መንደርደሪያ፤ “የሕይወት እንቆቅልሽ ሁሉም ፍቺ የለውም” የሚባለው ያለምክንያት አይደለም። አንዳንዴ፤ የተራራቁ ጉዳዮች ተቀራርበው ያልታሰቡ ግጥምጥሞሾች ተዋደው ስናስተውል “እንዴት ሊሆን ቻለ?” ብለን መጠየቃችንና መደነቃችን የተለመደ ሰብዓዊ ባህርያች ነው። እርግጥ ነው ተደጋግመው ተጠይቀው መልስ እንደማይገኝላቸው እየታዋቀ አሻፈረኝ በማለት የሙጥኝ የምንላቸው ተደጋጋሚ ክስተቶችም ቁጥራቸው የዚያኑ ያህል የበረከተ ነው። “ሕይወትና መኖር በእንቆቆልሽ የተሞሉ ናቸው” መባሉ ስለዚሁ ሳይሆን አይቀርም።
የሰው ልጅ ከሌሎች ፍጡራን ከሚለይባቸው ብቃቶቹ መካከል አንዱና ዋነኛው የራሱን ታሪክ ሰንዶ ማቆየቱ በቀዳሚነት ይጠቀስለታል። ቅድመ ታሪክ (Pre History) ውሎ አምሽቶውን በዋሻዎች፣ በድንጋይ እና በመሰል ቁሶች ላይ በገላጭ ሥዕሎች አማካይነት ሸሽጎ አኑሮልናል። የድህረ ታሪክ ዜና መዋዕሉንም እንዲሁ በፓፒረስ፣ በብራናና በወረቀት ላይ በጽሑፍ፣ በሥዕላ ሥዕሎች፣ በቅርጻ ቅርጾችና በመሰል የፈጠራ ውጤቶቹ እስከ ዛሬው የቴክኖሎጂ ዘመን ድረስ ለማሸጋገር በቅቷል። የነገውን ደግሞ በነገው ጀንበር እንመ ረምረዋለን።
የዘርፉ ምሁራን አዘውትረው እንደሚመሠክሩት፤ “ታሪክ የአሸናፊዎች ገድል የሠፈረበት ዜና መዋዕል ነው።” አባባሉን ትንሽ እናቃናው ካልን፤ “የአሸናፊዎች ገድል ተመርምሮ ገለባው ከአላባው ተለይቶ ከነጠረ በኋላ የሚገኘው የታሪክ ወርቅ ግን የቀዳሚው፣ የዛሬውና የነገው ትውልድ ማጌጫና መዋቢያ ነው።” – “ከታሪክ መሰዊያ ላይ አመዱን ሳይሆን እሳቱን መጫር” እንደ ማለት ነው። እነሆ በዚህ የመንደርደሪያ ሐቅ መሠረት እስካሁን እጅግም ያልተነገረለትን አንድ የተሰነደ ሀገራዊ የታሪካችንን እሴትና እግረ መንገዴንም እንደ ግጥምጥሞሽ ሊታይ የሚገባውን አስገራሚ የተፈጥሮ ክስተት ከራሴ ገጠመኝ ጋር እያዋዛሁ ለማስታወስ እሞክራለሁ።
እግዜር ያጥናሽ ኒውዮርክ፤
በገናናነታቸው ከፍ ብለው ከሚገኙት የዓለማችን ከተሞች መካከል (ፓሪስና ጄኔቫ እንዳይቀየሙ እንጂ) የኒውዮርክን ያህል በውበትም ሆነ በግርማ ሞገስ የመደነቅና የመናፈቅ አክሊልን በአናታቸው ላይ የደፉ ቀዳሚ ከተሞች ስለመጠቆማቸው እርግጠኛ መሆን ያዳግታል። ከዚሁ ውበቱ ጎን ለጎን የዓለም ፖለቲካ የሚመሳጠርበት (መስከረም 1948 ግንባታው ተጀምሮ በ1952 በተጠናቀቀው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጽ/ቤት ውስጥ የሚወሰኑትን ዓለም አቀፍ ውሳኔዎች ያስታውሷል)። ኢኮኖሚው የሚጦዝበትና ሲያሻም የሚረግብበት (በ1792 መሠረቱ የተጣለውና የዓለም ግዙፍ ኢኮኖሚ የሚዘወርበት የኒውዮርክ የስቶክ ገበያን ይመለከታል)። ሲያስፈልግ የጦርነት መቀስቀሻና ማብረጃ ስትራቴጂ የሚጠነሰስበት፣ የሚወሰንበትና እንዲተገበር ትዕዘዝ የሚሰጥበት የዓለም ቁንጮ ከተማ ጭምር ነው – ኒውዮርክ። “የታላቋ አሜሪካ ነፍስና መንፈስ የሚገኘው እዚሁ ኒውዮርክ ከተማ ውስጥ ነው። በዋሽንግቶኑ ነጩ ቤተ መንግሥት ውስጥ የሚገኘው ሥጋዋ ብቻ ነው” የሚባለውም ስለዚሁ ነው። ኒውዮርክ ሲያስነጥስ ሞስኮ፣ ቤጅንግ፣ ፒዮንግ ያንግ፣ ቴህራንና ሌሎች የዓለም ሀገራት የሚባንኑትም በዚሁ ምክንያት ይመስላል።
