ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ሰሞኑን ያወጣው አንድ ማስታወቂያ የብዙዎችን ትኩረት ስቦ ነበር። ኮርፖሬሽኑ በአረብኛ ቋንቋ በቅርቡ ለመጀመር ላሰበው የቴሌቪዥን ሥርጭት ባለሙያዎችን አወዳድሮ ለመቅጠር የወጣ ማስታወቂያ ነበር። ታዲያ ይኸ ምን አዲስ ነገር አለው? በእርግጥም ባለሙያ አወዳድሮ መቅጠር ምንም አዲስ ነገር የለውም። አዲሱ ነገር በአረብኛ ቋንቋ የቴሌቪዥን ሥርጭት ለመጀመር ዝግጅት መኖሩ መገለጹ ይመስለኛል። ጉዳዩ የመነጋገሪያ አጀንዳ ሊሆን የቻለው በብዙዎች ልቦና ቁጭት በመኖሩ ነው። «ለምን ተበለጥን?» ዓይነት ስሜት እያቆጠቆጠ በመምጣቱ ነው።
አዎ! ግብጾች ይበልጡናል። በዲፕሎማሲ ይበልጡናል። በሚዲያ አጠቃቀም፣ በፕሮፖጋንዳ አሳምረው ይበልጡናል። የሽብር ወሬ፣ የሥነልቦና የፕሮፖጋንዳ ጦርነት በማቀጣጠል ይቦንሱናል። እነሱ በበለጡን ቁጥር እኛ ደግሞ እንደለመድነው እንደው ዘራፌዋን እናቀነቅናለን። በድሮ በሬ ያረሰ ያለ ይመስል «እስቲ ትሞክረን» እያልን ወደሽለላ እና ቀረርቶ እንወርዳለን። ግብጾች ለምን ሊበልጡን ቻሉ? በአጭሩ በአባይ ወይንም በህዳሴ ግድብ ጉዳይ ስለሚናበቡ ነው። ገዥ ፓርቲ፣ ተቃዋሚ፣ አክቲቪስት፣ ፖለቲከኛ፣ ምሁር፣ ሚዲያ…የጋራ ጥቅማቸው በሆነው የናይል አጀንዳ ጉዳይ አብረው ቆመው፣ ተናበው ለመሥራት ውልፍት አይሉም። እናም ዓለም የናይል ምንጭ ግብጽ እስኪመስለው ድረስ በፕሮፖጋንዳ ሲያጠምቁት ኖረዋል።
ወደእኛ ስንመጣ ተቃራኒውን እናገኛለን። ወዳጄ፤ ቀድሞ ነገር በህዳሴ ግድብ ግንባታ ጉዳይ እንኳን መች ተግባብተን እናውቅና?! ቀዳሚ አጀንዳ አይደለም ብሎ አኩርፎ፣ በር ዘግቶ የተቀመጠ ተቃዋሚ ያለበት አገር እኮ ነው። መነጋገር፣ ማሳመን፣ ማመን.. ብሎ ነገር አይታወቅም። እስቲ በሞቴ ልብ ብለህ ተመልከት፤ በህዳሴ ግድብ ጉዳይ ያገባኛል ብሎ ሀሳብ የሚሰጥ ተቃዋሚ ፓርቲ ወይንም ፖለቲከኛ ምን ያህል ነው ብለህ ጠይቅ። ከ130 በላይ እንደአሸን የፈላ ፓርቲ ውስጥ ሦስትና አራት ካገኘህ ዕድለኛ ነህ። ይህ የሆነው ለምን ይመስልሃል? ግልጽ የሆነ ዓላማና ግብ፣ የመታገያ ስትራቴጂ፣ብቃት ያለው አመራር፣ እውነተኛ አባልና ደጋፊ ያላቸው ፓርቲዎች በቁጥር እጅግ አናሳ በመሆናቸው ነው። ብዙዎቹ አሳምረው የሚያውቁትና የተጠበቡበት ትናንት ኢህአዴግ ዛሬ ደግሞ የብልጽግና ፓርቲን ኮቴ እየተከተሉ የተቃውሞ መግለጫ ማውጣትን ነው። እነዚህ ፖለቲከኞች ቢያጡ ቢያጡ ቤተመንግሥት ደጃፍ ላይ ፒኮክ መታየቱ ምክንያት አድርገው የአገር ምልክት፣ ባልህና ወግ ጠፋ ብለው፣ ኀዘን ተቀምጠው ሙሾ ሲያወርዱ የሚታዩ ሥራፈቶች የተሰባሰቡባቸው ናቸው።
ጥቂት ብሔራዊ ጥቅም ያልገባቸው ወይንም በጥቅም የተደለሉ ፓርቲዎችና ግለሰቦች በቀጥታ በግብጽ መንግሥት ፋይናንስ ተደርገው ለጥፋት መሰለፋቸው በመንግሥት አካላት በኩል ተደጋግሞ የተገለጸ ነው።
ምሁሩስ ወዳጄ?..አብዛኛው የኢትዮጵያ ምሁር በረጅም ዝምታውና በር ዘግቶ በመቀመጥ የሚታወቅ ነው። የአፍሪካ ምሁራንን ጋናዊው ኢኮኖሚስት ጆርጅ አይቴ ከበዝባዥ ጋር አልጋ የተጋሩና አንሶላ የተጋፈፉ ነውረኞች ናቸው ሲል ይገልጻቸዋል። የኢትዮጵያ ምሁራን በተመለከተ ዶ/ር አለማየሁ አረዳ «የሰጎን ፖለቲካ…» በሚለው መጽሐፋቸው እንዲህ ይላሉ።«.. የኢትዮጵያ ምሁራን የሀገራቸውን ችግር በመፍታት ረገድ የነበራቸው ሚና ጎልቶ የማይታይ መሆኑን ነው። ይህ የሚያሳየው ትምህርት ወይንም የተማሩ ዜጎች ሀገሪቱ ያሉባትን በርካታና ውስብስብ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ችግሮች ከመፍታት አኳያ የሚፈለገውን አቅም ያልገነቡ መሆኑን ነው።…» አዎ! ምሁራን ሰፈር «ዝም ባለ አፍ ዝንብ አይገባበትም» ብሂል ዝምታ ጎልቶ ይታያል። ሌላው ቀርቶ በድንበር ተሻጋሪ ወንዞችና ውሀ አጠቃቀም እንዲሁም በውሀ ምህንድስና፣ በዓለም አቀፍ ሕግ እና ተያያዥ ዘርፎች ጥሩ አቅም የገነቡ ምሁራን እንደ መሐመድ አል አሩሲ፣ እንደጋዜጠኛ ኡመር ረዲ ዓይነቶች ብዙ አይደሉም። ጥቂት የማይባሉ ምሁራን በራሳቸው ተነሳሽነት ወጣ ብለው በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ስለህዳሴ ግድብ ሽንጣቸውን ገትረው ሲሟገቱ የማንሰማው ምሁራኑ የምንአገባኝ እና የበታችነት ስሜት ምርኮኞች በመሆናቸው ነው። ግድቡንም በጠባቡ የፖለቲካ መነጽር ብቻ አይተው የተወሰኑ ወገኖች ጥቅም አስጠባቂ አድርገው ከመቅረጻቸው ጋር የተያያዘ ነው።
መሐመድ አልሩሲ እና ጋዜጠኛ ኡመር ምን አደረጉ? ደጋግመን የሰማነው ነው። ለማስታወስ ያህል ብቻ በአረብኛ ቋንቋ ግብጻውያንን እና የአረቡን ዓለም ስለአባይ ግድብ ቁጭ አድርገው ያስተማሩ አገር ወዳድ ወጣቶች ናቸው። ጋዜጠኛ ኡመርም በእንግሊዝኛ ቋንቋ በሚተላለፉ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ላይ በራሱ ተነሳሽነት ስለአባይ እውነታውን አንስቶ ይናገራል፣ ከሌሎች ተንታኞች ጋር ይሟገታል፣ ያስረዳል። ሁለቱም በዚህ ቅን ተግባራቸው የታወቀው በሥራቸው ነው። ያነበቡትን፣ ያሰባሰቡትን መረጃ ተመርኩዘው ግብጻውያን ምሁራን ሳይቀር ፊት ለፊት ሞግተዋል። ይኸንን አገራዊ ግዴታቸውን ለመወጣት የማንንም ፈቃድ አልጠየቁም። እንዲህ ዓይነት በራሱ ሳንባ የሚተነፍስ፣ በራሱ የሚተማመን፣ ከጠባቂነት፣ ከአድርባይነት የጸዳ ምሁር በብዛት ማፍራት ያልቻልነው ለምንድነው? የጎደለን ምንድነው? የሚለው ዛሬም በጥያቄ መልክ ተደጋግሞ የሚነሳ ነው።
«በህዳሴ ግድብ ጉዳይ የሚዲያው ሚና ለምን አነሰ» የሚለውን ለማየት ትንሽ ዝርዝር ጉዳዮችን መቃኘት ይጠይቃል። ሚዲያው ስል መደበኛውን ሚዲያ ማለቴ ነው። ሚዲያውን ከህዳሴ ግድብ አንጻር በሁለት ምድብ መቃኘት እፈልጋለሁ። የመንግሥት እና የግል ሚዲያዎች በሚል።
የመንግሥት ሚዲያው (ቴሌቪዥን፣ ራዲዮና ጋዜጣ) የየዕለት ዜናዎችን፣ መግለጫዎችና ቃለምልልሶች ተገቢውን ሽፋን በመስጠት ረገድ ተወዳዳሪ የለውም። ለዓመታት ግድቡ 20 በመቶ፣ 30 በመቶ… ተጠናቀቀ ዓይነት አሰልቺ ዘገባዎችን በመሥራትም ተአማኒነታቸው አደጋ ላይ በመጣልም ይታወቃሉ። ደፈር ብለው በሕዝብ ገንዘብ እየተሰራ ያለው ግድብ አሠራሩ የቱን ያህል ከሙስናና ብልሹ አሠራር የጸዳ ነው? የፋይናንስ አጠቃቀሙ ምን ይመስላል? በተያዘለት የጊዜ ገደብስ ለምን ሳይጠናቀቅ ቀረ? ብለው ለመጠየቅ አልቻሉም። ሚዲያው ኃላፊነቱን በብቃት ባለመወጣቱ ምክንያት የለውጥ አመራሩ ወደፊት ሲመጣ ቀደም ሲል በሜቴክ በኩል ከግድቡ ጋር ተያይዞ ሲከናወኑ የነበሩ አሳፋሪና አሳዛኝ ታሪኮች ለመስማት በቃን። ያው ከሰሞኑ ጠ/ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ለፓርላማ አባላት እንዳሉት ግድቡ ከተያዘለት ጊዜ በስድስት ዓመት ዘግይቶ ነበር። በመዘግይቱም በሀገሪቱ ላይ 6 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ ደርሷል። ይኸም ፕሮጀክቱ በመቆየቱ ምክንያት በየጊዜው የሚያስወጣውን ተጨማሪ ወጪ አያካትትም ማለታቸው ሰምተናል። ጠንካራ ሚዲያ ቢኖረን ኖሮ እንዲህ ዓይነቱ አሳፋሪ ዜና ገና ድሮ ሰምተን አጥፊዎችን ከባሰ ጥፋት መታደግና ለፍርድም ማቅረብ በቻልን ነበር። ግን መንግሥትን መተቸት፤ የመንግሥትን ገመና አሳልፎ ከመስጠት ጋር አያይዞ የሚያይ የሚዲያ አመራር መኖሩ እንዲህ ዓይነት ዜናዎች እንዲደበቁ በር ከፍቷል።
በተጨማሪም ሚዲያው በራሱ ተነሳሽነት ስለግድቡ አጀንዳ ቀርጾ ተከታታይነት ባለው መልክ ዓለም አቀፍ ይዘት ያላቸው ዘገባዎችን፣ ዜናዎችን፣ ዶክመንተሪዎችን… በመሥራት አዎንታዊ ተጽዕኖ በማሳረፍ ረገድ ርምጃው ቀርፋፋ ነው። እንዲያውም ከተሞከረው ይልቅ ያልተሞከረው ይልቃል። ከእነ አልሐራም ጋዜጣ አንጻር ንጽጽር ውስጥ ከገባን ያለንበት ቁመና ጨርሶ የሚያኩራራን አይደለም። ቦርቀቅ አድርገን እንየው ከተባለ ጉዳዩ ከመገናኛ ብዙኃን ዕድገታችንም ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ሆኖ እናገኘዋለን። ያሉትም ቢሆኑ እንኳንስ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ለመፍጠር ይቅርና የአገር ውስጥ አንባቢና አድማጭ ፍላጎት በማሟላት ረገድ ውስንነት አለባቸው።
አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ግብጽ ሁለት ስመጥር መንግሥታዊ የቴሌቪዥን ጣቢዎች አሏት። ስድስት ያህል ክልላዊ ቻናሎችም አሉ። ናይል ሳት በመባል የሚታወቀው ሳተላይት በግብጽ ብቻ ሳይሆን በአረቡ ዓለም ፈር ቀዳጅ የሳተላይት ጣቢያ ነው። የሚገርመው ጥቂት የማይባሉ የኢትዮጵያውያን የሳተላይት የቴሌቪዥን ስርጭቶች አሁን ድረስ የናይል ሳት ኪራይ ጥገኛ ናቸው። እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ወደ 20 የሚጠጉ ዕለታዊ ጋዜጦች (የመንግሥትና የግል) በግብጽ ነበሩ።
በተጨማሪም ወደ 49 ነጥብ 2 ሚሊዮን የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች አሏት። እ.አ.አ በ2017 ከአጠቃላይ የሕዝብ ቁጥሯ 50 በመቶ ገደማ የሞባይል ኢንተርኔት ተጠቃሚ ናቸው። ወደ 34 ነጥብ 5 ሚሊዮን የፌስቡክ ተጠቃሚ በመያዝም ግብጽ የአረቡን ዓለም ትመራለች። (ምንጭ፡ ቢቢሲ)
እነዚህን መረጃዎች ያነሳሁት እንዲያው ወግ ለማሳመር ያህል አይደለም። ለግብጾች የሚዲያ ልማታቸው እያስገኘላቸው ያለውን ጥቅም ለመጠቆም ነው። የአፍሪካ መዲና፣ የዲፕሎማቶች መናኸሪያ ተብላ የምትጠራው አገራችን በአሁኑ ወቅት አዲስ ዘመን እና ኢትዮጵያን ሄራልድ ዕለታዊ ጋዜጦች ባለቤት ስትሆን ከግል ሞኒተር የተባለ ጋዜጣ ብቻ ያላት በሚዲያ ልማት እጅግ ወደኋላ የቀረች አገር ናት። በብሮድካስት ዘርፍ ቢሆን ጠንከር ያለ አደረጃጀትና የሰው ኃይል ያላቸው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል በስተቀር ሌሎች ገና ታዳጊ ናቸው ማለት ይቻላል። እነዚህም ቢሆኑ ከጎረቤት አገራት ከእነኬንያ ጋር ሲነጻጸሩ በቴክኖሎጂ፣ በሰለጠነ የሰው ኃይል፣ በአጠቃላይ በአቅም ገና ድክ ድክ የሚሉ ዓይነት ናቸው።
በኢትዮጵያ የግሉን ሚዲያ (በአመዛኙ ጋዜጣና መጽሔት) ስንቃኝ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ አጀንዳ አድርጎ ሽፋን በመስጠት ረገድ በአዎንታ ሊታይ የሚችል ታሪክ አላቸው።፡ ባለፉት ሰባትና ስምንት ዓመታት የህዳሴ ግድብን በተመለከተ በአዎንታና በአሉታ ሊነገሩ የሚችሉ ዜናና ዘገባዎችን ሰርተዋል።
እንደችግር ተደጋግሞ የሚነሳው የግሉ ፕሬስ አንዳንድ ጊዜ የግብጽ መገናኛ ብዙኃን የሚያወጧቸውን አፍራሽ ፕሮፖጋንዳ ሳይቀር ሳያላምጥ የመዋጡ ጉዳይ ነው። ወደኅብረተሰቡ እንደወረደ ማስተላለፉ በትልቁ የሚነሳ ችግር ነው። ለአብነት ያህል ግብጽ ጦሯን ለማዝመት መዘጋጀቷንና ያላትን የትጥቅ አቅም አጋኖ በማውራት በተዘዋዋሪ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የሥነልቦና ጉዳትና ሽብር በማድረስ ይወቀሳሉ። አንዳንዴ የእንዲህ ዓይነት ክስተቶች መደጋገም የግብጽ አጀንዳ አስፈጻሚ ሲያስመስላቸውም ኖሯል።
