በሕክምና የሰው የውስጥ አካላት ላይ የሚያጋጥሙ የጤና እክሎች ለመመርመር በተለያዩ መሳሪያዎች እንድንታይ ሐኪሞች ያዙልናል፤ ለምሳሌ ኤክስ ሬይ ወይም በተለምዶ ራጅ፣ አልትራ ሳውንድ፣ ሲቲ ስካን ኤም አር አይ እና ሌሎችም ሊሆን ይችላል። እነኝህ መሳሪያዎች የሰውነት የውስጥ አካላትን እንዴት ማየት ያስችላሉ? ሃኪሞች እና ተመራማሪዎች የሰው ልጅ የውስጥ አካላትን ገላልጠው እንዴት በነዚህ መሳሪያዎች ማየት ቻሉ? ለዛሬ ስለራጅ እና ስለአልትራ ሳውንድ የተወሰነ እንመልከት።
ራጅ (X-ray)
በተለምዶ በአገራችን ራጅ ተብሎ የሚታወቀው የሰውነት ምስል ማንሻ መንገድ ነው። ይህ መመርመሪያ መሳሪያ የኤሌክትሮማግኔቲክ ኃይል ክፍል የሆነውን ጨረር(X-ray) በሰውነት ላይ በመልቀቅ ነው ምስል የሚያነሳው፤ የተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ጨረሩን በተለያየ ደረጃ ይቀበላሉ። ብዙ ጨረር የሚቀበሉ የሰውነት ክፍሎች ፊልሙ ወይም ምስሉ ላይ ነጭ ሆነው የሚታዩ ሲሆን ጨረሩን የማይቀበሉ የሰውነት ክፍሎች ደግሞ ምስሉ ላይ ጠቁረው ይታያሉ። ለምሳሌ አጥንት በውስጡ ባለው ካልሲየም በተባለ ንጥረነገር አማካኝነት ብዛት ያለው ጨረር ስለሚቀበል የራጅ ምስሉ ላይ ነጭ ሆኖ ይታያል። አየር ደግሞ በጣም መጠነኛ ጨረር ስለሚቀበል የራጅ ምስሉ ጥቁር ሆኖ ይታያል። ሳንባ በውስጡ አየር ስለሚይዝ በራጅ በሚነሳበት ወቅት ጠቆር ብሎ ይታያል። ሌሎች የሰውነት ክፍሎችም እንደ ጨረር መቀበል መጠናቸው ግራጫ መልክ ምስል ይኖራቸዋል።
ራጅ ለብዙ የምርመራ መንገዶች አገልግሎት ይሰጣል። በብዛት አገልግሎት ላይ የሚውለው የአጥንት ስብራት መኖሩን ለማወቅ ሲሆን በተጨማሪ ደግሞ በሳንባ ውስጥ ቁስለት ወይም የአየር ወይም ደምን ጨምሮ ሌላ ፈሳሽ ያልሆነ ቦታ መቋጠርን ለመመልከት ይችላል። እንደ አንጀት የመሳሰሉትን ለማየት ደግሞ ሰዎች ጨረር በከፍተኛ መጠን መሳብ ወይም መቀበል የሚችል(Contrast) ፈሳሽ በመጠጣት ሆዳቸውን ራጅ በመነሳት የአንጀት ሁኔታን መመልከት ይቻላል።
ጨረር በሰውነት ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል፤ ነገር ግን በራጅ መሳሪያ አማካኝነት የሚለቀቀው የጨረር መጠን ቁጥጥር የሚደረግበት ስለሆነ ስጋታችንን ይቀንሰዋል፤ ጨረር ምንግዜም ጥንቃቄ ያስፈልገዋል። አናየውም፣ አንሰማውም፣ አናሸተውም፣ ምንም ስሜትም አይፈጥርብንም፤ ነገር ግን እንዲያም ሆኖ ከተጋለጥን ለከፍተኛ ጉዳት ሊዳርገን ይችላል። በመሆኑም የሚከተሉትን ጥንቃቄዎች ማድረግ ተገቢ ነው። በፅንስ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል ስለሚችል ነብሰጡር የሆኑ ሴቶች ራጅ ከመነሳታቸው በፊት ለሐኪሞቻቸው ፅንስ መቋጠራቸውን መንገር አለባቸው። ከነብሰጡር ሴቶች በተጨማሪ በማደግ ላይ ያሉ ሕፃናት ልጆች ሌላ አማራጭ ካልጠፋ በስተቀር ራጅ ባይነሱ ይመረጣል። በተደጋጋሚ ለጨረር መጋለጥ ሰውነት የሚቀበለውን የጨረር መጠን ይጨምራል፤ ስለዚህ በተደጋጋሚ ራጅ ከመነሳት መቆጠብ ወይም ከዚህ በፊት ተነስተው የሚያውቁ ከሆነ ፊልሙን ማስቀመጥ ይረዳል። ራጅ በሚነሳበት ጊዜ ደግሞ ባለሙያተኞች የማይፈለገውን የሰውነት ከፍል በተለይም የአባለዘር የሰውነት ክፍሎች ለጨረሩ እንዳይጋለጡ መከላከል የሚችል መሸፈኛ ማልበስ አለባቸው።
