በዓውዳ ዓመት ዋዜማ በቡጧ ጨረቃ፣
የተስፋዬ ቀንዲል ከአድማሱ ተጣብቃ፣
ለአዲስ ሕይወት ብሥራት ሰላምን አምቃ፣
በመስቀል ወፍ አምራ በዕንቁ ውበት ልቃ፣
በፀደይ ተኩላ በአደይ አሸብርቃ፣
ንጋትን አየኋት በኮኮቦች ደምቃ።
ኃ.ከ/1990 ዓ.ም/
መቼም አዲስ ዓመት ሲመጣ ሁሌም ቀድሞ ትዝ የሚለን አደይ አበባ ነው አይደል? ወይስ ደማቋን መስከረም… በተስፋና የደስ ደስ በተሞላው በጠና ስሜት የሚያስናፍቁን የአዲስ ዓመት የእንቁጣጣሽ ዜማዎች ናቸው? ከአደይ አበባ ፍካት ጋር አብረው ሆድ የሚያባቡ በርካታ ዜማዎች አዕምሯችን ውስጥ ይመላሉ።
«ምነው ተለየሽኝ መስከረም ሳይጠባ፣
እንቁጣጣሽ እያልን ሳናጌጥ በአበባ።
(የቀድሞው የስፖርት ጋዜጠኛው እና ድምጻዊ ግርማ ነጋሽ)
መስከረም ሲጠባ ዐደይ ሲፈነዳ፣
እንኳን ሰው ዘመዱን ይጠይቃል ባዳ።
ዐደይ አበባ የመስከረሙ፣
እነ ጉብሌ ወዴት ከረሙ?
ዐደይ አበባ የሶሪ ላባ፣
እፍ እፍ በይ እንደ ገለባ…»
ዐደይ ፈነዳ መስከረም ነጋ፣
እንግዲህ ልቤ ባንተ ላይ ይርጋ»
እቴዋ መስከረም አንቺም አረምሽን፣
እኔም መከራዬን ነይና እንታረም።
የክረምቱ ወቅት ወደ መጠናቀቂያው ሲቃረብ አንስቶ የዓመቱ የመጀመሪያ ወራት ጋራና ሸንተረሩ አረንጓዴ ከመልበሱ ባሻገር የተለየ ሕብር የሚፈጥረው አደይ አበባ የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት አብሳሪ ነው።
በበርካታ ኢትዮጵያውን ዘንድ አደይ አበባ የአዲስ ዓመት አብሳሪ የመስከረም ወር መለያ ተደርጎ ይወሰዳል። ለበርካቶች የመስከረም ወር፣የመስቀል ደመራና አዲስ ዓመት ከአደይ አበባ ውበትና መዓዛ ጋር በጥብቅ የተቆራኙ ናቸው።
እንዲያውም አደይ አበባ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኝ እፅዋት፣ የኢትዮጵያውያን ብቻ መለያ የሆነ ያህል ጠንካራ የስሜት ትስስር ተፈጥሯል፤ በርግጥ አደይ አበባ በኢትዮጵያ ብቻ ነው የሚበቅለው? በጭራሽ። ዓይነቱ የተለያየ ነው እንጂ በዓለም በተለያዩ ሀገሮች ይበቅላል። አደይ አበባ ለምን በአዲስ ዓመት ብቻ ይዘከራል?
ስለአደይ አበባ ሳይንሱስ ምን ይላል?
የሚሉ መጠይቆች ይነሳሉ። በተለያየ ዕይታም ሆነ የገደምዳሜ ጥናትም የተለያዩ ምላሾች ይኖራሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ብዝሀ ሕይወት ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰው በአማርኛ አደይ አበባ ወይም የመስቀል አበባ፣ በኦሮምኛ ‘ኬሎ’፣ በትግርኛ ደግሞ ገልገለ መስቀል ተብለው የሚጠሩት የእፅዋት ዓይነቶች በሳይንስ መጠሪያቸው ‘ባይደንስ’ እንደሚባሉ ያስረዳሉ።
ተመራማሪው እንደሚሉት የእነዚህ እፅዋት ቤተሰቦችም ‘አስትሬይሲያ’ ወይም’ ኮምፖሲታይ’ ይባላል።
በኢትዮጵያ ሃያ የሚሆኑ የባይደንስ ዝርያዎች አሉ። ከእነዚህ መካከል’ባይደንስ ማክሮፕተራ’፣ ‘ባይደንስ ፕሬስቲናሪያ’ እና’ ባይደንስ ፓክሎማ’ የተባሉት ዝርያዎች ብርቅዬና ሰፊ ሥርጭት ያላቸው ናቸው።
እነዚህን ሦስት ዝርያዎች በደንብ ቀረብ ብለው ካላዩዋቸው ወይም በጥናት ካልተለዩ በስተቀር ለዕይታ የመመሳሰል ባህርይ አላቸው ይላሉ ፕሮፌሰሩ።
እንደ ተመራማሪው ከሆነ ‘ባይደንስ ማክሮፕተራ’ የሚባለው ዝርያ የሚገኘው በኢትዮጵያ ብቻ ሲሆን በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎችም ይበቅላል። ‘ማክሮፕተራ’ የተባለው ዘሩ ክንፍ የመሰለ ትንሽ ነገር ስላለው ነው። ዝርያውን መለየት የሚቻለውም ይህንኑ ክንፍ በማየት ነው።
በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኘው ‘ባይደንስ ማክሮፕተራ’ ነው ‘ባይደንስ ፕሬስትራኒያ’ የተባለው ዝርያ ደግሞ ከኢትዮጵያ ውጭ ሱዳን ውስጥ የሚበቅል ነው እንጂ እርሱም ቢሆን ሌላ ሀገር ውስጥ አይገኝም። በመሆኑም ‘ማክሮፕተራ’ በኢትዮጵያ ብቻ ስለሚገኝ ‘ብርቅዬ’ ሲባል ‘ፕሬስትናሪያ’ ደግሞ በኢትዮጵያና በጎረቤት ሱዳን ስለሚገኝ ‘የቅርብ ብርቅዬ’ እንደሚባል ፕሮፌሰር ሰብስቤ ያስረዳሉ። ‘ባይደንስ ፓክይሎማ’ የተባለው ዝርያ ግን አፍሪካ ውስጥ በብዛት ይገኛል።
በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኘው የአደይ አበባ ዝርያ ‘ባይደንስ ማክሮፕተራ’ በዓለም ብርቅዬ እፅዋቶች መዝገብ ውስጥ አይስፈር እንጂ፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተዘጋጀው የመጤዎችና ሀገር በቀል እፅዋቶችን መረጃ የያዘ ጥራዝ ውስጥ ተመዝግቦ እንደሚገኝ ፕሮፌሰር ሰብስቤ ገልጸዋል።
«የሰይጣን መርፌ
(ባይደንስ ፒሎሳ)»
ከሃያዎቹ የባይደንስ ዝርያዎች መካከል አንዱ ‘ባይደንስ ፒሎሳ’ ይባላል። ይህ የአደይ አበባ ዝርያ ቀለሙ ነጭ ነው። የሚበቅለው ግን ቢጫው አደይ አበባ በሚበቅልበት ወራት ነው። በተለምዶ ‘የሰይጣን መርፌ’ ይባላል። “የሰይጣን መርፌ የተባለው ጫፉ ላይ እሾህ መሳይ ነገር ስላለውና በቀላሉ ስለሚጣበቅ ነው” ይላሉ ፕሮፌሰር ሰብስቤ።
“ለመሆኑ የሱፍ አበባ እና የአደይ አበባ ዝምድና አላቸው?”
