪ ፣ የትግራይ ክልል የሴቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ፤ በፓርቲው ውስጥም የገጠር ዘርፍ ኃላፊ በመሆን ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ ለ17 አመታት የፈላጭ ቆራጩን፣ የአምባገነኑን፣ የኢ -ሕገመንግስታዊውን ፣ የጸረ ዴሞክራሲውን ትህነግ የአፈና ብቅል አብረው ሲፈጩ ፣ የግፍ ጽዋ ሲጠምቁ፣ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ ጋር እልል በቅምጤ ሲሉ የእድሜአቸውን ግማሽ ያባከኑ ፣ በሌኒንና በስታሊን የማንነት ፖለቲካና በአልባኒያ ሶሻሊዝም ጥርሳቸውን የነቀሉ አብዮታዊ ካድሬ ዛሬ ድንገት ተነስተው፤ እሳቸውም ሆነ ነጻ አውጪ ፓርቲያቸው ከቃል ውጪ በተግባር ለማያውቀው ፣ አንድ ቀን እንኳ ላልኖረበት ዴሞክራሲ እና ሕገ መንግስታዊነት ጠበቃ የመሆን ሞራል የላቸውም ። አበው ፣ እማት ጅብ በማያውቁት ሀገር ሄዶ ቁርበት አንጥፉልኝ ይላል እንዲሉ ።
ይህ ትህነግ እንደለመደው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያለውን ንቀት ያሳየበት ከመሆኑ ባሻገር ፖለቲካዊ ሸፍጥና ደባ የተወነበት አጋጣሚ ነው ። ለዚህ ነው ብዙዎች ትህነግ የተፈጥሮ ሕግ ተሽሮ እንኳ እንደገና በደደቢት ማህጸን ተጸንሶ ቢወለድ አይለወጥም የሚል ድምዳሜ ላይ የደረሱት ። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ለትግራይ ሕዝብ ፍቅራቸውንና አክብሮታቸውን በገለጹበት ፤ በዘወርዋራም ለትህነግ የወይራ ዝንጣፌ በላኩበት ማግስት፤ በህዳሴው ግድብ የተነሳ ማንኛውም ጥቃት ቢሰነዘርባት በአንድነት ለመመከት አንድ መሆኗ ከምንጊዜውም በላይ በሚያስፈልጋት በዚህ ቀውጢ ሰዓት ፤ ትህነግ የትናንትና፣ የትናንት በስቲያውን ታሪካዊ በደል በሀገር ላይ ዛሬም በተከበሩ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሒም አማካኝነት ፈጽሞታል። የለውጥ ኃይሉ ባጎረሰ ጣቱ ተነክሷል ። ከብልጽግና ጋር አልዋሀድም ላለ ፣ በአገኘው አጋጣሚ ሁሉ የለውጥ ኃይሉን በፈጠራ ወሬ እያንቋሸሸ ፤ በሪሞት እንዳሻው በሚዘውራቸው የጥፋት ኃይሎች ቀውስ እየቀፈቀፈ፤ በልበ ሰፊነትና ለትግራይ ሕዝብ ሲባል የተሰጠውን ኃላፊነት ጥርሱን ለነቀለበት የሴራ ፣ የደባ ፖለቲካ ተጠቅሞበታል ። ትህነግ ለጊዜያዊ የፖለቲካ ጥቅም ሲል ምንም ከማድረግ እንደማይመለስ ዛሬም አረጋግጦልናል። ለዛውም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዜጎች መርገፍ መጠቃት በጀመሩበት ፤ ግብጽ በህዳሴው ግድብ የተነሳ የጦርነት ነጋሪት እየጎሸመች ባለችበት ሰዓት ሁል ጊዜም እንደሚያደርገው ከሀገርና ከሕዝብ ጥቅም ይልቅ እርካሽና ምንም የማያስገኝ የፖለቲካ ጥቅሙን አስቀድሟል ። ለዚህ እኩይ ተግባርም መቀሌ መሽጎ በሚገኘው የአቦይ ስብሀት ሳንባ የሚተነፍሱትን አፈ ጉባኤውን ተጠቅሟል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤም ከአለቆቻቸው ተፅፎ የተሰጣቸውን መልቀቂያ ሸምድደው ፤ በጠሩት የምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባ ዋዜማ ሕጋዊነትን በጣሰ አግባብ ከኃላፊነታቸው ለቀዋል። ” አምባገነናዊ መንግሥት ሲመሰረት ተባባሪ ላለመሆን በገዛ ፈቃዴ ኃላፊነቴን ለቅቄያለሁ። ” ሲሉ ለአማርኛው ቢቢሲ ተናግረዋል። በአምልኮ 11 የተለከፈው ትህነግ የካቲት 11 ቀን 1967 ዓ .