አልትራ ሳውንድ ወይም ሶኖግራም(Ultrasound or sonogram)
የአልትራ ሳውንድ ምርመራ መሳሪያ የሰውነት የውስጥ አካላትን ለማየት ከሚያስችሉ የምርመራ መንገዶች ውስጥ አንዱ ነው። ከሌሎች የሰውነት የውስጥ አካላት ምስል ማንሻ መንገዶች የሚለየው ከጨረር ይልቅ በሰው ጆሮ መሰማት የማይችል ድምፅ ወደ ሰውነት ውስጥ በመላክ ነው። አንዳንድ የሰውነት አካላቶች የተላከውን ድምፅ ተቀብለው የሚያስቀሩ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ድምፁን መልሰው የሚያነጥሩ ናቸው። መሳሪያው ነጥሮ የተመለሰውን ድምፅ በመለካት ወደ ምስልነት ይቀይረዋል።
የአልትራሳውንድ የውስጥ አካላት መመልከቻ መሳሪያ
የአልትራ ሳውንድ ምርመራ መንገድ በሰውነት ውስጥ ስጋነት ያላቸውና በውስጣቸው ፈሳሽ ያለባቸውን የሰውነት ክፍሎች ላይ መረጃ መስጠት አይችልም። የዚህ ምርመራ መንገድ ምንም መዘዝ ወይም የጎንዮሽ ጉዳት የማያስከትል ሲሆን ምንም ሕመም የሌለውና ውጤት ለመናገርም ጊዜ የማይወስድ ነው።
አገልግሎቱ በብዛት የሚሰጠው በማህፀን ውስጥ ያለ ፅንስን ጤንነትና እድገት ለመከታተል ነው። በተጨማሪም በሆድ ዕቃ ውስጥ ያሉ የሰውነት ክፍሎችን ዕብጠቶችና ዕጢዎችን፣ የማህፀን ክፍልን፣ የሃሞት ከረጢትን፣ የሃሞት ጠጠርን፣ ጉበትን፣ ኩላሊትን፣ የኩላሊት ጠጠርንና ጣፊያ የመሳሰሉትን አካላት ለመመርመር ያገለግላል። በእግር የደም ስሮች የደም መርጋትን ለማየት የሚታዘዝ ሲሆን ከሰውነት ውስጥ ለምርመራ በመርፌ ወይም በሌላ መንገድ ናሙና ወይም ቅንጣቢ በሚወሰድበት ጊዜ መርፌ ወይም መቁረጫ መሳሪያው ወደ ሰውነት ውስጥ ሲጋባ ለማየት ወይም የሚፈለገው ቦታ መድረሱን ለማወቅ አገልግሎት ላይ ይውላል።
እንደሚመረመረው የሰውነት ክፍል ለምርመራ ከመሄድዎ በፊት ዝግጅት ማድረግ ሊያስፈልግ ይችላል፤ ስለዚህ በምርመራው ውጤታማ ለመሆን የሚሰጠውን ትእዛዝ መከተል ተገቢ ነው። ለምሳሌ የሽንት ፊኛ የሚመረመር ከሆነ ፊኛው ሙሉ እንደሆነ ሲገኝ ትክክለኛ ውጤት ለማግኘት ስለሚረዳ በቂ ፈሳሽ መጠጣትና ሽንት ሳይወጡ መቅረብ ያስፈልጋል። የሆድ ዕቃ ምርመራ ከታዘዘ ደግሞ የሚበሉትን የምግብ ዓይነት መጠየቅ ተገቢ ነው። ጌጣጌጦችንም ቤት ትቶ መሄድ አስፈላጊ ነው።
የአልትራ ሳውንድ ምርመራ በሆስፒታል ውስጥ ወይም በክሊኒክ ውስጥ በቀላሉ መሰራት ይችላል። ምርመራው ሲደረግም የሚመረመረው የሰውነት ከፍል ልብስ ከተወለቀ በኋላ የሚመረመረው አካባቢ ላይ ማለስለሻ ቅባት በማድረግ መርማሪው ሰው በእጅ በሚያዝ መሳሪያ ሰውነት ላይ ጫን በማድረግ ወደ ሚፈለገው አቅጣጫ በማንቀሳቀስ ምስሉን ይቀርፃል። ይህ ምስል በቪዲዮ መልክ ወይም እንደፎቶግራፍ በወረቀት ላይ በመታተም ይወጣል። የተቀረፀውን ምስል የሚያነቡ አብዛኛውን ጊዜ ራዲዮሎጂስት የተባሉ የምስል ምርመራ ባለሞያተኞች ናቸው። ለእርግዝና ክትትል ግን የማህፀን ሐኪሞች ምስሉን ማንበብ ይችላሉ።
የአልትራ ሳውንድ ምርመራ በሰውነት ላይ የሚያስከትለው ጉዳት የለም። ሆኖም ግን ምርመራ ከሰውነት ውስጥ ቅንጣት ናሙና ለመውሰድ እርዳታ አገልገሎት ላይ ከዋለ፣ መርፌ ወደ ሰውነት በገባበት አካባቢ ጠንከር ያለ ሕመም ሊኖር ይችላል፤ ይህ ችግር ሊከሰት የሚችለው በአልትራ ሳውንዱ ምክንያት ሳይሆን ናሙና(Biopsy) ለመውሰድ በሚደረገው ምርመራ ነው።
አዲስ ዘመን ሰኔ 6/2012