ፕሮፌሰር ሰብስቤ እንደሚሉት ኑግ፣ ሱፍና ግራዋ የአደይ አበባ ቤተሰብ አባላት ናቸው።
ሁሉም የሚገኙት ‘አስትሬይሲያ’ በሚባል የእፅዋት ቤተሰብ ውስጥ ነው። እነዚህ የቤተሰብ አባላት በብዛት የሚገኙትና የሚስፋፉት ብዛት ያላቸው ዘሮችን ስለሚያፈሩ ነው።
አደይ አበባ ዓይናችንን የሚስበውም የተለያዩ ዝርያዎች ብዙ ዘሮች ኖሯቸው በአንድ ላይ ሲያብቡ ብዙ ስለሚሆኑ ነው። ከዚህም ባሻገር የየአካባቢው ባሕል እንዲሁም ሃይማኖታዊ በዓላት ይበልጥ እንዲጎሉ አድርጓቸዋል።
“እነዚህ ብቻ ሳይሆኑ እያንዳንዱ እፅዋት ቤተሰብ አለው” የሚሉት ፕሮፌሰሩ፤ እነዚህ ዝርያዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙ ቁጥር ያላቸው ናቸው ይላሉ። እንደ ተመራማሪው ከሆነ በቁጥር ምን አልባት የአተር ዝርያዎች ቢበልጧቸው ነው።
አደይ አበባ የመስከረም ወር ጌጥ ነው፤ በተለይ በገጠር አካባቢ የሚኖሩ ታዳጊዎች ይህ ወቅት የሚቦርቁበት ነው።
በአረንጓዴ የተሸፈነው ለምለም ሜዳ በአደይ አበባ ተቀይጦ አንዳች ውበትን ያላብሳል። ወደ መስክ ወርዶ አደይ አበባ መልቀም የተለመደ ነው።
የመስቀል በዓል ላይ ደመራውን ከሚያስውቡት ድምቀቶች አንዱ አደይ አበባ ነው። ጫፉ ላይ ከቄጠማ ጋር ይታሰራል። ከደመራው ሥርም ይጎዘጎዛል።
በኦሮሞ ማሕበረሰብ ዘንድ በድምቀት በሚከ በረው የኢሬቻ ክብረ በዓልም የክብረ በዓሉ ታዳሚዎች ወደ በዓሉ ቦታ የሚያመሩት አደይ አበባ እና እርጥብ ሳር በእጃቸው ይዘው ነው።
በተፈጥሮ በለመለመው ሳርና በፈካው አበባ ፈጣሪያቸውን ያመሰግኑበታል። ልምላሜንና
በጎ ምኞታቸውንም ይገልጹበታል።
አደይ አበባ በአንዳንድ አካባቢዎች ከነሐሴ ወር መገባደጃ ጀምሮ ጳጉሜን ይዞ በየጫካውና በየጥሻው ብቅ ብቅ ማለት ይጀምራል።
መስከረም አንድ ብሎ ከጀመረ በኋላ እስከ ኅዳር ድረስ ግን መስኩ፣ ተራራው፣ ሜዳው በዚሁ አበባ ያሸበርቃል። ቢበዛ ከሦስት ወራት በኋላ ግን አደይ አበባን ማግኘት ይከብዳል።
‘የመስቀል ወፍና የአደይ አበባ፣
ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ’
ማን ያውቃል?
እንዳለው ገጣሚው።
አደይ አበባ ለምን በእነዚህ ወራት ብቻ ታይቶ ይጠፋል?
ይሄ የዕረፍት ሂደት እንጂ መጥፋት አይደለም” የሚሉም ጥቂት ወገኖች አሉ።
እኚህ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-እፅዋት መምህር ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰው” እንደተናገሩት የአደይ አበባንና የመስከረምን ቀጠሮ የሚያመሳስሉት ከሰዓት ጋር ነው።
“ማታ ተኝተን ጠዋት እንድንነቃ ሰዓት እን ሞላለን፤ ልክ እንደዚያው እፅዋት የራሳቸው ጉዳዮች ከተሳካላቸው፣ የሚፈልጉትን ያህል ዝናብና ፀሐይ ካገኙ ‘አሁን ነው የምታብቡት’ በሚል ውስጣዊ ግፊት ያብባሉ ይህም’ ባዮሎጂካል ክሎክ’ በመባል ይታወቃል። ይላሉ
BEHAILU ABERA, [9/13/2024 11:58 AM]
አበቦቹ ምንም እንኳን ማበቢያ ጊዜያቸው አዲስ ዓመትን ተንተርሶ ቢሆንም እንዲያብቡ የሚያደርጋቸው ግን ውስጣዊ ባህርያቸው እንደሆነ ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል።
“ግንዳቸው ጠንከር ያላሉት የአደይ አበባ ዝርያ ዓይነቶች ለማበብና ለማፍራት ባላቸው ተፈጥሯዊ ሂደት አንድ ዓመት ይቆያሉ” ይላሉ ፕሮፌሰር ሰብስቤ።
ከዚያም ለውስን ጊዜያት አብበው ይሞታሉ።
ይሞታሉ ሲባል ይጠፋሉ ማለት ሳይሆን ዘራቸው መሬት ውስጥ ይገባል ማለት ነው።
ፕሮፌሰር ሰብስቤ እንደሚሉት “አደይ አበባ መሃል ላይ ያለው ፍሬው የእሾህነት ባህርይ ስላለውና በብዛትም ስለሚመረት በቀላሉ መሬት ውስጥ ለመግባት ያስችለዋል።
መሬት ውስጥ ሲቆይ ልክ ጉንዳን ለክረምት ምግብ እንደሚሰበስበው ሁሉ አደይ አበባም ለዘር የሚያበቃውን ምግብ ይዞ ይቆያል።
“አመቺ ሁኔታ ሲያገኝ፣ ዝናብ ሲዘንብ፣ ከዚያም ፀሐይ ሲወጣ፤ ‘አሁን ነው ማበብ ያለብህ’ የሚል የተፈጥሮ ግፊት ይገፋፋዋል። ይህ የተፈጥሮ ባህርያቸው ነው” ይላሉ ፕሮፌሰር ሰብስቤ።
አደይ አበባ ዓመቱን ሁሉ ማበብ ቢችልም ከክረምቱ ወራት ማሳረጊያ እስከ ፀደዩ ማብቂያ በጉልህ ማበብ ይችላል የሚሉት ተመራማሪው፤ የመስከረም ወር ግን በተለየ ከፍታ ለአብነት የቀረቡ ዝርያዎች ይበልጥ አመቺ ነው ይላሉ።
አደይ አበባን ልዩ የሚያደርገውም ከኢትዮጵያ አዲስ ዓመት እና ተከታትለው ከሚመጡ በዓላት ጋር መገናኘቱ ነው። “አደይ አበባ እና የዘመን መለወጫ መገጣጠም ግን ያጋጣሚ ጉዳይ ነው” ብለዋል ተመራማሪው።
በኢትዮጵያ አደይ አበባ የማይበቅልበት ቦታ አለን?