ም በ11 ሰዎች ምን አልባትም በ 11 ኋላቀር ጠመንጃና ጦር ወይም ዱላ ከንጋቱ ወይም ከቀኑ 11 ሰዓት በምዕራብ ትግራይ ቆላ በሽሬ አውራጃ ልዩ ስሙ ደደቢት በተባለ ስፍራ 11 ቅርንጫፍ ባላት ግራር ጥላ ስር በ11 ድንጋይ ተቀምጦ ከተመሰረተ አንስቶ መስራቾቹን ጨምሮ ማንም የራሱ ፈቃድ እንደሌለው የማናውቅ ይመስል” በፈቃዴ ስልጣኔን ለቅቄያለሁ ። ” ሲሉ ተሳልቀውብናል ። በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ፣ በቡድን ውሳኔና በአንድ ለአምስት አመራር ተጠርንፎ በኖረና የአልባኒያ ሶሻሊዝም ግርፍ የሆነ ቁሞ ቀር ፓርቲ ከመቼ ወዲህ ነው የአባሉን ፈቃድ ፈጻሚ የሆነው ። ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ በአቋም የተለዩ ጓዶችን እንደ ድመት አልበላም ? አላባረረም ? እነ አይተ ገብሩ አስራትን ከስንጥቃቱ በኋላ የፈጸመባቸው ግፍ የተረሳ መስሎት ነው ዛሬ ቁጭ በሉ ላሞኛችሁ የሚለን ።
አፈ ጉባኤዋ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት የአገሪቱን “ሕገ መንግሥት በየቀኑ ከሚጥስና አምባ ገነንነትን ከሚያራምድ ቡድን ጋር ለመስራት ፈቃደኛ ስላልሆንኩ ነው” ብለዋል። የሚገርመኝ የትህነግ አመራሮች ይህን የትግራይን ሕዝብም ሆነ ኢትዮጵያዊነትን የማይመጥን አይን ያወጣ ቅጥፈት ከየት ተማሩት ብዬ ልጠይቅ ስል የናዚ ጀርመኑ አዶልፍ ሒትለር ቀኝ እጅና ፕሮፓጋንዲስት ዶ/ር ጆሴፍ ጎብልስ ትዝ አለኝና ተውኩት ። ከፍ ብዬ እንደገለጽሁት ትህነግ በአስኳልነት የሚመራው አገዛዝ ለ27 ተከታታይ አመታት በሰብዓዊ መብተት ጥሰት ፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ጠርቅሞ በመዝጋት ፣ ጋዜጠኞችን በማሳደድ በማሰር ፣ የሕዝብን ድምፅ በማጭበርበር ፣ ወዘተረፈ በመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ፣ በአሜሪካ ኮንግረስ ፣ በአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽን ፣ በአመነስቲ ኢንተርናሽናል፣ በሂውማን ራይትስ ዋች ፣ በሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ፣ በጋዜጠኞች መብት ተሟጋች / ሲፒጄ / እና ሌሎች በተደጋጋሚ ሲከሱ መኖራቸው አይዘጋም ። ሰሞኑን ከኳታሩ የሶፍት ዲፕሎማሲው ክንድ ከእንግሊዘኛው” አልጀዚራ” ቴሌቪዥን ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት በኖርዌ ኦስሎ ቢዮርኬስ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና የግጭት ጥናት ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ጄቲል ትሮንቮል በትህነግ ይዘውር የነበረው አገዛዝ አፋኝና ፈላጭ ቆራጭ እንደነበር አስታውሰዋል ። ታዲያ ወይዘሮዋ ለምን የዛን ጊዜ አለቀቁም ?
