የሰው ልጅ ከጋርዮሽ ሥርዓት ጀምሮ አሁን ወደደረሰበት የእድገት ደረጃ ሲመጣ ባለው ሂደት ሀገራት በበርከታ ውጣ ውረዶች እና ምስቅልቅሎች ውስጥ ለማለፍ ተገደዋል፡፡ ትናንትና ያጋጠሟቸውን ፈተናዎች በጥብብ እና በጠንካራ የሥራ ባህል ያለፉ ሀገራት ዛሬ ላይ በከፍተኛ ተድላ ላይ ናቸው። በሁለንተናዊ መልኩ ከዓለም ሀገራት ቀድመው መቀመጥ ችለዋል፡፡ ትናንትን በዋዛ ፈዛዛ ያሳለፉ እና የሚጠብቅባቸውን ያህል ያልሠሩ ሀገራት ደግሞ በማያቋርጥ ጦርነት እና በድህነት አረንቋ ወስጥ ተዘፍቀው ይገኛሉ፡፡ አንድ አንዶቹም ከእነጭራሹ ከዓለም ካርታ ተፍቀው ጠፍተዋል፡፡
የዛሬ ትጋታችን ለነገ ትሩፋታችን ምንጭ ስለመሆኑ በርካታ ማሳያዎች ቢኖሩም ለዛሬው ግን የህዳሴው ዘመን በአውሮፓ (Renaissance) እና የምሁራን እንቅስቃሴ “ኢላይትመንት” (Enlightenment) በአውሮፓ ማየቱ በቂ ነው፡፡
የህዳሴው ዘመን በአውሮፓ (Renaissance) የዓለምን አጠቃላይ ሁኔታ በብዙ መልኩ እንደቀየረ ይታመናል፡፡ አውሮፓውያን በዘመነ የህዳሴ የጣሉት የመዘመን ፣ የመለወጥ እና የማደግ እርሾ ዛሬ ላይ ሁለናተናዊ እድገት ማምጣት እንዲችሉ ረድቷቸዋል።
በአውሮፓ ከሬናይሰንስ ቀጥሎ የነበረው የምሁራን እንቅስቃሴም “ኢላይትመንት” (Enlightenment) እንዲሁ በርካታ ሳይንሳዊ አስተሳሰቦች የፈለቁበት ነበር፡፡ ይህም ለመንግሥታዊ የአሠራሮች እና የአደረጃጀቶች አጋዥ የሆኑ ቢሮክራሲ መፈጠር ምክንያት የሆነ ነው፡፡ ከኢላይትመንት (Enlightenment) ቀጥሎ በአውሮፓ ለመጣው የኢንዱስትሪ አብዮትም ጥሩ መደላድል የፈጠረ ነው፡፡
በዘመነ ህዳሴ (Age of Renaissance) እነሊዮናርዶ ዳቪንች ፣ ቶማስ ሞር ፣ ኒኮሎ ማኪያቪሊን ፣ ዊሊያም ሼኪስፒር ፣ ጋሊሊዮ ጋሊሊ ፣ ኒኮላስ ኮበርኒከስ እና መሰል ሊቃውንት በርካታ ፈጠራዎችን ለአውሮፓውያን ብሎም ለዓለም አበረከቱ፡፡ አውሮፓውያንም የምሁራኑን ፈጠራዎችን እንዲሁ አልተመለከቱትም፡፡ ይልቁንም ለሀገር ተረካቢዎቻቸው በትምህርት ቤቶቻቸው እና በዩኒቨርሲቲዎቻቸው አስተማሩ፡፡
ይህ አስተምሮ እያደገ ሄዶ ዘመነ ኢላይትመንትን (Age of Enlightenment) ፈጠረ፡፡ ዘመነ ኢላይትመንት (Age of Enlightenment) እነጆን ሎክ ፣ ሞንቲስኩ ፣ ሩሶ ፣ ዲድሮት፣ ኒውትን ወዘተ ወለደ፡፡ እነዚህ ሰዎች ከቀደሙት ምሁራን የቀሰሙትን እውቀት በራሳቸው ዘመን አስተሳሰብ እና ፈጠራ በመዋጀት አዲስ እውቀት ለአውሮፓውያን አበረከቱ፡፡ ይህም የአውሮፓውያን ሁለንተናዊ እውቀት አንድ ደረጃ ከፍ ማድረግ የቻለ ነው፡፡
ለምሳሌ እንግሊዛዊው ጆን ሎክ በፍልስፍናው ስለነጻነት አውሮፓውያኑን ለማስተማር ብዙ ደከመ። ነጻነት ምንድን ነው? ሊያስገኛቸው የሚችላቸው ትሩፍቶች ምን ፤ ምን ናቸው ? ወዘተ የሚለውን በአውሮፓውያን አእምሮ አሰረጸ፡፡ የነጻነት አባት (the father of liberty) ለመባልም በቃ። ይህ የትናትና ትጋት እና ጥረት አሁን ላይ አውሮፓውያን የነጻነትን ፍሬ ከበቂ በላይ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል።