ይህ እንደ ባቢሎኑ ጥንታዊ ንጉሥ እንደ ናቡከደነፆር የዙፋኑ መንበረ ሥልጣን እጅግ ገዝፎ የሚፈራውና የሚደነቀው የኒውዮርክ ከተማ የቀዳሚ ዘመናቱን እንኳን ትተን ባለፉት ሁለት ዐሠርት ዓመታት ብቻ “እግዚኦ አቤት!” የሚያሰኙ ክፉ አደጋዎች ገጥመውት ለመሪር እንባ ተዳርጓል። አንዳንድ ታዛቢዎች እንደሚሉት ኢጣሊያዊው ሀገር አሳሽ Giovanni da Verrazzano በእግሩ ረግጦ ህልውናውን ካበሰረበት ከ1524 ዓ.ም ጀምሮ እና አውሮፓውያን ሠፋሪዎች ወርረው ከተማውን ቋሚ መኖሪያቸው ካደረጉ ከ1608 ጀምሮ ባለፉት ሃያ ዓመታት ውስጥ እንደ ደረሰበት መከራ የከፋ አሳር ከተማውን ስለመግጠሙ ያጠራጥራል ባዮች ናቸው።
የመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ዋሽንግተን መንበረ ሥልጣናቸውን የጨበጡበት፣ የአሜሪካ የመብቶች ድንጋጌ (Bill of Rights) እና የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ (Supreme Court) ረቂቆች የተጠነሰሱበት የኒውዮርክ ከተማ በውጭ ወራሪዎችና በእርስ በእርስ ጦርነቶች መመሳቀሉ፣ በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ ወለድ አሳሮች እየተጠቃ ፈጥኖ በማገገም አቅሙን እያሳየ ዘመናትን ቢያሳልፍም እንደ አለፉት ሃያ ዓመታት የመከራ በትር አድቅቆት የሚያውቅ ግን አይመስልም።
ሁለቱን ግዙፍ የድንጋጤውን ክስተቶች ብቻ እናስታውስ። እ.ኤ.አ ሴፕቴምበር 11 ቀን 2001 ዓ.ም አሸባሪዎች በዓለም የንግድ ማዕከል (World Trade Center) መንትያ ሕንጻዎች ላይ ባደረሱት አደጋ በደቂቃዎች ዕድሜ ብቻ 2606 ንፁሃን ዜጎችን እምሽክ አድርጎ በልቷል። ሕይወታቸውን ካጡት መካከልም ኢትዮጵያውያን እንደሚገኙበት አይዘነጋም። የሴፕቴምበር አሥራ አንድ ትራዤዲያዊ ክስተት በተፈጸመበት በዚያ አሰቃቂ ዕለት የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ነዋሪነቱ በዚያው በአሜሪካ ምድር ስለነበር የአስከፊነቱን መጠን በሚገባ ለመረዳት ችሏል።
ሁለተኛው ክስተት እስከዛሬዋ ዕለት ድረስ የዓለም ዜጎችን ቀለምና ዘር ሳይለይ እየቀጠፈ ያለው የኮቪድ 19 ክፉ ወረርሽኝ ጉዳይ ነው። የመጀመሪያው የቫይረሱ ተጠቂ በኒውዮርክ ከተገኘበት ከማርች 1 ቀን 2020 ጀምሮ እስከ ጁን 9 ቀን 2020 ድረስ ምርመራ ከተደረገላቸው 2.6 ሚሊዮን ዜጎች መካከል 379,500+ በወረርሽኙ የተለከፉ ሲሆን የ24,348 ኒውዮርካዊያን ሕይወት ተነጥቋል። ይህ አሃዝ አስደንጋጭ መሆኑ ብቻም ሳይሆን ከመላው የአሜሪካ ግዛቶች ጋር ሲነጻጸር ምንም እንኳ ዓለም አቀፉ ወረርሽኝ እኛንም ሳይምር የዓለም ሕዝቦችን በሙሉ መከራ ላይ የጣለ ቢሆንም የሰብዓዊያን ሁሉ ልማድ ስለሆነ “ወዳጃችን ኒውዮርክ ሆይ እግዜር ያጥናህ!” ብሎ መልካም ምኞትን መግለጹ አግባብ ይሆናል።