በተቃራኒው ካለፉት ሁለት አመታት ወዲህ ወደ ኃላፊነት የመጣው የለውጥ አመራር በጅምላ ታስረው የነበሩ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞችን ነጻ ያደረገ ፣ የፖለቲካ ምህዳሩ በትህነግ በመጠርቀሙ ነፍጥ ለማንሳት ተገደው የነበሩትንና በአሸባሪነት ተፈርጀው የነበሩ ኃይሎችን ፣ በአሸባሪነት ተወንጅለው ተዘግተው የነበሩ መደበኛና ማህበራዊ ሚዲያዎችን እግድ በማንሳት፤ ጋዜጠኛ በመሆናቸው የተለያየ ታርጋ ተለጥፎባቸው በእስር ሲማቅቁ የነበሩ ጋዜጠኞችንና ጦማሪያን በመፍታት ፤ ሀቀኛ የዴሞክራሲያው ስርዓት ግንባታውን ተቋማዊ ለማድረግ ሕጎችን ማሻሻል ፤ ገለልተኛ ተቋማትን ገለልተኛ በሆኑ ግለሰቦች እንዲመሩ ማድረጉ ፤ ትህነግ ስልጣን ላይ ለመቆየት ሲል ሻእብያን እንደማስፈራሪያ ይጠቀምት የነበረ ስሁት ፖሊሲ በለውጡ ማግስት ተቀይሮ እርቅ በመውረዱ ፤ ወዘተርፈ ምዕራባውያንና አለማቀፉ ማህበረሰብ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትርን በሰላም የኖቤል ተሸላሚ በማድረግ እውቅና ከመስጠታቸው ባሻገር አለማቀፍ የፋይናንስ ተቋማትና ረጂ ድርጅቶች ሀገር በቀል ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያውን በመደገፍ ወደ 10 ቢሊዮን ዶላር እገዛ አድርገዋል ። እንግዲህ ይሄ ለውጥ ነው ፤ የእነ ስብሀታውያን ጭፍራ / legion / ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሒም ሕገ መንግስት በመጣስ፣ አምባገነናዊ መንግስት ለመመስረት ጥረት በማድረግ የሚከሱት ። ለመሆኑ እሳቸው ወደ አመራርነት ከመጡ ከ17 አመታት ወዲህ በእናት ድርጅታቸው ሕገ መንግስቱ በቁሙ ተገፎ እርቃን ፣ መለመሉን ቀርቶ ፣ የወረቀቱን ዋጋ ያህል ክብር ሲያጣ ፣ የሕዝብ ድምጽ በአደባባይ ሲዘረፍ ፣ በዜጎች ላይ ያ ሁሉ ግፍ ሲፈጸም ፣ የሀገር ሀብት በጠራራ ሲዘረፍ፣ ወዘተርፈ የት ነበሩ ። ሇየ ኒውትን እንደሳቸው ያሉትን ስብሐታዊያን ነው ፤ ” አብዮተኛ ሊገነዘብ የሚገባው ቀዳሚው ሀቅ ውድቀቱ የማይቀር መሆኑን ነው ። ” ያሏቸው ።
አቶ መሀመድ ረሺዲ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የቀድሞ ምክትል አፈ ጉባኤ ፣ የትግራይ ብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አቶ ሙሉ ነጋ ( ፒኤችዲ ) ፣ አቶ አወሉ አብዲ የብልፅግና ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ፣ የትግራይ የብልፅግና ፓርቲ ኃላፊ አቶ ነብዩ ስሁልሚካኤል በአንድ ድምጽ ፤ የአፈ ጉባኤዋ መረን የለቀቀና ድንገቴ ስራ መልቀቂያ ሕግና ስርዓትን ያልተከተለ ከመሆኑ ባሻገር የሕዝብን አደራ የበላ ነው ብለውታል ። በተለይ አቶ ነብዩ የለውጥ ኃይሉ ለትግራይ ሕዝብ ክብር ሲል ይህን ትልቅ ኃላፊነት ቢሰጥም ለህወሀትም ሆነ ለግለሰቧ አይገባም ነበር ብለዋል ። አቶ መሀመድ በበኩላቸው የአፈ ጉባኤዋ ስራ አሳፋሪና ስነ ምግባር የጎደለው መሆኑን ተናግረዋል ።
እንደ መውጫ
በኮቪድ 19 አደገኛ ወረርሽኝ የተነሳ ምርጫውን በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ማካሄድ እንደማይችል ለመወሰን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተከተለው መንገድ ፤ መንግስት በገለልተኛ ልሒቃን አስጠንቶ አራት አማራጮችን ያቀረበበት አግባብ፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ሕገ መንግስታዊ ትርጉም እንዲሰጥበት ለኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት የመራበት ሒደት ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ለሕገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ የወሳኔ ሃሳብ እንዲሰጥበት የጠየቀበት አግባብ ፤ በመጨረሻም የሕገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ ድረስ የተመጣበት ሒደትም ሆነ ጉባኤው በሀገሪቱ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እና የዳኝነት ስርዓት ታሪክ ለመጀመሪያ በግልፅ በሚዲያ በቀጥታ እንዲተላለፍ በማድረግ ፤ የፍርድ ቤት ወዳጆች / አሚኪ ኪውሬ / ማለትም በሕገ መንግስት ላይ እውቀት ያላቸውን ሊቃውንት ፣ ሕገ መንግስቱን በማርቀቅ ሒደት የተሳተፉ ፣ የሙያ ማህበራት ፣ ባለሙያዎችና የመንግስት ተቋማትን ለመጀመሪያ ጊዜ በግልጽ ያሳተፈና በሀገሪቱ የሕገመንግስት ታሪክ እንደዚህ ሒደት ግልጽ ፣ ተጠያቂና አሳታፊ ሕገመንግስታዊነት ታይቶ እንደማያውቅ ያለ ልዩነት እውቅና የተሰጠውና ታሪካዊ ሒደት ነው ። ሕገ መንግስታዊነቱ ከትህነግ የደባና የሴራ ተሸናፊ ፖለቲካ በላይ ስለሆነ ሊጠይምና ሊጠልሽ አይችልም ።
ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ፈጣሪ አብዝቶ ይጠብቅ !
አሜን ።
አዲስ ዘመን ሰኔ 6/2012
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com