በተመሳሳይ ጃክስ ሩሶ ሶሻል ክንትራክት (social contract theory) በተሰኘው ንድፈ ሃሳብ “መንግሥት የሚመሠረተው የሕዝብን ሉዓላዊነት ለማስከበር ነው፡፡ ሥልጣን የሕዝብ እንጂ የመንግሥት አይደለም (the government should exist to enforce the sovereign will of society, as society is the real holder of power, not government)” ሲል አስተማረ፡፡ አውሮፓውያኑም የሩሶን አስተሳሰብ ተረዱት፤ ወደዱትም፡፡ ተግባራዊም አደረጉ፡፡
ሥልጣን የሕዝብ ሲሆን አንድ ሀገር ምን ያህል ማደግ እንደሚችል ተገነዘቡ፡፡ ይህን የመሰለ ሥራ ትናንት የሠሩት አውሮፓውያኑ ዛሬ ላይ በምን አይነት ተድላ ውስጥ መሆናቸውን ሁላችንም የምንገነዘበው ነው፡፡ ሁልጊዜም በሀገራቸው እና በማህበረሰባቸው ጥቅም አይደራደሩም፡፡
ሀገራቸውን በጎራ ከፋፍለው እና አቧድነው ዜጎቻቸውን እርስ በርስ አያባሉም፡፡ ይህም የምግብ ፍላጎታቸውን ከማሟላት አልፈው የምግብ ሉዓላዊነታቸውን ማስጠበቅ አስችሏቸዋል፡፡ አሁን ላይ የምግብ ሉዓላዊነት ከማሰብ ተሻግረው ለማመን የሚያስቸግሩ የተለያዩ ቅንጡ ነገሮችን እያደረጉ ነው፡፡
በኢላይትንመንት ዘመን ተጽኖ ፈጣሪ የነበረው ሌላኛው ተጠቃሽ ምሁር ሞንቲስኩ ነው። ይህ ሰው “The Spirit of Law” በተሰኘ ሥራው የሶስቱ መንግሥት አካላት የሥልጣን ክፍፍል (separation of power) ምን መምሰል እንዳለበት አስተማረ፡፡ አውሮፓውያን እና ምእራባውያን ይህን ሃሳብ በቅጡ ተረድተው እና አብላልተው ዘመናዊ ሕገ መንግሥት አወጡ ፡፡ የልዕለ ሃያሏ አሜሪካን ሕገ መንግሥት መሠረቱ የሞንቲስኩ “The Spirit of Law” ሥራ ስለመሆኑ ምሁራን ምስክር ናቸው።
ዴሞክራት የሆኑ ሀገራት ዛሬ ላይ በስፋት እየተገበሩት ያለው የሶስቱ መንግሥት አካላት የሥልጣን ክፍፍል (separation of power) እንዲሁ የሞንቲስኩ ሥራ ነው ፡፡ ይህን አስተሳሰብ ለማሳገድ አውሮፓውያን ብዙ ደክመዋል፡፡ ትናንት ይህን አስተሳሰብ መሠረት እንዲኖረው በብዙ የደከሙ እና የጣሩ ሀገራት ዛሬ ላይ የት እንደደረሱ ማየቱ በቂ ነው፡፡
ሌላኛው በዘመነ ኢላይትመንት ስማቸው ከገነኑ ምሁራን ቮልቴር አንዱ ነው፡፡ ቮልቴር በስፋት የሚታወቀው “መንግሥት እና ሃይማኖት መለያየት አለባቸው፣ ሰዎች የመናገር እና ሃሳባቸውን በነጻነት የመናገር መብት አላቸው” በሚለው አስተሳሰቡ ነው፡፡ አውሮፓውያኑም ይህን ተረድተው መንግሥታቸውን ከሃይማኖት ከለዩ ቆዩ፡፡ ይህን ስለ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ምክር አያስፈልገንም ለማለት አይደለም፡፡
ይህን ሁሉ ለማንሳት የሞከርኩት ነገ ለሚፈለገው ለውጥ ዛሬ ላይ በሁለንተ ናዊ መልኩ በሃላፊነት መንፈስ በአስተሳሰብ ለመታደስ እራሱን ያዘጋጀ ጠንካራ ሕዝብ ስለሚያስፈልገን ፤ ለዚህም ጠንክሮ መሥራት ስለሚኖርብን ነው፡፡ ለነገ ያማረ ፖለቲካዊ ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትሩፋቶች ዛሬ ላይ ለለውጥ / ለመለወጥ አአስተሳሰቦች ሰፊ ጊዜ እና ሥፍራ ሰጥተን ጠንክረን መሥራት ይኖርብናል፡፡
አሸብር ኃይሉ
አዲስ ዘመን መስከረም 7/2017 ዓ.ም