በማህበራዊ ሚዲያው በኩል የሚታየው ተመሳሳይ ችግር ነው። የግብጾችን የማያባራ ፕሮፖጋንዳ እንዳለ ገልብጦ የማስተላለፍ ችግር አሁንም ድረስ የዘለቀ ነው።
እንደማሳረጊያ
ግብጾች አንድ የሚያግባባ የጋራ አጀንዳ አላቸው፤ የህዳሴ ግድብ። በግብጽ በህዳሴ ግድብ (ናይል ወንዝ) ጉዳይ ትንሹም ትልቁም በአንድነት ለመቆም አያመነታም። ሚዲያዎቻቸው አጀንዳ በመቅረጽ የመንግሥታቸውን ፍላጎት በተከታታይ የማስተጋባት ትልቅ አቅም ፈጥረዋል። ፖለቲከኞቻቸው የሚነዙት ፕሮፖጋንዳ የኢትዮጵያን ድምጽ አፍኗል ማለት ይቻላል። እናም ጥያቄው በዚህ ደረጃ የሚስተካከል አቅም እንዴት እንፍጠር ነው። በእኔ ዕይታ መንግሥት በዚህ ረገድ የአንበሳ ድርሻውን እንዲወጣ ይጠበቃል። በተለይ በአረቡ ዓለም የሚመደቡ ዲፕሎማቶች የፖለቲካ ታማኝነት እና እንግሊዝኛ ማወቃቸው ብቻ በቂ አይደለም። በተጨማሪ የአረብኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ፈልጎ መሾም በብዙ መልኩ ጥቅሙ የላቀ ነው።
በተጨማሪ የሚዲያ ልማት ጉዳይ በብርቱ ሊታሰብበትና በፍጥነት ሊሰራበት የሚገባ ነው። በተለይ የመንግሥት ሚዲያዎቻችን አጀንዳ ቀርጸው በራሳቸው መሥራት እንዲችሉ ሊለቀቁ ይገባል። በኤዲቶሪያል ፖሊሲያቸው መሠረት ያለማንም ጣልቃ ገብነት በነፃነት ራሳቸውን ሊመሩ ይገባል። ለመንግሥትም ቢሆን እጣንና ከርቤ ይዘው ለውዳሴ የሚቆሙ እንዳይሆኑና መንግሥትን በአግባቡ መተቸት ማገዝና ሙያዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት መሆኑን እንዲረዱ ተከታታይ ሥራዎች ሊከናወኑ ይገባል።
አጫጭር የጋዜጠኞች ሥልጠናዎች በገጠመኝ ሳይሆን ወቅቱ በሚጠይቀው ፍላጎት እንዲሰጥ አሁንም መንግሥት በስሩ የሚገኙ የጋዜጠኛ ማሰልጠኛ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ሊነጋገር ይገባል።
መንግሥት በተለይ ማህበራዊ ሚዲያውን ዜጎች በአግባቡ እንዲጠቀሙ ንቁ ተሳታፊ ለሆኑ አክቲቪስቶች ተከታታይ ሥልጠናዎችን በመስጠትና አቅም በፈቀደ በማገዝ በተለይ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የተሻለ አቅም እንዲፈጠር መትጋት ይጠበቅባቸዋል።
ፖለቲከኞች፣ ምሁራን እና ሲቪክ ማህበራትና መሰል ተቋማት ከህዳሴ ግድብ አንጻር የበኩላቸውን እንዲወጡ በመንግሥት በኩል ተቀራርቦ ለመሥራት ያለውን ፍላጎት ማሳደግ ይጠበቅበታል። እነሱም ቢሆኑ በተመሳሳይ መልኩ ራሳቸው ማየትና መፈተሽ የሚገባቸው ጊዜ ቢኖር አሁን ነው።
አዲስ ዘመን ሰኔ 6/2012
ፍሬው አበበ