«ኒውዮርክ ሀገራዊ ባለውለታችን»
ዛሬ መከራ ተጭኖት “እግዜር ይማርህ!” የምንለው የኒውዮርክ ከተማ ከእኛ ከኢትዮጵያውያን ጋር በተለየ ሁኔታ ከሚያቆራኙት ታሪካዊ ምክንያቶች መካከል አንዱን ብቻ ማስታወስ ይቻላል። ከኒውዮርክ ጋር ሀገራችን የተቆራኘችበትን ቀሪዎቹን ታሪኮች ወደፊት እንዳስፈላጊነቱ እየመዘዝኩ ለማስታወስ እሞክራለሁ። ለማንኛውም በሦስተኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ቶማስ ጄፈርሰን የአገዛዝ ዘመን (እ.ኤ.አ 1801-1809) በአቢሲኒያ ስም ትታወቅ ከነበረችው ከዛሬይቱ ኢትዮጵያ እንዴትና በምን ሁኔታ እንደሄዱ ለጊዜው በቂ መረጃ ማግኘት ባይቻልም በኒውዮርክ ከተማ በንግድ ሥራ ተሠማርተው ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ወገኖች በአንድ ዕለተ ሰንበት ማለዳ የመንፈሳዊ አምልኳቸውን ለመፈጸም ወደ አንድ የአካባቢው የመጥምቃዊያን ቤተ ክርስቲያን (Baptist Church) ጎራ ይላሉ።
እነዚህ “እንጀራ አሳሽ” ኢትዮጵያውያን ዜጎች ለክርስትና እምነት ቀድሞውንም ቢሆን እንግዳ አልነበሩም። ህንደኬ ለተባለችው የኢትዮጵያ ንግሥት የገንዘብ ሚኒስትርና ዲፕሎማት ለነበረው ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ ሐዋርያው ፊሊጶስ በኢየሩሳለም (ጋዛ በረሃ) ውስጥ የምሥራቹን ወንጌል ሰብኮለት ጃንደረባውም ወደ ሀገሩ ከተመለሰ በኋላ የኢትዮጵያ የክርስትና እምነት መሠረቱን እንደጣለ ብዙዎች የተረዱላቸው አይመስሉም ነበር (የሐዋርያት ሥራ ምዕ. 8)።
እነዚያ ኢትዮጵያውያን ነጋዴዎች ከዛሬ ሁለት መቶ ዓመታት በፊት ጎራ ካሉበት የኒውዮርኩ ቤተ ክርስቲያን እንደደረሱ የቤተ እምነቱ አስተናጋጆች ጥቁረታቸውን (ደማቅ ጠይምነታቸውን) በማየት ብቻ በወቅቱ በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ለባሪያዎች ብቻ በተከለለው ቆጥ መሳይ ጥግ እንዲቀመጡ ያደርጓቸዋል። በቀለማቸው መገፋታቸውና በዘመኑ ገንኖ የነበረው የባርነት ግፍ ያስቆጣቸው የሀገሬ ነጋዴዎች “እናንት የአንግሎ ሳክሰን ዝርያዎች ገና የሥልጣኔን ጭላንጭል ከማየታችሁ አስቀድሞ የእኛ ኢትዮጵያ በክርስትናውም ሆነ በሥልጣኔ ማማ ላይ የደረሰችበት ደረጃ የላቀ ነበር” በማለት በቁጭት ተነሳስተው በዚያው በኒውዮርክ ከተማ ውስጥ ሀርለም በሚባል አካባቢ የራሳቸውን ገንዘብ አሰባስበው የአቢሲኒያ መጥምቃዊያን ቤተ ክርስቲያን (Abyssinian Baptist Church)ን እ.ኤ.አ በ1808 አቋቋሙ።
ይህ ቤተ ክርስቲያን በኒውዮርክ ውስጥ በረጂም ዕድሜው ሁለተኛው የመጥምቃዊያን ቤተ ክርስቲያን ሲሆን ከአጠቃላዩ ከሰሜናዊ የአሜሪካ ግዛቶች ውስጥ ከሚገኙት መሰል አብያተ ክርስቲያናት መካከል ከዘረኝነት ነፃ የሆነ የመጀመሪያው የመጥምቃዊያን (ባፕቲስት) ቤተ ክርስቲያን ለመሆን በቅቷል።