ተመራማሪው እንደሚሉት አደይ አበባ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል ይበቅላል። ይሁን እንጂ በመሬት አቀማመጥ ከፍታና ዝቅታ መጠኑና ቆይታው ሊለያይ ይችላል።
በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኘው ‘ባይደንስ ማክሮፕተራ’ በብዛት የሚገኘው ከመሬት ወለል በላይ ከ2000 እስከ 3600 ሜትር ከፍታ ባሉ ደጋማ አካባቢዎች እንደሆነ ተመራማሪው አስረድተዋል። ከ1750 ሜትር በታች ባሉ አካባቢዎች ግን አይበቅልም።
የእፅዋት ሥርጭት ከመሬት ወለል በላይ ባለ ከፍታ ይወሰናል የሚሉት ፕሮፌሰር ሰብስቤ፤ አደይ አበባ በትግራይ፣ በአዲስ አበባ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ሐረር፣ ደሴ፣ ወለጋ፣ ነቀምት፣ ጂግጂጋ እና ሌሎች ከፍተኛ ቦታዎች ላይ ይበቅላል ይላሉ።
“ለምሳሌ አፋር ውስጥ ከፍተኛ ተራራ ላይ ሊገኝ ይችላል። ወደ ዳሎል ወረድ ሲባል ግን ሊገኝ አይችልም” ሲሉም ያስረዳሉ።
አደይ አበባ ከውበትና
ከድምቀት ሌላ . . .
አደይ አበባ ውበቱ፣ ለሥነ ምኅዳሩ፣ ለሃይማኖታዊና ባሕላዊ ክብረ በዓላት ያለው አስተዋፅኦ ራሱን የቻለ እሴት ነው ይላሉ ፕሮፌሰር ሰብስቤ።
ከዚህ ባሻገር ግን የመድኃኒትነት ባህርይ ያላቸው የአደይ አበባ ዝርያዎች እንዳሉም ተናግረዋል።
በተለምዶ ‘የሰይጣን መርፌ’ ተብሎ የሚጠራው የአደይ አበባ ዓይነት በባሌ አካባቢ ሰው በእባብ ሲነድፍ በሕላዊ እውቀት ለመድኃኒትነት እንደሚጠቀሙበት ምሳሌ አጣቅሰዋል።
“ምንም እንኳን በተፈጥሮ የተሰጠን ፀጋ እና በረከት በገንዘብና በአገልግሎት መመዘን ብቻ ተገቢ ባይሆንም፤ ኬሚካላዊ የሆነ ባህርያቸው ላይ ቢሰራ አዲስ የምርምር ውጤት እንደሚገኝ በመጠቆም ኢትዮጵያ እንደ አደይ አበባ መጠሪያዋ የሆኑ ብርቅዬ እፅዋቶች እንዳሏትም ፕሮፌሰር ሰብስቤ በአፅንዖት ይገልፃሉ።
ለመላው ኢትዮጵያን በሙሉ እንኳን ከዘመን ወደ ዘመን አሸጋገራችሁ!!
መልካም አዲስ ዓመት እንዲሆንላችሁም ከልብ እንመኛለን!!
ኃይረዲን ከድር/ከአሰላ ውበት/
አዲስ ዘመን መስከረም 7/2017 ዓ.ም