ከአንድ ዓመት በኋላ በ1809 የቤተ ክርስቲያኒቱ መሥራቾች ለኒውዮርክ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ባስገቡት የምዝገባና የምሥረታ ሰንድ ውስጥ “አቢሲኒያ” የሚለው መጠሪያ ሳይነካ ከትውልድ ትውልድ እንዲተላለፍ መወሰናቸውና ውሳኔውም እስከ ዛሬ እንደ ፀና መኖሩ ሌላው የቤተ ክርስቲያኒቱን ጥንካሬ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። (ታላቁ ጥቁር ሰው፤ ኢትዮ-አሜሪካ ዘዳግማዊ ምኒልክ፤ በንጉሴ ተካ አየለ፤ 2010 ዓ.ም ይመልከቱ)
የአድዋው የኢጣሊያ ወረራና የፋሽስቱ ሙሶሎኒ ዳግም ወረራ በተፈጸሙብን ዓመታት የሀገራችን መጠቃት ያንገበገባቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላትና በርካታ ጥቁር አፍሪካ አሜሪካውያን ወዳጆቻችን ከፍተኛ ቅስቀሳዎችን በማድረግና ገንዘብና ቁሳቁሶች በማሰባሰብ ወደ ኢትዮጵያ ይልኩ እንደነበር በታሪክ ተመዝግቧል። በተለይም በአምስቱ የፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት ጆን ሮቢንሰንን መሰል የጦር አውሮፕላን አብራሪዎችና ሌሎች በርካታ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በጦርነቱ ውስጥ በመሳተፍ አጋርነታቸውን አሳይተዋል። ክብርና ሞገስ ይገባቸዋል።
እ.ኤ.አ በ1954 ዓ.ም ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ አሜሪካንን በይፋ በጎበኙበት ወቅት በአቢሲኒያ ባፕቲስት ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው ምእመኑንና መሪዎችን በማመስገን አንድ ትልቅ መስቀል አበርክተውላቸው ነበር። ይህ ታሪካዊ መስቀል ከዚያን ጊዜ በኋላ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልዩ መለያና ምልክት በመሆን ዛሬም ድረስ በመድረካቸው ላይ ከፍ ተደርጎ እንደተሰቀለ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ወደ ሦስተኛው ሚሊኒዬም ሽግግር ባደረገችበት 2000 ዓ.ም የመጀመሪያው ወር የመጀመሪያ ቀናት የአቢሲኒያ ባፕቲስት ቤተ ክርስቲያን ምሥረታ ሁለት መቶኛ በዓል እየተከበረ ስለነበር ይህንኑ የታሪክ ግጥምጥሞሽ ምክንያት በማድረግ በዋናው የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋይ በቄስ ካልቪን ኦ. በትስ (Rev. Calvin O. Butts) የሚመራ 150 የሚሆኑ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት ኢትዮጵያ በመምጣት ሚሊኒዬሙን ከእኛ ጋር አክብረዋል። በዘመኑ ደማቅ የደመራ በዓል አከባበር ላይ የተገኙ ሲሆን አክሱምና ላሊበላን የመሳሰሉ ታሪካዊ ሥፍራዎችንም ጎብኝተዋል። በትልቅ የፕሮቶኮል ማዕረግ አቀባበልና ጥበቃ የተደረገለት የልዑካን ቡድኑ ከወቅቱ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከአቶ መለስ ዜናዊና ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ፓትርያክ ከብፁዕ ወቅዱስ አብነ ጳውሎስ ጋር ተገናኝተው ውይይቶች አድርገዋል። የዚህ ጽሑፍ አቅራቢም ከልዑካን ቡድኑ ጋር የመገናኘት ዕድል ገጥሞት ስለነበር ልዑኩ ከወቅቱ የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት ዋና ጸሐፊ ከቄስ ዓለሙ ሼጣ ጋር ተገናኝተው እንዲወያዩ ለማድረግም ተችሏል።
«የኮንሶው ተፈጥሯዊ የኒውዮርክ ከተማ»
የእኛው ኮንሶ የሚገኘው በደቡብ ክልል ውስጥ ሲሆን ከአዲስ አበባ ከተማ 595 ኪሎ ሜትር ይርቃል። ኮንሶ በዋነኛነት የሚታወቀው በእርከን ጥበቡ ነው። እ.ኤ.አ በ2011 ዓ.ም ዩኔስኮ አካባቢውን ለሀገራችን የእርከን ምጥቀት መገለጫ ዘጠነኛው ቅርስና የዓለም ታላቅ እሴት አድርጎ መመዝገቡ ይታወቃል። የዩኔስኮ እውቅና ተረጋግጦ በዓሉ በኮንሶ በተከበረበት ቀናት የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በቦታው ተገኝቶ የደስታው ተካፋይ በመሆኑ ኩራት ተሰምቶታል።
ከኮንሶ ዋና ከተማ ከካራት በ17 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ጌሴርጂኦ በሚባለው አካባቢ የሚገኘው “ተፈጥሮ ሠራሽ የኒውዮርክ ከተማ” በጎብኚ ቱሪስቶች እጅግ ተወዳጅ የሆነ ቦታ ነው። በነፋስና በዝናብ ተሸርሽሮ የተራቆተው የተራሮች ሰንሰለት በርግጥም ምስለ ኒውዮርክ ገጽታ ስላለው ስያሜው ከተፈጥሮው ጋር በአግባቡ የሚስማማ ነው። ስያሜውን የአካባቢው ነዋሪ ይስጥ ወይንም ቱሪስቶች ለጊዜው የጠራ መረጃ ባይገኝም አካባቢው ቁርጥ ዘመናዊውን የኒውዮርክን ታላላቅ ሕንጻዎች ስለሚመስልና ስለሚያስታውስ “ኒውዮርክ” ከጥሩ እይታ የመነጨ ስያሜ እንደሆነ በግሌ አምናለሁ። በጉብኝቱ ወቅት ያረጋገጥኩትም ይህንኑ እውነታ ነው።
ከሁለት መቶ ዓመታት በፊት በኒዮርክ ከተማ በሀርለም አካባቢ 13ኛው መንገድ ላይ ጎልቶ ለቆመውና የሀገራችንን ስም ለሚያስጠራው የአቢሲኒያ ባፕቲስት ቤተ ክርስቲያን እኛም የኮንሶ ጌሴርጂኦን ተዓምራዊ ተራራዎች በኒውዮርክ ከተማ መሰየሙን ተቀብለን ማጽደቃችን ውለታን እንደመመለስ የሚያስቆጥር ይሆን የሚል ደብዛዛ እምነት አለኝ። በራሳችን ምድርም የኒውዮርካዊያንን ውለታ በሚወዷት ከተማቸው የስያሜ ማስታወሻ ማቆማችን ለሀገራችን ትልቅ ክብር ይመስለኛል። ውለታን በፍቅር መመለስ የትልቅነት መገለጫ ስለሆነ። በኒውዮርክ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ይህንን ታሪክ በማክበር ለከተማዋና አብረው ለሚኖሩት ሕዝብ አክብሮታቸውን ሁሌም በደስታ እንደሚገልጹና በችግሯም ቀድመው እንደሚደርሱ ተስፋ አደርጋለሁ። ሰላም ይሁን!
አዲስ ዘመን ሰኔ 6/2012
(ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ)